Friday, May 24, 2024

የሰሜኑ ጦርነትና የከበቡት ዓለም አቀፋዊ ፍላጎቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ጦርነት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ አዳዲስ ክስተቶችን ሲያስተናግድ ተስተውሏል፡፡ የጦርነቱ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች መስፋፋትን ጨምሮ፣ በጦርነቱ ውስጥ ፍላጎት ያላቸው አካላት መበራከት የግጭቱ አንድ ባህርይ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ክልል የነበራቸው ተሳትፎ በበርካታ አገሮችና ዓለም አቀፍ ተቋማት ወቀሳ ሲያስተናግድ የቆየ ሲሆን፣ በክልሉ ከ100 በላይ የአክሱም የንፁኃን ግድያን ጨምሮ በኤርትራ ወታደሮች የደረሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሳይቀር መገለጹ ይታወሳል፡፡ ከዚህ ባለፈም የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) አመራሮች በትግራይ ጦርነት ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ወገኖችና የሌሎች አገሮች መሣሪያዎች በጥቅም ላይ ውለዋል ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡

በቅርቡ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ ‹‹አፍሪካዊ ያልሆኑ አገሮች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ መሆኑ አሳስቦኛል›› በማለት ደብዳቤ የጻፉት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ሊቀ መንበር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ በጦርነቱ ኢራን፣ የቱርክና የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ጣልቃ እየገቡ ሊቢያን፣ ሶርያንና የመንን እንዳተራመሱ ሁሉ፣ ተመሳሳይ ሁኔታን በኢትዮጵያ እየፈጠሩ ነው ሲሉ መክሰሳቸውም ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ከትግራይ ተዋጊዎች ጎራ የተሠለፉና ኢትዮጵያዊ ያልሆኑ ነጭና ጥቁር ሰዎች ተሰውተዋል ብለዋል፡፡

በተለይ የሰሜኑን ጦርነት አስመልክቶ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ መንግሥትና ባለሥልጣናት ላይ በጣላቸው ማዕቀቦች ሳቢያ፣ ከመንግሥት ይልቅ ሕወሓትን የሚደግፍ አቋም አላቸው የሚል ትርክት መደመጥ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡ ይኼ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ ነው በሚል የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ የእጅ አዙር ጦርነት (Proxy war) እና ድቅል ጦርነት (Hybrid War) እያደረገ ነው ሲባልም ይደመጣል፡፡ እንዲህ ያሉና ያልተገቡ ያሏቸውን የውጭ፣ በተለይም በአሜሪካ የሚመራውን የምዕራቡ ዓለም ተፅዕኖዎች ለማውገዝ ሠልፍ ያደረጉት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሠራተኞች፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳዮቻቸውን ለመፍታት በቂ ዕውቀትና ጥበብ አላቸው፤››፣ ‹‹በውስጥ ጉዳዮቻችን ጣልቃ መግባት አቁሙ፤›› እና ‹‹No More›› ወይም ‹‹በቃ!›› የሚሉ መፈክሮችን ይዘው ታይተዋል፡፡ አንዳንዶቹም የእነ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ቶማስ ሳንካራ፣ ኔልሰን ማዴላና የተለያዩ ታዋቂ አፍሪካዊ መሪዎችን ፎቶግራፎች ይዘው ከሠልፉ ታይተዋል፡፡

በተደጋጋሚ በአገር ውስጥና በውጭ አገሮች በተለያዩ ከተሞች የተደረጉ የተቃውሞ ሠልፎች ላይ ከሚደመጡ ተቃውሞዎች አንዱ የምዕራቡ ዓለም በሕዝብ ከተመረጠ መንግሥት ይልቅ አሸባሪ ተብሎ ለተፈረጀው ሕወሓት ይበልጥ ሲያደሉ ይስተዋላሉ የሚል ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የምዕራቡ ዓለም ጦርነቱን አስመልክቶ በሚሰጣቸው አስተያየቶችና ምክረ ሐሳቦች ላይ በፌዴራል ፓርላማ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀውን ሕወሓትንና በሕዝብ የተመረጠውን መንግሥትን እኩል የማድረግ አዝማሚያዎችን ያሳያል ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሬድዋን ሁሴን (አምባሳደር) እና የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሬታሪያት የውጭ ቋንቋዎችና የዲጂታል ሚዲያ ኃላፊ ቢልለኔ ሥዩምን ጨምሮ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሲተቹ ይስተዋላሉ፡፡ በተጨማሪም መንግሥት የዓለም አቀፍ ተቋማትና የውጭ አገሮች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ነው ሲል በተደጋጋሚ ወቀሳን ሲሰነዝር የተስተዋለ ሲሆን፣ ይኼንንም የሚያጠይቅበትን ደብዳቤ ለዓለም ማኅበረሰብ መጻፉ ይታወሳል፡፡

ያም ሆነ ይህ አንድ ዓመቱን ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም. የተሻገረው የሰሜኑ ጦርነት አጥቂውና ተጠቂው እየተለዋወጠ ቢሰነብትም፣ ግጭቱ የሳበው ዓለም አቀፍ ትኩረት ግን ቀጥተኛ የአሜሪካ ወታደሮችን ተሳትፎ ሊጋብዝ ይችላል የሚል ሥጋትም ሲደቅን ተስተውሏል፡፡ ምንም እንኳን ይኼ ሐሳብ በአንዳንድ ባለሙያዎች የማይመስል ሥጋት ነው ተብሎ የሚያስተባበል ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካና የእስያ ጥናት ማዕከል መምህሩ ሳሙኤል ተፈራ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ይኼ የምዕራብ ዓለም ጥቅሙን ለማስጠበቅ የሚጠቀምበት የመጨረሻው አማራጭ ሊሆን ይችላል ይላሉ፡፡

እነዚህ ጣልቃ ገብነቶች ደግሞ በኢትዮጵያ የመንግሥት ግልበጣ ለማከናወን የታለሙ ናቸው የሚሉ ድምፆች ከመንግሥት ሳይቀር ይደመጣሉ፡፡ ቢልለኔ ሥዩም ኅዳር 21 ቀን 2014 ዓ.ም. በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንዳሉት፣ ‹‹በሰብዓዊ ዕርዳታ፣ በሰብዓዊ መብቶችና በዴሞክራሲ ስም ለመንግሥት ግልበጣ ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር የተለያዩ ዴሞክራሲያዊ ዕድሎችን ያላግባብ ከጥቅም ላይ እንደሚውሉ ግልጽ ነው፤› ያሉ ሲሆን፣ ‹‹ከሉአላዊውና ከተመረጠው የኢትዮጵያ መንግሥት ጋር መሥራትን ሊተካ የሚችል አንዳች የለም፡፡ በልሒቃን ቡድኖች ከተቀነባበረና በሕዝብ ካልተመረጠ የሽግግር መንግሥት ጋር የሚደረግ ንግግርም ሆነ የሥርዓት ለውጥ ንዝላልነትና ውጤት አልባ ነው፤›› በማለት ተከራክረዋል፡፡

በአፍሪካ ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ የሪሶርስ ማዕከል ዳይሬክተርና የአትላንቲክ ካውንስል የአፍሪካ ማዕከል አባል አቶ ገብርኤል ንጋቱ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ የማምጣት ፍላጎት ያላቸው ሕወሓትና እንደ ሱዳን፣ ግብፅና አንዳንድ የባህረ ሰላጤው አገሮች ናቸው በማለት፣ ይኼም የሕወሓትን የበላይነት ለመመለስ ያለመ ነው ይላሉ፡፡

‹‹እንደሚታወቀው ኢትዮጵያውያን ለጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በምርጫ ከፍተኛ የማሸነፊያ ድምፅና ሥልጣን ሰጥተዋል፡፡ ስለዚህም ከዚህ የሕዝብ ፍላጎት በተቃራኒ ሊሄድ የሚሻና ሥርዓቱን ሊለውጥ የሚዳዳ ካለ፣ ከሕዝብ ቁጣ ሊያመልጥ አይችልም፡፡ ይኼንን ማድረግ የማይቻልና በኢትዮጵያም ሆነ በቀጣናው ያልተገመተ ጥፋትን ሊያስከትል የሚችል ነው፡፡ የምዕራቡ ዓለም በኢትዮጵያ መረጋጋት እንዲኖር ይሻል፡፡ በዚህ ጊዜ ደግሞ ይኼንን መረጋጋት ሊያረጋግጥ የሚችለውና ሥልጣኑ ያለው ኃይል ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው ብቻ ናቸው፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ፖሊሲና አሠራር የማይስማሙ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ብቸኛው ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን የተሰጣቸው አካል ናቸው፤›› ሲሉ ይከራከራሉ፡፡

ሳሙኤል (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የምዕራቡ ዓለም የአፍሪካ ቀንድ ፍላጎት የሚመነጨው ከፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ፍላጎታቸው ነው ይላሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያለችና ወደብ የሌላት አገር የኢኮኖሚና የወታደራዊ ጥንካሬን የሚያስገኝላትን የባህር ኃይል ለማቋቋም ስትነሳ፣ በዚህ ረገድ የሚያግዛትን ትብብር መሻቷ ስለማይቀር የምዕራቡ ዓለም ሥጋት ገብቶት ነበር ይላሉ፡፡ ስለዚህም ለራሳቸው የኢኮኖሚና ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚስማማ መንግሥት ለመመሥረት ይፈልጋሉ፣ ይኼም ካልሆነ ጣልቃ ይገባሉ ይላሉ፡፡

የምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አንፃራዊ ሰላምና መረጋጋት ኖሯቸው ከኢትዮጵያ ጋርም ሰላማዊ ግንኙነት የነበራቸው ቢሆንም፣ በውስጥ የፀጥታ ችግርና እርስ በርሳቸው የሌላውን አገር ተቃዋሚ ቡድን በማስተናገድ የተጠመዱ ነበሩ ይላሉ፡፡ ስለዚህም ተፅዕኖ ለመፍጠር የሚያስችላቸውን ቁመና የሚሰጣቸውን ቀጣናዊ ትስስር ለመፍጠርና ኃያል ሆነው ዲፕሎማሲያዊ ጫና ማሳደር የሚያስችል ጥንካሬ የላቸውም ይላሉ፡፡

ሆኖም ግን ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ጥቅም የራሷ ብቻ ሳይሆን የሌሎቹም ነው የሚል እምነት ተፈጥሯል፡፡ በዚህም የቀጣናው ሁኔታ የመስተካከል አዝማሚያ አሳይቶ ነበር በማለት የሚያክሉት ሳሙኤል (ዶ/ር)፣ ይኼ የሆነው ኢትዮጵያ ስታድግ አካባቢዋን የምታሳድግ ስለመሆኗ ጠንካራ ሥራ በመሠራቱ ነው ሲሉ ያስረዳሉ፡፡ ስለዚህም ከፋፍለው ለመግዛት የሚፈልጉ ኃይሎች እንዳይመቻቸው ሆኗል ይላሉ፡፡ በተለይም ኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማሊያ የፈጠሩትን ጥምረት ተከትሎ፡፡

‹‹እነዚህ አገሮች ያሉበት ስትራቴጂካዊ ቦታ የዓለማችን አንድ ሁለተኛ ገደማ የባህር ላይ ንግድ የሚከወንበት ነው፡፡ በዚህ አካባቢ ያለውን ሁኔታ በራሳችን ለመወሰን የሚያስችል አቅም ሊፈጠር ይችላል፤›› ሲሉ በተለይም በቅርብ ጊዜ የተከሰተውን ጂኦ ፖለቲካዊ ለውጥና ተያያዥ ፍላጎቶች ያወሳሉ፡፡

አቶ ገብርኤል ንጋቱም በዚህ ሐሳብ የሚስማሙ ሲሆን፣ የምዕራቡ ዓለም በዚህ አጋርነት ደስ እንዳላለው በመጥቀስ፣ እንዲህ ያለው ጥምረት ጠንካራ መንግሥታት እንዲፈጠሩና ሌሎቹም ከውጭ ከሚመጡ ፍላጎቶች በተቃራኒ እንዲቆሙ ሊያደርግ ይችላል የሚል ሥጋት ስላለ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

‹‹በእኔ ዕይታ የምዕራቡ ዓለም ቀዳሚ ፍላጎት የአፍሪካ ቀንድ መረጋጋት ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚፈጠር ማንኛውም አለመረጋጋት መላ ቀጣናውን እንደሚያናጋ ያውቃሉ፡፡ ይኼ ቢሆንም በኢትዮጵያ፣ ኤርትራና ሶማልያ መካከል በተፈጠረው ጥምረት ደስተኛ እንዳልሆኑ እጠረጥራለሁ፡፡ ይኼ እጅግ ስትራቴጂካዊ በሆነው ቀጣና ጠንካራው ጥምረት ሊሆን ይችላል፡፡ ስለዚህም በእኔ አረዳድ እንደ መለስ ዜናዊ ያለ ጠንካራ የሆነ፣ ነገር ግን የእነሱን ፍላጎት የሚያሳካ፣ እንዲሁም በተመሳሳይ ጊዜ የቀጣናውን ሰላም የሚጠብቅ መሪ ይሻሉ፡፡ ዓብይ ግን ሲበዛ ነፃና እንደ ቀድሞ የቡርኪና ፋሶ መሪ ቶማስ ሳንካራ ጠንካራ ፓን አፍሪካኒስት በመሆናቸው ላይስማሙ ይችላሉ፡፡ ቀጣናውን ሊያነቃቁ የሚችሉና ሌሎችንም የአፍሪካ አገሮች ሊያነሳሱ የሚችሉ እንደሚሆኑ ያስተውላሉ፡፡ ስለዚህም እሳቸውን ማስወገድ መላ ቀጣናውን ሊያምስ የሚችል እንደሆነ ቢያውቁም፣ እጅግ ስትራቴጂያዊ በሆነው ቀጣና ያላቸውን ፍላጎት ሊጎዳ የሚችልና ሌሎችንም ሊያነሳሳ የሚችል ጠንካራ መንግሥት በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ማየት አይፈልጉም፤›› በማለት አቶ ገብርኤል ይከራከራሉ፡፡

አንዳንዶች የምዕራቡ ዓለም ለጥቅሙ የሚሆኑት ስለሆነ ሕወሓትን መልሶ ወደ ሥልጣን የማምጣት ፍላጎት አለው በማለት የሚከራከሩ ቢሆንም፣ አቶ ገብርኤል ግን የምዕራቡ ዓለም ሕወሓት ያለቀለት ኃይል መሆኑን ስለሚረዱ መልሰው እነርሱን ለማምጣት መሻት የላቸውም ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን አሁን ያለው ግጭት ከቁጥጥራቸው ውጪ ሊሆኑ ይችላል ብለው የሚሠጓቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይንና አስተዳደራቸውን ሊያዳክም ስለሚችል በዚህ ውስጥ ዕድል ይታያቸዋል ይላሉ፡፡ አሜሪካ በተለይ ሕወሓትን ባለመኮነን በእርግጥ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባች እንደሆነ የማያጠራጥርና፣ ለሕወሓት የአገርና የኃይል ድጋፎችንም አቅርባ ሊሆን ሁሉ ቢችልም፣ አሜሪካ በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ ማምጣት አትፈልግም፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያን አንድ አድርጎ ሊይዝ የሚችለው ኃይል ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መሆናቸውን በቅጡ ይረዳሉ፤›› ባይ ናቸው፡፡

‹‹እኔ የማየው በኢትዮጵያ የሥርዓት ለውጥ ለማምጣት ነው የሚፈልጉት ወይስ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን መንግሥት ማዳከም ነው የሚለውን ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ያው አማራጭ ዓብይ ብቻ መሆናቸውን አውቀዋል ብዬ እንዳምን ሆኛለሁ፡፡ ስለዚህም የሕወሓትን ጥቃት እሳቸውን ለማዳከም እንደሚጠቅም እንጂ ለማስወገድ አይደለም የሚፈልጉት፡፡ የእሳቸው መወገድ ኢትዮጵያን የሚበታትናት እንደሆነ ስለሚያውቁ ያንን አይፈልጉም፡፡ በዚህም ምክንያት ሕወሓት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ለማዳከም መልካም አማራጭ ቢሆንላቸውም እሳቸውን መተካት ግን ምርጫ አይደለም፤›› ይላሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ ወደ ሥልጣን በመጡበት ጊዜ የምዕራቡ ዓለም ተወዳጅ መሪ ነበሩ፡፡ በዚህም ሳቢያ ከገንዘብ ድጋፍ እስከ ወታደራዊና የደኅንነት ድጋፎችን ለማድረግ ቃል እስከ መግባት ደርሰዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደ ዓለም ባንክና ዓለም አቀፉ የገንዘብ ፈንድ ያሉ የምዕራቡን ዓለም ተቋማት ሲያንቆለጳጵሱ የተደመጡ ሲሆን፣ ‹‹ከእነዚህ ተቋማት መበደር ከእናት እንደ መበደር ነው፤›› ሲሉም ተደምጠው ያውቃሉ፡፡ ነገር ግን ይኼ ብዙም ያልዘለቀ ወዳጅነት ሲሆን፣ በተለይም በጦርነቱ ሳቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የምዕራቡን ዓለም ገሸሽ አድርገው ወደ ቱርክና ቻይና ማማተራቸው ቅራኔውን እንዳሰፋው ሳሙኤል (ዶ/ር) ይጠቅሳሉ፡፡ ስለዚህም በስለላ፣ በተደራጀ መፈንቅለ መንግሥት፣ እንዲሁም በሕዝቡ መካከል ያሉ ክፍተቶችን በመጠቀም ሕዝባዊ አመፅ መፍጠርን ጨምሮ የተለያዩ አማራጮችን ተጠቅመው ይኼንን ለመቀልበስ መጣራቸው አይቀሬ እንደሚሆን ይገልጻሉ፡፡

ነገር ግን ችግር የሚሆነው የራስ ድክመት ሲጨመርበት እንደሆነና፣ ኢትዮጵያ ወታደራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ አቅሟን መገንባት አዋጭ አማራጭ እንደሆነ በመጠቆም፣ ለአብነትም አሜሪካ ኢትዮጵያን ከአጎዋ ተጠቃሚነት ለማገድ ስትነሳ ሌላ ተቃራኒ አማራጮችን ማማተር አስፈላጊ ነው ይላሉ፡፡

በቅርቡ የቻይና መንግሥት በቀጣይ ሦስት ዓመታት ውስጥ ከአፍሪካ ጋር ያለውን የንግድ ትስስር ለማሳደግና ከአፍሪካ ወደ ቻይና የሚላኩ ምርቶች ዋጋ 300 ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ እንደሚሠራና፣ ለአፍሪካ የግብርና ምርቶች ደግሞ በተቀላጠፈ መንገድ ወደ ቻይና እንዲገቡ ‹‹አረንጓዴ መስመር›› እንደምትዘረጋ መግለጿ መልካም አጋጣሚ እንደሆነም ሳሙኤል (ዶ/ር) ይናገራሉ፡፡ ይኼ ደግሞ ሌላ ፍላጎቶች ጋር ያልታሰረና የዲፕሎማቲክ ግንኙነት ያለው አገር መሆንን ብቻ የሚጠይቅ እንደሆነ በማስገንዘብ፣ የቻይና በሌሎች አገሮች ጣልቃ የመግባት መርህን የተከተለ ስለሆነ የተሻለ አማራጭ እንደሚሆንም ያመላክታሉ፡፡ ይኼም እንደ ኢትዮጵያ ላሉ አገሮች የመደራደር አቅማቸውን ማሳደግ የሚችል ሲሆን፣ ጣልቃ የሚገቡ የምዕራቡ ዓለም አገሮችም ውሳኔዎቻቸውን ዳግም እንዲያጤኑ ያደርጋቸዋል ባይ ናቸው፡፡ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት የኢትዮጵያን ተፈላጊነት የሚያሳይና የአማራጭ ዕድል የሚያመቻች እንደሆነም አመላካች ነው ይላሉ፡፡

ከዚህ ባለፈም ባለፈው አንድ ዓመት በሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ የተሠራው ሥራ ደካማ እንደሆነና፣ የኢትዮጵያም መገናኛ ብዙኃን የጎረቤት አገሮች በሚሰሙት ቋንቋ የሚቀርቡ ስላልሆነ፣ ስለኢትዮጵያ ሌላ ፍላጎት ካላቸውና በሌላ መንግሥታት ቁጥጥር ሥር ካሉ መገናኛ ብዙኃን እንዲሰሙ ሆነዋልና ሊስተካከል ይገባል ይላሉ፡፡

‹‹ስለእኛ ከእኛ መስማት አለባቸው፤›› ብለው በማስረገጥ፣ ኢትዮጵያን ለማጥፋትም ሆነ ለማልማት የጎረቤት አገሮች ዋና ስለሚሆኑ፣ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል ሲሉ ይመክራሉ፡፡ በዚህም አግባብ በኢትዮጵያ የሚሠሩ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉ ልማቶች እነሱንም የሚጠቅሙ እንደሆኑ ማሳወቅ ዓለም አቀፍ ጫናዎችን ለማርገብ ያግዛሉ ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያን ለማጥቃት የሚፈልግ ማንም ኃይል እነሱን አስፈቅዶ ካልሆነም አጥቅቶ የሚመጣ ነውና፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -