የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምና አስተዳደርን በተመለከተ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው አዲሱን መመርያ ባንኮች መተግበር ጀምረዋል፡፡ ይህ መመርያ በተለይ ከውጭ ምንዛሪ አፈቃቀድ ጋር በተያያዘ አዳዲስ አሠራሮችን የያዘም ነው፡፡ ባንኮች ከዚህ ቀደም ለደንበኞቻቸው ኤልሲ ሲከፍቱ ይተገብሯቸው የነበሩ አንዳንድ አሠራሮችን እንደሚከለክልና መመርያውን አለመተግበር የሚያስቀጣ እንደሆነም ያመላክታል፡፡
ከመመርያው መረዳት እንደተቻለው ከኤልሲ አፈቃቀድና አስተዳደር ጋር በተያያዘ ‹‹ክልከላ›› በሚል ራሱን በቻለ አንቀጽ ያስቀመጠው ድንጋጌ፣ ከዚህ ቀደም ይሠራባቸው የነበሩ አንዳንድ አሠራሮች ተፈጻሚ የማይሆኑ መሆኑን የሚያመለክትባቸው ናቸው፡፡ በዚሁ መሠረት በዚህ መመርያ በዋናነት ክልክል ተግባራት ናቸው ብሎ ካስቀመጣቸው መካከል በልዩ ሁኔታ ከሚፈቀደው ውጪ ማንኛውም ባንክ በምንም ሁኔታ ከኤክስፖርት የተሰባሰበ የውጭ ምንዛሪን ለገቢ ንግድ ሥራ ማዋል የማይቻል መሆኑን የሚደነግገው ክፍል አንዱ ነው፡፡ በዚህ በመመርያ የተከለከለ ተግባር መሆኑን ያስቀመጠው ጉዳይ ደግሞ የግዥ ትዕዛዞችን ለመፍቀድ ደንበኛው ሙሉ በሙሉ የሚፈለግበትን የገንዘብ መጠን ገቢ ከማድረግ ጋር ይያያዛል፡፡ ይህንንም ‹‹በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ግልጋሎት ላይ የሚውል ካልሆነ በስተቀር፣ ማንኛውም ባንክ ሙሉ የገንዘብ መጠኑን ገቢ ሳያደርግ የሲኤዲ (ካሽ አጌንስት ዶክመንት) ግዥ ትዕዛዞችን መፍቀድ አይችልም›› በሚል አስቀምጦታል፡፡
ከእነዚህ ሁለት ክልከላዎች ባሻገር ማንኛውም ባንክ ቢያንስ ሰላሳ በመቶውን የኤልሲ (ሌተር ኦፍ ክሬዲት) መጠን በቅድሚያ በጥሬ ገንዘብ ገቢ ሳይደረግ፣ የሌተር ኦፍ ክሬዲት (ኤልሲ) ማምልከቻዎችን መፍቀድ የማይችል መሆኑንም መመርያው አመልክቷል፡፡ ሆኖም የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የወጪ ንግድን ከዚህ ገደብ ነፃ ማድረግ የሚቻል መሆኑን ጠቁሟል፡፡
በዚህ መመርያ እንደ አዲስ አሠራር ተደርጎ የተቀመጠውና ክልከላ በሚለው አንቀጽ ውስጥ የተቀመጠው ድንጋጌ፣ በዓለም አቀፍ የክፍያዎች አፈጻጸም ልምድ መሠረት ለአቅራቢ ክፍያ ሳይፈጸም ማንኛውም ባንክ የሲኤዲ ሰነዶችን ለደንበኞቻቸው መስጠት የሌለባቸው መሆኑን ነው፡፡ ይህንኑ ድንጋጌ በማመሳከርም የውጭ ምንዛሪን መተላለፍን ለማረጋገጥ በሦስት ቀናት ውስጥ የተጠቃሚነት ደረሰኝ (ዩቲላይዜሽን ቲኬት) መዘጋጀት እንዳለበት አመልክቷል፡፡ ሌላው ክልከላን የተመለከተው ድንጋጌ፣ ማንኛውም ባንክ ጊዜው ያለፈበት