Wednesday, March 22, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሐርላዎች እነማን ናቸው?

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

ሐርላዎች ለረዥም ዘመናት በምሥራቁ የኢትዮጵያ ግዛት የራሳቸው የሆነ ሡልጣኔት የነበራቸው ቢሆንም በአንዳንድ የውጭ አገር ጥናቶች ሐርላዎች ከምድር ገጽ እንደጠፉ ይገልጻሉ፡፡ የአገራችንም ሰዎች አስገራሚ አፈታሪክ ፈጥረዋል፡፡ ስለሆነም አንባቢዎች ‹‹እውነት ሐርላዎች ጠፍተዋል? ወይስ አሁንም አሉ? እነሱ ከሌሉ እንዴት ማንነታቸውን ፈልገን ማግኘት እንችላለን?›› የሚሉትን ለመረዳት ይችሉ ዘንድ ይህ ጽሑፍ ማዘጋጀት አስፈልጓል፡፡ ስለሆነም ወደ ትክክለኛው የሐርላዎች ሡልጣኔት ወይም ኢሚሬት በቀጥታ ከመግባታችን በፊት እነሱን በተመለከተ የሚነገሩ ተረት የሚመስሉ አፈ ታሪኮችን፣ ሐርላዎች ስለመኖራቸው የሚፈነጥቁ የአፈ ታሪኮችንና ትውፊቶችን፣ እንዲሁም ጥናቶችና የአርኪዮሎጂ ግኝቶችን እንመለከታለን፡፡

ከሁሉ አስቀድመን በምሥራቅ ኢትዮጵያ በተለይም ከድሬዳዋ እስከ ጅግጅጋ ባለው ግዛት በወቅቱ የነበሩ ሐርላዎች (በአንዱ በሌላ መልኩ በመጥፋታቸው ምክንያት የተፈጠረ ሊሆን ይችላል)፣ በሰፊው የሚነገር አፈ ታሪክ ማየቱ ጠቃሚነት ይኖረዋል፡፡ ከዚህም  አፈ ታሪክ የሚገኙ ቁም ነገሮች ስላሉ በቅድሚያ አፈንዲ ሙተቂ ነሐሴ 30 ቀን 2005 ዓ.ም. ያጠናቀረውን ድንቅ ትረካ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡ 

ስለሐርላዎች የሚነገር አፈ ታሪክ

አፈንዲ ሙተቂ በመጽሐፉ እንደሚተርክልን ‹‹ከታችኛው አዋሽ አካባቢ ተነስታችሁ እስከ ጅግጅጋ ድረስ በተዘረጋው መሬት ባሉት መንደሮች ውስጥ ስትጓዙ የጥንታዊ ግንባታ ፍርስራሾች በብዛት ያጋጥሟችኋል። የየመንደሮቹን ነዋሪዎች ስለግንባታዎቹ እንዲነግሯችሁ ብትጠይቋቸው ‹‹ሐረላ›› የሚባል ጥንታዊ ነገድ መኖሪያዎች እንደነበሩ ያወጓችኋል፤›› ካለ በኋላ ከጋሊቨርስ ትራቭልስ ተወዳዳሪ ስለሆነው አስገራሚውንና አስደናቂውን አፈ ታሪክ ይተነትናል፡፡  በመሠረቱ ‹‹ጋሊቨርስ ትራቭልስ›› (Gulliver’s Travels) በሚል ርዕስ ጆናታን ስዊፍት በ1726 ለንባብ ያበቃው ምፀታዊ ልቦለድ ታሪክ መቼቱ በሰሜን ምዕራብ አካባቢ ይሁን እንጂ አፈ ታሪኩ የኛን አገር ይመስላል፡፡ ለምሳሌ የዘጠኝ ዓመቱ ሕፃን 40 ጫማ (12.192 ሜትር) ያህል ቁመት ሲኖረው አጭር የተባለችው ንግሥታቸው 30 ጫማ (9.144 ሜትር) ያህል ቁመት ነበራት፡፡ ይህም የሚያመለክተው ሕፃኑ ከኛ አገር ረዥም ሰው ቁመት በሰባት እጥፍ ሲበልጥ አጭሯ ንግሥት የረዥም ሰው ቁመት አምስት እጥፍ የነበራት መሆኑን ነው፡፡

