Sunday, June 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳ ኢንሹራንስ ከኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ገበያ 3.1 በመቶ ድርሻ መያዙን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

አንበሳ ኢንሹራንስ ኩባንያ በ2013 የሒሳብ ዓመት አጠቃላይ የዓረቦን ገቢውን 395.2 ሚሊዮን ብር ማድረሱንና ከኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ገበያ 3.1 በመቶ ድርሻ መያዙን ገለጸ፡፡

ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ያሰባሰበው የዓረቦን መጠን በ9.2 ሚሊዮን ወይም የ6.8 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብርሃም ገብረ አምላክ ቅዳሜ ኅዳር 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ገልጸዋል፡፡

አንበሳ ኢንሹራንስ ካሰባሰበው ዓረቦን ውስጥ 59.1 በመቶ የሚሆነውን ከሞተር ኢንሹራንስ የተገኘ ስለመሆኑም ለማወቅ ተችሏል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ ለካሳ ክፍያ ያዋለው የገንዘብ መጠን ደግሞ 188 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ በቦርድ ሊቀመንበሩ የቀረበው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ የአንበሳ ኢንሹራንስ አጠቃላይ የሀብት መጠን 978.8 ሚሊዮን ደርሷል፡፡

የኩባንያው ሀብት በ16.3 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በቀደመው ዓመት መጨረሻ ላይ ኩባንያው የነበረው የሀብት መጠን 842 ሚሊዮን ብር እንደነበር የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኩባንያው መረጃ እንደሚያመለክተው እስከ ሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ኩባንያው የሰጠው የኢንሹራንስ ሽፋን በገንዘብ 134.1 ቢሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ባለፉት 14 ዓመታት የከፈለው የጉዳት ካሳ ደግሞ ከ1.4 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል፡፡  

የኩባንያውን ኢንቨስትመንት ገቢን በተመለከተ እንደተጠቀሰው፣ በሒሳብ ዓመቱ ከተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ያገኘው ገቢ 63.3 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ከእነዚህ ገቢዎች መካከል በተለያዩ ባንኮች የተቀመጠው ገንዘብ ወለድ ከፍተኛውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ከአንበሳ ባንክ፣ ከእናት ባንክ፣ ከኢትዮጵያ ጠለፋ መድንና ከሰላም ባስ አክሲዮን ማኅበሮች ባለው የአክሲዮን ድርሻ ያስገኘለት የትርፍ ድርሻም በተጨማሪነት ተጠቅሷል፡፡

ባለአክሲዮን ከሆነባቸው ባንኮችና የኢንሹራንስ ኩባንያ ያገኘው ትርፍ 13.1 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ከነዚህ ኢንቨስትመንቶች ያገኘው ገቢ ከቀዳሚው ዓመት አንፃር ሲታይ 24.1 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡

ከሒሳብ ዓመቱ አፈጻጸሙ የኢንሹራንስ ኩባንያው ከታክስ በፊት 59.1 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታውቋል፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ከ2012 የሒሳብ ዓመት አንፃር ሲታይ የ5.8 ሚሊዮን ወይም የ10.9 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ 53.3 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህም ኩባንያው በሒሳብ ዓመቱ ኢንቨስትመንቶች ያገኘው ገቢ ከታከስ በፊት ካገኘው ትርፍ በላይ ብልጫ ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡

የውል ሥራ ውጤትን በተመለከተ በቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት እንደተጠቀው፣ በሒሳብ ዓመቱ ከውል ሥራ 115.5 ሚሊዮን ብር ያተረፈ ሲሆን፣ ይህ ትርፍ ግን ከቀዳሚ ዓመት የ7.5 በመቶ ወይም የ9.3 ሚሊዮን ብር ቅናሽ አሳይቷል፡፡

አንበሳ ኢንሹራንስ የተከፈለ ካፒታሉ 166.2 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ 36 ቅርንጫፎች ያሉት ሲሆን፣ በሒሳብ ዓመቱ ማጠቃለያ ላይ ያሉት ሠራተኞች ቁጥር 347 ደርሷል፡፡

አንበሳ ኢንሹራንስ በ16 ሚሊዮን ብር በተከፈለና በ66.4 ሚሊዮን ብር በተፈረመ ካፒታል የተቋቋመ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት የተፈረመ ካፒታሉ ደግሞ 300 ሚሊዮን ብር እንደሆነ የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች