በአዲስ አበባ ከተማ የተከሰተውን የምርት አቅርቦት እጥረትና የዋጋ ንረት ለማቃለል እየተሠራ ቢሆንም፣ አሁንም ክፍተት ይታያል፡፡ በተለይም በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተከፈተው ጦርነትና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ኢኮኖሚያዊም ሆነ ማኅበራዊ ቀውስ ላይ ትልቅ ተፅዕኖ በመፈጠሩ በከተማዋ ላይ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር መንገድ ከፍቷል፡፡
በዚህም የተነሳ አብዛኛዎቹ ሸማቾች ሲማረሩ ተደምጧል፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት እየታየ ያለውን የምርት አቅርቦትና የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮና ሌሎች ተቋማት በጋራ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡
ከእዚህም መካከል ጆርካ ኢቨንት በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ጆርካ ኤቨንት ከኅዳር 25 እስከ ታኅሣሥ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ለሁለተኛ ጊዜ የ‹‹አስቤዛ›› ባዛርና ኤግዚቢሽን እያካሄደ ይገኛል፡፡
ባዛሩ ሲከፈት የተገኙት የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መስፍን አስፋ እንደገለጹት፣ በከተማዋ እየታየ ያለውን የዋጋ ንረት ለማረጋጋት የከተማ አስተዳደሩ እየሠራ ነው፡፡ በተለይም ሸማቹን ከአምራቹ ጋር በቀጥታ ለማገናኘት በሚደረግበት ጊዜ በሕገወጥ መልክ ለሸማቾች የሚሸጡ ነጋዴዎች ላይ አስፈላጊ የሆነ ዕርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የግብርናና የኢንዱስትሪ ምርቶችን አቅርቦት ለማሻሻል፣ እንዲሁም የግብይት ሰንሰለቱን ለማሳለጥ እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣ ከ19,251 በላይ የንግድ ድርጅቶች ላይ የተለያዩ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ዕርምጃ መወሰዱ ተችሏል ሲሉ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 17,251 የሚሆኑ ተቋማት ሕጋዊ አሠራርን እንዲከተሉ መደረጉንና 1,974 ተቋማት ንግድ ፈቃዳቸው ተሰርዞባቸዋል፡፡
የዋጋ ንረትን ለማረጋጋት ሰፊ ሥራ እንደሚጠይቅ፣ ለዚህም ከ45 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች ጋር ውይይት በማካሄድ ምርቶችን ለሸማቹ ኅብረተሰብ በተመጣጣኝ ዋጋ በማቅረብ የኑሮ ውድነት ለማቃለል እንደተቻለ አቶ መስፍን አስረድተዋል፡፡
በባዛሩም አምራቾች፣ አርሶ አደሮችና አስመጪዎች በቀጥታ የሚሳተፉ ሲሆን፣ በወቅቱ የሚቀርቡ ምርቶች በምን ያህል ዋጋ እየተሸጠ እንደሆነ የሚከታተሉ ባለሙያዎችን መመደባቸውን ምክትል ኃላፊው አብራርተዋል፡፡
በቅርቡም የተጀመረው የእሑድ ገበያን ጨምሮ እንደ እነዚህ ዓይነት ባዛሮች በሚዘጋጁበት ጊዜ የኢንዱስትሪ ምርቶች፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ እንዲሁም ሌሎችም ምርቶች እንደሚቀርቡ፣ ይህም የዋጋ መረጋጋትን በተወሰነ መልኩ ሊቀርፍ ችሏል ሲሉ አክለዋል፡፡
በቀጣይም በከተማው እንደዚህ ዓይነት ባዛሮችን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በማዘጋጀት የሸማቹን ፍላጎት ማሟላት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በዚህ የፈተና ወቅት ያላግባብ ትርፍ ለማግኘት የተለያዩ አሻጥሮችን በመሥራት ማኅበረሰቡን በማማረር ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች ከዚህ ተግባር እንዲቆጠቡም አስጠንቅቀዋል፡፡
ከጥቅምት 24 እስከ 28 ቀን 2014 ዓ.ም. የመጀመርያ ዙር የአስቤዛ ባዛር መከናወኑን፣ በዚህም ባዛሩ ላይ ከ500 ሺሕ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች ተሳታፊ መሆን እንደቻሉ የጆርካ ኢቨንትስ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ታምራት ደስታ ተናግረዋል፡፡
ባዛሩም በተካሄደበት ወቅት የምርት እጥረትና የተዘጋጀበትን ጊዜ አናሳ መሆኑን ከሸማቾች እንደተነገራቸው የተናገሩት ኃላፊ፣ ይህንን በመቀበል ምርቶችንም ሆነ ከዚህ በፊት ከተካሄደው የጊዜ ገደብ ላይ ሦስት ቀናትን በመጨመር የአምራቾችን ፍላጎት ማሟላት ተችሏል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ንግድ ቢሮ፣ የኤግዚቢሽን ገበያ ልማት፣ እንዲሁም አርሶ አደሮች ባዛሩ እንዲዘጋጅ ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ጠቁመዋል፡፡
በሽንኩርት ንግድ ከ20 ዓመት በላይ የሠራው አቶ ተስፋዬ ካሳ በመጀመርያውም ሆነ በሁለተኛው ዙር ባዛር ላይ ሽንኩርት ይዞ ለገበያ ማቅረቡን አንድ ኪሎም ከ27 ብር ጀምሮ እየሸጠ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጿል፡፡
ማኅበረሰቡም በፍላጎት እየገዛ መሆኑን የሚናገረው አቶ ተስፋዬ፣ የምንጃር ሽንኩርት ከአርሶ አደሩ በቀጥታ በመቀበል ለማኅበረሰቡ በትክክለኛ ዋጋ በመሸጥ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስረድቷል፡፡
በመጀመርያ ዙር ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሸማቾች ሲገበያዩ እንደነበር፣ የሁለተኛ ዙር ላይ ገና ከመጀመርያው ቀናት ላይ መቀዛቀዝ እንደታየም አክሏል፡፡
የሁለተኛው ዙር ባዛር ላይ የተለያዩ ነገሮች ሲሸምት የነበረው አቶ አሳየ፣ ከውጭ ገበያ ጋር ሲነፃፀር በሰባት ብር የሚያንስ እንደሆነ፣ ይህም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ ዜጎች ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጿል፡፡
ዘይት፣ ሽንኩርት፣ መኮሮኒና ሌሎች መሰል ምርቶችን ነጋዴዎች በብዛት ማቅረባችውን፣ ማኅበረሰቡም በሙሉ ፍላጎት እየተገበያየ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡
መንግሥት በከተማዋም በተለያዩ ቦታዎች ላይ እንደዚህ ዓይነት ባዛሮች በማዘጋጀት የኑሮ ውድነት ማረጋጋት እንዳለበት፣ ከዚሁ ጎን ለጎን ባለሀብቶች በዘርፉ በመሳተፋቸው በጅማሮው ላይ ትልቁን ድርሻ መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
ሪፖርተር ባዛሩ በተከፈተበት ዕለት በተለያዩ መገበያያዎች ላይ ተዘዋውሮ ሸመታውን የተመለከተ ሲሆን፣ የሸቀጣ ሸቀጥም ሆነ የተለያዩ ምርቶች ከውጭ ከሚሸጡት ምርቶች አንፃር ሲታይ በተወሰነ መልኩ የገንዘብ ልዩነት እንዳለው ማየት ችሏል፡፡
በባዛሩም በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚውል የአስቤዛ የድጋፍ መርሐ ግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