ካለፈው ቅዳሜ ኅዳር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው፣ ተመላላሽ ነጋዴዎች ያለ ምንም ቀረጥ የግል መገልገያ ዕቃዎች ማስገባትን የሚከለክለው አዲሱ አሠራር ማወዛገቡን ቀጥሏል።
የዓለም አቀፍ መንገደኞች ከውጭ ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡ፣ እንደ ልብስና ጫማ ያሉ የግል መገልገያ ዕቃዎችን ማስገባት ይፈቅድ የነበረው መመርያ አፈጻጸም ላይ ዕግድ ያስቀመጠው አዲሱ አሠራር፣ በጉምሩክ ኮሚሽን ትዕዛዝ የተተገበረ ሲሆን፣ ሕገወጥ ንግድን ለማስቀረት ያለመ ነው።
አዲሱ ክልከላ ቱሪስቶችን፣ ዲፕሎማቶችን እንዲሁም ተመላላሽ ያልሆኑ መንገደኞች የግል መገልገያ ዕቃዎቻቸውን ማስገባት ባይከለክልም የሚያመጧቸው ዕቃዎች አዳዲስ ከሆኑ ቀረጥና ታክስ እንዲከፍሉ ያስገድዳል።
ምንም እንኳን የጉምሩክ ኮሚሽን ዕርምጃው ግብር የሚከፍሉ ነጋዴዎች የሚያበረታታና ሕጋዊ አስመጪዎችን ከኪሳራ የሚያድን ነው ቢልም፣ በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎችና ባለሙያዎች ውሳኔውን ተቃውመዋል።
ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ ችርቻሮ ንግድ የገባው አቶ ኪሩቤል (የአባቱ ስም እንዳይገለጽ የጠየቀ) መጀመርያ የአገር ውስጥ ጫማዎችን ይነግድ እንደነበር ይናገራል፡፡
መገናኛ አካባቢ በግምት 20 ካሬ ላይ ያረፈ ጫማ ቤት ተከራይቶ ሥራ የጀመረው ኪሩቤል፣ ንግድ የጀመረ ሰሞን ትርፋማ የነበረ ቢሆንም የውጭ አልባሳትና ጫማዎችን የሚሸጡ ሱቆች በሚሠራበት አካባቢ ቁጥራቸው በመጨመሩ መተው የሚገዙ ቀርቶ በደጃፉ የሚያልፉ ሸማቾች ሳይቀር እንደጠፉና ከዓመት በኋላ ዘርፍ ለመቀየር መገደዱን ያወሳል።
ዘርፉን በመቀየር ፒያሳ አካባቢ ከአራት ዓመታት በፊት ሱቅ የከፈተው ኪሩቤል የንግድ እንቅስቃሴው ከሞላ ጎደል ጥሩ እንደነበር ይናገራል፡፡
በየዓመቱ ያለበትን የገቢ ግብር እንደሚከፍል የሚገልጸው አቶ ኪሩቤል፣ በየወሩ ከ30 ሺሕ ብር በላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግሥት ሰብስቦ ያስረክባል።
የተለመደ ሥራውን እየሠራ ግዴታውንም እየተወጣ መሆኑን የሚገልጸው አቶ ኪሩቤል፣ ተመላላሽ ነጋዴዎችን አስመልክቶ የወጣውን አዲሱ የጉምሩክ አሠራርን ከሰማ አንስቶ እንቅልፍ ማጣቱን ይናገራል፡፡
ከሚሸጣቸው ምርቶች ውስጥ ከ75 በመቶ በላይ የሚሆነውን ከተመላላሽ ነጋዴዎች የሚያገኘው ኪሩቤል ‹‹አዲሱ አሠራር መሬት ላይ ያለውን እውነታ ያላገናዘበ ነው›› ይላል።
በከተማ ያሉ ቸርቻሪዎች ከሚሸጡት አልባሳትና ጫማ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻውን ከተመላላሽ ነጋዴዎች እንደሚያገኙና ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ አስመጪዎች ምርቶችን ከውጭ ሲያመጡ ጥራት ላይ ስለማያተክሩ፣ ሸማቾች ትኩረት የሚያደርጉት ጥራት ላይ መሆኑን የሚያሳይ ከመሆኑ አንፃር ውሳኔው ተገቢ አለመሆኑን ተናግሯል፡፡
ችግሮቹ ሳይፈቱ ተመላላሽ ነጋዴዎች ላይ ዕገዳ ማስቀመጡ ተገቢ አለመሆኑን የሚሞግተው አቶ ኪሩቤል፣ የውሳኔው አሉታዊ ተፅዕኖ ከወዲሁ እየታየ መምጣቱን ያነሳል። ለዚህም አዲሱ አሠራር በተገበሩ በሦስት ቀናት ውስጥ የገጠመውን ያነሳል።
‹‹ገና ውሳኔው በተሰማ ቀናት ውስጥ በመርካቶ የሚገኙ አስመጪዎች ከውጭ የሚመጡ ጫማዎች ላይ ከ1,200 ብር ላይ ጭማሪ አድርገዋል›› ሲል ወቀሳውን የሰነዘረው አቶ ኪሩቤል ‹‹ከሳምንት በፊት በጅምላ 2,000 ብር ይሸጡ የነበሩ ጫማዎች 3,000 ብር እንደገቡ›› ይናገራል። ይህም የክልከላው ውጤት ነው ሲል ወቀሳውን ጉምሩክ ኮሚሽን ላይ ሰንዝሯል።
አስመጪዎች በዚህ ሐሳብ አይስማሙም። በተደጋጋሚ ለጉምሩክ ኮሚሽንና ለፋይናንስና የገቢዎች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ባቀረቡት ቅሬታ የተመላላሽ ነጋዴዎች መብዛት ተወዳዳሪ እንዳላደረጋቸውና በዚህም የተነሳ ገበያው ላይ መፎካከር እንዳልቻሉ ሲገልጹ ቆይተዋል።
ተመላላሽ ነጋዴዎች ከሃዋላ የሚገኝ ገንዘብን ከትይዩ ገበያዎች በመግዛታቸው የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ይወስድባቸው የነበረውን ጊዜ እንዳረዘመባቸው በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የሆኑት አቶ ጥሩነህ አሰፋ ውሳኔው ከሚደግፉት መካከል ናቸው። ለዚህም ሁለት ምክንያቶች ያነሳሉ።
በውሳኔው ለመደገፋቸው እንደ መጀመርያ ምክንያት የጠቀሱት ተመላላሽ ነጋዴዎች በአልባሳቶች ላይ ለታየው ዋጋ ግሽበት ያደረጉት አስተዋጽኦ ሲሆን፣ በተለይም በተለያዩ አገሮች በሚጓዙበት ወቅት ለመኝታና ትራንስፖርት የሚያወጡት ወጪ ከሚያመጡት ዕቃዎች መጠን አነስተኛ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ፣ ወጪያቸውን ለመሸፈን የሚያስገቡትን ዕቃ በውድ ዋጋ በመሸጥ የዋጋ ግሽበት መፍጠራቸውን ይገልጻሉ፡፡
ነገር ግን እንደ ባለሙያው ገለጻ በሕጋዊው መንገድ በመርከብ አስጭነው የሚያስመጡ ነጋዴዎች የሚያመጡት ዕቃዎች ብዙ ስለሆነ በዋጋው አኳያ በተመጣጣኝ መልኩ ምርቶችን ማከፋፈል እንደሚችሉ ያነሳሉ። ጉምሩክ ኮሚሽንም ሕጋዊ አስመጪዎችን ለመደገፍ ተመላላሽ ነጋዴዎች መከልከሉ ትክክልኛ ውሳኔ ነው ይላሉ።
የተለያዩ ድርጅቶችን በመምራት ከ15 ዓመት በላይ ልምድ ያካበቱት የቢዝነስ አመራር ምሩቁ አቶ ፍፁም ደምሴ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም።
የተመላላሽ ነጋዴዎች የሚያገለግሉት መካከለኛና ከፍተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን መሆኑን የሚገልጹት አቶ ፍፁም፣ አስመጪዎች ምርቶችን ከቻይና በብዛት እንደሚያመጡ በመጥቀስ የሚያገለግሉት አነስተኛ አቅም ያላቸውን ሸማቾች እንደሆነ ገልጸዋል።
‹‹አስመጪዎች በተመላላሽ ነጋዴዎች አይጎዱም›› ሲሉ የሚሞግቱት አቶ ፍፁም፣ ዕርምጃው ሥራ እጥነት ሊያስፋፋ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት ከግብር ባለፈ የተመላላሽ ነጋዴዎች ሁኔታ መመልከት እንዳለበትና ብዙኃኖቹም ሴቶችና የዩኒቨርስቲ ምሩቆች እንደሆኑም አክለዋል፡፡
በተመሳሳይ ከዚህ ቀደም የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩትና በሙያቸው የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አቶ ሙሼ ሰሙ ውሳኔውን የተቃወሙ ሲሆን፣ ከሻንጣ ንግድ ዋነኛ ተጠቃሚ የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሆኑን በመጥቀስ፣ አገሪቷ ፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ባለችበት ወቅት ዕግዱ ተግባራዊ መሆኑ ኢመደበኛ ለፍቶ አዳሪዎችን እንደሚጎዳ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ሞግተዋል።
ዜጎች ለዕርዳታ ተቀባይነትና ለማኅበራዊ ቀውስ እንዳይዳረጉ ሲባል ኢመደበኛ ሥራዎችን ቢቻል ከግብር ነፃ በማደረግ ወይም በዝቅተኛ ታክስ ሠርተው የመኖር ዕድል ሊነፍጋቸው አይገባም ሲሉ ሞግተዋል።
የጉምሩክ ኮሚሽን ሥራ ኃላፊዎች ተግባራዊ የተደረገው ዕግድ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ያነሳሉ። በሕጋዊ መልኩ ከውጭ ምርቶችን የሚያስገቡ ነጋዴዎችን ያበረታታል ይላሉ። የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር የሆኑት አቶ ደበሌ ቃበታ የሚያነሱትም ተመሳሳይ ምክንያት ነው። እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ ተመላላሽ ነጋዴዎች ከጅምሩ አንስቶ ያደርጉት የነበረው የንግድ እንቅስቃሴ በመመርያ የተፈቀደ አልነበረም፡፡ በመሆኑም ዕቃዎችን ከውጭ እያስመጡ መሸጣቸው ሕገወጥ ነበር ብለዋል፡፡
ይሁን እንጂ በመመርያው ላይ የነበረውን ክፍተት በመጠቀም ከሌሎች ተጓዦች ጋር በመመሳሰል ምርቶቹን ያስገቡ ነበር የሚሉት አቶ ደበሌ፣ ዕግዱ ሕገወጦችን ለመለየት ትልቅ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
እሳቸው የሚመሩት ኮሚሽንም አዲሱ አሠራር የማይተገብሩ ተመላላሽ ነጋዴዎች ለመጀመርያ ጊዜ ከሆነ ቀረጥ ከፍለው እንዲገቡ በድጋሚ ይህን መሰል ተግባር ላይ ከተገኙ በወንጀል ጉዳያቸው እንደሚታይ አስጠንቅቋል።
እነዚህ ተመላላሽ ነጋዴዎች ከፈለጉ በሕጋዊ መንገድ ሌተር ኦፍ ክሬዲት (ኤልሲ) ከፍተው በመሥራት ይህን መሰል ከሆነ ችግር መዳን እንደሚችሉ አቶ ደበሌ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