Friday, June 9, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የአገር ጉዳይ ከፍተኛ ብልኃትና ጥንቃቄ ይፈልጋል!

ኢትዮጵያ የተጋረጠባትን ፈተና ተሻግራ የውስጥ ጉዳይዋን መልክ ለማስያዝ በምታደርገው ጥረት፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ ኅብረትና አንድነት አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ ኅብረትና አንድነት ደግሞ በከፍተኛ ብልኃትና ጥንቃቄ መታጀብ ሲኖርበት፣ ጦርነቱ ተጠናቆ ሰላማዊ ሕይወት በፍጥነት እንዲመለስ ያግዛል፡፡ ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ አሁንም ታላቅነቷን ማስመስከር የምትችለው፣ ልጆቿ በከፍተኛ ብልኃትና ጥንቃቄ ለመጪው ጊዜ ዝግጅት ሲያደርጉ ነው፡፡ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተደረገው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ሕይወት ተገብሮበታል፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ወገኖች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ተፈናቅለውበታል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ንፁኃን ለማመን የሚያዳግቱ ሥቃዮችን ተቀብለውበታል፣ ሕፃናትና አቅመ ደካሞች ያለ ጥፋታቸው መከራ ዓይተውበታል፣ መጠኑ አስደንጋጭ የሆነ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት ወድሞበታል፡፡ ይህ ሁሉ መከራና ሥቃይ የታየበት ጦርነት መደምደም ያለበት፣ በማስተዋልና በዕርጋታ በሚደረግ ምክክር በሚደረስበት የተጠና ውሳኔ ነው፡፡ ኢትዮጵያዊያን የሚታወቁበትን ጨዋነትና አስተዋይነት በመጠቀም፣ አላስፈላጊ መስዋዕትነት ሊያስከትሉ የሚችሉ ሕገወጥ ድርጊቶችን መከላከል አለባቸው፡፡ ጦርነቱ እንዴት መጠናቀቅ አለበት ከሚለው ጀምሮ ድኅረ ጦርነት ሊከናወኑ የሚታሰቡ ተግባራት በሙሉ፣ በብርቱ ምክክርና በተጠና ውሳኔ ላይ ሲመሠረቱ ኢትዮጵያ አሸናፊነቷ በተግባር ይረጋገጣል፡፡ ብልኃትና ጥንቃቄ የሚያስፈልገውም ለዚህ ነው፡፡

በፖለቲካም ሆነ በተለያዩ ጉዳዮች የኃይል አሠላለፍ ለውጥ የሚኖረው፣ የተሻለ አቅም ያለውን ለመወዳጀት ሲባል የፖሊሲ ወይም የስትራቴጂ ማሻሻያ ወይም ማስተካከያ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ በአሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታም ነገሮች በፍጥነት ተለዋውጠው መንግሥት በሕወሓት ኃይሎች ላይ የበላይነት ሲይዝ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃም ከዚህ ቀደም ይስተዋሉ የነበሩ መዛነፎች ማስተካከያ ተደርጎላቸው የሻከሩ ግንኙነቶች ገጽታቸውን መቀየራቸው አይቀርም፡፡ ይህም እውነታ በተለያዩ አገሮች በተለያዩ ጊዜያት የተከሰተ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ ሲስተዋል እንደ እንግዳ ጉዳይ ግራ ሊያጋባ አይገባም፡፡ ይልቁንም ከኃይል አሠላለፍ ለውጡ በኋላ ኢትዮጵያውያን መገንዘብ የሚገባቸው፣ ከተለዋዋጩ የዓለም የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ባህሪ አኳያ በርካታ ልምዶች መኖራቸውን ነው፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በአንድ ጉዳይ ላይ አቋም ሲይዝ የመረጃ ምንጮቹ ታዋቂ ኮርፖሬት ሚዲያዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በዓለም ዙሪያ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው አግባቢ ድርጅቶች (Lobbying Organizations) ጭምር ናቸው፡፡ እነዚህ ደግሞ የምዕራባውያንን ጥቅም ለማራመድ ሽንጣቸውን ገትረው የሚሠሩና ልምድም ያካበቱ ስለሆነ፣ የአሠላለፍ ለውጥ ሲኖርም ከማንም በፊት ነገሮችን ለመለዋወጥ የሚቀድማቸው የለም፡፡ የዓለም ፖለቲካና ዲፕሎማሲ የሚመራው በዚህ ዓይነቱ መሰሪ አካሄድ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ለዚህ መሰሉ ዓይን አውጣ እንቅስቃሴ ባዕድ ሊሆኑ አይገባም፡፡ ለዚህም ነው ብልኃትና ጥንካሬ የሚያስፈልገው፡፡

ኢትዮጵያ መከራ ውስጥ በገባችበት ጊዜ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን ኃይሎች የሠሩት ደባ መቼም ቢሆን የሚረሳ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያ ከዚህ አስከፊ ጦርነት ውስጥ ወጥታ ብሔራዊ ደኅንነቷና ጥቅሟ መረጋገጥ አለበት፡፡ በዚህ ውስጥ ደግሞ የዲፕሎማሲው ጓዝ አስከትሎት የሚመጣው ራሱን የቻለ ፍትጊያ አለው፡፡ በዚህ ፍትጊያ ለጋራ ተጠቃሚነት መርህ በመገዛት አሸናፊ ሆኖ ለመውጣት፣ ብልኃትና ጠንቃቃ ሥራ ይፈልጋል፡፡ አሜሪካና ምዕራባውያን የሠሩት ደባ አንጀትን የሚያሳርር ቢሆንም፣ እነሱ በአካባቢው ከኢትዮጵያ በላይ የተሻለ ወዳጅና አጋር ሊያገኙ እንደማይችሉ ሆደ ሰፊ ሆኖ ማሳየት ተገቢ ነው፡፡ በተለይ ኢትዮጵያውያን ምሁራንና ልሂቃን ለምዕራባውያን ከኢትዮጵያ በላይ ለብሔራዊ ጥቅማቸው ማንም ሊኖር እንደማይችል በማስረዳት፣ የሠሩት ክፋት መቼም ቢሆን እንደማይረሳ ማሳወቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ማፍረስም ሆነ ማተራመስ በፍፁም ጥቅማቸው ሊሆን እንደማይችል፣ የተዛባውን የውጭ ፖሊሲያቸውን በፍጥነት አስተካክለው ለትብብር ዝግጁ መሆን እንደሚበጃቸው ደጋግሞ ማሳሰብ ተገቢ ነው፡፡ በኢራቅ፣ በሶሪያ፣ በየመን፣ በሊቢያ፣ በአፍጋኒስታን፣ ወዘተ. የፈጸሙዋቸው አፍራሽ ድርጊቶች ያተረፉላቸው ጥላቻና ንቀት ብቻ ስለሆነ፣ አሁን በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም እንዲያስተካክሉ ማሳሰብ ያስፈልጋል፡፡ ይህም በከፍተኛ ብልኃትና ጥንቃቄ መከናወን ይኖርበታል፡፡

ኢትዮጵያ የውስጥ ችግሯን በራሷ መፍታት ብቻ ሳይሆን፣ ከማን ጋር መወዳጀትና አብራ መሥራት እንዳለባት የመወሰን ሉዓላዊ መብት ያላት አገር ናት፡፡ አሜሪካኖች በኢትዮጵያ ጉዳይ ናይሮቢ ወይም ፕሪቶሪያ ድረስ ሄደው ሲመክሩና ማሳሰቢያ ሲሰጡ፣ በኢትዮጵያ ውስጣዊ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ መሆናቸው የታወቀ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የኒዮ ኮሎኒያሊስት አስተሳሰብም ሆነ ፍላጎት በኢትዮጵያ ምድር እንደማይሠራ ግልጽ ተደርጎ፣ በእኩልነትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል፡፡ በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ከሩሲያም ሆነ ከቻይና፣ ከህንድም ሆነ ከኩባ ጋር ወዳጅነቷን ማጠናከር ትችላለች፡፡ ውስጣዊ ችግር ሲያጋጥማትም ሆነ የውጭ ሥጋት ሲኖርባት ከወዳጆቿ ዘንድ ድጋፍ የማግኘት መብት ይኖራታል፡፡ ወዳጆቿም በሁለትዮሽ ግንኙነት ወቅት በቀጥታ ከኢትዮጵያ ጋር ይገናኛሉ እንጂ፣ የአሜሪካ ሹማምንት እንደሚያደርጉት ወደ ኬንያ ወይም ወደ ሌላ ሥፍራ መሄድ አይኖርባቸውም፡፡ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው መስክ ዕድሜ ጠገብ ልምድ ያላት አገር ስለሆነች፣ ከአገሮች ጋር የምትፈጥረው ግንኙነት ‹‹የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው›› በሚል ስሜት መሆን የለበትም፡፡ በእኩልነትና በመጠቃቀም ስሜት ላይ ለሚመሠረት ወዳጅነት ጠንክሮ መሥራት የግድ መሆን አለበት፡፡ ዲፕሎማሲው በዚህ መንፈስና መርህ ላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ብልህ መሆን አስፈላጊ ነው፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አዲሱ መንግሥት፣ በኢትዮጵያ ዘንድሮ ሁሉም ሰላማዊ የፖለቲካ ኃይሎች የሚሳተፉባቸው ብሔራዊ የመግባባት መድረኮች እንደሚኖሩ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት የመላ አገሪቱ ትኩረት ጦርነቱ ላይ ሆኖ እነዚህ መድረኮች መዝግየታቸው የታወቀ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ምድር ውስጥ ዳግም አውዳሚ ግጭቶችና ጦርነቶች እንዳይከሰቱ ከወዲሁ ለመድረኮቹ መካሄድ አመቺ መደላድል ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ሳትወድ የገባችበት ጦርነት እንዲከሰት ካደረጉ ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ ሕጋዊና ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር እንዳይለመድ ተደርጎ ጉልበት የሥልጣን ምንጭ መሆኑ በመለመዱ ነው፡፡ ይህ ጦርነት ሲጠናቀቅ ለሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር ባህል መቆርቆዝ ምክንያት የነበሩ ችግሮች አንድ በአንድ ተነቅሰው፣ ለመጪው ብሩህ ጊዜ መፈጠር ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች ወደ አደባባይ እንዲወጡ ኢትዮጵያውያን ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ለአገር የሚጠቅሙ ሐሳቦች ታፍነው ጉልበተኞች እንዳሻቸው የሚሆኑበት ኋላቀር የፖለቲካ ባህል ከኢትዮጵያ ከሥሩ ተመንግሎ መወገድ አለበት፡፡ የብሔራዊ ዕርቅም ሆነ መግባባት መድረኮች ላይ የተለያዩ ሐሳቦች ሲንሸራሸሩ፣ ለኢትዮጵያ መፃኢ ዕድል መልካም መሆን የሚረዱ መፍትሔዎችም ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያውያን በከፍተኛ ብልኃትና ጥንቃቄ ተግባራቸውን ሲያከናውኑ አገር ከያዛት ደዌ በፍጥነት ትገላገላለች፡፡

ከአሁን በኋላ በኢትዮጵያ ምድር አምባገነንነት፣ ሌብነት፣ ሥልጣንን እንደ ርስት በመያዝ በአድልዎ መጠቃቀም፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን መደፍጠጥ፣ በማንነትና በእምነት ትስስር ሌሎችን ማግለልና የውንብድና ሥርዓት ማስፈን ማብቃት ይኖርበታል፡፡ ይህ ሲባል ደግሞ ለሕግ የበላይነት ትልቅ ሥፍራ መሰጠት አለበት፡፡ ክልሎችን እንደ ግል ርስት በመያዝ የምዝበራ ማሳና ማዕድ ማድረግ፣ በኢትዮጵያውያን መካከል የዜግነት ደረጃ በማውጣት ማበላለጥና ሲከፋም ማጥቃትና ማሳደድ ሊቆም ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ ጦርነት ተከፍቶባት ይህ ሁሉ መከራ የታጨደው፣ እኔ ያልኩት ብቻ ካልሆነ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ትፈርሳለች ብሎ በተነሳ ኃይል ምክንያት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ አምባገነንነትን ከዝርፊያና ከአፈና ጋር ካቆራኘ ኃይል ጋር አብሮ የሚያኗኑረው አንዳችም ምክንያት ስለሌለ፣ ለአገሩ ህልውና ሲል ማንኛውንም መስዋዕትነት በመክፈል እንቢ አሻፈረኝ ብሎ ተነስቷል፡፡ በአራቱም ማዕዘናት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው አንገፍጋፊውን አምባገነንነት አንቀበልም ሲሉ፣ በእኩልነት የሚኖርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለመገንባት ቁርጠኛ መሆኑን እያስመሰከረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይህ ሥርዓት ፀንቶ ሊቆም የሚችለው ግን ብልኃትን ከጥንቃቄ ጋር በማስተሳሰር መራመድ ሲቻል ነው፡፡

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ሒጂራ ባንክ የ143 ሚሊዮን ብር ኪሳራ አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት ወደ...

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...

የባንክ ማቋቋሚያ መሥፈርት እንደሚጠነክር ሚኒስትሩ ተናገሩ

 ባንኮች ስለውህደት እንዲያስቡም መክረዋል በኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለማቋቋም የሚያስፈልገው መሥፈርት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...