Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተጥሎ የነበረው የብድር ዕግድ መነሳት ለባንኮችና ተበዳሪዎች የፈጠረው መነቃቃት

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከኢኮኖሚ አሻጥር፣ ከዋጋ ግሽበትና ተያያዥ ነገሮች ጋር በተያያዘ ባንኮች ብድር  እንዳይሰጡ አስተላልፎት የነበረውን መመርያ በማንሳት፣ ለሁሉም የቢዝነስ ዘርፎች ብድር ማቅረብ እንደሚችሉ ማስታወቁ የኢኮኖሚው እንቅስቃሴ ላይ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ኅዳር 20 ቀን 2014 ዓ.ም. ለባንኮች ባስተላለፈው መልዕክት፣ የብድር ክልከላው መነሳቱንና ባንኮች ለሁሉም ዘርፎች ብድር መስጠት እንደሚችሉ ማስታወቁ፣ በኢኮኖሚው ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ እንደሚኖረው እየተገለጸ ነው፡፡ የብድር ክልከላው መነሳቱን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር የገለጹት የዳሸን ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አስፋው ዓለሙ፣ ላለፉት ሦስት ወራት ተግባራዊ ሆኖ የቆየው የብድር ክልከላ ባንኮች ላይም ሆነ የተለያዩ ቢዝነሶች ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎ እንደነበር ጠቅሰው፣ አሁን መፈቀዱ ኢኮኖሚው ላይ መነቃቃት ይፈጥራል ብለዋል፡፡ ብሔራዊ ባንክ የብድር ክልከላውን ተከትሎ ከባንኮችና ከተበዳሪ ደንበኞች እየቀረበ ያለውን አቤቱታ ከግምት በማስገባት፣ የተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች በተናጠል የብድር ጥያቄዎችን ማስተናገዳቸውን ሲያሳውቁ የነበረ ቢሆንም፣ በርካታ የብድር ጥያቄዎች ሳይስተናገዱ ቆይተው ነበር፡፡ ዕግዱ መነሳቱ ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ሌላው የፋይናንስ ባለሙያ አቶ አሰግድ ገብረ መድኅን፣ ባንኮች ብድር እንዳይሰጡ ተግባራዊ ሲደረግ የነበረው መመርያ መነሳቱ ትልቅ ዜና ነው ይላሉ፡፡ ኢኮኖሚው እንዲነቃቃ ብቻ ሳይሆን በፋይናንስ እጥረት ቆመው የነበሩ ቢዝነሶች ሥራቸውን በተሻለ እንዲሠሩ ያስችላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ብድር እንዳይሰጡ በተላለፈው መመርያ መሠረት የተፈቀደ ብድር ሳይቀር እንዳይንቀሳቀስና እንዳይለቀቅ በመደረጉ፣ የተለያዩ ቢዝነስ ዘርፎች የሥራ እንቅስቃሴዎቻቸው ላይ ተግዳሮት ፈጥሮ እንደነበር ሲገለጽ መቆየቱም አይዘነጋም፡፡ አቶ አሰግድ እንደገለጹትም፣ ለየትኛውም የቢዝነስ እንቅስቃሴ ገንዘብ ወሳኝ ነው፡፡ ያለ ገንዘብ ምንም ማድረግ አይቻልም፡፡ መንግሥት ብድር እንዲቆም ማድረጉ በወቅቱ ከነበረው ሁኔታ አንፃር ትክክል ነው፡፡ አሁን ብድሩን መልቀቁ ደግሞ ኃላፊነቱን በሚገባ መወጣቱን ያሳያል ብለዋል፡፡

የብድር ክልከላው ተግባራዊ በነበረበት ወቅት ባንኮች ምን ያህል ተፅዕኖ ፈጥሮባቸዋል የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አስፋው፣ የባንኮች የሀብት መግለጫ ሚዛናቸውም ሆነ አጠቃላይ የባንክ እንቅስቃሴ ዋነኛ መሠረት ባንኮች የሚሰጡት ብድር ነው ብለው፣ ከአጠቃላይ ገቢያቸው ከፍተኛውን ድርሻ የሚያገኙት ከሚሰጡት ብድር በሚያገኙት ወለድ በመሆኑ፣ የብድር መቆም ገቢያቸው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡ ስለዚህ ብድር እንዳይሰጡ ተከልክለው መቆየታቸው ባንኮች ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን ያመለክታል በማለት፣ ክልከላው በባንኮች ገቢ ላይ የሚታይ ጫና ስለመፍጠሩ አስረድተዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ባንኮች ብድር አቁመዋል በሚባልበት ጊዜ ኅብረተሰቡ ‹ብድር መቼ እንደማገኝ ስለማላውቅ፣ ያለብኝን ብድር በቅጣትም ቆይቼ እከፍላለሁ› በሚል ዕሳቤ ያለበትን ብድር እንዳይከፍል ማድረጉም ሊጠቀስ የሚገባው ተግዳሮት እንደነበር አክለዋል፡፡ ስለዚህ የብድር ክልከላው በብድር አመላለስ ላይም የራሱ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳርፎ እንደነበር አመልክተዋል፡፡ አሁን ብድር እንዲሰጥ መፈቀዱ ደግሞ በርካታ ጠቀሜታዎችን ይዞ ይመጣል ብለዋል፡፡ ባንኮች ብድር በሚሰጡበት ጊዜ ገንዘብ ይፈጥራሉ ያሉት አቶ አስፋው፣ በአንድ ባንክ የተሰጠ ብድር፣ ብድሩ ከዚያ ብቻ አይቀርም፣ ከሌላው ባንክ ደንበኛም ጋር ይደርስና ተቀማጭ ይሆናል፣ ተቀማጭ ያገኘው ባንክ ደግሞ ተጨማሪ ብድር ለመስጠት ዕድል ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህ የገንዘብ መፍጠርና ማባዛቱ ሒደት ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የብድር ገደቡ መነሳቱ እንደተሰማ ከየአቅጣጫው እየታየ ያለው ስሜት የሚያመለክተው ነገር ያለ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሰግድ፣ የብድር ገደቡ በዚህ ወቅት መነሳቱ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሊከሰት ይችል የነበረውን ጉዳት እንዳይሰፋ በማድረግ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

