Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የበቆሎ ምርት ብክነትን ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር መፈልፈያ ተሠራ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ፣ የቴክኒክና ሙያ ማሠልጠኛ ተቋም መምህራን የሠሩት የበቆሎ መፈልፈያ ከዚህ ቀደም የነበረውን የምርት ብክነት ሙሉ ለሙሉ የሚያስቀር መሆኑ ተነገረ፡፡

ማሽኑ የውጭ ቴክኖሎጂ በመቅዳት ዲዛይኑ ቢሠራም ብዙ ማሻሻያ ተደርጎበት የቀረበ በመሆኑ፣ የምርት ብክነትን ሙሉ ለሙሉ ያስቀራል ሲሉ የፈጠራው ባለቤቶች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የበቆሎ መፈልፈያ ማሽኑ ምላጭ በመቀየር ብቻ ለስንዴ መውቂያነት በቀላሉ መዋል እንደሚችልም የፈጠራው ባለቤቶች ገልጸዋል፡፡ 

አቶ ነስሩ ሙንተሲር፣ አቶ ተፈራ ደምሴ፣ አቶ አዲሱ ታደሰና አቶ ሀጁ ኑረዲን በተባሉ አራት የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ አሠልጣኞች፣ ከውጭ የመጣ የወረቀት ዲዛይንን በማሻሻል መሥራታቸው ታውቋል፡፡ ስለፈጠራው ማብራሪያ የሰጡት አቶ ነስሩ፣ ‹‹የውጭ ማሽን ለኢትዮጵያ በቆሎ መፈልፈያነት አይመችም፣ ብዙ ምርትም ያበላሻል፡፡ ለእኛ በቆሎ ዘር መፈልፈያ አመቺ የሆነና ብክነትን የሚከላከል ማሽን ለማጎልበት አስበን ነው የሠራነው፤›› ብለዋል፡፡   

ማሽናቸው የበቆሎ ፍሬ መሰባበርን የሚያስቀር መሆኑን የተናገሩት አቶ ነስሩ በቆሎውን ሳይሸለቀቅ ቢሰጠው ይፈለፍላል፣ ገለባውን፣ ቆረቆንዳውንና ምርቱን ለይቶ ያወጣል ብለዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ለዘር ብዜት ወሳኝ የሆነውን በቆሎ የሚያጎነቁልበትን ክፍል ሳይሰበር ያወጣል የሚሉት አቶ ነስሩ፣ የበቆሎ ምርጥ ዘር ለአርሶ አደሮች ለማሠራጨት ወሳኝ ጠቀሜታ ፈጠራው እንዳለው አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከ30 እስከ 40 በመቶ የሰብል ምርት ብክነት የሚከሰተው በመሰብሰብ፣ በመፈልፈል/በመውቃትና በማበጠር ሒደት እንደሆነ በዘርፉ የተደረጉ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ በቆሎም በመፈልፈል ሒደት እስከ 40 በመቶ ብልሽት እንደሚገጥመው የሚነገር ሲሆን፣ ምርቱ በከፍተኛ ደረጃ ለምግብነት በመዋል ከሚጠቀሱ የሰብል ዓይነቶች ከጤፍና ከስንዴ ቀጥሎ የሚታወቅ ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2020 8.6 ሚሊዮን ቶን በቆሎ ያመረተችው ኢትዮጵያ፣ በየዓመቱ የሰብሉ ምርት 7.6 በመቶ እያደገ መሆኑ ይነገራል፡፡

በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ መምህራን የተገነባው ቴክኖሎጂ የ2013 ዓ.ም. የአገር አቀፍ የክህሎት፣ የቴክኖሎጂና የተግባራዊ ምርምር ሥራ ውድድር አሸናፊ መሆኑን የተናገሩት የፌዴራል ቴክኒክና ሙያ ሥልጠና ማዕከል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበራ አባተ፣ ‹‹ፈጠራውን ወደ አርሶ አደሩ ለማውረድ ይሠራል፤›› ብለዋል፡፡

አሁን በሥራ ፈጠራና ክህሎት ሚኒስቴር ሥር እንዲደራጅ የተደረገው የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ዘርፍ ዋነኛ ተልዕኮው የአገር ችግር ፈቺ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ማፍራት ነው ያሉት አቶ አበራ፣ በዚህ ረገድ ዘርፉ ከኢንዱስትሪዎች ጋር ተቀናጅቶ የሚሠራበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን አመልክተዋል፡፡

አንዱን ማሽን ለመሥራት እስከ 200 ሺሕ ብር የወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ማውጣቱን፣ ከውጭ ከሚመጣው ማሽን ዋጋው በእጅጉ መወደዱን የፈጠራ ባለሙያዎቹ ይናገራሉ፡፡ ፈጠራውን በገንዘብና በተለያዩ መንገዶች የሚደግፈው አካል ከተገኘ፣ ከዚህ ባነሰ ዋጋ ለአርሶ አደሮች ሠርቶ ለማቅረብ ዕቅድ መኖሩንም አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች