Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት‹‹የተለያዩ ክለቦችን እንዳላሠለጥን ስደረግ ነበር›› ፍሬው ኃይለ ገብርኤል፣ የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ብሔራዊ...

‹‹የተለያዩ ክለቦችን እንዳላሠለጥን ስደረግ ነበር›› ፍሬው ኃይለ ገብርኤል፣ የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አሠልጣኝ

ቀን:

በርካታ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እግር ኳስ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን ለማድረግ ቢሾፍቱ ከተማን ያዘወትራሉ፡፡ የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳ ችግር የሌለባት ከተማዋ፣ ለተለያዩ ተጫዋቾች እንዲሁም አሠልጣኞች የሥራ ዕድል ፈጥራለች፡፡ የቅድመ ማጣሪያ የዝግጅት ጨዋታ በመመልከት የሚያዘወትሩ የአካባቢው ወጣቶች  ገሚሱ በተጫዋችነት ሲቀጥል ከፊሉ ደግሞ አሠልጣኝ የመሆን ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ በጊዜው የነበሩትን ታላላቅ አሠልጣኞች እየተመለከት ወደ አሠልጣኝነት መግባቱን የሚናገረው ፍሬው ለቅድመ ማጣሪያ ጨዋታ የሚመጡት ክለቦች ዕድል ከፈጠሩለት መካከል አንደኛው ነው፡፡ በሰፈር ውስጥ ታዳጊዎችን በማሰልጠን የጀመረው ፍሬው የብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂውን አቤል ማሞ እና የቀድሞ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ግብ ጠባቂን ታሪክ ጌትነት በማፍራት የአሠልጣኝነት ጉዞውን ጀምሯል፡፡ ከዛም የሪፍቲ ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅና የቀበሌ ክለቦችን ማሠልጠን ችሏል፡፡ ከሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ በስፖርት ሳይንስ ከተመረቀ በኋላ የደደቢትና ሲዳማ ቡና ሴት እግር ኳስ ክለቦችን እንዲሁም የቢሾፍቱ አወቶሞቲቭ ወንዶች እግር ኳስ ክለብን ማሠልጠን ችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድንን ተረክቦም በዑጋንዳ አስተናጋጅነት በተሰናዳው የሴካፋ ዋንጫ ተካፍሎ ሻምፒዮን መሆን ችሏል፡፡  ከስኬታማው ብሔራዊ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ፍሬው  ጋር ዳዊት ቶሎሳ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በርካቶች የአሠልጣኝነት መነሻቸው ተጫዋችነት ነው፡፡ አንተ በእግር ኳሱ ለምን መዝለቅ አልቻልክም?

ፍሬው፡- የትውልድ አካባቢዬ ለተጫዋችነትም ሆና ለአሠልጣኝነት አመቺ ነች፡፡ እኔም በተጫዋችነት ለተወሰነ ጊዜ ገፍቼበታለሁ፡፡ ነገር ግን የእኛ አገር እግር ኳስ መለኪያው አቅም ብቻ ሳይሆን ጎንበስ ብሎ መሄድ መቻልን ይፈልጋል፡፡ እኔ ደግሞ ቤተሰቤም ሲያሳድገኝ ነገሮችን ፊት ለፊት እንድናገርና እንድጋፈጥ አድርጎኝ ስለሆነ ለእንደዚህ አይነት ነገር የምመች አልነበርኩም፡፡ ችግር ብዙ ነገር ሊያስደርግ ይችላል፡፡ እኔ ግን በጊዜው የጎደለብኝ ነገር ስለሌለና እናቴም ትደግፈኝ ስለነበር በዛ መንገድ እግር ኳስ መጫወቱ ላይ መቀጠል አልቻልኩም፡፡ በእርግጥ እናቴም እግር ኳስ እንደጫወት ሳይሆን ትምህርት እንድማር ነበር የምታበረታታኝ፡፡ ለቅድመ ማጣሪያ ክለቦችን ይዘው የሚመጡትን አሠልጣኞች እነ አሥራት ኃይሌ፣ ሰውነት ቢሻው እንዲሁም ሥዩም አባተን ሳይ አሠልጣኝ የመሆን ፍላጎቴ ጨመረ፡፡ ከዛ በኋላ በግሌ አሁን የኢትዮጵያ ቡና ግብ ጠባቂ የሆነውን አቤል ማሞን እና የቀድሞ ደደቢት እግር ኳስ ክለብ ግብ ጠባቂ ታሪክ ጌትነት በግሌ ማሠልጠን ችያለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ቀድሞ በዩኒቨርሲቲዎች መካከል ከፍተኛ ፉክክር ያለው ውድድር ይደረግ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ ቆይታህ ምን ይመስል ነበር?

ፍሬው፡- በዩኒቨርሲቲ የነበረኝ ቆይታ በጣም ጥሩ ነበር፡፡  ሀሮማያ ዪኒቨርስቲ መሆን የምፈልገውን ሆኜ እንድወጣ የረዳኝና የተለያዩ ዕድሎችን ያገኘሁበት ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው አንድ ተማሪ በሥነ ሥርዓት፣ በሥነ ልቦና እንዲሁም በአካላዊ ብቃት ታንጾ እንዲወጣ የሚያደርግ ነው፡፡ በተለይ በዩኒቨርሲቲው በተለያዩ ዲፓርትመንቶች መካከል የሚደረገው የእግር ኳስ ጨዋታ ደማቅ ነበር፡፡ እግር ኳስን በዕውቀት መጫወት እንደሚያስፈልግ የተረዳሁት ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በዲፓርትመንቶች መካከል ከነበረው ፉክክር ነው፡፡ እኔ የስፖርት ሳይንስ ዲፓርትመንትን አሠለጥን ነበር፡፡ በሲቪል ኢንጂነሪንግና በስፖርት ሳይንስ መካከል የሚደረገው ጨዋታ ከፍተኛ ፉክክር የነበረው ነው፡፡ ከዛም ባሻገር ያስተማሩኝ፣ የገሠፁኝና በአሠልጣኝነቴ የተሻለ ቦታ እንድደርስ መንገድ ያሳዩኝ በርካታ መምህራንን ያገኘሁበት ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአሠልጣኝነት ጉዞ የጀመርከው በደደቢት ነው፡፡ ቆይታህ ምን ይመስላል?

ፍሬው፡- ከዩኒቨርሲቲ ከተመለስኩ በኋላ ለአንድ ዓመት ያለ ሥራ ቤት ቁጭ ብያለሁ፡፡ ከዛ በኋላ በቀድሞው ተጫዋቹ ዳዊት ፍቃዱ አማካይነት ደደቢትን እንዳሠለጥን በ2008 ዓ.ም. ዕድል አገኘሁ፡፡ በጊዜው የሴቶቹን ቡድን እንድይዝ ተስማማን፡፡ ግን ምንም የተፈራረምነው ስምምነት አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ከሁለት ጨዋታ በኋላ ሊያባርሩኝ ሐሳብ ስለነበራቸው ነው፡፡  በደደቢት ብዙ ፈታኝ ጊዚ አሳልፊያለሁ፡፡ ግን ዳዊት ፍቃዱ ያበረታታኝ ነበር፡፡ የ2008 ዓ.ም የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ ካነሳሁ በኋላ ከክለቡ ጋር ተለያይተናል፡፡ በጊዜው  ክለቡ እኔን የገመገመበት መንገድ ትክክል አልነበረም፡፡ ግምገማው ማንነትን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ ከዛም ክፍያዬ አምስት ሺሕ ብር ሆኖ  33 ሺሕ ብር  ልንከፍለው አቅርበንለት ነበር ብለው የውሸት ወሬ አስወርተው ነበር፡፡ በዚህም ዋንጫ አንስቶ የተሰናበተ ብቸኛ አሠልጣኝ እኔ ብቻ  ነኝ ማለት እችላለሁ፡፡ ከዛም ለአንድ ዓመት ያለ ሥራ ዳግም ቤቴ ቁጭ አልኩ፡፡ መጨረሻ ላይ የሲዳማ ቡና ሴቶች እግር ኳስ ክለበ እንዳሠለጥን ጥሪ ቀረበልኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ከክለቡ ጋር ስትሰናበትም ውዝግቦች ነበሩ፡፡ ምን ነበር የተፈጠረው?

ፍሬው፡- ከአንድ ዓመት ቆይታ በኋላ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ዋና ሥራ አስኪያጅ መንግስቱ ሳሴሙ ፈርሶ የነበረውን የሲዳማ ቡና ሴት ቡድን እንዳሠለጥን ጠየቀኝ፡፡ በ2009 ዓ.ም. ላይ  በወር 30 እና  40 ሺሕ ብር ክፍያ ከሚያገኙት ታላላቅ ክለቦች የተሸለ ቡድን መመሥረት ችለናል፡፡ በውድድሩም ይወርዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የእኛ ቡድን ሦስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቀቅን፡፡ በቀጣይ ዓመትም በሐዋሳ በነበረው ምድብ ጥሩ ተፎካካሪ መሆን ችለን ነበር፡፡ ሆኖም የሊጉን ስምንተኛ ጨዋታ እያደረግን እያለ ሁለት ልጆች ለምክትልነት ተቀጥረናል ብለው መጡ፡፡ እኔ ደግሞ የራሴ የሆኑ ምክትል አሠልጣኞች ነበሩኝ፡፡  በጊዜው መንግሥቱ ሳሴሙ እና አባተ ኪሾ የክለቡ የቦርድ አባል ነበሩ፡፡ እነሱ ከክለቡ ጋር እንዳልለያይ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡፡ ግን ከላይ የማላውቀው ሰው ጣልቃ ገብቶ ውሳኔ እንደወሰነ ተረዳሁ፡፡ በዚህም ክለቡን ለመልቀቅ ወሰንኩ፡፡ በመጀመሪያው ዙር 14 ነጥብ ይዞ ሦስተኛ የነበረ ቡድን ዘጠኝ ጨዋታ በተከታታይ ተሸንፎ ከሊጉ ወረደ፡፡ የተለያዩ ቡድኖችን እንዳላሠለጥን ብዙ ተንኮል ተሠርቶብኝ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥሩ ነገር የሚሠራ ይወደዳል የሚል ሐሳብ የለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ የኢትዮጵያን ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ጋር የሴካፋን ዋንጫ ማንሳት ችለሃል፡፡ ብሔራዊ ቡድንን የማሠልጠን ዕድል እንዴት አገኘህ?

