Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የበርበራ-ኢትዮጵያ መንገድ ግንባታ 85 በመቶ መድረሱ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የድንበር ከተማዋን ቶጎ ጫሌና የሶማሌላንድ የወደብ ከተማ በርበራን የሚያገናኘውና 234 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው የበርበራ-ኢትዮጵያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 85 በመቶ መጠናቀቁ ተጠቆመ፡፡ ባሳለፍነው ወር የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረቡት በኢትዮጵያ የሶማሌላንድ አምባሳደር ሞሐመድ አህመድ ሞሐሙድ፣ እ.ኤ.አ. 2022 ከማለቁ በፊት የፕሮጀክቱ ሦስቱም ምዕራፎች እንደሚጠናቀቁ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

እንደ አምባሳደሩ ገለጻ የግንባታ ፕሮጀክቱ በጥሩ ሁኔታ እየተካሄደ ሲሆን፣ አሁን ባለው ሁኔታ ሦስቱንም ምዕራፉች ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ሥራ መጀመር ይችላል፡፡ እንደተያዘው ዕቅድ ከሆነ ከበርበራ ሀርጌሳ ያለው መንገድ እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2022፣ ከካላቢድ ውጫሌ ያለው መንገድ በሐምሌ 2022 እና በሀርጌሳ በኩል የሚኖረው መተላለፊያ ደግሞ በታኅሳስ 2022 ይጠናቀቃሉ፡፡

ከተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስና ከእንግሊዝ በተገኘ ፈንድ በ2011 ዓ.ም. መጋቢት ወር ላይ ግንባታው የተጀመረው የበርበራ-ኢትዮጵያ መንገድ ግንባታን ለማጠናቀቅ የ400 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዞለታል፡፡ የመንገድ ግንባታው ሲጠናቀቅም በኢትዮጵያና በሶማሌላንድ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ በ30 በመቶ ያሳድገዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ኢትዮጵያን ከሶማሌላንድ የሚያገናኘው ይኼ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ ታዋቂ የወደብ አስተዳዳሪ ዲፒ ወርልድ፣ በርበራ ወደብን ለማልማትና ለማስተዳዳር ከሶማሌላንድ ጋር ያደረገው ስምምነት አካል ነው፡፡ ዲፒ ወርልድ የበርበራ ወደብ ኮሪደር መሠረት ልማትን ለመገንባት በሚቀጥለው አሥር ዓመት ውስጥ አሥር ቢሊዮን ዶላር ፈሰስ የማድረግ ዕቅድ ያለው ሲሆን፣ በሰኔ 2013 ዓ.ም. ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡ የኮሪደር መሠረተ ልማት ግንባታው ደረቅ ወደቦችንና መጋዘኖችን ያካትታል፡፡

አምባሳደር ሞሐመድ አገራቸው ወደብና ደረጃውን የጠበቀ መሠረተ ልማት በማቅረብ ከኢትጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር ያላትን ዕቅድ የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ ዓለም መግቢያ ዋንኛ በራችን ነች፣ ካላት የሕዝብ ቁጥር አንፃርም ከአንድ በላይ ወደብን መጠቀም አለባት፤›› ብለዋል፡፡ የኮሪደሩ ግንባታ መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ባሏት ኢንዱስትሪ ፓርኮች የምታመርታቸውን ምርቶች ለዓለም ለማቅረብ የሚወስድባትን ጊዜ እንደሚያሳጥርም አክለው ገልጸዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያን የበርበራ ወደብ ተጠቃሚነት መጨመር የምንፈልገው የወደቡንና የኮሪደሩን መሠረተ ግንባታ በማከናወን ብቻ አይደለም፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብ ባለቤትነት እንዲኖራት ያስቻለው ስምምነት ለሁለቱም አገሮች ጠቃሚ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ፣ በሶማሌላንድና በዲፒ ወርልድ መካከል በተደረገው ስምምነት መሠረት ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብ ላይ 19 በመቶ ድርሻ አላት፡፡ ወደቡን ለ30 ዓመታት የሚያስተዳድረው ዲፒ ወርልድ ወደቡን 51 በመቶ ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ሶማሌላንድ ደግሞ 30 በመቶ ድርሻ አላት፡፡

ሶማሌላንድ ወደብና ኮሪደሮችን በመገንባት በቀጣናው ጠንካራ ተፎካካሪ የመሆን ዕቅድ እንዳላት የተናገሩት አምባሳደር ሞሐመድ፣ የተሻለ መሠረተ ልማትን በመገንባት በተለይ ወደብ የሌላቸው አገሮች ፊታቸውን ወደ ሶማሌላንድ እንዲያዞሩ የማድረግ ዓላማ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በሰኔ ወር ከዲፒ ወርልድ ጋር በተደረገው ስምምነት ኢትዮጵያን የወከሉት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የሎጂስቲክስ ኢንዱስትሪው ዕድገት ኢትዮጵያ ለምታደርገው ‹‹የብልፅግና ጉዞ›› የሚኖረው አስተዋጽኦ ቀላል እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ያለውን የወደብ አማራጭ የማስፋት ዕቅድ ያለው ሲሆን፣ የበርበራ-ኢትዮጵያ ኮሪደር ግንባታ አገሪቱ ምርቶቿን በማቅረብ በኩል ያላትን ቅልጥፍና እንደሚጨምርና በዓለም ገበያ ላይ ከፊት ተሠላፊ እንድትሆን የሚያስችል አቅም እንዳለው ገልጸዋል፡፡

በፋይናንስና ኢንቨስትመንት ዘርፍ ላይ ሲሠሩ የቆዩትና ባለፈው ወር የሹመት ደብዳቤያቸውን ለኢትዮጵያ መንግሥት ያቀረቡት አምባሳደር ሞሐመድ፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ ቀጣይ ደረጃ የማሳደግ ዓላማ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ በአምባሳደርነት በተሾሙባት ኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ፣ ሁለቱ አገሮች በቀጣናው ያላቸውን ተፎካካሪነት የሚጨምር የሁለትዮሽ ስምምነቶችን በተለያዩ ዘርፎች ለማድረግ እንደሚሠሩ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች