Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገትየኢትዮጵያን ነገር ምን አለ ባላገር?

የኢትዮጵያን ነገር ምን አለ ባላገር?

ቀን:

በሙሉቀን እጅጉ

ከፈረንጅ ወዳጆቻችንም ሆነ ከኢትዮጵያዊ አገር ወዳጆች አካባቢ፣ የእነ አሜሪካ ጫናና አድሏዊነት በእጅ አዙር ቅኝ በማስገባት ፍላጎት ሲተረጎም በተደጋጋሚ ይሰማል፡፡ የተወሰኑ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ባዘጋጁት ውይይት ላይ ይኼው ነገር ሲነገር ነበር፡፡ በዚሁ መስመር ውስጥ ከምሁራን አካባቢም ብዙ ተብሏል፡፡ ልዕልናን የናቀና የተዳፈረ ጫና ሲመጣብንና የተሳሳተ ሥዕል ሲሰጥ እውነቱን እያሳዩ መቆጣት አይበዛብንም፡፡

‹‹የእጅ አዙር ቅኝነት›› ለኢትዮጵያም ሆነ ለአፍሪካ (በአጠቃላይም ለዓለም ደሃ አገሮች) አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ሞቅ ያለውን አጠራር ትተን ‹‹ጥገኝነት›› እያልን የምንጠራው እሱኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለምሥራቃዊም ሆነ ለምዕራባዊ ጥገኝነት እንግዳ አይደለችም፡፡ ኢትዮጵያ ‹‹ሶሻሊስት ነኝ›› ባለችበት ጊዜ በይፋ ርዕዮተ ዓለም፣ በፖለቲካ፣ በወታደራዊና በንዋይ ረገድ የምሥራቃዊ ልዕለ ኃያል ጥገኛ እንደነበረች ሁሉ፣ ከሥር ደግሞ የምዕራባዊ ርዕዮተ ዓለምና ባህል ምርኮኛ ነበረች፡፡ የምዕራብ እርጥባን ጥገኛነትንም ኖራበታለች፡፡ ብዙ ነገሮች ቢለዋወጡም ዛሬም አገራችን ያለችበት እውነታ የምሥራቃዊና የምዕራባዊ ጥገኝነት የተጎዳኙበት ነው፡፡ የምናደርገው የልማት እንቅስቃሴ በቻይናም በምዕራብም የንዋይ ምንጭ ላይ በአያሌው የተመረኮዘ ሆኖ ቆይቷል፡፡

እናም በአሁኑ ደረጃ ከምዕራብ በኩል ከብድር ባሻገር ሲመጣ የነበረው በጀት ደጓሚ ዕርዳታ መድረቅ ብዙ እንደሚያጎድለን ጥርጥር የለውም፡፡ እሱን ትተን ዛሬ ባለንበት የቀውስና የጦርነት ሁኔታ ውስጥ እኛ በራስ ለራስ መዋጮ ለዕርዳታ ፈላጊ ወገናችን ለመድረስ ከምናደርገው ጥረት ባሻገር፣ በቀጥታም በተዘዋዋሪም ከምዕራብ የሚገኝ ዕርዳታን ከመፈለግና ከመጠበቅ ውጪ አይደለንም፡፡ ከዚህ ባሻገር፣ በአሁኑ ወቅት ለህዳሴ ግድብና ለዚህ/ለዚያ ድጋፍ እየተባለ በውጭ ካሉ የአገር ልጆች የሚሰበሰበውና ለዘመድ አዝማድ በሐዋላ የሚላከው አብዛኛው ገንዘብ ምንጩ ‹‹በእጅ አዙር ቅኝ ‹‹ሊያንበረክኩን›››› እያልን ከተናደድንባቸው፣ ከአሜሪካና ከምዕራብ አውሮፓ አገሮች መሆኑን መዘንጋት የለብንም፡፡ ማለትም ኩነኔ ስናበዛ፣ በአሁኑ የፈተና ጊዜና የውጭ ምንዛሪ የማስፋት ደካማ አቅማችን ደረጃ ገመድ የማሳጠር/ሸምቀቆ የማጥበቅ ጅልነት እንዳንሠራ መጠንቀቅ ይገባናል፡፡

ከየትኛውም ዓይነት ጥገኝነት የመላቀቅና ነፃነትን ሙሉ የማድረግ ተጋድሏችን ከምንም ነገር በላይ ብልህ እልህ፣ በአጭር መታጠቅና በደንብ የተሠላ አካሄድ ይሻል፡፡ ከዚህ አኳያ አንዳንድ ነገሮችን እንጠቃቅስ፡፡

አሁን ባለንበት በኢኮኖሚ፣ በቴክኖሎጂ፣ በበሽታና በብክለት ነክ አሉታዊና አዎንታዊ ተራክቦዎች እየተሳሰረ በመጣ ዓለም ውስጥ ከየትኞቹም ታላላቅና ከተራመዱ አገሮች ጋር አነሰም በዛ ለስላሳ ግንኙነት ውስጥ ለመሆንና ይህንኑ ለማስቀጠል መሥራት አስፈላጊ ነው፡፡ ሁሉንም ማሳካት ባይቻል እንኳን በአግባቡ ከተሠራበት ከብዙዎቹ ጋር ዕድሉ አለ፡፡ ዕድል አለ ለማለት የሚያስደፍረው፣

አንደኛ አሁን የምንገኝበት ዓለም በአንድ ልዕለ ኃያል ወይም በሁለት ተቃራኒ ልዕለ ኃያላን የሚሾር ሳይሆን፣ ከሁለት የበለጡ የተፎካካሪነት ዝንባሌዎች ጎልምሶ ለመውጣት የሚፍተለተሉበትም ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ምዕራብ አውሮፓ ውስጥ ብልህ ሥራ ያሻል፡፡ ይህንን ማቃናት እስከቻልን ድረስ ያላደገደገልንን መሪ አናምንም ያሉ አንዳንድ ጉልበተኛ አገሮች የሚያደርጉብንን ጉንተላ እጅግም ላያጎሳቁለን ይችላል፡፡ 

ሁለተኛ ለሕወሓት ድጋፍ ከሚሰጡት ውስጥ አንዳንዶቹ በሕወሓት ተራማጅ መሳይ ወይም ተበዳይ መሳይ ለምድ የተታለሉ ናቸው፡፡ በዚህም ተባለ በዚያ ተደራድራችሁ ሰላም ካላወረዳችሁ ብለው ጫና ከሚያደርጉትም አንዳንዶቹ፣ የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ማብቂያ የሌለው ትርምስ ውስጥ ይገባል የሚል ሥጋት ያላቸው ናቸው፡፡ እነዚህ ሁለቱን ለመርታት መንግሥትም፣ ምሁራኖቻችንም ካወቁበት የስብከትና የማሳመን ብዙ ድካም አይኖርባቸውም፡፡ ሕወሓት ራሱ ሁሉንም ነገር አብስሎና ፈትፍቶ ጨርሶላቸዋል፡፡ ሕወሓት በኢትዮጵያም ሆነ በትግራይ ሕዝብ ሕይወት ውስጥ በራስ ገዥነትም ሆነ በአገር ገዥነትም ቢቀመጥ ለምንም ነገር የማይታመን፣ ለኢትዮጵያም ሆነ ለትግራይ (በጥቅሉ ለቀጣናው) ሰላም ጠንቅ ከመሆን የማይፀዳ፣ ለዴሞክራሲና ለልማት የማይሆን ሸር ካልሠራ፣ ጥላቻና በቀል እየተመገበ ጦር ካልሰበቀ የሚያመው/‹‹ባርባራስ ታይራንት› የሆነ ቡድን መሆኑን ሲያስመሰክር ኖሯል፣ አሁን እየሠራውም ያለው የቡድኑን ማንነት ለማሳየት ከበቂ በላይ ነው፡፡

መንግሥት ከልሂቃኑ ጋር ተባብሮ ማድረግ የሚጠበቅበት

ሀ) ሕወሓት የሠራውን የግፍ ድግስ እንካችሁ፣ ዓይናችሁን ገልጣችሁ ተመልከቱና ፍረዱ ማለት ነው፡፡

ለ) የሰላም ድርድርንና ዕርቅን ከሕወሓት ጥርነፋ ከተላቀቀ የትግራይ ሕዝብ ጋር አዛምደው እንዲያዩት ማድረግ ነው፡፡

ሦስተኛ ከዚህ በላይ ጉዳዩ በቀረበበት ማዕቀፍና ድባብ ውስጥ መንግሥት ከአገሬው/ከኅብረተሰቡ ጋር ተባብሮና አገሬውን/ኅብረተሰቡን አስተባብሮ ማድረግ የሚጠበቅበትንና ያለበትን ገልጸናል፡፡ ይህ በሁለት ነጥቦች ሥር የሚጠቃለል ነው፡፡ አንደኛው ሕወሓት የሠራውን የግፍ ድግስ ዘርዝሮ፣ በማስረጃ አስደግፎና ሰንዶ እንካችሁ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛውና እጅግ በጣም ሲበዛ ግልጽ ሆኖ መውጣት፣ የአገር አቋምና የመላው ሕዝብ መገናኛና አደራ ሆኖ መታወቅ፣ ‹‹ሊታወጅ›› የሚገባው የሰላም ድርድሩና የዕርቁ ጉዳይ መታየት ያለበት ከሕወሓት ውጪ፣ ከሕወሓት ጥርነፋ ከተላቀቀ የትግራይ ሕዝብ ጋር ብቻ ተዛምዶ እንዲታይ የማድረጉ ጉዳይ ነው፡፡ እዚህ ሁለተኛው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የሠፈረው ነጥብ ትርጉም የሚያገኘው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ለማራመድ የማይችል እኩይ ቡድን መሆኑን አፍረጥርጦ ከማሳየት ጋር ነው፡፡ ሕወሓት ከትግል እስከ ገዥነት ታሪኩ በግፍ የተጨማለቀ፣ ግፉን የመደባበቅ ተግባርና ከአዲስ ግፍ ለመፆም አለመቻል የሰነከለው በመሆኑ፣ ለትግራይ ሕዝብ የዴሞክራሲ ነፃነት አማጭ መሆን አይችልም፡፡ ትግራይን ከኢትዮጵያ መነጠልን ዓላማ አድርጎ የያዘውም ኢትዮጵያን በመቀበል ጥማት ተይዞ እንደመሆኑ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ማዕቀፍ ውስጥ ገዥነት ቢኖረውም፣ ትግራይን ከኢትዮጵያ ለይቶ ቢይዝም ኢትዮጵያን እርስ በርስ ለማናከስ ከመሥራት፣ በነፃነት ስም ብሔረሰባዊ ቆዳ ያላቸው ሽፍቶች እየፈጠሩ ከማሳመፅ ወይም ጥሩ ጎረቤቶቿን ከማስከዳትና ግንኙነትን ከማደፍረስ አይመለም፡፡ እናም እሱ ባለበት ከንቁሪያ፣ ከግጭትና ከጦርነት የትግራይ ሕዝብ የሚለማበት ዕድል በመርፌ ቀዳዳ የማለፍ ያህል ጠባብ ነው፡፡ ይህንን በደንብ በመተንተን ሕወሓትን በመደገፍ የትግራይን ሕዝብ ጥቅም የደገፉ የመሰላቸውን አገሮች ማባነን ይቻላል፡፡

አራተኛ ለአገራቸውና ለራሳቸው አገር ብሔራዊ ጥቅም ‹‹ሲሉ›› ሕወሓትን የሚደግፉ ቢኖሩ ይህንንም መሞገት ይቻላል፡፡ ተላላኪ ወይም ታዛዥ መንግሥት ‹‹በወዳጅ›› ተረጂ አገር ውስጥ መፍጠር ለኃያላን አገሮች ራሱ በራሱ ግብ አይደለም፡፡ አዛላቂ የጥቅማቸው መከበሪያም አይደለም፡፡ በአገሮች ግንኙነት ውስጥ ማስደግደግ ኖረም አልኖረ ዋናው ጉዳይ ከየአገሮች ጋር ያላቸው የጋራ ጥቅም በሁለት በኩል ጥርት ብሎ መውጣትና መንቀሳቀሻ መሆን መቻሉ፣ ይህም ትርምስና ግጭት ሳያውከው መቀጠሉ ነው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ፣ የመሪ ግለሰባዊ ባህርይና ጥበብ የውጭ ግንኙነትን በማሳመር ረገድ የራሱ አስተዋጽኦ አለው፡፡ እነዚህን ሁለቱን አዘማምዶ በመሥራት ረገድ መንግሥት ማድረግ ያለበትን ይስታል ብለን አናምንምና እዚያ ውስጥ አንገባም፡፡ ነገር ግን ስለ ‹አሁናዊ የእጅ አዙር ቅኝ ፍላጎት› ከማውራትና ሕወሓትን እነ አሜሪካ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚደግፉት ተላላኪያቸው ስለነበርና ያንን ጥቅሙን ፈልገው ነው የሚል አስተሳሰብ ውስጥ ከመሽከርከር ይበልጥ ለእኛ የሚጠቅመን፣ የግፈኛው ቡድን አጫፋሪ የሆኑ ውስን የአውሮፓ አገሮችና አሜሪካ፣ ከአገራቸው ጥቅም ጋር የሚጋጭ ተግባር ውስጥ መሆናቸውን ምሁራኖቻችን ገላልጠው የማሳጣት ሚና ቢጫወቱ ነው፡፡

‹‹ከኢትዮጵያ ላይ እጃችሁን አንሱ…›› ከማለት ባሻገር፣ በውጭ ያሉ የአገር ልጆችም (የውጭ ዜግነት ያላቸው)፣ ከዜግነት አገራቸው ጥቅም አኳያ መንግሥታቸው በኢትዮጵያ ላይ የሚከተለውን ፖሊሲ መቃወም መቻላቸውም አስፈላጊ ነው፡፡ አጋላጭነቱ ቀላል አይደለምና፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት ያላትን አገር በአድሎኛና በሐሰተኛ መረጃ፣ እንዲሁም በማዕቀብ አዋክቦ የመጣልና ለሥርዓት አልባነት አደጋ ማጋለጥን ወይም ተቃራኒ ልዕለ ኃያላን ጉያ ውስጥ እንድትገባ መግፋትን የአውሮፓም ሆነ የአሜሪካ አገራዊ ጥቅም ነው ብሎ የትኛውም የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚ መርታት አይችልም፡፡ ከፍተኛ የሕዝብና የመንግሥት መሳመር፣ የክርስቲያንና የሙስሊም መግባባት ያለባትንና በዴሞክራሲ፣ በግስጋሴና በትልቅ ገበያ ዕድል ውስጥ ያለች አገርን በጥብጦ ጠቅላላ ቀጣናውን ወደ የሚያምስ የጦር አበጋዞችና የስደት መፈልፈያ ገሃነም መውሰድ፣ እንኳን ለምዕራባውያን ለግብፅም ጥቅም እንደማይሆን በእርግጠኝነት ተንትኖ ማሳየት ይቻላል፡፡

አምስተኛ የሚካሄደውን ጦርነት በድፍኑ ‹‹የእርስ በርስ›› ብሎ ማውገዝ ቀርቶ መጥራት ልክ እንደማይሆንም የሚያሳይ የመረጃ ምስክርነት ከበቂ በላይ አለ፡፡ ዋናው የሽብር ቡድን ሕወሓት ጥላቻና በቀል ለጠነነበት ግፉ ሕዝብን ቱታና መሣሪያ አድርጎ እያጋዘ የሚዋጋና ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ወረራ የከፈተ ቡድን ነው፡፡ የወረራ ግፉ አረመኔያዊነት በሰሜን ዕዝ ላይ ጭፍጨፋ ከጀመረበት ከጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን አማራና አፋር ድረስ ባስፋፋው ወረራ ንሮ የቀጠለ ነው፡፡ የእሱ ጦርነት ‹‹የአገር ልጅ ወገኔ›› ባይነት የማያውቅ፣ የጦርነት ሕግ የማያውቅ፣ ለሰው ፍጡር መራራት የማያውቅ አውሬያዊ ነው፡፡ ጭካኔው ሰው ከመጨፍጨፍና ከመግደል፣ ንብረት ዘርፎ ከማጋዝና ሊያግዘው ያልቻለውን ከማውደም አልፎ የሚሄድም ነው፡፡ ከብትና ግመል ብሔረሰብ ያለው ይመስል ይረሽናል፣ በነዶ ክምር፣ በአረንጓዴነት/በተፈጥሮ ቅርስነት የሚጠበቅ ሥፍራ ላይ እሳት ይለኩሳል፡፡ በልጅ ፊት እናትን፣ በወላጅ ፊት ልጅን፣ በባል ፊት ሚስትን የመድፈር ተግባር ይፈጽማል፡፡ ቤተ እግዚአብሔር ብሔር ያለው ይመስል ካህናትንና ቤተ መቅደስን ያረክሳል፣ ይመዘብራል፡፡ ዓብይ አህመድ በሚመሩት ፌዴራዊ መንግሥት ዙሪያ የተሠለፈው የኢትዮጵያ ሕዝብ (ከሕወሓት የህሊናና የአገዛዝ ወህኒ ውጪ የሆኑ ትግራይ ልጆችን ጨምሮ)፣ ተቆጥቶ የተነሳው በዚህ ግፍ ላይ ነው፡፡ የሚዋጋውም ይህንን ግፍ ለማስወገድና አገራዊ ህልውናውን ለማዳን ነው፡፡ ለዚህም ነው የሚካሄደው ውጊያ፣ የቁስለኛና የምርኮኛ አያያዙ በበቀል ያልታወረ የሆነው፡፡ ይህንን የባህርይ ልዩነት አጉልቶ ማውጣትም ይገባል፡፡

ስድስተኛ አውራው አሸባሪ ሕወሓት፣ ከሸኔ ሌላ ራሱ የፈጠራቸው የግፍ አሽከሮች ከተለያየ ብሔረሰብ (ከአማራ ጭምር) እንዳሉት ይታወቃል፡፡ የጥፋት ሚናቸውም በተግባር ታይቷል፡፡ እነዚህን የጥፋት አካላት በሕዝብ ንቁ ተሳትፎ በማነፍነፍ ረገድ ብዥታና መዘናጋት ዛሬ የለም ማለት ይቻላል፡፡ በዚህ አጠቃላይ ንቁ ጠንቃቃነት ውስጥ አውራው አሸባሪ ቡድን ሕወሓት ትግራዊነትን ዋና መሣሪያው አድርጎ የሚሠራ እንደመሆኑ፣ የጥንቃቄያችንም ዋና ማትኮሪያ ትግራዊነት ላይ መሆኑ ሳንፈልገው የገባንበት እውነታ ነው፡፡ ለዚህም የጥቅምት 24ቱ ጭፍጨፋ፣ የደሴና የኮምቦልቻ ልምድ በቂ ምስክር ናቸው፡፡ እነዚህ ጥፋቶች በሌሎች ሥፍራዎችና በአዲስ አበባ እንዳይደገሙ የሚቻለውን ሁሉ ጥንቃቄ ማድረጋችን የምናፍርበት አይደለም፡፡ ማፈር ያለባቸው ይህ ጊዜ የማይሰጥ ሁኔታችን፣ ያደባ ልብን በጥንቆላ ወይም በመሣሪያ አስሶ ማወቅ የማይቻልበት መሆኑን እያወቁ፣ አገርንና ሕዝብን ከማዳን ተግባር ይልቅ ግለሰባዊ ‹‹መብቴ›› ባይነትን አብልጠው ‹‹እንደምን ተጠረጠርኩ/ቤቴ ለምን ተፈተሸ/ለምን ተመረመርኩ፣ ወዘተ› የሚሉ ሰዎች ናቸው፡፡ በማንነት መስመር ሰብዓዊ መብት ስለመነካቱ አሳቢ መስለው የሚመፃደቁብን አገሮች፣ ከማንነት ጋር የተያያዘ የሽብርና የጦርነት ጥቃት ሲደርስባቸው ለቀውጢ ጊዜ ጥንቃቄና የተረገዘ አደጋ ለማምከን ከእኛ የባሰ ነገር ሲያደርጉ ዓይተናል፡፡ ቀውጢ ሁኔታ በሌለበት ጊዜም የሽብር ምንጭ ይሆናል ያሉትን ማንነት በተለየ የስለላ ዕይታ ውስጥ አስገብተው የሰዎችን የግል ሚስጥር በድብቅና በርቀት ዕለት በዕለት እንደሚበረብሩ ይታወቃል፡፡ ከዚህ ሁሉ አኳያ፣ ሳንወድ እያመመን የምናደርገው ጥንቃቄ በሞራል ከእነሱ ያበልጠን እንደሆን እንጂ አያሳንሰንም፡፡

በጥገኝነትና በቀውስ ሁኔታ ውስጥ መሆናችንን አስተውለን ከውጭ የሚመጣብንን ጫናና የተዛባ አመለካከት ለማለዘብና ለማቃናት ብልህ ሥራ ከመሥራት ጋር፣ የሕወሓት ጦረኞች የከፈቱትን አማሽና ሰው አስጨራሽ ጦርነት በቶሎ አሸንፎ የትግራይ ሕዝብ ወህኒ የገባ ህሊናውንና የተሰለበ ነፃ ድምፁን መልሶ እንዲያገኝ ማስቻል ነው፡፡ ሰው አስጨራሹን ጦርነት በቶሎ በማሸነፍ ተግባር ውስጥ ፖለቲካ የሞተባቸው የሕወሓት ጦረኞች የትግራይን ሕዝብና ወጣት በምን ፕሮፓጋንዳ አስክረው ለአረመኔያዊ ተግባር እንደሚያሰማራቸው መረዳት፣ ያንን መርዝ የሚያረክስ ተስፋና ውጥን ላይ መክሮ ዘክሮ ሕዝብን ከሕወሓት ወህኒ ማውጣትና የጦርነቱን እየታደሰ የመመላለስ ዕድል ማንኮታኮት ያስፈልጋል፡፡ መንግሥትና ፖለቲከኞች ይህ አደራ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡

የተሸነፈውን ሕወሓት ከፈጣጠራቸው የሽብር ተቀጽላዎቹ ጋር የሚያከስምና የመላው ኅብረተሰባችንን የተሻለ ሕይወት ተስፋ የሚያበራ የልማት ርብርብ ማቀጣጠል ተከታዩ ተግባራችን ነው፡፡ በውስጥም በውጭ ያሉ ልጆች በአጭር ታጥቆና አንጀትን አስሮ የብርና የውጭ ምንዛሪ ጥሪትን በተለያየ መልክ አስተባብሮ የማንሠራራትና የመልሶ ግንባታ ተጋድሎው የሚካሄድበት ዋና ምዕራፍ ያለው እዚህ ላይ ነው፡፡

ከጎረቤቶቻችን ጋር ያለን የአጋርነት ግንኙነት፣ ፅናትም፣ መንሸራተትም፣ አገም ጠቀምም የተንፀባረቀበት ነበር፡፡ እነዚህ መገለጫዎች የጉርብትና ግንኙነታችንን ችግሮች ከእነ ምክንያቶቻቸውና ከድክመቶቻችን ጋር በደንብ መርምሮ የእኔን ጉርብትና ጣል ጣል አደረጉት/አገለሉት፣ ወዘተ የሚል ቅሬታ በማይፈጥር አኳኃን ዙሪያ ግንኙነትን መጠገን ሌላው ተግባር ነው፡፡

የተጠቃቀሱትን ሁሉንም ተግባሮች የሚያላልሳቸው ደግሞ የሁሉም ትልም ወደ አንድ ወንዝ የሚያመራ መሆኑ ነው፡፡ በታደሰ ጉርብትናና በለስላሳ ዓለም አቀፍ ግንኙነት ውስጥ ሆኖ በአግባቡ ነፃ አገር ነን ለማለት በሚያበቃ ሁለገብ የልማት ተጋድሎ ላይ አለን የምንለው ዕውቀት፣ ብልኃት፣ ወኔና እልህ ሁሉ ማፍሰስ፣ ብሔራዊ (አገራዊ) የአርበኝነት ግዴታችን ነው፡፡

(ይህ አጭር ጽሑፍ፣ በዚህ ቀውጢ ሰዓት ደህነኛውንና ለሕወሓት መሣሪያ ሆኖ ያደባውን ለይቶ ማወቅ ከባድ መሆኑን ለተረዱ፣ የደሴና የኮምቦልቻ ዓይነት ከውስጥ የመጠቃት ልምድ እንዳይደገም ለህልውናችን አስፈላጊ ጥንቃቄ ሁሉ መወሰድ እንዳለበት ለተገነዘቡ፣ በውስጥና በውጭ ላሉ የአገር ልጆች (ሔርሜላ አረጋዊ ጨምሮ) መታሰቢያ ይሁንልኝ፡፡)        

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...