አፈንዲ ሙተቂ እንደሚለው ‹‹የሐረላ ነገድ ሰዎች ቁመተ ረጃጅም ነበሩ፡፡ አንድ የሐረላ ሰው በቁመቱ የዘመናችንን ሰው ስድስት ጊዜ ያህል ይበልጠዋል፡፡ ግዝፈቱ ደግሞ ወደር የለውም፤›› በማለት ጥንታዊ ሐርላዎች ይኖሩበት ከነበረው ሠፈር አግኝቶ ያነጋገራቸው ሰዎች ገልጠውለታል፡፡ አስረጅዎቹ እንደሚሉት ቅድመ አያቶቻቸው ከሐረላ ጋር በአንድ መሬት ላይ ቢኖሩም ከእነሱ ጋር ብዙም ቀረቤታ አልነበራቸውም። እንዲያውም ሐረላዎች ዘራቸውን እንዳያበላሹባቸው ስለሚሠጉ ከእነሱ ጋር አይኖሩም ነበር፡፡ አስረጅዎቹ ለአፈንዲ ሙተቂ እንደገለጡለት ቅድመ አያቶቻቸው ሐርላዎች ወገናቸውን ገድለውባቸው  የሟቹን ደም ለመበቀል በርከት ብለው ጦርነት ቢያውጁ ሰባት ሐረላ ብቻ ይመረጥና ይላክባቸዋል፡፡ ከዚያም አንድ ሐረላ አንስቶ የሚወረውረው ቋጥኝ ድንጋይም 100 ያህሉን ሰው ይጨረግደው ነበር፡፡ በዚህ ሥሌት መሠረት ሰባት ሐርላዎች እያንዳንዳቸው አሥር ቋጥኝ ቢወረውሩ 7,000 በአንድ ጊዜ ሊደመስሱ ይችላሉ ማለት ነው፡፡

እርግጥ ነው አፈንዲ ሙተቂ በአፈ ታሪኩ የሐርላዎች ከብቶች፣ ዛፎችና ትንኞች ወዘተ. አይነግረንም፡፡ ጆናታን ስዊፍት ግን ቁመታቸው 18 ሜትር ያህል ትከሻቸው ደግሞ ዘጠኝ ሜትር ይህል እንደነበር ይነግረናል፡፡ አይጥ ትልቅ ውሻ ያህል፣ ውሻ ደግሞ አራት ዝሆን ያህል እንደነበር ይነግረናል፡፡ ሆኖም እያንዳንዱ ሐረላ ለመቶ ዓመት የሚሆነውን ቀለብ ቀደም ብሎ እንደሚያጠራቅም፣ በየዓመቱ የሚያገኘውን አዲስ ምርት ለፈንጠዚያና ለፌሽታ እንደሚያውለው፣ ሁሉም ያሰኘውን ነገር ‹‹ታዲያ የሐረላ ፌሽታ የዋዛ እንዳይመስላችሁ! በተለይ ሠርግ ሲሠረግ ከሙሽራው ቤት አንስቶ እስከ ሙሽሪት ቤት ድረስ እንጀራ ይነጠፍና ሠርገኞች በዚያ ላይ እንዲሄዱ ይደረጋል። የሠርጉ ታዳሚዎች እጃቸውን የሚታጠቡትም በወተት ነው። ማርና ቅቤ 24 ሰዓት ይበላል፡፡ ጭፈራና ዳንኪራው ይቀልጣል፤›› ካለ በኋላ ‹‹ሆኖም በአጠገባቸው የሚኖሩትን አጫጭር ሰዎች (የአስረጅዎቹ ቅድመ አያቶች) ሲመጡ ወደ ድግሳቸው አያስጠጓቸውም፡፡ በረሃብ ቢሞቱ እንኳ ዞር ብለው አያዩዋቸውም፡፡ በተለይ በአንድ ወቅት ኃይለኛ ረሃብ በሃገሩ ገብቶ አጫጭሬዎቹ ለዕርዳታ ቢማፀኗቸው ‹‹እንዲያውም ጥርግ ብትሉንና ያለአንዳች ቀላዋጭ በደስታ በኖርን!›› አሏቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ቅድመ አያቶቻችን በሐረላ ጭካኔ አዘኑ፡፡ እምባ ለእምባ ተራጩ! ወደ ፈጣሪ ጮሁ፡፡ ‹‹ፍርድህን በቶሎ አሳየን!›› አሉት፡፡ ፈጣሪም ፀሎታቸውን ሰማቸው፡፡ ፍርዱንም እንደሚከተለው በየነ፡፡ ሁሉም ሐረላዎች ለትልቅ ጉባዔ በመተሐራ ተሰበቡ፡፡ ጉባዔውንም አደረጉ፡፡ ከጉባዔው በኋላም እንደ ለመዱት ፌሽታቸውን ጀመሩ፡፡ በዚህን ጊዜ ምክንያት ከየት መጣ የማይሉት እሳተ ጎመራ ፈነዳ፡፡ ምድር ተቀወጠች፡፡ ሐረላዎች  ነደዱ፡፡ ለወሬ ነጋሪ እንኳ አንድ ሰው ሳይተርፍ ሁሉም አለቁ፡፡ በሐረላ ከርሰ መቃብርም ላይ የአሁኑ የመተሐራ (በሰቃ) ሐይቅ ፈለቀ፡፡ ያም ሐይቅ ሐረላዎች ያኔ ሲፈነጥዙ የሸኑት ሽንት ነው፤›› በማለት ይገልጸዋል፡፡

እርግጥ ነው፣ በዚህ አፈ ታሪክ የምንማራቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ግዙፍ ሰዎች ነበሩን ወይ? ከነበሩ በሌሎች አካባቢዎች ለምሳሌ በሰሜን፣ በደቡብና በምዕራብ ኢትዮጵያ ነበሩ? ከኖሩ ስለነዚያ ሰዎች ለምን በ3,000 ዓመት ታሪካችን አልተጠቀሰም? ስለሐርላዎች የ16ኛው ክፍለ ዘመን ታሪካችን ይነግረናል፤ ነገር ግን የነገሥታቱ ገድልም ሆነ ዜና መዋዕል አይነግረንም፡፡ ከሰባተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ ወደ አገራችን የመጡ የዓረብ ጸሐፊዎች አይነግሩንም፡፡ ሆኖም በተረት የሚነገሩ የጭራቅ ታሪኮች አሉ፡፡ እነሱም ቢሆኑ መምጫቸው ከየት እንደሆነ የማይታወቅ፣ ቁመታቸውም ሆነ ትከሻቸው ከተራው ሰው በእጥፍ ቢበልጡ እንጂ ከዚያ በላይ እንደማይሆኑ የማይገመቱ ናቸው፡፡ ሐርላዎች ግን ለምን ቁመታቸውም ሆነ ኃይላቸው ግዙፍ ሆነ? የነዚህ ሰዎች ታሪክ ምናልባት በአካባቢው ወድቀው ከተገኙ ጥንታዊ አጥንቶች ጋር የተያያዘ ይሆን?

አፈንዲ  ሙተቂ ባጠናቀረው አፈ ታሪክ መሠረታዊ ቁም ነገሮችን የምናገኝ ሲሆን ከሁሉ አስቀድሞ በጊዜ ባይጠቀሰም ከታችኛው አዋሽ አካባቢ እስከ ጅግጅጋ ድረስ በተዘረጋው መሬት ባሉት መንደሮች ውስጥ የጥንታዊ ግንባታ ፍርስራሾች በብዛት መኖራቸውን መግለጹ ነው፡፡ መንደሮቹ በብዛት መኖራቸው ታሪኩን ለማወቅ በሚደረገው ጥናትና ምርምር እጅግ አስፈላጊ ግብዓት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሐርላዎች ግዙፎች፣ ሀብታሞችና ጀግኖች መሆናቸውን ያስገነዝበናል፡፡

ሌሎች አፈ ታሪኮች እንደሚያወሱት ሐርላዎች በጣም ግዙፎች የነበሩ ሲሆን፣ በፈጸሙት ግፍ ፈጣሪ ማዕበል አስነስቶ እንደቀጣቸውና ባቢሌ አካባቢ ወደሚገኘው የድንጋይ ቁልልነት እንደቀየራቸው ያወሳሉ፡፡ በእርግጥም የባቢሌን ቁልል ድንጋይ አተኩረን ስንመለከት ተቃቅፈው የተቀምጠው፣ የተሠለፉ፣ የተሰበሰቡ፣ ወይም አጎንብሰው፣ ወይም በሌላ እንቅሰቃሴ ያሉ ሰዎች ይመስላሉ፡፡ የባቢሌን የድንጋይ ቋጥኝ በተመለከተ ብዙ ጥናትን የሚጠይቅ በመሆኑ በዚህ አጋጣሚ አውስቶ ማለፍ የሚሻል ይመስላል፡፡ 

ሐርላዎች በሌሎች የውጭ ጸሐፊዎች

ሐርላን በሚመለከት አሥር ያህል ጥናቶች የሚገኙ ሲሆን፣ አንደኛው ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ የሚገኘው የተጠቃለለ ታሪክ ነው፡፡ በዚህ ጥንቅር አውሮፓውያን አጥኝዎች ያቀረቡት ጥናት በአንድ ላይ ሰፍሮ ይገኛል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ድሬዳዋ አካባቢ የተደረገው አርኪዎሎጂያዊ ቁፋሮ ሲኖር የዚህም ጥናት ውጤት በታወቀ ጆርናል ሰፍሯል፡፡  የዚህ ጽሑፍ አጠናቃሪ ‹‹ኮናባ›› በሚል ርዕስ በጻፈው መጽሐፍ ስለሐርላ ዶዶራ አጭር የዳሰሳ ጥናት ተደርጓል፡፡ ሁሉም ጥናቶች የሐርላዎችን ማንነት የሚያሳውቁ ስለሆኑ ደረጃ በደረጃ እንመለከታቸዋለን፡፡ በቅድሚያ በጎርጂዮ ቤንቲ ተጠናቅሮ ኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካ የሠፈረውን እንመልከት፡፡

ሐርላ ከ14ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በታሪክ ምዕራፎች የሚወሱ ነገዶች ሲሆኑ፣ አል ሙፈዲላ የተባለ ዓረባዊ የታሪክ ጸሐፊ እንደጠቀሱት ከዳሞቶች ጋር በአማራዎች ግዛት ሥር ነበሩ፡፡ በአፄ ዓምደ ጽዮን መዋዕለ ዜና ጸሐፊና ‹‹ዓረብ ፈቂ›› እየተባለ የሚጠራው የፉቱሑል ሐበሽ ጸሐፊ (ሸሀበዲን አሕመድ ቢን አብዱልቃድር፣ ቢን ሳሊሀ፣ ቢን ኡስማን) ደግሞ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ሙስሊም ኅብረተሰብ አባላት ተደርገው ቀርበዋል፡፡ ፉቱሑል ሐበሽ ጨምሮ እንደሚያብራራው የኢማም አሕመድ ዋነኛ ተባባሪዎች ሐርላዎች፣ ሱማሌዎች፣ መለሳዮችና ዓረቦች እንደሆኑ ይጠቁማል፡፡ ዓረብ ፈቂ ሐርላዎችን በሚመለከት ‹‹ቀቢለተል ሐርላ› ማለትም የሐርላ ነዋሪዎች፣ የሐርላ ተወላጆች እያለ  ያቀረባቸው ሲሆን፣ ሶማሊያ ውስጥ በዓረብኛ በተጻፈውና በገጽ 79 እና 112 የጠቀሳቸው ሲሆን በፖል ሌስተር ስቴንሀውስና በፐሮሬሶር ሪቻርድ ፓንክረስት የተተረጎመው መጽሐፍ ደግሞ በሰባት ገጾች (69፣ 76፣ 82፣ 85፣ 104፣ 122 እና 123) ሰፍሯል፡፡ ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹ኢትዮፕያን ቦርደር ላንድስ›› በሚል ርዕስ በ1997 ለኅትመት ባበቁት መጽሐፍ በገጽ 45 ላይ ገልጠዋል፡፡ ስፔንሰን ትሪምግሀምም ‹‹ኢስላም ኢን ኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በ1965 ባሳተመው መጽሐፍ በገጽ 69 ገልጧቸዋል፡፡ ረጀብ ሙሐመድ ዓብዱልሐሊም (ዶ/ር) ‹‹የሐበሾችና የዘይላዕ ሙስሊሞች ታሪክ›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፍ (ዓብደላ ሙሐመድ ዓሊ በ2001 ተርጉመው አሳትመውታል) በገጽ 185፣ 190፣ 191 እና 200 አስፍረውታል፡፡

ፈትሕ መዲነቱል ሐረር የተባለው ልሳን ደግሞ ምንም እንኳን በሐረር አካባቢ በተለያዩ ምክንያቶች የተበታተኑ ቢሆኑም በሐረር አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦች ናቸው በማለት ይገልጻቸዋል፡፡ በምሥራቅ ሸዋ የሚገኙ ከረዩ ኦሮሞ ጎሳዎች፣ ዛሬ እነሱ የሚኖሩበት አካባቢ የሐርላዎች እንደነበረ ከልጅ ወደ ልጅ ሲተላለፍ በመጣ ታሪክ እንደተነገራቸው ያስረዳሉ፡፡

ሙሐመድ ዓብዲ ሙሐመድ በ1990 ጥናታቸው እንዳሰፈሩት ግን ከድሬዳዋ እስከ ሐረር በለው መንገድ የሐርላዎች ተብለው የሚታወቁ መንዶች እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ በተደረገው ጥናት መሠረት መቃብሮቹ ላይ በድንጋይ ላይ የተጻፈ የዓረብኛ ጽሑፍ የተገኘ ሲሆን፣ ይህም ጽሑፍ በ44 ዓመተል ሒጅራ አካባቢ ማለትም ከ1048 እስከ 1057 ባለው ጊዜ የተጻፈ ሊሆን እንደሚችል የሽናይደር (1969) ጥናቶች  ያመለካክታሉ፡፡ ፖሊሽኪ ደግሞ በ1893 ለንባብ ባበቃው ሥራው ሐርላዎች በደቡብ ምዕራብ ዘይላ ይኖሩ የነበሩ የዒሳ ሱማሊ ጎሳ አባሎች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይጠቁማል፡፡ ቸሩሊም በ1964 ለኅትመት ባበቃው የጥናትና ምርምር ሥራው ሐርላዎች በሐረርና በጅግጅጋ መካከል በሚገኝ ግዛት ራሳቸውን በራሳቸው ሲያስተዳድሩ የነበሩ ጎሳዎች እንደነበሩ በጥናቱ ያመለክታል፡፡ ቸሩሊ ከዚህም በተጨማሪ ሐርላዎች ዳሩዶች ነን ብለው ራሳቸውን የዚያ ጎሳ አባላት አድርገው የሚመድቡ ሲሆን፣ አያት ቅድመ አያቶቻቸው ጋሪና ሐርቲ እንደሆኑ ይገልጻሉ፡፡ ዳሩዶች ከጅግጅጋ ወደ ሐረር በሚወስደው መንገድ ዙሪያ የሚኖሩና በግብርና ሲተዳደሩ የነበሩ ሱማሌዎች ሲሆኑ፣ ጋሪና ሐርዎች ደግሞ በሰሜን ምሥራቅ ዶማሌ አካባቢ የሚኖሩ መጀርቲኖች፣ ወርሰንገሊዎችና ዱል ባሀንቲዎች እንደሆኑ ይነገራሉ፡፡ ቸሩሊ በተጠቀሰው ሥራው የላይኛው ፋፋን ግዛት ሱማሊ ነዋሪዎች ሐርላድ በተባለ የሐርላዎች ቋንቋ ጥቂት ቃላትንና ዓረፍተ ነገሮች እንደሚናገሩ ገልጾ፣ የይሪብና ሚዥጋን ጎሳዎች የተወሰኑ ሰዎች የሚያውቁት የምስጢር ቋንቋ (ጃርገን) አድርገው እንደሚጠቀሙበት ጠቁሟል፡፡ ቸሩሊ በጥናቱ የትኛዎቹ ቃላት፣ ሐረጎችና ዓረፍተ ነገሮች የሶማሊኛ ቋንቋዎች ሳይሆኑ የሐርላ ቋንቋዎች እንደሆኑ ለይቶ አሳይቷል፡፡

ኪን ዳሹ (ፕሮፌሰር) የተባሉ ቻይናዊ የሳንቲሞች ሥራ ተመራማሪ ደግሞ በደንገጎ መቃብር የሐርላዎች መኖሪያ ተብሎ በሚታወቀው ሥፍራ በአንድ ገበሬ እጅ ያገኘሁት ሳንቲም ቻይና ውስጥ ከ1039 እስከ 1053 (ኢኤኢ) በአገልግሎት ላይ የነበረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይህም ማርኮ ቪጋኖ አለኝ ከሚለው ሳንቲም ጋር ተመሳሳይ ሲሆን፣ የተሠራው በሶንግ ዳይናስቲ በተለይም በሬን ዞንግ ዘመነ መንግሥት ነው፡፡ ኪን ዳሹ (ፕሮፌሰር)  በሳንቲሙ ላይ ሁዋንግ ሶንግ ቶንግ ባኦ የሚል ስምና 1039 እና 1035 የሚል ዓመት ሰፍሮበታል፡፡ የቻይናዊው ፕሮፌሰር የምርመራ ውጤት ቸርነት ጥላሁን የተባሉ ኢትዮጵያዊ  ተመራማሪ በ1984 ‹‹ዩዋንግ ፌንድ ቶንግ ባኦ›› የሚል ጽሑፍና 1079 እና 1085 የሚል ዓመት የሰፈረበት ሳንቲም መገኘቱን የሚያመለክት ጥናታቸው ትክክል እንደሆነ ያረጋገጡ ሲሆን፣ ዘመኑም በሰሜናዊ ሶንግ ኢምፓየር የንጉሠ ነገሥት ሸን ዞንግ ዘመን እንደሆነ ጨምረው ገልጠዋል፡፡

ሐርላዎች አፋሮች ናቸው?

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከ2006 ዓ.ም. በፊት ከታሪክ መጻሕፍት አንብቦ የሚያውቀው ከላይ የተጠቀሰውን ነበር፡፡ ሆኖም በ2006 የዓፋርን ታሪክ ሲያጠና በተለይም የሰሜን ዓፋር አካል የሆነችው ኮናባ ወረዳን ተዘዋውሮ ሲመረምር በተለይ በበልበል ቀበሌ አካባቢ መኖራቸውን ተረዳ፡፡ ይህን ሐሳብ ይዞ ወደ ሰመራ በመመለስ የአፋር የባህልና ቱሪዝም ባልደረባ የሆነውን ሐቢብ መሐመድ (በአሁኑ ጊዜ የፒኤችዲ ማሟያ ቴሲሱን በማዘጋጀት ላይ ሲሆን፣ ስለ አፋርና ስለ አዳል ሡልጣኔት ትልልቅ መጻሕፍት አሳትሟል)፣ ሐርላዎች አለመጥፋታቸውንና ከአፋር ጎሳዎች አንዱ እንደሆኑ አስረድቶታል፡፡ በዚህም ሒደት የሐርላ ዶዶራ ሡልጣኔት መኖሩንንም ተገነዘበ፡፡ ስለሆነም የሐርላ በአፈ ታሪኩም ሆነ በታሪኩ እንደሚገለጠው አልጠፋም፡፡ እንኳንስ ሊጠፋ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የራሱ ሡልጣኔት ነበረው ማለት ከዚያ በፊት ነበር ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ በአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ክፍለ ዘመን የነበሩት ኢማም መሐመድ ገዓስ የሐርላ ጎሳ አባል ሲሆኑ፣ ለመጀመርያ ጊዜአዳል መንግሥት ዋና ከተማ ከሐረር ወደ አውሳ ያዘወሩ የዓፋር/አዳል/ገዥ ናቸው፡፡

በመጨረሻ ኢማም መሐመድ ገአስ 1583 .ም.  በአፋርና በኦሮሞ መካከል በተደረገ ጦርነት በውጊያ ውስጥ ተገደሉ፡፡ ከሳቸውም ቀጥሎ ኢማም ኡመር መዲቲ (1600 እስከ 1612) ሥልጣን ያዙ፡፡ ኢማም ኡመር ዚያድ (1612 እስከ 1621) ሥልጣናቸውን የተረከቡት ከኢማም ኡመር መዲቲ ሲሆን፣ እሳቸውም በኢማም አድርሁ (1621 እስከ 1628) ተተኩ፡፡ ኢማም ደርሁ 1628 ዓ.ም. ሲገደሉም ኢማም ኡመር ዲኒ አህመድ (1628 እስከ 1629) ወደ ሥልጣን ወጡ፡፡ ይሁንና ኢማሙ እንደ ኢማም ኡመር ዚያድና ኢማም አድርሁ ሁሉ ብዙም ሥልጣናቸው ላይ ሳይቆዩ በዓመቱ ተሻሩ፡፡ በምትካቸውም ኢማም መሐመድ ገረድ ኢሳ (1629 እስከ 1635) ሡልጧን ሆኑ፡፡ እኒህ ሡልጧን በቤተ መንግሥት ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ደም ያፈሰሰና የሥልጣን ሽኩቻ በማስወገድ ሕዝቡን በሰላምና በፍቅር ሲመሩ ቆይተው 1635 ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ በምትካቸውም ወንድማቸው ኢማም አደም ገረድ ኢሳ (1635 እስከ 1649) የሐርላ ዶዶራ ሡልጧነት መሪ ሆነዋል፡፡ እኒህ ኢማም መናገሻ ከተማውን አውሳ አደረጉ፡፡ ኢማም ኢብራሂም ገረድ ኢሳ (1649 እስከ 1659) ወንድማቸውን በመተካት ሡልጧን ከሆኑ በኋላ ሐረር ከአውሳ ግዛት ተገንጥላ ራሷን ማስተዳደር ጀምራለች፡፡ ኢማም ኢብራሂም ገረድ አሥር ዓመት ያህል ሲያስተዳድሩ ቆይተው በመጨረሻ 1659 .. ከዚህ ዓለም በሞት ሲለዩ አጎታቸው ኢማም ሰልማን አደም ገረድ (1659 እስከ 1668) በእግራቸው ተተኩ፡፡ ኢማሙ በመልካም ፀባያቸውና በሃይማኖት አክባሪነታቸው ይታወቁ ነበር፡፡ በመጨረሻ ኢማም ሰልማን አደም ገረድ በሮመዳ ወር 1668 የመግሪብ ሶላት በመስገድ ላይ እያሉ ማንታቸው ባልታወቁ ሰዎች እጅ ተገደሉና ኢማም አብዲረህማን አደም ገረድ (1668 እስከ 1685) ተሾሙ፡፡ ኢማሙ ሕዝባቸውን 17 ዓመት ያህል ሲመሩ ቆይተው በ1685 ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ እሳቸው እንዳለፉም የመሩት ኢማም ስልማን ዳግማዊ መሐመድ ገረድ (1685 እስከ 1733) ኢማም ሰልማን የደርዶራ ጎሳ ተወላጅ ናቸው፡፡