መንግሥት ከገንዘብ ፖሊሲ አንፃር ይህንን ዕርምጃ ሲወስድ ለአገር ኢኮኖሚ የሚጠቅሙ ሁኔታዎችን መከላከል የፈለጋቸውን ነገሮች ከመከላከል አኳያ የተወሰዱ መሆኑን ያስታወሱት አቶ አስፋው፣ ከአገራዊ ሁኔታ አንፃር ዕርምጃው በመልካም የሚታይ መሆኑንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡ ገደቡ ስለተነሳ አሁን ወደ ሥራ መግባት የሚቻል ቢሆንም፣ ብድር እንዳይሰጥ መከልከሉ በመመርያ ደረጃ ተነገረ እንጂ፣ አንዳንድ ጊዜ ባንኮችም በቂ የሆነ ጥሬ ገንዘብ በማይኖርበት ሰዓት ላይ በፖሊሲ ደረጃ ባይከለከልም ብድሮችን የሚይዙበት ጊዜ እንዳለ መታወቅ አለበት ይላሉ፡፡

በግብር መክፈያ ወቅት ከጥቅምት ወር ጀምሮ ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ግብር የሚከፍሉ ስለሆነ ሁልጊዜ ባንኮች በዚህ ጊዜ ውስጥ ከፍተኛ ጫና ይገጥማቸዋል፡፡ ስለዚህ ብድር መስጠት ይቻላል ሲባል የባንኮችም አቅም አብሮ መታየት እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡ እኛም ከዚህ አንፃር እንደምንረዳውና እንደምናየው ዛሬ ብድሩ ተፈቀደ እንበል እንጂ ብድር ተፈቀደ መባሉ ብድር እንደ ልብ ይሰጣል ማለት ላይሆን እንደሚችልም አቶ አስፋው ይገልጻሉ፡፡

ለዚህም እንደ ምክንያት የሚጠቀሱት ደግሞ በቅርቡ ተግባራዊ መሆን የጀመረው የብሔራዊ ባንክ አዲስ መመርያ መሠረት ባንኮች በብሔራዊ ባንክ ማስቀመጥ ያለባቸው የመጠባበቂያ የገንዘብ መጠን ከአምስት በመቶ ወደ አሥር በመቶ በማደጉ ይህንን መጠባበቂያ ገንዘብ ለማሟላት ገንዘባችንን በሙሉ ወደዚያ እናስገባ ስለነበር የገንዘብ እጥረት ሊኖር ስለሚችል ነው፡፡ በሌላ በኩልም ከግብር ክፍያ ጋር በተያያዘ የወጣ ገንዘብም ስለነበር እንደተፈለገ ብድር ይሰጣል አለማለት እንደሆነም ሳያመለክቱ አላለፉም፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለውን ጫና፣ አካክሰን ወደ ብድር የምንገባበት ሒደት እንፈጥራለን ብለዋል፡፡ እንደፈለግነው ባይሆንም ግን ብድር መስጠቱ እንደሚቀጥ ገልጸዋል፡፡ በጥቅል ሲታይ ግን ብድር ክልከላው መነሳቱ ለኢንዱስትሪውም፣ ለባንክ ደንበኞችም ሆነ በአጠቃላይ ለኢኮኖሚው መልካም እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ የአቶ አስፋው ሌላ ምልከታ ደግሞ ብድር ክልከላው መነሳቱ ብቻ በቂ አለመሆኑን ነው፡፡ ይህንንም፣ ‹‹የብድር ገደቡ አንድ ነገር ሆኖ፣ ብድር ለመስጠት ከዚህ መመርያ ጋር በተመሳሳይ ወቅት የወጣው ቋሚ ንብረቶችን ለማስያዣነት መጠቀም የማይችል መሆኑን የሚደነግገው መመርያ ጉዳይ መታየት አለበት፤›› ይላሉ፡፡ ይህ መመርያ አብሮ ካልተስተካከለ ባንኮች ብድር ለመስጠት የሚቸገሩ ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ብድር በምንሰጥበት ጊዜ እንደ ቤት ያሉ ቋሚ ንብረቶችን አስመዝግበን ነው፡፡ ከዚሁ መመርያ ጋር የወጣው ቋሚ ንብረትን ለብድር ማስያዝ መመርያ ስለመነሳቱ የተነረ ነገር የለምና ይህም መታየት አለበት፤›› ያሉት አቶ አስፋው፣ ነገር ግን ብድር ኖሯቸው ኦቨር ድራፍታቸውን ለመጠቀም ወይም ደግሞ ያልተላቀቀ ብድር ኖሯቸው ሒደት ላይ ያሉና ለመሳሰሉት ግን ብድሩ ይለቀቃል ብለዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች