Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሕዝባችንን ከጦርነት ውስጥ ብቻ ሳይሆን ከዕርዳታ ጠባቂነት አስተሳሰብ ማውጣት አለብን›› ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር)፣ የገንዘብ ሚኒስትር ደኤታ

ከሦስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ የተከሰተው ለውጥ ወደ መጀመርያው አሠላለፍ ካመጣቸው አዳዲስ ፊቶች ውስጥ ኢዮብ ተካልኝ ቶሊና (ዶ/ር) አንዱ ናቸው፡፡ በኢሕአዴግ መዳፍ ሲዘወር የነበረውን ምጣኔ ሀብት ወደ ትክክለኛው መስመር ለማስገባት ከለውጡ በፊት በግል ድርጅት ውስጥ፣ እንዲሁም እንደ ዓለም ባንክ ባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ በጥቅሉ ለ18 ዓመታት መሥራታቸው ጠቅሟቸዋል፡፡ በእነዚህ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከቀድሞው ፕላንና ልማት ኮሚሽን ኃላፊነት ወደ ገንዘብ ሚኒስትር ደኤታነት የተሸጋገሩ ሲሆን፣ የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያና የአሥር ዓመቱ የልማት ዕቅድ ላይ አሻራቸውን አኑረዋል፡፡ ይሁን እንጂ አገገመ ሲባል በጦርነት ምክንያት ወደ ሌላ አዙሪት ውስጥ የገባው የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት፣ ከሜሪላንድ ስኩል ኦፍ ፐብሊክ ፖሊሲ የተመረቁትን ፖለቲካል ኢኮኖሚስት ሥራቸውን ከባድ ቢያደርገውም፣ ኢኮኖሚው አሁንም ትልቅ አቅም እንዳለው ያምኑበታል፡፡ አሸናፊ እንዳለ ከኢዮብ (ዶ/ር) ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡

ሪፖርተር፡- በአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ሥር የማክሮ፣ የመዋቅራዊና የዘርፍ ለውጦችን ለማምጣት ከሦስት ዓመት በፊት የጀመራችሁት ንቅናቄ ዛሬ የት ደርሷል?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ዘላቂና ጥራት ያለው ዕድገት ለማስገኘት ትልቅ ዕቅድ ይዘን ነበር፡፡ የሪፎርም ሐሳቡን የኢትዮጵያ ሕዝብ ገዝቶት ነበር፡፡ ግን ሕወሓት በጀመረው ጦርነት ምክንያት ባለፈው አንድ ዓመት ብዙ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይህ እንግዲህ ኢኮኖሚው ከኮሮና ወረሽኝ ማገገም በነበረበት ጊዜ የመጣ ጉዳት ነው፡፡ ግን ለአንድም ሰከንድ ዓይናችንን ከሪፎርሙ ላይ አልነቀልንም፡፡ ማሻሻያዎቹን ቀድመን ባንጀምር ኖሮ ዛሬ ኢኮኖሚው ከባድ ችግር ውስጥ ይገኝ ነበር፡፡ አሁን ግን በየዘርፉ ውጤታማ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ በተለይ የባንክ ዘርፉ ትልልቅ ትርፎችን እያስመዘገበ ነው፡፡ ንግድ ባንክ እንዲያውም ትሪሊዮን ጥግ ደርሷል፡፡ ብድር ያዝ አድርገን ነበር፡፡ ነገር ግን ኢኮኖሚውን በቅርብ ስንከታተል ስለቆየን፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ አስፈላጊነቱን ዓይተን ለቀቅ አድርገናል፡፡ ግብርና ላይ ትልቅ መነቃቃት አለ፡፡ የማዕድን ዘርፉ ተሻሽሎ ትልቅ የውጭ ምንዛሪ እያስገኘ ነው፡፡ የድንጋይ ከሰልን በአገር ውስጥ እየተካን ነው፡፡ ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ የካፒታል ገበያ እንጀምራለን፡፡ ይኼ ትልቅ መንደርደሪያ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ግን አይኤምኤፍ የዚህ ዓመት የኢትዮጵያ ዕድገት ትንበያ ሳያደርግ ቀርቷል፡፡ ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን በጦርነት ከሚታመሱ አገሮች ተርታ እኩል ያደርጋታል ማለት ነው፡፡

ዶ/ር ኢዮብ፡- ባለፈው ዓመት ስድስት በመቶ አድገናል፡፡ የዚህ ዓመትም እዚህ አካባቢ ነው፡፡ ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሲነፃፀር የእኛ ትልቅ ዕድገት ነው፡፡ አይኤምኤፍ የዚህ ዓመት ትንበያውን የዘለለው ሠራተኞቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ የኢኮኖሚው ሁኔታ ላይ የማጣራት ሥራ ስላላከናወነ ነው፡፡ አጣሪ ቡድን ያላኩት በጦርነቱ ምክንያት ነው ቢሉም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የፀጥታ ሁኔታ ቡድኑን ላለመላክ የሚያደርስ አልነበረም፡፡

ሪፖርተር፡- አይኤምኤፍ አጣሪ ቡድኑን ያልላከው በምዕራባውያኑ ጫና ነው ማለት እንችላለን?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ምዕራባውያኑ አንዴ አዲስ አበባ ተከባለች፣ አንዴ ሚሌ ተይዟል እያሉ ሠራተኞቻቸውን ሲያስወጡ ነበር፡፡ የአይኤምኤፍም የዚህ ዘመቻ አካል ሊሆን ይችላል፡፡ ፕሮፖጋንዳው ውዥንብር መፍጠር ላይ ተሳክቶም ሊሆን ይችላል፡፡ የምዕራባውያን ሠራተኞች ከኢትዮጵያ ለመውጣት መራኮት ግን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ገቢ  ነው የፈጠረው፡፡ የእነሱ ስህተት ለእኛ ገቢ ሆኗል፡፡

ሪፖርተር፡- የጦርነቱን ጉዳት በምጣኔ ሀብቱ ላይ እንዴት ይገለጻል?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ትልቅ ጉዳት ነው፡፡ ሕወሓት እስከ ዛሬ ያደረሰው ጉዳት አንሶት፣ አላስፈላጊ የመደናበር ጦርነት ከፍቷል፡፡ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ዋናው ተጎጂ ደግሞ የትግራይ ሕዝብ ነው፡፡ ከጦርነቱ ነፃ በወጡ አካባቢዎች ያየነው ጉዳት እጅግ ከባድ ነው፡፡ እጅግ ብዙ የመልሶ ማልማት ሥራ ከፊታችን ይጠብቀናል፡፡ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ሞራልና እሴት የምንፈትንበት ሰዓት ደርሷል፡፡ ትልቅ የመልሶ ማልማት ፍኖተ ካርታ እየነደፍን ስለሆነ፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውነት ሊደግፈን የሚፈልግ መሆኑን በቅርቡ በተግባር እንፈትናለን፡፡

ሪፖርተር፡- ለመልሶ ማልማቱ ምን ያህል ሀብት ለማሰባሰብ ታቅዷል? ከውስጥና ከውጭስ?

ዶ/ር ኢዮብ፡- የመጀመርያው ሥራ በጦርነቱ የተጎዱና የተፈናቀሉ ሰዎችን መልሶ ማቋቋም ነው፡፡ ቤታቸውን፣ እርሻቸውን፣ ከብቶቻቸውን ስላጡ ምትክ ይፈልጋሉ፡፡ ማኅበራዊ አገልግሎቶች፣ ትምህርት ቤቶችና የጤና ማዕከላት፣ እንዲሁም መሠረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡ እነዚህን ገንብተን ቶሎ ወደ ሥራ ማስገባት አለብን፡፡ በየዘርፉ ባለሙያዎች ተልከው እያጠኑ ነው፣ አላለቀም፡፡ በፊት ለትግራይ ብቻ የመልሶ ማልማት ፍኖተ ካርታ ተሠርቶ ነበር፡፡ እሱ ጊዜያዊ አስተዳደሩ መቀሌ እያለ ነበር፡፡ አሁን ባለሙያዎች የአፋርና የአማራ ክልልን እያጠኑ ነው፡፡ ሕወሓት ሌላ ጦርነት ካወጀ በኋላ በትግራይ የደረሰውን ጉዳት ደግሞ ገና እናጠናለን፡፡ መንግሥት ያለውን አቅም ሁሉ መልሶ ማቋቋም ላይ ያውላል፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በታክስ ላይ ጭማሪዎችን ሊያደርግ አስቧል? በጀት ለማዳረስ ፕሮጀክቶችን ያጥፋል?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ፕሮጀክቶችን እንደገና እያየን ነው፡፡ የተወሰኑትን ለአንድ ዓመት ብናሳድር የዓለም መጨረሻ አይሆንም፡፡ ያሉትም ፕሮጀክቶች አፈጻጸማቸው ሊቀንስ ይችላል፡፡ ምክንያቱም መንግሥት የሁሉንም ወጪ መሸፈን ስለሚከብደው ነው፡፡ ኢኮኖሚውን በዚህ ፍጥነት ማስቀጠል ምሽግ ከመስበር አይተናነስም፡፡ ኢኮኖሚው ለአደጋዎች ደንዳና ሆኖ እዲቀጥል ልክ እንደ ጦርነቱ ታክቲክ እየቀያየርን እንቀጥላለን፡፡ የውጭ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት ለመግታት ያልተሞከረ ነገር የለም፡፡ ግን አሁን ያገኘነው ወታደራዊ የበላይነት ሁሉንም ነገር ይቀይራል፡፡

በታክስ ላይ የተለየ ምጣኔ (Tax Rate) አናመጣም፡፡ ግን ለውጦች ይኖራሉ፡፡ ታክስ የመሰብሰብ አቅማችንና ቴክኖሎጂን መጠቀም ላይ ትልቅ ክፍተት እንዳለ ግምገማ ላይ ነበርን፡፡ የታክስ አሰባሰብ መፍጠን አለበት፡፡ ሱር ታክስና ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ ክለሳ እያካሄድን ነበር፡፡ ነገር ግን አስቸኳይ ስላልሆነ ለአንድ ዓመት ልናቆየው እንችላለን፡፡ እንዲህ ዓይነት ለውጦችን ማምጣታችን አይቀርም፡፡ ግን ደግሞ እንደ የንብረት ታክስ (Property Tax) ያሉትን ደግሞ ፈጠን አድርገን በሚቀጥሉት ወራት ወደ ሥራ እናስገባለን፡፡ እንደዚህ ዓይነት በቀላሉ ተጨማሪ ገቢ ሊሆኑ የሚችሉ አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- አገር በቀል ሪፎርሙ ሲጀምር ከውጭ አሥር ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ ቃል የተገባው አልመጣም፡፡ የዓለም አቀፍ አበዳሪዎች የዕዳ ሽግሽግ ላይ ቅድመ ሁኔታ በመቀመጡ የአይኤምኤፍ ብድር ቆሟል፡፡ መንግሥት እጅ ላይ ሌሎች አማራጮች አሉ?

ዶ/ር ኢዮብ፡- የዕዳ ሽግሽጉን በቅርበት እየተከታተልን ነው፡፡ ፈረንሣይና ቻይና የሚመሩት የብድር ኮሚቴም በየጊዜው እየተገናኘ የትኞቹ የኢትዮጵያ ዕዳዎች መሸጋገር እንዳለባቸው እየመከረ ነው፡፡ በተለይ የግሉን ሴክተር እንዴት ማካተት እንዳለባቸው እየመከሩ ነው፡፡ የአይኤምኤፍ ብድር በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የሚያልቅ ነበር፡፡ ግን በዚያ ጊዜ ውስጥ አይኤምኤፍ ቡድኑን ልኮ የኢኮኖሚ ምልከታ ስላላደረገ፣ ብድሩም ሳይለቀቅ (ወደ ሦስት ቢሊዮን ዶላር) ጊዜው አልፏል፡፡ አሁን ፀጥታው ሲስተካከል በአጭር ጊዜ ውስጥ አይኤምኤፍ ሰዎቹን ወደ ኢትዮጵያ ልኮ ብድሩን እንደሚለቅ ተስፋ እናደርጋል፡፡ ቃል የተገባውን አሥር ቢሊዮን ዶላር በተመለከተ መቆም ሳይሆን ገንዘቡ ሳይለቀቅ ዘግይቷል፡፡ ካለፈው ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ከውጭ ስንጠብቃቸው የነበሩ የበጀት ድጋፎች እየመጡ አይደሉም፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት የሕልውና ጦርነት መጥቶበት እንጂ ሰላም ፈላጊ ነው፡፡ መጀመርያ አካባቢ ሕወሓት ተጎዳሁ በማለት የፈጠረው ውዥንብር በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ላይ ብዥታ ፈጥሯል፡፡ ብዥታው ሲጠራ እነዚያን ገንዘቦች መልሰን ገቢ አናደርጋቸዋለን፡፡ የአይኤምኤፍ ሁለት የብድር መስኮቶች (EFF & ECF) ጊዜ ካለፈባቸው ወዲህ እነሱን የሚተካ ጥያቄ አቅርበናል፡፡ እስካሁን ቃል ተገብተው ያልተለቀቁ ድጋፎች ከውጭ አንድ ላይ ከመጡልን የመልሶ ማቋቋም ሥራችንን በሚገባ ያግዙልናል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአይኤምኤፍ ልዩ ወጪ የመጠቀም መብት (Special Drawing Right (SDR)) ኢትዮጵያ እስካሁን የወሰደችው ገንዘብ አለ?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ከራሳችን የመጠቀም መብት 600 ሚሊዮን ዶላር ወስደናል፡፡ ሁለት አማራጭ ነው ያለው፡፡ ወይ ገንዘቡን መጠቀም ነው፣ እኛ ግን የውጭ ምንዛሪያችን መጠባበቂያ (ሪዘርቭ) ላይ ጨምረን ተቀማጭ አድርገነዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አፍሪኤግዚም ባንክም ወደ አሥር  ቢሊዮን ዶላር ለኮሮና ወረርሽኝ ለአፍሪካ አገሮች ብድር አቅርቧል፡፡ እሱንም መጠቀም አስባችኋል?

ዶ/ር ኢዮብ፡- አሁን የተማርነው አንድ ጥሩ ነገር ከአፍሪካ ባንኮች ጋር በቅርበት መሥራት እንዳለብን ነው፡፡ ጥሩና ጠንካራ የአፍሪካ ባንኮች አሉ፡፡ የኮሜሳ ባንክ (TDB) ጠንከራ እየሆነ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ በኮሜሳ ባንክ ውስጥ ምን ያህል አክሲዮኖች አሏት?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ኢትዮጵያ ትልቋ ባለአክሲዮን ናት፡፡ ባንኩ ብዙ የብድር አማራጮችን እያቀረበ ነው፡፡ ወርቅ የማውጣት ፕሮጀክቶችን ጨምሮ እነዚህንም እንጠቀማለን፡፡ ጠንካራ የአፍሪካ ባንኮች መመሥረት እንዳለባቸው ግንዛቤ አለ፣ ቢዘገይም፡፡ ኮሜሳ የእኛ ባንክ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በቅርቡ ገንዘብ ሚኒስቴር ከሞሮኮ ጋር በኢትዮጵያ የማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ለመጀመር ስምምነት ላይ ቢደርስም ግንባታው አልጀመረም፡፡ በቻይናው ፖሊ ጂሲኤል የተጀመረው የተፈጥሮ ጋዝ ፕሮጀክትም እንደተቋረጠ ነው፡፡

ዶ/ር ኢዮብ፡- እነዚህ ሁለቱ በጣም አስፈላጊ ግን ደግሞ ውስብስብ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡ የማዳበሪያ ፋብሪካው ከተፈጥሮ ጋዝ የጥሬ ዕቃ ግብዓት ይፈልጋል፡፡ በሚኒስትሮች የሚመራ ከፍተኛ ኮሚቴ ተቋቁሞ እነዚህን ሁለቱን ፕሮጀክቶች እየተከታተለ ነው፡፡ በሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ማለቅ አለባቸው፡፡ ፖሊ ጂሲኤል የተባለው የቻይና ኩባንያ የተጠየቀውን መሥፈርት አሟልቶ በቅርቡ ወደ ሥራ ይመለሳል ብለን እንጠብቃለን፡፡ የተፈጥሮ ጋዝ ውጤታማነት ጥናት ያለቀለት ነው፡፡ ኩባንያው መሥፈርቶቹን ካላሟላ ግን ፈቃዱን ሰርዘን ለሌላ እንሰጣለን፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ የውጭ ኢንቨስተሮች ፕሮጀክቶችን እያቋረጡ እየወጡ ነው፡፡ የኢንቨስትመንት አለመረጋጋቱን እንዴት ያዩታል?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ ሳፋሪኮም ከኢትዮጵያ ወጥቻለሁ ባለ ከሦስት ቀናት በኋላ ደግሞ ተመልሶ መጥቷል፡፡ የተወሰኑ የውጭ ኢንቨስተሮች በዓለም አቀፍ ሚዲያው በተከፈተብን ፕሮፓጋንዳ ተወናብደዋል፡፡ ግን ደግሞ በዚህ ዓመት የመጀመርያ ሩብ ዓመት የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ በ32 በመቶ አድጓል፡፡ ይኼ ነው ግራ የሚያጋባው፡፡ ጦርነቱ እንዳለቀ ትልቁ ሥራችን የኢንቨስተሮችን በራስ መተማመን መገንባት ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡- ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውነት በፕሮፓጋንዳ ተወናብዶ ነው? ወይስ በራሱ ውሳኔ ነው?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ታቅዶ የተደረገ ጫና ነው፡፡ በግለሰብ ደረጃ የተወሰኑ ኢንቨስተሮች ተወናብደው ሊሆን ይችላል፡፡ ግን የምዕራባውያኑና የተቋማቶቻቸው ጫና የታቀደና በሚዲያ የታገዘ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አፍሪካ የአሜሪካና የቻይና ጦርነት ዓውድማ እየሆነች ነው?

ዶ/ር ኢዮብ፡አፍሪካ የራሷን ዓላማና መንገድ ለይታ ማስፈጸም አለባት፡፡ ለማንም የጦርነት ዓውድማ እንድትሆን የሚፈቅድ አፍሪካዊ ትውልድ መኖር የለበትም፡፡ አፍሪካ የራሷን ኃይል መፍጠር ትችላለች፡፡

ሪፖርተር፡- የቻይና ሲልክ ኤንድ ሮድ የመሠረተ ልማት ግንባታ ብቻ ነው?

ዶ/ር ኢዮብ፡- አፍሪካ በራሷ አቅም ሰላምና ልማት ማምጣት ላይ ልታተኩር ይገባል፡፡ ይኼንን በዚሁ እንለፍ፡፡

ሪፖርተር፡- የመንግሥት ድርጅቶችን ወደ ግል ለማዞር የተጀመሩ ዕቅዶችስ ከምን ደርሰዋል?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ብዙ ኪሳራ ውስጥ የነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን ትርፋማ አድርገናል፡፡ የመጀመርያው የግል ቴሌኮም ድርጅት ሥራ ለመጀመር ዝግጅቱን እያጠናቀቀ ነው፡፡ የኢነርጂ ዘርፉን ወደ ግል ማዞር ላይ ከዕቅዳችን ትንሽ ዘግይተናል፡፡ በተለይ የኃይል ማከፋፈል ሥራን ወይ ወደ ግል ከማዞር ወይም ደግሞ በጣም ማዕከላዊ ከማድረግ አማራጭ እያየን ነው፡፡ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል፡፡ የስኳር ፕሮጀክቶችን ወደ ግል የማዞር ሒደቱ የተቋረጠው በጦርነቱ ሰበብ ገዥዎችና ባለሙያዎች ወዳሉበት ሄደው ማየት ስላልቻሉ ነው፡፡ ባቡርን በተመለከተ እንዴት የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ እንዳለብን እያየን ነው፡፡ ከጂቡቲ መንግሥት ጋርም እየመከርን ነው፡፡ አሁን የኢትዮጵያ ባቡር ኮርፖሬሽንን በመንግሥት ድርጅቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ሥር አካተነዋል፡፡ ይኼንንም ባስቀመጥነው የኮርፖሬት አስተዳደርና ‹‹ሆልዲንግ›› ሥር ሁሉም የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ለማካተት የፍኖተ ካርታ መሠረት ለማከናወን ነው፡፡ በአንድ ባቡር መስመር ውስጥ ብዙ ሐዲዶችና ማመላለሻዎች እንዲኖሩ አቅደናል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮ ቴሌኮም ሁለተኛ ፈቃድና የ40 በመቶ አክሲዮኖች ሽያጭስ በታቀደው ፍጥነት እየሄደ ነው?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ጥሩ እየሄዱ ነው፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ባለው ጦርነት ምክንያት ልናገኝ ካሰብነው ገቢ የወረደ ከቀረበልን ጨረታውን ልናራዝም እንችላለን፡፡ ይኼንን በሚቀጥሉት ወራት ውስጥ እንወስናለን፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት በተከታታይ ሲያደርጋቸው የነበሩት የብድርና የምንዛሪ ዋጋ መቀነስ የዋጋ ግሽበትን ከማቀጣጠል አንፃር ትክክለኛ ውሳኔ ናቸው?

ዶ/ር ኢዮብ፡- የዋጋ ግሽበት ሊኢኮኖሚው መዋቅራዊ ተግዳሮት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ደግሞ የፊሲካልና የሞኒተሪ ዕርምጃዎችን እየወሰድን ነው፡፡ የባንኮችን ተቀማጭ ገንዘብ ከፍ አድርገናል፡፡ ከፍተኛ የገንዘብ ሥርጭቱም ለዋጋ ግሽበቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ይኼ ከፍተኛ ገንዘብ በምርት እንዲታገዝ መሥራት አለብን፡፡ የእሑድ ገበያዎችንም እያቋቋምን ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ገበያ የዋጋ ጭማሪም የአገር ውስጡን እያባባሰው ነው፡፡ የአገር ውስጥን ምርታማነት ለማሳደግ ግን ዋናው ነገር ጦርነቱ ማለቅ አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- የውጭ ጫናዎችና የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለአገር ውስጥ ምርቶች መልካም ዕድል ሊሆኑ ይችላሉ?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ይኼ በእርግማን ውስጥ እንደሚገኝ ምርቃት ነው፡፡ በተለይ የግብርና አብዮት ለማምጣት ሊያግዝ ይችላል፡፡ ሌላው ከውጭ ዕዳ ለመላቀቅና የዕርዳታ ጠባቂነት ባህልን ሊያጠፋ ይችላል፡፡ ከሕወሓት ትሩፋቶች አንዱ ሕዝቡን ዕርዳታ ጠባቂ አድርጎ መሄዱ ነው፡፡ ከትግራይ ሕዝብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሴፍቲኔት ተገልጋይ ነው፡፡ ከተማረኩት የትግራይ ተወላጆች ወታደሮች ኪስ ውስጥ እንኳ የሴፍቲኔት ካርዶችን አግኝተናል፡፡ የፈንታሌ፣ የሸዋ፣ የባሌና የሌሎች አካባቢዎች ነዋሪዎች የጀመርነውን የስንዴ እርሻ ዛላ እያዩ ተገርመዋል፡፡ ለዓመታት ዕርዳታ ጠባቂ የነበሩ ማምረት እንደሚቻል አይተዋል፡፡ ሕዝባችንን ከጦርነት ብቻ ሳይሆን ከዕርዳታ ጠባቂነት አስተሳሰብ ነፃ ማውጣት አለብን፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ራሱ የውጭ ዕርዳታና ብድር ከመጠበቅ ራሱን አላላቀቀም፡፡ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነት ላይ ለምን አልተሠራም? ልክ እንደ ፖለቲካ ሉዓላዊነት ማለት ነው?

