Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገራዊ የምግብ ዋጋ ግሽበቱ መጠነኛ ቅናሾች እንዳሳየ ተጠቆመ  

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ሸማቾች ግን የዋጋ ጭማሪ የተደረገባቸው ምርቶች እንዳሉ ተናግረዋል

በኅዳር ወር 2014 ዓ.ም. የተመዘገበው አገራዊ የምግብ ዋጋ ግሽበት ካለፉት ሁለት ወራት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ ቅናሾች የተስተዋሉበት ቢሆንም፣ ጭማሪ የሚስተዋልባቸው ምርቶች መኖራቸው ተገለጸ፡፡

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ለችርቻሮ ዋጋ ጥናት የመረጣቸውን 119 የገበያ ቦታዎችን መሠረት ያደረገውን የኅዳር 2014 ዓ.ም. ወርኃዊ የሸማቾች ዋጋ መመዘኛ ኢንዴክስ ሪፖርት ይፋ አድርጓል፡፡

የምግብ ዋጋ ግሽበት ባለፉት ሁለት ተከታታይ ወራት መጠነኛ ቅናሽ የታዩበት እንደሆነ አገልግሎቱ ያስታወቀ ሲሆን፣ ይህም በመስከረም ወር ከነበረው 42.0 በመቶ፣ እንዲሁም በጥቅምት ወር ከተመዘገበው 40.7 በመቶ አነስ ብሎ 38.9 እንደ ደረሰ አኃዙ ያሳያል፡፡

በወርኃ ኅዳር የነበረው አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት 33 በመቶ እንደደረሰ የስታትስቲክስ አገልግሎት ያስታወቀ ሲሆን፣ ምንም እንኳን አኃዙ በጥቅምት ወር ከነበረው ጋር ሲነፃፀር የ0.6 በመቶ ቅናሾች ቢታይበትም፣ ዓምና በተመሳሳይ ወር በነበረው አኃዝ ላይ በ33 በመቶ ከፍ ያለ እንደሆነ አመላክቷል፡፡

በኅዳር ወር እህሎች፣ አትክልትና ጥራጥሬ የመሳሰሉ የምግብ ዓይነቶች እንዲሁም እንደ ጤፍ፣ ስንዴ፣ ገብስ፣ በቆሎ፣ ማሽላና የመሳሰሉት የሰብልና የጥርጥሬ እህሎች የዋጋ ቅናሽ እንዳሳየ አሳውቋል፡፡ በተጨማሪም ሥጋና ወተትን ጨምሮ በቅመማ ቅመም መደብ ሥር የሚገኙት ጨውና በርበሬ በኅዳር ወር ቅናሽ ታይቶባቸዋል ከሚባሉት የምግብ ምርቶች ውስጥ  እንደሚገኙ አስታውቋል፡፡

ምንም እንኳን የኤጀንሲው የኅዳር ወር መመዘኛ ሪፖርት ከላይ የተገለጸውን ቢመስልም ሪፖርተር ከወቅታዊ የምግብ ዋጋ ሁኔታ ጋር በተገናኘ ያነጋገራቸው ሸማቾች እንዳስረዱት፣ በምግብ ዋጋ ላይ ያለው ገበያ ቶሎ ቶሎ ተለዋዋጭ በመሆኑ በዚህ ወቅት በይበልጥ ቀነሰ ተብሎ የሚገለጸው ጉዳይ ጥንቃቄ የሚያሻው ነው፡፡

የሰብል ምርቶች ዋጋ ከቀደመው ወር ጋር ይሀ ነው የሚባል የዋጋ ልዩነት እንዳላስተዋሉበት ያስረዱት ሸማቾች፣ በአንፃሩ እንደ በርበሬ ባሉ መሠረታዊ የቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ፣ በአንድ ኪሎ ከ50 እስከ 60 ብር የደረሰ ጭማሪ እንደታየ አስታውቀዋል፡፡

እንደ ድንችና ቃሪያ የመሳሰሉ የአትክልት ምርቶች ቅናሽ እንደታየባቸው የማይካድ ነው ያሉት ሸማቾች፣ ሆኖም የቀይ ሽንኩርት ዋጋ ቀስ በቀስ ጭማሪ እያሳየ እንደሚገኝ፣ በሸማቾች ማኅበራት ሱቆች በኩል የሚከፈፈለው የፉርኖ ዱቄትም በተመሳሳይ ከቀደሙት ወራት ጋር ሲነፃፀር በኪሎ እስከ 15 ብር የሚደርስ ጭማሪ ማሳየቱን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 25.2 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፡፡ ከምግብ ነክ ያልሆኑ የኢንዴክሱ ክፍሎች የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ከፍ እንዲል ካደረጉት ዋና ምክንያቶች ውስጥ በተለይም በአልኮልና ትምባሆ፣ ልብስና ጫማ፣ የቤት መሥሪያ ግብዓቶች ማለትም ሲሚንቶ፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮዎችና የቤት ማሰጌጫዎች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ እንደሆነ ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

በክልል ደረጃ ሲታይ ደግሞ በኅዳር ወር እንደ አዲስ አበባ፣ አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ክልሎች ከሌሎች ክልሎች ጋር ሲነፃፀር የተሻለ የዋጋ መቀነስ የተስተዋለባቸው እንደሆኑ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች