Sunday, November 27, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየባቢሌ ዝሆኖች ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት አመላከተ

  የባቢሌ ዝሆኖች ህልውና አደጋ ላይ መሆኑን የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት አመላከተ

  ቀን:

  • ‹‹ጥናቱ ሆን ተብሎ የተጋነነ ነው››

  የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን

  በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ በሚገኘው የባቢሌ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖች፣ በሕገወጥ ሠፈራ ምክንያት ህልውናቸው አደጋ ውስጥ እንደገባ፣ በእንግሊዝ ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲና ቦርን ፍሪ በተባለ የእንስሳት ክብካቤ ድርጅት የተደረገ ጥናት አስታወቀ፡፡ አጥኚዎቹ ባደረጉት የሳተላይት ምሥል ጥናት በመጠለያው ውስጥ ከ50 ሺሕ በላይ ሕገወጥ ቤቶች እንደሚገኙ ማረጋገጣቸውን በጥናቱ ጠቁመዋል፡፡

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ ዱር ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ ግን የጥናቱን ውጤት፣ ‹‹ሆን ተብሎ የተጋነነና መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ የማይገልጽ ነው›› ብለውታል፡፡

  የባቢሌ መጠለያ ጣቢያ በውስጡ ያሉትን ዝሆኖች በመጠበቅ ረገድ ስኬታማነቱን መፈተሽን መነሻ ያደረገው ጥናቱ፣ እ.ኤ.አ. በ2006፣ በ2014 እና በ2017 የተነሱ የሳተላይት ምሥሎችን በመጠቀም፣ በመጠለያው ውስጥ የሕገወጥ ቤቶች ቁጥር በምን ያህል መጠን እንደጨመረ መመርመሩን አስታውቋል፡፡ የጥናቱ ውጤት እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ. በ2006 ብቻ 18 ሺሕ የነበረው የሕገወጥ ቤቶች ቁጥር፣ በ2017 ወደ 50 ሺሕ አድጓል፡፡ ይህም በ11 ዓመታት ውስጥ ወደ ዝሆኖች መኖሪያ የተጠጋ የሕገወጥ ሠፈራ ቤቶች ቁጥር በ 32 ሺሕ ማደጉን አመላክቷል፡፡

  አጥኚዎቹ የሳተላይት ምሥሎቹን በማጉላት በምሥል የሚታዩትን ቤቶች እንደቆጠሩ የገለጹ ሲሆን፣ ይህ ዓይነቱ የጥናት ዘዴ በተለያዩ መስኮች ላይ የሚተገበር እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በቆጠራው ወቅት በተለይ ጊዜያዊ ቤቶችን ለመቁጠር አዳጋች እንደነበር፣ ቤትና ተመሳሳይ መጠን ባለው እንደ ቋጥኝ ዓይነት የተፈጥሮ አካል መካከል ለመለየት አዳጋች ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ፣ ቆጠራው ወስጥ ሳይካተት እንደቀረ ተገልጿል፡፡ በእንደዚህ ዓይነት መንገድ የተደረገው ቆጠራም በ11 ዓመታት ውስጥ በዝሆኖቹ መኖሪያ አካባቢ የሕገወጥ ቤቶች ቁጥር በአራት እጥፍ እንደጨመረ አሳይቷል ተብሏል፡፡

  የኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ጥናት በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ ለታየው ሕገወጥ ሠፈራ ዋንኛው ምክንያት የውኃ ፍላጎት መሆኑን ጠቅሶ፣ ዝሆኖቹም ኑሯቸውን ያደረጉት ውኃና ዛፍ ባለበት አካባቢ መሆኑን አስፍሯል፡፡ በዚህም ምክንያት በሰዎችና በዝሆኖች መካከል ተደጋጋሚ ግጭት እንደሚነሳና በሁለቱም ላይ ጉዳትና ሞት ማስከተሉን አክሏል፡፡

  ከሕገወጥ ሠፈራው በተጨማሪም በመጠለያው ውስጥ ያለውን መሬት ለእርሻ የሚያውሉ ነዋሪዎች በመበርከታቸው፣ ለዝሆኖቹ በምግብነት የሚውሉ ዕፅዋት መመናመናቸውን ጥናቱ ጠቅሷል፡፡ በዚህና ሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በባቢሌ የዝሆን መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ዝሆኖች ላይ የተደቀነው አደጋ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ፣ ዝሆኖቹን በሕይወት ማየት አዳጋች እንደሚሆን አጥኚዎቹ ገልጸዋል፡፡

  ከተመሠረተ ከ50 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ በውስጡ ‹‹ሎክሶዶንታ አፍሪካና›› የሚባሉትንና በዓለም ላይ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑትን የዝሆን ዝርያዎች ይዟል፡፡ በሶማሌና በኦሮሚያ ክልሎች የሚገኘው ይህ መጠለያ ጣቢያ 6,937 ስኬዌር ካሬ ሜትር ስፋት ያለው ሲሆን፣ 300 ያህል ዝሆኖች መኖሪያ ነው፡፡

  መጠለያ ጣቢያው የተቋቋመው ዝሆኖቹን ከሚደርስባቸው አደጋና ችግር ለመከላከል ቢሆንም፣ በመጠለያው ውስጥ የሚደረጉ ሕገወጥ ሠፈራ፣ አደን፣ እርሻና ከሰል የማውጣት ሥራዎች የዝሆኖቹን ሕይወት መፈተናቸው ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

  ሪፖርተር ያነጋገራቸው የባቢሌ የዝሆን መጠለያ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም መሐመድ፣ በተለይ በሕገወጥ ሠፈራ በኩል ያለው ችግር አሁንም መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡ እንደ ኃላፊው ገለጻ ዝሆኖቹ በብዛት የሚኖሩበት የኤረርና ጎበሌ ሸለቆዎች ውኃ ስለሚገኝባቸው ነዋሪዎችም በብዛት ሠፍረውባቸዋል፡፡ ይኼንን ተከትሎ በዝሆኖችና በሰዎች መካከል በተደጋጋሚ ግጭት እንደሚነሳ የጠቀሱት አቶ አደም፣ ከአራት ወራት ገደማ በፊት አምስት ዝሆኖችና ሦስት ሰዎች መሞታቸውን አስረድተዋል፡፡

  በተለይ በኦሮሚያና በሶማሌ ክልሎች ድንበር ላይ ግጭት በተነሳበት ወቅት ወደ መጠለያው የገቡ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ እንደነበር፣ ይህም በመጠለያ ጣቢያውና በዝሆኖቹ ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡ አቶ አደም አሁን 37 ሺሕ አባወራዎች በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ እንደሚኖሩ ገልጸው፣ ነዋሪዎችን ‹‹እያደራጁ›› የማስፈር አዝማሚያ መታየቱን ገልጸዋል፡፡

  ‹‹አሁን በመንግሥት ደረጃ ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ ሰጪ ነው፤›› ያሉት ኃላፊው፣ ከአባ ገዳዎች ጋር በመነጋገር መፍትሔ ለማምጣት መታሰቡን አስታውቀዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ያለው ሁኔታ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ዝሆኖቹ እንደሚጠፉ ጥርጥር አይኖርም፤›› በማለት ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

  ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊ ጥናቱን መመልከታቸውንና በመጠለያ ጣቢያው ውስጥ የሕገወጥ ሠፈራ ችግር እንዳለ የተናገሩት ኃላፊው፣ ጥናቱ ላይ የተጠቀሰው ቁጥር ግን ‹‹ሆን ተብሎ ተጋነነ ነው›› የሚል እምነት መኖሩን አስታውቀዋል፡፡

  ‹‹የሠፈሩት ሰዎች መጠለያው ውስጥ ያሉ፣ በፈር ዞን ውስጥ ያሉና ከበፈር ዞን ውጪ ተብለው ይከፋፈላሉ፤›› ያሉት ኃላፊው፣ በእንዲህ ዓይነት ጥናት ላይ የሳተላይት ምሥልን ተጠቅሞ ቆጠራ ማድረግ ቤቶቹን በትክክል ለመለየት አያስችልም ብለዋል፡፡

   

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...