ዶ/ር ኢዮብ፡- አሁን የተፈጠረው ሁኔታ ሁሉንም ነገር እንደገና እንድንጠይቅ አድርጎናል፣ ዕርዳታ ከውጭ መጠበቅን ጨምሮ፡፡ አርበኝነት፣ ብሔራዊ ስሜትንና በአገር ምርት መኩራትን በሕዝቡ ውስጥ መትከል አለብን፡፡ ቻይናና ኮሪያ ከውጭ ቴሌቪዥን እንዳይገባ ከልክለው ነው የራሳቸውን ምርት ከፍ ያደረጉት፡፡ ለዓመታት ከራሳቸው ጉርስ ቀንሰው ሲቆጥቡ ነበር፡፡ በኢኮኖሚ ራስን ለመቻል አንድ ትውልድ መስዋዕትነት መክፈል አለበት፡፡ ይኼም ትውልድ በራሱ ምርት መጠቀም በመጀመር ያንን መስዋዕት መክፈል መቻል አበበት፣ ቅጠል መብላትም ካለብን ማለት ነው፡፡

ሪፖርተር፡-  ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን በተመለከተ ከቀረጥ ነፃ የሚደረጉትን ምርቶችና አገልግሎቶች መለየት ተችሏል?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ምርትና አገልግሎቶችን ለይተን ጨርሰናል፡፡ ቴክኒካዊ ሥራው አልቋል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ ኮሚቴው ዓይቶ ለማፅደቅ ጊዜ ሲያገኝ የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣናን ኢትዮጵያም ታስጀምራለች፡፡ በዚህ ዓመት ይጠናቀቃል፡፡

ሪፖርተር፡- አጎዋ (AGOA) ከተቋረጠ በኢንዱስትሪ ፓርክ ውስጥ ያሉ አምራቾች ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲሸጡ ሊፈቀድላቸው ይችላል?

ዶ/ር ኢዮብ፡አሜሪካ አጎዋ በዘላቂነት ታቋርጣለች ብለን አንገምትም፡፡ አሜሪካኖች ካደረጉት ምንም ትርጉም የማይሰጥ ውሳኔ ነው የሚሆነው፡፡ ለእኛም ለእነሱም ማቋረጡ አይጠቅምም፡፡ ካደረጉት ሌሎች የገበያ አማራጮችን እናፈላልጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ቻይና በሰሞኑ የዳካር ፎካክ (FOCAC) ስብሰባ ለአፍሪካ ተጨማሪ ድጋፎችን ቃል ገብታለች፡፡ ኢትዮጵያ ምን ያህል ትጠብቃለች?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ቻይና ለኢትዮጵያ ጠንካራና የማይዋዥቅ ድጋፏን ትቀጥላለች፡፡

ሪፖርተር፡-  የኢትዮጵያ ግማሽ የውጭ ዕዳ የቻይና ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ምዕራባዊያኑ ብድር ካልተሸጋሸገ አላለችም፡፡ ምዕራባዊያን እንደሚሉት ለልማትና ድህነትን ለመዋጋት ቆመዋል ይቻላል?

ዶ/ር ኢዮብ፡- የዕዳ ሽግሽግ ለእኛ ጥሩ ነው፣ አንጠላውም፡፡ ግን ኢትዮጵያ ዕዳዎቹን መክፈል አቅቷት ሰዓቱን አዛንፋ አታውቅም፡፡ የዕዳ ሽግሽግ ማለት ዕዳውን የተወሰነውን ለጥቂት ዓመታት አራዝሞ ገንዘቡን ለልማት ማዋል ነው፡፡ ያለውን ዕዳ ስታሸጋሽጉ ሌላ አትወስዱም መባሉን በጥሩ ጎኑ ነው የምናየው፡፡

ሪፖርተር፡- ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው ስድስት በመቶ ያህሉ ለማበረታቻ ተብሎ ሲሰጥ እንደነበር ጥናቶች አመልክተዋል፡፡ አብዛኞቹ ግን ማበረታቻዎቹን ወስደው እየዘጉ ነው፡፡ የማበረታቻ ውጤት ምንድነው?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ለዚህ ነው ማበረታቻዎቹ በሙሉ ለገንዘብ ሚኒስቴር ሥር ብቻ እንዲፈቀዱ ያደረግነው፡፡ የማበረታቻ ምላሽ ምን እንደሆነ ለይቶ አዳዲስ ዕርምጃዎችንም ማሻሻያዎችንም ለማድረግ ጥልቅ ጥናት እያደረግን ነው፡፡ ማሻሻያዎችን ለማድረግ አዲስ የማበረታቻ መመርያ አዘጋጅተን በሚኒስትሮች ምክር ቤት እስኪፀድቅ እየጠበቅን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በጦርነቱ ምክንያት ሳፋሪኮም በደቡብ ኢትዮጵያ ብቻ ነው መሠረት ልማት የሚገነባው መባሉ እውነት ነው?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ሳፋሪኮም ፈቃድ ለማሸነፍ የቻለው በጣም ጥሩ የአዋጭነት ጥናት ስላቀረበልን ነው፡፡ በገባው የኮንትራት ስምምነት መሠረት በመላ አገሪቱ ኔትወርክ ለማዳረስ ቃል ገብቷል፡፡ መሠረት ልማት በማይገነባበት አካባቢ ከኢትዮ ቴሌኮም ለመከራየት ድርድር እያደረገ ነው፡፡ ሁሉም አካባቢዎች በስምምነቱ ቀነ ገደብ መሠረት የተሟላ ኔትወርክ ያገኛሉ፡፡ ከፋይበር ኦፕቲክስና ከሳተላይት ኔትወርክ የሚያመቸውን መጠቀም ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኮች አትራፊ ስለሆኑ ብቻ ኢኮኖሚው በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ማለት ይቻላል?

ዶ/ር ኢዮብ፡ቁልፍ የሆኑ መሥፈርቶችን ስንለካ ኢኮኖሚው በጥሩ ሁኔታ ላይ ነው፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንትን ፍሰት፣ የውጭ ንግድ ዕድገትና ሌሎች ማሳያዎች ይኼን ይገዛሉ፡፡ ኢኮኖሚው በከፍተኛ ጫና ሥር መሆኑ ሀቅ ነው፡፡ ነገር ግን በከፍተኛ ሁኔታ የሚቋቋም መሠረቱ ሰፊ ኢኮኖሚ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ ካቢኔ ተቋቁሞ የተቋማት ማሻሻያ በመዘግየቱ በርካታ ፕሮግራሞችና ፕሮጀክቶች አየር ላይ እየተንሳፈፉ መሆናቸው ይነገራል፡፡

ዶ/ር ኢዮብ፡- የተቋማት ሽግሽግ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ የአሥር ወራት ጥናት ከፈጀ በኋላ የመጣ ነው፡፡ የአዳዲስ ተቋማት ሽግሽግና ኃላፊነት ለሚቀጥሉት አሥር ዓመታት የብልፅግና ዓላማዎች እስኪሳኩ ለውጥ እንዳይኖር ታስቦ የወጣ ነው፡፡ ተቋማትን ሽግሽጋቸው በአንድ ወር ውስጥ እንዲያልቅ ብለናቸው ነበር፡፡ ትራንስፖርትና ንግድ ፈጥነው ጨርሰዋል፡፡ አሁን ግን የተቀሩት ከ100 ቀናት እንዳያልፉ በአዲስ ዕቅድ ውስጥ ተካተዋል፡፡ በመደበኛ ሁኔታ ውስጥ ብንሆን ኖሮ ተቋም ማስተካከል አንድ ዓመት ይፈጅ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- በመጨረሻም ከኢትዮጵያውያን ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ዶ/ር ኢዮብ፡- ሁሉም ሰው እንዴት ለሁሉም ምቹ የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት እንደምንችል ማተኮርና መግባባት አለበት፡፡ ጠንካራ አገረ መንግሥት መገንባት አለብን፡፡ በድጋሚ የተኩስ ድምፅ መስማት የለብንም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የኦሮሞን ሕዝብ ታሪክ አልባ በማድረግ ታሪክ አይሠራም

በኢተፋ ቀጀላ​​  ከዛሬ ሃምሳ ዓመት ወዲህ ከተፈጠሩት የኦሮሞ ድርጅቶች መካከል ከኢጭአት በስተቀር፣...

የኢትዮጵያ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት ሥጋቶች

ዘ ኮንቨርሴሽን ላይ ‹‹What Next for Ethiopia and its...

‹‹ወልቃይት የአማራ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም እስትንፋስ ነው›› አቶ ዓብዩ በለው፣ የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት

ለወልቃይት የአማራ ማንነት መከበር የሚታገለው የልሳነ ግፉአን ድርጅት ፕሬዚዳንት...