ሐርላዎች በፉቱሑል ሐበሽ

ቀደም ሲል ከተጠቀሰው በተጨማሪ፣ ስለሐርላዎች  የምናገኘው ‹‹ዓረብ ፈቂ›› እየተባለ የሚጠራው የፉቱሑል ሐበሽ ጸሐፊ (ሸሀበዲን አሕመድ ቢን አብዱልቃድር፣ ቢን ሳሊሀ፣ ቢን ኡስማን) ስለኢማም አሕመድ ኢብራሂም ታሪክ በጻፈው መጽሐፍ ነው፡፡ ኢማም አሕመድ ኢብራሒም (ጸሐፊው ኢማም አሕመድ ኢብራሂም በሚል ርዕስ ካዘጋጀው መጽሐፍ የተወሰደ) በአባታቸው በኩል በኡጋዴን የሱማሌ ብሔረሰብ በተለይም ከሆባት ሱማሌ ጎሳ­ዎች የሚወለዱ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በእናታቸው ከሐርላዎ­ ይወለዳሉ፡፡ ኢማም አሕመድ ኢብራሂም በአባታቸው በኩል ያለው የዘር ሐረግ ትንታኔ እንደሚያመለክተው፣ ገራድ ኢብራሂም የኦጋዴን ሱማሌ ባላባቶች ወገን ሲሆኑ የዘር ግንዳቸውንም እነ ዓረብ ፊቂ ሲተነትኑት ከረንሌ፣ ኮራን፣ ገራን፣ እያለ በስምንተኛው ኡመርን፣ ኡመር ገራድ ኢብራሂምን፣ ገራድ ኢብራሂም አሕመድን ይወልዳሉ፡፡

ሐርላ በዚያን ጊዜ በምሥራቅ ኢትዮጵያ የነበረ ሰፊ ግዛት ሲሆን፣ ይህም ሥፍራ በዛሬው አፋር፣ ኦሮሚያና ሐረሪ፣ በስልጢ በጉራጌ፣ በሐዲያ፣ በአርጎባ ውስጥ የሚገኝ መሆኑ ነው፡፡ ከተጠቀሱት ብሔረሰቦች መካከል ሐረሪን፣ ስልጢን፣ አርጎባን ነጥለን የወሰድን እንደሆንሐርላ ዝርያ አለን የሚሉ ዜጎች ከትግራይና፣ ከአማራ ጋር የቅርብ ዘመዶች ሲሆኑ ቋንቋቸው ከትግርኛና ከአማርኛ ጋር እንደሚቀራረብ ይስተዋላል፡፡ ምናልባትም እነዚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች የሰሜን ኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት በዛጉዌ መንግሥት ሲተካ ተቆርጠው የቀሩ ወይም ለብዙ ዓመታት በኦሮሞ ብሔረሰብ ውስጥ በመዋጣቸው ምክንያት ቀስ በቀስ አሁን ወዳሉበት ሁኔታ ተለውጠው ቢሆኑና ከሐርላዎች ተጋብተው የኖሩ እንደሆን ተጨማሪ ጥናት ማድረግ ያስፈልግ ይሆናል፡፡ አንዳንድ አጥኝዎ­ እንደሚሉት ደግሞ ሐርላዎች የበለው/መለሳይ ጎሳ­ዎች ዝርዮች ናቸው፡፡ በለውና መለሳይ ከሆኑ ከሰሜን ኤርትራ እስከ ዘይላዕ በተዘረጋው የባህር ዳርቻና ወደ ውስጥም በምሥራቅ ኤርትራ፣ ትግራይና ዓፋር ግዛት ይኖሩ የነበሩ ሊሆኑ ይችሉ እንደሆነ ተጨማሪ ጥናት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡

በተጨማሪም፣ ሐርላዎችን የባሌ በተለይም የድሬ ሸኽ ሑሴን መስኮት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚኖሩ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ በዚህ አካባቢ ቁመቱ ከሁለት ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው በርካታ መቃብሮች ሲኖሩ የአካባቢው ሰዎች ሐርላዎች ግዙፍ ተክለ ቁመና እንደነበራቸው ከአባቶቻቸው ትውፊት በመነሳት ያስረዳሉ፡፡ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ የኢማም አሕመድ ታሪክን ለማጥናት በ2000 ሄዶ በነበረበት ጊዜ በድሬ ሸኽ ሁሴን መግቢያ በስተግራ መቃብሮችን ያየ ሲሆን፣ እነዚህም መቃብሮች በሚያስገርም ሁኔታ በሐረር፣ በትግራይ፣ በሰሜን ጎንደርና በሰሜን ወሎ ካሉት ቀብሮች ጋር መመሳሰላቸውን ለመገንዘብ ችሏል፡፡ በድሬ ሸኽ ሁሴን፣ በሐረር፣ በአርጎባ፣ በደንገጎ፣ በትግራይ፣  በአፋር፣  በተለይም በአውሳ ያሉት የቤት አሠራሮች ተመሳሳይ መሆናቸው ራሱ የሚናገረው ትልቅ ቁም ነገር አለ፡፡ ይህም ሌላ የውጭ ተፅዕኖ ከሌለ በስተቀርኦሮሞ መስፋፋት በፊት በተጠቀሱት አካባቢዎች ሥልጣን ይዘው ይኖሩ የነበሩ ጎሳዎች ሊሆኑ እንደሚችሉ መገመት አያስቸግርም፡፡ ይህንንም ግምት የሚያዳብርልን ባሌ 16ኛው ክፍለ ዘመን የአዳል ሡልጧኔት አካል የነበረች መሆኗ ነው፡፡ ሆኖም እነሱ የነበሩበት ዘመን ከመሆኑም በላይ የሸኽ ሁሴን ዝርዮች ከአዳል (ሐረር) የመጡ እንደሆኑ ዛሬ በሕይወት ያሉ የአካባቢው ነዋሪዎች ይገልጣሉ፡፡ በዚህ መጽሐፍ አዘጋጅ ስሌት የድሬው ሸኽ ሑሴን ከኢማም አሕመድ ሙጃሂዶች አንዱ እንጅ ሌላ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ይልቁንም ዝርያቸውን ከአሚር ኑር ሙጃሂድ ጋር አያይዘው የሚቆጥሩ ስላሉ አስተሳሰቡን የሚያዳብር እንጅ የሚያኮሰምን አይደለም፡፡ ስለሆነም በድሬ ሸኽ ሁሴን አካባቢ የሚገኘው የመኖሪያ ቤቶች የኢማም አሕመድ ኢብራሂም ሠራዊት አባላት ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ቀደም ሲል በተጠቀሰው መጽሐፉ ‹‹ስለ ሐርላ ዶዶራ ሡልጣኔት›› በሚል ርዕስ ባቀረበው ጽሑፍ ‹‹ሐርላዎች ከምድረ ገጽ ጠፍተዋል›› የሚለው አስተሳሰብ ትክክል አለመሆኑን ጠቅሶ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የራሱ ሡልጣኔት የነበረው መሆኑን ማስረጃ በማቅረብ የመከራከሪያ ሐሳቡን ያቀርባል፡፡ ባቀረበው ጥናት መሠረት ሐርላ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የራሱ ሡልጣኔት ነበረው ማለት ከዚያ በፊት ነበር ማለት ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles