Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትየሰርቢያዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሠልጣኝ ስንብት

የሰርቢያዊው የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሠልጣኝ ስንብት

ቀን:

  • ክለቡ ከአሠልጣኝ ምርጫ ጋር ያለውን አሠራር ሊያጤን ይገባል የሚሉ አሉ

የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ በማንሳት በቀዳሚነት የሚጠቀሰው አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ከዋንጫም ሆነ ከሁነኛ አሠልጣኝ ተራርቋል፡፡ በውድድር ዓመቱ መጀመርያ ክለቡን በዋና አሠልጣኝነት ለመያዝ የተስማሙት የ62 ዓመቱ ሰርቢያዊ ዝላትኮ ክራምፓቲች ከወራት ቆይታ በኋላ ምንም እንኳ ይህ ዘገባ እስከ ተጠናቀረበት ድረስ ክለቡ አሠልጣኙን በሚመለከት በይፋ የገለጸው ነገር ባይኖርም ከኃላፊነታቸው መሰናበታቸው እየተነገረ ነው፡፡

በአፍሪካ የተለያዩ ክለቦችን በማሠልጠን ትልቅ ልምድ እንዳላቸው ሲነገርላቸው የነበሩት ሰርቢያዊ አሠልጣኝ ክራምፓቲች፣ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ከጥቂት ወራት የአሠልጣኝነት ዕድሜ በኋላ ስንብት የገጠማቸው ብቸኛው አሠልጣኝ ስለመሆናቸው ጭምር የሚናገሩ አልጠፉም፡፡

የቅዱስ ጊዮርጊስን ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ በሥራ ላይ ካሳለፉበት ጊዜ ይልቅ ምክንያት በመደርደር አገራቸውን ጨምሮ ወደ ተለያዩ አገሮች ተደጋጋሚ በረራዎችን አድርገዋል በሚል፣ በሁኔታው ደስተኛ ካልነበሩ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ጋር ተወያይተው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ቢደረግም፣ ከድርጊታቸው ግን ሊቆጠቡ አለመቻላቸው ሲነገር ነበር፡፡

በበርካታ የብሔራዊ ቡድን ተጨዋቾች ስብስብ መዋቅሩ የሚነገርለት ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ እንዲህም ሆኖ ክለቡ ከሚታወቅበት የአሸናፊነት ሥነ ልቦና እየራቀ መምጣቱ የአደባባይ ምስጢር ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በክለቡ ውጤትና አካሄድ ደስተኛ ያልሆነው የክለቡ አመራር ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. አሠልጣኙን ከእነ ረዳቶቻቸው ጭምር ውድድሩ ከሚደረግበት ከሐዋሳ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለሱ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ክለቡ በዚያኑ ቀን ከሐዋሳ ጋር የነበረበትን ጨዋታ ደግሞ በምክትሉ ዘሪሁን ሸንገታ አማካይነት ለጨዋታው እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡

ሰርቢያዊ አሠልጣኝና ረዳቶቻቸው በእዚያኑ ዕለት ከክለቡ የቦርድ አመራሮች ጋር ሰዓታት የፈጀ ውይይት ማድረጋቸው፣ የውይይቱ ማጠቃለያም አሠልጣኙ ክለቡን ባላቸው ኃላፊነት ይዘው አሁን ባለው ሁኔታ የሚቀጥሉ ከሆነ፣ በቡድኑ ቀጣይ ጉዞ ላይ ሊኖር የሚችለውን ተግዳሮት ከግምት በማስገባት አሠልጣኙ እንዲሰናበቱ መግባባት ላይ ከደረሱ በኋላ፣ ውላቸው እንዲቋረጥ ስለመደረጉ ጭምር ምንጮች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ቡድኑን በጊዜያዊነት ምክትል አሠልጣኝ በነበሩት ዘሪሁን ሸንገታ እንዲሁም ዓምና የዋናው ቡድን ምክትል ሆኖ ሲሠራ ከቆየ በኋላ በክለቡ ቦርድ ውሳኔ ወደ “ቢ”ው ቡድን ዝቅ ብሎ እንዲሠራ ተደርጎ ከነበረው ደረጀ ተስፋዬ ጋር በጋራ እንዲሠሩ ተወስኗልም ተብሏል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስና የሰርቢያዊ አሠልጣኝ መለያየትን ተከትሎ የተለያዩ ዘገባዎች እየወጡ ይገኛል፡፡ ሰርቢያዊ አሠልጣኝ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ክለቦችን በማሠልጠን ቢታወቁም፣ ይህ ነው የሚባል ውጤት እንደሌላቸው በሰፊው ይነገራል፡፡ ይህ ከሆነ ታዲያ አሠልጣኙ ወደ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት እንዴት ሊመጡ ቻለ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ማስነሳቱ አልቀረም፡፡

ጥያቄውን እንደሚያነሱት አስተያየት ሰጪዎች ከሆነ፣ ሰርቢያዊ አሠልጣኝ ባለፉት ዓመታት በተለይም በተለያዩ የአፍሪካ ክለቦች በሠሩባቸው ዓመታት ውስጥ በየክለቦቹ ብዙም የመቆየት ልምድ የላቸውም፡፡

አሠልጣኙ በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት በነበራቸው በጥቂት ወራት የሥራ ቆይታቸው፣ እንደ ዋና አሠልጣኝነታቸው ተጨዋቾችን በማስተባበር ለአንድ ዓላማ ከማሠለፍ ይልቅ፣ በቡድኑ ውስጥ መከፋፈል እንዲፈጠር ይሠሩ እንደነበር እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች ይናገራሉ፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2017 ጀምሮ የአፍሪካ አገሮች ማለትም በዛምቢያ፣ በቦትስዋና፣ በሩዋንዳ፣ በደቡብ አፍሪካና በታንዛኒያ በአሠልጣኝነት ተቀጥረው የመሥራት ዕድሉን ቢያገኙም፣ በሁሉም ክለቦች የአንድ ዓመት የአገልግሎት ጊዜ እንኳ እንዳልነበራቸው ነው የሚናገሩት፡፡

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ከሆነ የሰርቢያዊ አሠልጣኝና በአሠልጣኝነት የነበራቸው ታሪክ ይህን ከመሰለ፣ ከአሠልጣኞች ቅጥር ጀምሮ ጠንካራ የአሠራር ልምድና ተሞክሮ እንዳለው የሚነገርለት አንጋፋው ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አሁንም የምርጫ ሥርዓቱን በሚገባ ሊያጤን እንደሚገባ ይመክራሉ፡፡ በዚህ ጉዳይ በክለቡ በኩል ያለውን አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...