Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ዕውቅናቸውን ተገን አድርገው አገራችንን ከሚያዳክሙ እንጠበቅ

ከሰሞኑ ከግንባር እየሰማን ካለነው መልካም ዜና ባሻገር ልብ የሚያደሙ መረጃዎችንም ሰምተናል፡፡ በሽብር ቡድኑ ተይዘው የነበሩ ከተሞች የደረሰባቸው ውድመት ሲታይ ወዴት እየሄድን ነው ያስብላል፡፡

በአንፃሩ ግን የተከፈተብንን ጦርነት በአጭር ለመቋጨት የሚቻል ስለመሆኑ የሚያመለክቱ ክስተቶች በመኖራቸው፣ ከድል በኋላ የሚጠበቅብንን ብርቱ ሥራዎች ከወዲሁ እንድናስብ የሚያደርግ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡

የጥፋት ኃይሉን በሥውር በመደገፍ ኢትዮጵያን የመበታተኑ ዕቅድ አስፈጻሚዎች የሆኑ ታዋቂ የሚባሉ ሰዎችን ሴራም ሰሞኑን ከሰማናቸው ዜናዎች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡

እንደ አገር ብርቱ ብለን ያከበርናቸው፣ ዕውቅና የሰጠናቸውና በየዘርፋቸው ጎምቱ ብለን ከምንጠቅሳቸው ሰዎች መካከል ስንደምራቸው የነበሩ የአገር ልጆች የማይሆን ቦታ ተገኙ ሲባል ማስደንገጡ አይቀርም፡፡

የአገር ሽማግሌ ስለመሆናቸው የመሰከርንላቸው ፕሮፌሰር፣ ዘመናዊ ግብይት ፈጣሪ አድርገን የሸለምናትና ያከበርናት ከኢትዮጵያ ትፍረስ አቀንቃኞች ጋር ተሠልፈው መታየታቸው ኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው ጦርነት ዘርፈ ብዙ ስለመሆኑ ያሳየናል፡፡

በዚህን ያህል ደረጃ አገር ለማፍረስ መነሳታቸው ለምን? ብለን እንድንጠይቅ ቢያደርገንም ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ይህ ክስተት ዓይናችንን የበለጠ ከፍተን አካባቢያችንን በንቃት እንድንጠብቅ በማድረጉ ረገድ እንደማንቂያ ደወል አድርገን መውሰድ ይገባናል፡፡

አሁንም ዕውቅናቸውን መሸሸጊያ ያደረጉ የሽብርተኛው ቡድን አገልጋዮች መሀላችን እንዳሉ ማሳያም ነው፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ ሀብታም ያደረገቻቸው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲቆጥሩ ዕድል የሰጠቻቸው ባለሀብቶች ቢሮ ውስጥ የጦር መሣሪያ ተደብቆ ተገኘ ሲባል ኧረ ማንን ነው የምናምነው? እንድንል ያደርገናል፡፡

ዶክተር እሌኒን እንዲህ ባለው አገር ለማፍረስ በሚደረግ ሸፍጥ ውስጥ እናገኛታለን ብሎ ማን ገመተ? ስለዚህ መሀላችን ቁጭ ብለው ያልተጠረጠሩ ስንት ይሆኑ? የአገራችንን ስቃይ ያበዙ፣ ቢቀናው ክላሽ ይዘው ከመተኮስ የማይመለሱ ብዙዎች ስለመኖራቸው ከዚህ ወዲያ ማሳያ የለም፡፡

ቀድሞ በነበረው መንግሥት የጥቅም ተጋሪ የሆኑ፣ ያለ ጨረታ ሥራዎች እየወሰዱ ሀብት አካብተው ከሀብታቸውም ሲያካፍሉ የነበሩና አሁን ደግሞ በሥውር ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦች ጉዳይ ሊያሳስበን ይገባል፡፡

ከመንግሥት የወገኑ በመምሰል የሽብርተኛውን ቡድን በተለያዩ መንገዶች ሲደግፉ የቆዩ ሰዎች በመንግሥት የሥልጣን ዕርከን ውስጥ ጭምር የሉም ማለት አይቻልም፣ አሉ!

ሥልጣናቸውን መከታ አድርገው እንዳይጠረጠሩ የሕዝብን ድምፅ እየሰሙ የአገር መከራን ያበዙ ከሃዲዎች ጥጋቸውን እንዲይዙ ካልተደረገ እየተሰማው ያለው ድል ውጤት አልባ ይሆናል፡፡

እንዲህ ባለው እኩይ ተግባር ውስጥ ያሉ በየትኛውም ቦታ የተሰባሰቡ አካላት የተሸፋፈኑበትን ጭንብል መግለጥ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ ወቅት እገሌ እንዲህ አያደርግም የሚባልበት ወቅት አይደለም፡፡ የህልውና ጉዳይ ነውና ጥርጣሬ ካለ ያለይሉኝታ መፈተሽ፣ መበርበርና እንዲጋለጡ በማድረግ ቀድሞ አደጋቸውን መከላከል ይገባል፡፡

አሸባሪው ቡድን በየቦታው ሰተት ብሎ የተለያዩ ከተሞች የገባውና ከተሞችን ያወደመው፣ ሕፃንና አዛውንት ሳይል ሲደፍርና ሲገል የነበረው ሕዝቡን መስለው መሀላችን በተቀመጡ ከሃዲዎች መረጃና ድጋፍ ተመርኩዞ ነው፡፡ ይህ በተግባርም ታይቷል፡፡

የጦር መሣሪያ ቀብሮ ጭምር አገር ሊያፈርስ የተዘጋጀ ቡድን ለጥፋት ያዘጋጀው ዕቅዱ በመሀልም በተለያዩ መንገዶች አይፈጸምም ብሎ መዘናጋት ስለማይገባ የትኛውም ወገን ንፁህ መሆኑን በሕግና አግባብ ባለው መንገድ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ደግሞ ማንኛውም ሰው ተባባሪ መሆን አለበት፡፡ ለምን እፈተሻለሁ አይሠራም፡፡ እገሌ ኧረ እዚህ ውስጥ አይገባም እየተባለ መተውም ዋጋ ያስከፍላል፡፡ ዶክተር እሌኒ የዶክተር ዓብይን ምስል የያዘ ቲሸርት አድርጋ ያየ ሰው እንዴት ይጠረጥራል?

ቤታቸው መሣሪያ ባይገኝም መሣሪያው ከሚያደርሰው ጉዳት በላይ አገር የሚያፈራርስ ዕቅድ ሲተነትኑ ተገኝተዋልና አሁንም መንግሥት ውስጡን ያጥራ፡፡ ዕውቅናቸውን ተገን አድርገው በሥውር አገር እየወጉ ያሉትን አደገኛ ሰዎች ለመያዝ በጥብቅ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ኅብረተሰቡም የራሱን ኃላፊነት እየተወጣ መቀጠል አለበት፡፡

አገር ለማዳን ጠበቅ ያሉ ዕርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ እንዲህ ያሉ ሰዎች አሁን ካልተደረሰባቸው ከድል በኋላም የአገር ነቀርሳ ሆነው መቀጠላቸው አይቀርምና ወንጀለኛን ከንፁኃን የመለየቱ ሥራ ትልቅ ቦታ ይሰጠው፡፡ ከአጥቂዎች እንጠበቅ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት