Friday, April 19, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በአዲስ አበባ የቡድን ዋስትና የብድር አሰጣጥ እንዲሻሻል ተጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ ለሥራ ተደራጅተው ብድር ለሚጠይቁ ነዋሪዎች፣ ብድር የሚሰጥበት የቡድን (ጠለፋ) ዋስትና የብድር አሰጣጥ፣ ብድሩን ለማስመለስ አስቸጋሪ ሁኔታን በመፍጠሩ እንዲሻሻል ተጠየቀ፡፡ ጥያቄውን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ያቀረበው የአዲስ አበባ ብድርና ቁጠባ ተቋም፣ ተበዳሪዎች በቡድን ዋስትና አሰጣጥ ብድሩን ከወሰዱ በኋላ እየጠፉ ገንዘቡን ለመሰብሰብ መቸገሩን አስታውቋል፡፡

ኅዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት የአራት ወር አፈጻጸም ግምገማ ላይ ጥያቄውን ያቀረቡት የአዲስ ብድርና ቁጠባ ተቋም ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳምጠው ዓለማየሁ፣ በሩብ ዓመቱ በከተማ ግብርና ላይ ለተሰማሩ 762 ኢንተርፕይዞች ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ብድር መቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 336 ሥራ ላይ መሆናቸውን ተናግረው፣ 138 ወደ ሥራ አለመግባታቸውንና 286 ያህሉ ደግሞ ሥራውን ጀምረው ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል፡፡

እንደ አቶ ዳምጠው ገለጻ ሥራቸውን ያቋረጡት ኢንተርፕራይዞች አባላት ያሉበትን ለማወቅ ባለመቻሉ፣ ተቋሙ በበቂ ሁኔታ ብድሩን ተከታትሎ ማስመለስ አልቻለም፡፡ ‹‹እርስ በርስ ዋስ ሆነው ገንዘቡን ከተበደሩ በኋላ ከጠፉ ብድሩን ከማንም ማስመለስ አይቻልም፤›› ብለዋል፡፡

የቡድን (የጠለፋ) ዋስትና ብድር አሰጣጥ ከ2010 ጀምሮ መተግበር እንደ ጀመረ ለሪፖርተር የተናገሩት አቶ ዳምጠው፣ በዚህ የብድር አሰጣጥ ሁሉም የኢንተርፕራይዙ አባላት በቡድንና በተናጠል ለሚበደሩት ገንዘብ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ተበዳሪዎቹ ለሚበደሩት ገንዘብ ሌላ ዋስትና ወይም ማስያዣ እንዳይጠየቁና ይልቁስ አንደኛቸው ለሌላኛው ዋስትና እንደሚሆኑ አስረድተዋል፡፡

‹‹የኢንተርፕራይዝ አባላት ብድሩን ከወሰዱ በኋላ ተያይዘው ይጠፋሉ፤›› ያሉት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፣ በዚህም ምክንያት በተለይ በከተማ ግብርና ዘርፍ የተሰማሩ ተበዳሪዎች ላይ የብድር አመላለሱ ከ58 በመቶ ሊዘል እንዳልቻለ ገልጸዋል፡፡ ለዚህ መፍትሔ እንዲሆንም ከእርስ በርስ ዋስትናው በተጨማሪ የተበዳሪ ቤተሰቦች ተጨማሪ ዋስትና እንዲሆኑ ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል፡፡

ችግሩ ጎልቶ እንደታየበት የተገለጸው የከተማ ግብርና ዘርፍ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ የሥራ አጥ ነዋሪዎች ቁጥርን ለመቀነስና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራበት እንደሆነ ያስታወቀው ዘርፍ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ዓመታት በዚህ ዘርፍ ከ57 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድሎች እንደተፈጠሩ የተገለጸ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱም ከ21 ሺሕ በላይ ተጨማሪ የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዷል፡፡ ይኼንንም ለማሳካት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ እንደሚያስፈልግና ከዚህ ውስጥ 71.2 ሚሊዮን ብሩ በከተማ አስተዳዳሩ የሚሸፈን መሆኑ ታውቋል፡፡

የብድር አሰጣጡ ላይ ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የሚፈጠሩት የሥራ ዕድሎችን በተመለከተ ‹‹የአስተሳሰብ ችግር›› በመኖሩ፣ መሬትና ብድር ካገኙ በኋላ የሚበተኑ ነዋሪዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ብድር ከወሰዱ በኋላ የሚበተኑ ከሆነ ወደ ራሳችን ዞረን እንዴት ነበር ያሠለጠንናቸው ብለን መጠየቅ አለብን፤›› ብለዋል፡፡

የሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፉና ብድሩን ያመቻቸው አዲስ ብድርና ቁጠባ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸውና ብድር ያገኙ ኢንተርፕራይዞችን የመከታተል ሥራን አጠናክረው እንዲሠሩ ያሳሰቡት ወ/ሮ አዳነች፣ ‹‹ብድሩን ማስመለስ ሳይቻል ሲቀር ጥናት አድርገን እንዳልመለሱ ደረስንበት ማለት አያዋጣም፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አሁንም ቢሆን በብድር መልክ የተሰጠው ገንዘብ በቁጠባ ከሕዝብ የተገኘ በመሆኑ ‹‹በየትኛውም መንገድ›› መመለስ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የሥራ ዕድልናምግብ ዋስትና ዘርፍ ኃላፊ አቶ ይመር ከበደ በበኩላቸው፣ ብድር ከተሰጣቸው ኢንተርፕራይዞች ጋር ስምምነት የተደረገው ውጤታማ ሲሆኑ ብሩን እንዲመልሱ በሚል ቅድመ ሁኔታ ላይ መሆኑን አስረድተው፣ ውጤታማ ሆነው ብድሩን እየመለሱ ያሉ ኢንተርፕራይዞች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹የሥራ ዕድል ፈላጊዎቹ ቤተሰቦቻቸውን በዋስትና እንዲያመጡ ማድረግ ግዴታ የሚሆን ከሆነ ቤተሰቦቻቸው ፈቃደኛ የማይሆኑላቸው የሥራ ዕድል ፈላጊዎች ችግሩን ያበረታዋል፤›› ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳዳር ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ከ55 ሺሕ በላይ የሥራ ዕድሎችን መፍጠር መቻሉ የተገለጸ ሲሆን፣ ይኼም ከተያዘው ዕቅድ ውስጥ 35 በመቶው እንደተፈጸመ አሳይቷል፡፡ ከንቲባ አዳነች፣ ‹‹አፈጻጸሙ ዝቅተኛ ቢሆንም አገሪቱ ካለችበት ሁኔታ አንፃር የተሠራው ሥራ ደህና ነው፤›› ብለዋል፡፡

ባለፈው በጀት ዓመት ተመዝግበው የሥራ ዕድል ካልተፈጠረላቸው 119 ሺሕ የከተማዋ ነዋሪዎች በተጨማሪ፣ በበጀት ዓመቱ ተጨማሪ 350 ሺሕ የሥራ ዕድል ፈላጊዎች ይመዘገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ወ/ሮ አዳነች የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ዕድል ፈላጊዎችን እየመዘገበ ያለው ወዲያው ሥራ ለመፍጠር ሳይሆን፣ ምን ያህል የሥራ ዕድል መፈጠር እንዳለበት ለመለየት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች