Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ ገቢውን 50 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ዕቅድ ያዘ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ለመሰብሰብ ያቀደውን 48.5 ቢሊዮን ብር ገቢ ከፍ በማድረግ፣ እስከ 50 ቢሊዮን ብር የሚደርስ የገቢ ግብር ለመሰብሰብ ማቀዱ ተገለጸ፡፡

  በገቢዎች ቢሮ የኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዋና ዳይሬክተር አቶ ደምሰው በንቲ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ ዓምና ከተሰበሰበው 42 ቢሊዮን አጠቃላይ ገቢ በመነሳት፣ በዘንድሮው የበጀት ዓመት 48.5 ቢሊየን ብር ለመሰብሰብ ግብ ተቀምጦ ነበር፡፡ ይህም የሆነው መሠረታዊ የሆኑ ነገሮቸን መነሻና ታሳቢ በማድረግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

  ለምሳሌ የፋይናንስ ተቋማት ላይ የደመወዝ ገቢ ግብር አሰባሰብን አስመልክቶ የተተገበረው የገቢ አሰባሰብ እንቅስቃሴ  ከታሳቢ ጉዳዮች የሚመደብ እንደሆነ የገለጹት አቶ ደምሰው፣ ይህም የፋይናንስ ተቋማቱ ለሠራተኞቻቸው ያደረጉትን ጭማሪ ቀድሞ ታሳቢ በማድረግ ከደመወዝ የሚገኘውን ገቢ ግብር በተሻለ መንገድ ለመሰብሰብ መቻል መጀመሩ ተጠቃሽ ነው፡፡

  በተጨማሪም የኪራይ ገቢ ግብር ሌላው በትኩረት እንዲሠራበት ከተለዩ ጉዳዮች  ተጠቃሽ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን፣ የንግድ ገቢ ግብር ላይም ያለውን አሠራር በመፈተሽ አዳዲስ ወደ ግብር ሥርዓቱ ውስጥ ያልገቡ የንግድ ማኅበረሰቦች ወደ ግብር ሥርዓቱ ለማምጣት በሰፊው በመሠራቱና አልፎ ተርፎም የሕግ ተገዥነቱን በማጠናከር ረገድ የተደረጉት እንቅስቃሴዎች የከተማዋን ገቢ በበለጠ መንገድ ለመሰብሰብ ገፊ ከሆኑ ምክንያቶች ተጠቃሾቹ እንደሆነ ተገልጿል፡፡

  የማዘጋጃ ቤታዊ የግብር አሰባሰብ ዓምና ከነበረው አጠቃላይ ድርሻ ተለጥጦ ተጨማሪ ገቢ እንዲያስገኝ ግብ መጣሉ የተነገረ ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም የገቢዎች ቢሮ ሙሉ ለሙሉ ኃላፈነቱን ወስዶ ይሰበስባቸው ያልነበሩትን የማስታወቂያና የቴምብር ግብር ገቢዎችም ትኩረት እንደተሰጣቸው ተነግሯል፡፡

  ለአብነት ከሐምሌ 1 ቀን 2013 ጀምሮ እስከ ጥቅምት 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በቆየው የግብር መክፈያ ወቅት 448,133 ከሚደርሱ ግብር ከፋዮች 91 በመቶው ያህሉ ግብር እንደሳወቁ የተናገሩት አቶ ደምሰው፣ በአራቱ ወራት ውስጥ ለመሰብሰብ የታቀደው ወደ 22 ቢሊዮን የሚደርስ ገቢ እንደነበረ፣ ሆኖም በተባለው ወቅት 25 ቢሊዮን ብር ገቢ እንደተሰበሰበ ገልጸዋል፡፡

  አገር በዚህ ወቅት የምትገኝበት ሁኔታ ታሳቢ ሆኖ ይህን መሰል አፈጻጸም መመዝገቡ ትልቅ ጉዳይ ነው ያሉት አቶ ደምሰው፣ በግብር መክፈያ ወራት ውስጥም ከዚህ በፊት በተወሰኑ ነጋዴዎች ይፈጠር የነበረው የግብር ሥወራ እንቅስቃሴ፣ በወቅቱ ያለ መክፈል ችግሮች አገር የምትገኝበትን ሁኔታ በመረዳት የቀነሰበትና ግብር ከፋዩ አገር በዚህ ችግር ውስጥ ግብር መክፈል የህልውና ጉዳይ ነው በሚል ዕሳቤ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ በመክፈል ተሳትፏቸው የጎላ እንደነበር አስታውቀዋል፡፡

  የነጋዴው ማኅበረሰብና የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ማኅበር በግብር አሰባሰቡ ሒደት ውጤታማነት ላይ የራሳቸው የሆነ ጉልህ አስተዋጽኦ ነበራቸው ያሉት የኮሙዩኒኬሽን ዋና ዳይሬክተሩ፣ ነጋዴውን ከማነሳሳት አንስቶ በርካታ ተግባራት እንደተከናወኑ አስታውቀዋል፡፡

   

  ቀደም ሲል የንግዱ ማኅበረሰብ ለኦዲት የሚያቀርባቸውን መዛግብት በተጠናከረ መንገድ ያለ መያዝ ክፍተት በደንብ ተጠናክሮ ሊሠራበት እንደሚገባ ያስታወቁት አቶ ደምሰው በመሆኑም የኦዲት፣ የሰው ኃይልና የመሳሰሉትን በስፋት በማከናወን በዓመቱ መጨረሻ ለመሰብሰብ የታቀደውን የ48.5 ቢሊዮን ብር ገቢ አኃዝ ከፍ በማድረግ፣ በዓመቱ መጨረሻ 50 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ርብርብ እንሚደረግ አስታውቀዋል፡፡

  በዚህ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ግብር ሊከፍል የሚገባው የንግድ ማኅበረሰብ በተጠቀሰው ቁጥር ደረጃ ብቻ ያለ ነው ተብሎ መውሰድ አይቻልም ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በቀጣይ  ጉዳዩን አስፍቶ መሥራት ከገቢዎች ቢሮው የሚጠበቅ ተግባር እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

  አዲስ አበባ ቁልፍ የንግድና የኢኮኖሚ መንሸራሸሪያ ማዕከል በመሆኗ በአግባቡ ለግብር አሰባሰቡ እንቅስቃሴ አስተዋጽኦ የሚያርጉ አካላት እንደሚገኙ ሁሉ፣ በገቢ አሰባበሰብ ሥርዓቱ ላይ የተለየ ዕይታ ለመፍጠርና እንከን እንዲፈጠር ለማድረግ የሞከሩ ሰዎች አልነበሩም ማለት አይቻልም ያሉት አቶ ደምሰው፣ ሆኖም ጥቅል ውጤቱ ከተማዋን ሊጎዳ የሚችል ነው ብሎ ለመውሰድ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች