የፌደራል መንግሥት ከሕወሓት ታጣቂዎች ጋር እያካሄደው ባለውና ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት፣ ቢያንስ ከ45 ሺሕ በላይ መምህራን ከሥራ ገበታቸው ውጪ መሆናቸውን የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አስታወቀ፡፡
በመላ አገሪቱ ከ600 ሺሕ በላይ አባላት እንዳሉት የሚናገረው ማኅበሩ፣ በጦርነቱ ሳቢያ ያለ ሥራ የተቀመጡና በችግር ውስጥ የሚገኙ የመምህራን ብዛት ከተጠቀሰው በላይ ሊሆን እንደሚችል፣ የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱ ከተከሰተ ጀምሮ በነበሩበት አካባቢ መቀጠል ባለመቻላቸው በርካታ መምህራን ከአማራ፣ ከአፋርና ከትግራይ ክልሎች ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ተዘዋውረው እንዲሠሩ ጥያቄ ማቅረባቸውን የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ ማኅበሩ ጥያቄውን ተቀብሎ ከገንዘብ ሚኒስቴርና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር እየተነጋገረ እንደሆነ ገልጸዋል፡
ይሁን እንጂ ችግሩ ከማኅበሩ አልፎ ከአገር አቅም በላይ ስለሆነ፣ በርካታ ፍላጎቶች ቢቀርቡም፣ ማኅበሩ ከመንግሥት ጋር በመነጋገር የመፍትሔ ሐሳቦችን ከማፈላለግ ውጪ የተለየ ነገር ማድረግ አለመቻሉን አስረድተዋል፡፡
በአማራና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠው የመምህራን ደመወዝ ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ ተመልሶ እንዲከፈላቸው፣ ከየክልሎቹ የትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡
የትምህርት ሚኒስቴር ኅዳር 23 ቀን 2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጠው መግለጫ በጦርነቱ ምክንያት በአማራና በአፋር ክልል ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርታቸው እንደተስተጓጎሉ አስታውቋል፡፡ በተጨማሪም ከ300 በላይ ትምህርት ቤቶች መውደማቸው ተገልጿል፡፡
በሌላ በኩል በአገር አቀፍ ደረጃ ጦርነቱ እያመሳቸው በሚገኙ አካባቢዎች ከሥራ ገበታቸው የተስተጓጎሉና የተለያየ ዓይነት ጉዳት የደረሰባቸው ሠራተኞች ምን ያህል እንደሆኑ በቅርቡ ጥናት እንደሚጀምር፣ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የደረሰውን የጉዳት መጠን በቁጥር ለይቶ መግለጽ እንደማይችል የገለጹት ፕሬዚዳንቱ፣ አሁን የደረሰውን ጊዜያዊ መረጃ ለማጠናቀር ከሠራተኞች ፌዴሬሽኖች ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የጦርነቱ ሁኔታ መፍትሔ ባገኘ ማግሥት በሚያደርገው ጥናት የሚገኘውን ውጤት መሠረት በማድረግ ጉዳት የደረሰባቸውን አካላት እንዴት ማቋቋም እንደሚገባ፣ የደረሰውን ኪሳራ በምን ሁኔታ መደገፍ እንደሚቻል ከመንግሥት ጋር እንደሚሠሩ አቶ ካሳሁን አክለው ገልጸዋል፡፡