ፍሬው፡- ከዚህ ቀደም በሊጉ ላይ ዋንጫ ያነሳ አሠልጣኝ ብሔራዊ ቡድኑን ለማሠልጠን ይረከባል ተብሎ ነበር፡፡ እኔም ከደደቢት ጋር በአነሳሁት ዋንጫ መሠረት የመያዝ መብት ነበረኝ፡፡ ግን በወቅቱ የነበሩት አመራሮች እኔን መሾም አልፈለጉም፡፡ እኔም በግሌ በተደጋጋሚ ፌዴሬሽን ድረስ ሄጄ ብጠይቀም ሊያነጋግሩኝ  ፈቃደኛ መሆን አልቻሉም ነበር፡፡  እኛ አገር አንድ አሠልጣኝ ቤቱ ተቀምጧል ብሎ ሥራ የሚከለከልበት አገር ነው፡፡ ይሄ ትክክል አይደለም፡፡ ሌላ አገር አንድ አሠልጣኝ ሥራ ለቆ ሦስት ወይም ስድስት ወር ቤቱ ከተቀመጠ በኋላ ይቀጠራል፡፡ እኛ አገር ግን ቤቱ ቁጭ ያለ ነው በሚል ሥራ ይከለከላል፡፡ ሆኖም የአሁኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ቤት መቀመጤን ተመልክቶ፣ ጥሪ አድርጎልኝና ዶክመንቴን በአግባቡ ከገመገመ በኋላ እንዳሠለጥን ዕደሉን አግኝቼዋለሁ፡፡ አሁን ለዓመት ኮንትራት ፈርሜያለሁ፡፡ እስካሁን ከዘጠኝ በላይ ኢንተርናሽናል ውድድሮችን አድርገናል፣ በሁሉም  አልተሸነፍንም፡፡

ሪፖርተር፡- የሴካፋ ውድድር እንዴት ነበር?  ዋንጫውን አንስታችሁ ስትመለሱ የነበረው አቀባበል ምን ይመስላል?

ፍሬው፡- የሴካፋ ውድድር ቀላል የሚባል አልነበረም፡፡ ለ12 ቀን ዝግጅት አድርገናል፡፡ በዑጋንዳ የነበረው የአየር ሁኔታ መልመድ ፈታኝ ነበር፡፡ ሴቶች ግን ዓላማና ጽናት ስላላቸውና ጠንካራ ስለሆኑ ማሳካት ችለናል፡፡ በውድድሩም መጀመሪያ ከጁቡቲ፣ ኤርትራ፣ ታንዛንያ፣ ብሩንዲና ዑጋንዳ ጨዋታዎችን አድርገናል፡፡ ከአንዱ ቡድን በቀር በሌሎቹ ቡድኖች ላይ ከሦስት በላይ ጎል አስቆጥረናል፡፡ በተጫዋቾቼ ጥንካሬና ዓላማ ዋንጫውን ማንሳት ችለናል፡፡ ስንመለስ ጥሩ አቀባበል ተደርጎልናል፡፡ ከዛ ባሻገር ሴቶቹ ብዙ ማበረታቻ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ አሁንም ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ አለብን፡፡ ስለዚህ ማበረታቻውና ድጋፉ መቀጠል ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ቀጣይ ዕቅድህ ምንድነው?  

ፍሬው፡- አሁን ላይ በሞያዬ እየሠራሁ ነው፡፡ ስለዚህ ሞያዬን አክብሬ አገሬን ማገልገል እፈልጋለሁ፡፡ ያለሁበት ቦታ ላይ መቆም አለፈልግም፡፡ ይሄ ዋንጫ አልፏል፡፡ ሌላ ዋንጫ አንስቼ ሌላ ታሪክ መጻፍ እፈልጋለሁ፡፡ ስለዚህ አሁን ከብሔራዊ ቡድን ጋር ውል ስላለኝ  ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር እቀጥላለሁ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...