Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊከመፈክር ያለፈ ትጋት የሚሻው ፀረ ፆታዊ ጥቃት

ከመፈክር ያለፈ ትጋት የሚሻው ፀረ ፆታዊ ጥቃት

ቀን:

በዓለም አቀፍ ደረጃ 736 ሚሊዮን የሚጠጉ ሴጎች ፆታዊ ጥቃት እንደደረሰባቸው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡ ጥቃቱ ከደረሰባቸው ሴቶች መካከል አንዷ በሕይወቷ ውስጥ አካላዊ ወይም ወሲባዊ ጥቃት ደርሶባታል፡፡ ይህም የወደፊት ሕይወታቸው ላይ ሥነ ልቦናዊ ቀውስን ከመፍጠር አልፎ ሞት ሲያስከትል ይታያል፡፡

እንደ አፍሪካ ባሉ አገሮች ላይ ይህ ችግር በከፍተኛ ሁኔታ በመስፋፋት የብዙ ሴቶችን ሕይወት እያስተጓጎለ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ ፆታዊ ጥቃትን የምታስተናግድ አገር መሆኗ ይታወቃል፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ሴቶችና ሕፃናት መደፈራቸውና ከቤተሰቦቻቸው መለያየታቸው ተነግሯል፡፡ በሴቶች ላይ እየደረሰ ያለው በደል ከባድ መሆኑን ደግሞ ባለፈው ሳምንት የ16ቱ ቀን የፀረ ፆታዊ ጥቃት ዘመቻ ሲጀመር የተገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመቅረፍ እየሠሩ ከሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት መካከል የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር አንዱ ነው፡፡ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴት ልጆችንና ወንዶችን በማዕከሉ በመደገፍ የድርሻውን እየተወጣም ይገኛል፡፡

- Advertisement -

በማዕከሉ አገልግሎት ከሚያገኙት ርብቃ (ስም ተቀይሯል) አንዷ ናት፡፡ በኮልፌ ቀራኒዮ አካባቢ ከአጎቷ ጋር እየኖረች ባላሰበችው አጋጣሚ መደፈሯን ታስታውሳለች፡፡ ርብቃ አጎቷን ለማገዝና ኑሮዋን ለማሸነፍ በምዕራብ አዲስ አበባ አካባቢ ፑል ቤት ውስጥ ተቀጥራ ትሠራ ነበር፡፡ ክፍለ አገር ካሉ ቤተሰቦቿ ተለይታ በዘጠኝ ዓመቷ ወደ አዲስ አበባ መምጣቷን የምትናገረው ርብቃ፣ ፑል ቤት በምትሠራበት ወቅት በተደጋጋሚ የሚያስቸግራት ልጅ እንደነበር፣ በአንድ አጋጣሚም የሥራ መውጫዋን ሰዓት በመጠባበቅ ከጓደኞቹ ጋር ተከትሏት ፆታዊ ጥቃት እንዳደረሰባት ተናግራለች፡፡

በተደጋጋሚ ፑል ቤት ይመላለስ የነበረ ልጅ ፆታዊ ጥቃት ባደረሰባት ወቅት በአካባቢው ምንም ዓይነት ሰው እንዳልነበረ፣ ጥቃቱንም አድርሶባት በፍጥነት  ከአካባቢው እንደተሰወረ አስታውሳለች፡፡

ጥቃቱም ከደረሰባት በኋላ ለማንም ባትናገርም በወቅቱ የተከሰተው እርግዝና እየገፋ በመምጣቱ ከአጎቷ ቤት ወጥታ ከጓደኛዋ ጋር መኖር እንድትጀምር አድርጓት ነበር፡፡

ጓደኛዋ ቤት በምትኖርበት ጊዜ የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት ጊዜዋን እንደምታሳልፍ፣ ምጧ የመጣው ደግሞ መንገድ ላይ ሆና ስለነበር ፖሊሶች እንዳገኟትና ወደ ጤና ጣቢያ እንደወሰዷት፣ ልጇንም ከወለደች በኋላ ወደ ማዕከሉ መግባት እንደቻለች ተናግራለች፡፡ በማኅበሩም የተለያዩ ድጋፎችና የሥነ ልቦና ምክሮችም እየተሰጣቸው እንደሆነ፣ በተለይም ከአቅም ግንባታ አንፃር የሚደረግላቸው ድጋፍ የተለየ መሆኑን አስታውሳለች፡፡

በማዕከሉ ከገባች ጊዜ ጀምሮ መነቃቃቷን፣ እንደ አዲስ ሕይወቷን ለመኖርና ልጇን ለማሳደግ እንዲሁም ለቁም ነገር ለማብቃት ደፋ ቀና ብላ እንደምትሠራ አስረድታለች፡፡

የደረሰባት ጥቃት ጠባሳ እንደፈጠረባት የምትናገረው ርብቃ፣ ይህንንም በመርሳት ያላትን አቅም በማውጣትና ከማዕከሉ በሚደረግላት ድጋፍ የተሻለ ኑሮ ለመኖር ቆርጣ መነሳቷን ትናገራለች፡፡

ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶች ራሳቸውን በማጠናከር የበኩላቸውን መወጣት አለባቸው ስትል መልዕክቷን አስተላልፋለች፡፡

ሌላኛዋ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባት ሃና (ስም ተቀይሯል) በዲላ አካባቢ ከአባቷ ጋር ጎዳና ላይ ትኖር እንደነበር ተናግራለች፡፡ የተደፈረችውም እሷ ‹‹ታጣቂዎች›› በምትላቸው ነው፡፡

በወቅቱ አባቷ ላይ ድብደባ ስለተፈጸመ ሕይወቱ ማለፉን ታስረዳለች፡፡ በመደፈር ያረገዘችውን ልጅ እዚያው ዲላ እያለች እንደወለደችው የምትናገረው ሃና፣ በአንድ አጋጣሚ ወደ አዲስ አበባ መምጣቷን ታስረዳለች፡፡

አዲስ አበባ ግን ምንም ዘመድ አልነበራትም፡፡ ወደ ማዕከሉ የገባችውም በአዲስ አበባ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ አማካይነት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት ልጇ አንድ ዓመት ሊሞላው ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ማዕከሉም አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረገላት እንደሚገኝ ትናገራለች፡፡

ማዕከሉ የግንዛቤ ማስጨበጥና የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ እየረዳት መሆኑን፣ ከማዕከሉ በምታገኘው ድጋፍም ለመሥራት ቆርጣ መነሳቷንና ከነበረችበት ችግር ወጥታ የተሻለ እንድትሠራ ለተደረገላት ድጋፍ ምሥጋና አቅርባለች፡፡

የአዲስ አበባ ሴቶች ማኅበር ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ሙሴ ያሲን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ማዕከሉ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ከ1,000 ሺሕ በላይ ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችንና ወንዶችን በመደገፍና ለቁም ነገር አብቅቷል፡፡

በአሁኑ ወቅትም 39 እናቶችና 27 ሕፃናት እንደሚገኙ የገለጹት አቶ ሙሴ፣ 12 ሕፃናት በቋሚነት ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

ፆታዊ ጥቃት የደረሰባቸው ሴቶችም ሆኑ ወንዶቹም ወደ ማዕከሉ ከመግባታቸው በፊት የጤና ሁኔታቸው ምን እንደሚመስል የሚጣራ እንደሆነ፣ ለዚህም በማዕከሉ በኩል መዋቅር ተዘርግቶ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡

በማዕከሉ ከገቡ በኋላ የምግብ፣ የሕክምና፣ የሥነ ልቦና አገልግሎት እንደሚያገኙ ለሰብዓዊ መብታቸውም የሕግ ማስከበር አገልግሎት እንደሚሰጥና ፆታዊ ጥቃት ያደረሱባቸው ሰዎች ችግር እንዳያደርሱባቸው አስፈላጊው ጥንቃቄ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በፊት ጥቃቱን የፈጸሙ ሰዎች ከአንድም ሁለቴ ወደ ማዕከሉ በመምጣት ጥቃት ለመፈጸም እንደሞከሩ ያስታወሱት አስተባባሪው፣ ይህንን ለመካላከል ማዕከሉ ትልቁን ድርሻ እተወጣ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በማዕከሉም የሚገኙ ልጆችን ወደ የሕክምና አገልግሎት ለመውሰድ በሚደረግበት ወቅት የመኪና ችግር እንደሚገጥማቸውና በዚህም የተነሳ አብዛኞቹ ልጆች በደፈራቸው ሰው ጥቃት እንዳይደርስባቸው ፍራቻ እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡

ጥቃቱ የደረሰባቸው ልጆች በማዕከሉ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ ካልሆኑ በስተቀር፣ ለሦስት ወራት ያህል እንደሚቆዩ በዚህ ጊዜ ውስጥ አስፈላጊውን የሕክምና አገልግሎት በመስጠትና ለወደፊት ሕይወታቸው ምቹ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የሚሠራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የሕክምና አገልግሎታቸውን ሙሉ ለሙሉ ከጨረሱ በኋላ ከቤተሰቦቻቸው ጋር የማገናኘት ሥራ እንደሚሠራና ሥራው አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በርካታ ልጆችን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ማገናኘት እንደተቻለ አስታውሰዋል፡፡

ከቤተሰብ ጋር መቀላቀል ለማይፈልጉ ልጆችም ሥልጠናዎችን እንዲሁም ከብድርና ቁጠባ መነሻ የሚሆን ገንዘብ በመስጠት ሥራ እንዲሠሩ ቢደረግም ውጤታማ መሆን አልቻሉም፡፡   

ማዕከሉ ከሁለት ሺሕ በላይ በጎ ፈቃደኞችና 199 ቋሚ ሠራተኞች እንዳሉት አስተባባሪው ገልጸዋል፡፡

የሴቶችን ፆታዊ ጥቃት ለመከላከልና ሰብዓዊ መብቶቻቸው እንዲከበር በከተማዋ በሚገኙ 121 ወረዳዎች ላይ ኮሚቴዎችን በማዋቀር እየተሠራ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ሴቶችና ሕፃናት ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ ሜሮን አራጋው ተናግረዋል፡፡

ማኅበረሰቡ በሴቶችና በሕፃናት ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት አስቀድሞ እንዲከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ እንደሚሠራ የገለጹት ኃላፊዋ፣ ጥቃቱ ለደረሰባቸው ልጆች ነፃ የሕግ አገልግሎት እንደሚያገኙ አክለዋል፡፡

ፆታዊ ጥቃት ለደረሰባቸው ልጆች የአንድ መስኮት አገልግሎት ተጠቃሚ እንዲሆኑ በጋንዲ ሆስፒታል፣ በጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታልና በዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎት እንደሚያገኙ ጠቁመዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...