በወንጀል የተገኘ ሀብት በአገር ኢኮኖሚና ደኅንነት ላይ የሚፈጸሙ ከባድ ወንጀሎችን ለመከላከል፣ በወንጀል የተገኙና ለወንጀል ሥራ የሚውሉ ሀብቶችን ለመቆጣጠርና በሕዝብና በመንግሥት ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ ለመቀነስ በርካታ ተግባራት እየተከናወነ መሆኑና በበጀት ዓመቱ ሩብ ዓመት 23,062,782.59 ለመንግሥት ገቢ ማድረጉን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አስታወቀ፡፡
በፍትሕ ሚኒስቴር የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በወንጀል የተገኘ ሀብት ማስመለስ ዳይሬክቶሬት ጄነራል ወ/ሮ ፀጋ ዋቅጅራን ጠቅሶ ተቋሙ በድረ ገጹ በዝርዝር እንደገለጸው፣ በሩብ ዓመቱ በወንጀል የተገኘና ለመንግሥት ገቢ የተደረገው 23,062,782.59 ብር ሲሆን፣ ከዕግድ ጋር በተያያዘም 11 ድርጅቶች፣ 363,997,595.17 ብር፣ 10,183,139.16 ሼር፣ 21 ተሽከርካሪዎችና 12 ቤቶች ታግደዋል፡፡
ምርመራቸው የተጠናቀቀና የጥፋተኝነት ውሳኔ በሕጉ አግባብ በማይጠበቅባቸው 19 መዛግብት ላይ የውርስ አቤቱታ ቀርቦ ክትትል እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቁመው፣ መዝገቦቹ ጠቅላላ የያዙት የገንዘብ መጠን 166,945,494.00 ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ከዕግድ ጋር በተያያዘም 11 ድርጅቶች፣ 363,997,595.17 ብር፣ 10,183,139.16 ሼር፣ 21 ተሽከርካሪዎችና 12 ቤቶች በሩብ ዓመቱ ታግደው ጉዳያቸው በሒደት ላይ እንደሆነም አስረድቷል፡፡
በወንጀል ተግባር በአገር ውስጥና ከአገር ውጪ የተደበቀ ሀብት ለማሳገድና ለማስመለስ የሚችል አደረጃጀት ለመፍጠር አስፈላጊ የሆኑት ባለድርሻ አካላትና የመረጃ ሰጪ አካላትን በመለየት የመግባቢያ ሰነዶች መዘጋጀታቸውን፣ በሕገወጥ መንገድ የተመዘበሩና የወንጀል ተግባር ለመፈጸም ጥቅም ላይ የዋሉትን ሀብቶች የማስመለስና የማሳገድ ሒደቱን ለማሳለጥ፣ ዕርምጃው ተጠናክሮ የሚቀል መሆኑን አክሏል፡፡