ኤልሲና የግዥ ትዕዛዝ ሳይፀድቅ ለተጫኑ ዕቃዎች ፈቃድ መስጠት የማይችል መሆኑን ስለመሆኑ ማመላከቱ ነው፡፡ ሆኖም ዕቃዎቹ ከመጫናቸው አስቀድሞ የሚቀርብ አሳማኝ የኤልሲና የግዥ ትዕዛዝ አገልግሎት ጊዜ ማራዘሚያ ተቀባይነት እንደሚኖረው ይጠቅሳል፡፡ ኤልሲ ወይም ግዥ ትዕዛዝ ከመፅደቁ አስቀድሞ ለተጫኑ ዕቃዎች፣ ለአስመጪ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ በመስጠት የአስመጪ ፈቃድ እንዲሰጥ ማፅደቅ የሚቻል መሆኑንም ይኼው መመርያ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያወጣው መመርያ የውጭ ምንዛሪ አመዳደብና ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች በተመለከተ፣ እንዲሁም ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ምደባን በሚመለከት ማድረግ ያለባቸውን አሠራር በዝርዝር ያስቀመጠ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ የውጭ ምንዛሪ አፈቃቀድ ቅድሚያ የሚሰጣቸውን ዘርፎች በየደረጃው በማስቀመጥ የሚሠራበት ነው፡፡ ይህንንም ደረጃ መመርያው በሦስት ዋና ዋና ዘርፎች በመከፋፈል አስቀምጦታል፡፡ የውጭ ምንዛሪ ምደባን በሚመለከት ባንኩ በቀጣይ አንደኛ የመጀመርያ ደረጃ ቅድሚያ፣ ሁለተኛ ተከላካይ ደረጃ ቀዳሚና ቀጣይ፣ ሦስተኛ ደረጃ ቅድሚያ የገቢ ንግድ ዕቃ ዓይነቶች መደብና ክፍያዎች መሠረት እንደ ቅደም ተከተላቸው ወረፋቸው ቅድሚያ የሚሰጣቸው ይሆናል፡፡ በመመርያው መሠረት የመጀመርያ ወይም በአንደኛ ደረጃ ቅድሚያ የውጭ ምንዛሪ የሚፈቀድላቸው ዘርፎች ተብለው የተጠቀሱት በፋርማሲዩቲካልስ ዘርፍ ሥር የተዘረዘሩት መድኃኒቶች፣ የመድኃኒት ማምረቻዎች፣ አምራቾች፣ ግብዓቶችና የቤተ ሙከራ ውሁዶች፣ የላቦራቶሪ ኬሚካሎች፣ የምግብ ዘይት ማምረቻዎች፣ ግብዓትና ፈሳሽ ፔትሮሊየም ጋዝ ናቸው፡፡
በሁለተኛው ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ዘርፎች ተባለው የተጠቀሱት ደግሞ የግብርና ግብዓቶች መዳበሪያ፣ ዘር፣ ፀረ አረምና ኬሚካል፣ የማኑፋክቸሪንግ ግብዓቶች፣ የምርት ጥሬ ዕቃዎችና ኬሚካሎች ናቸው፡፡ መመርያው በሦስተኛ ደረጃ ያስቀመጣቸው ምርቶች ደግሞ በርካታ ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ በቀዳሚነት የተቀመጡት የሞተር ዘይት፣ ቅባቶች፣ የግብርና ግብዓቶችና ማሽነሪዎች ናቸው፡፡ የግብርና ግብዓቶችና ማሽኖች ሥር የመስኖ ውኃ ፓምፖች፣ የእንስሳት መኖዎች፣ ማሽነሪዎችና መሣሪያዎች፣ ትራክተሮች፣ መዝሪያ ማሽነሪዎችና የመለዋወጫ ዕቃዎች ሲሆኑ፣ በሦስተኛ ደረጃ ውስጥ የተቀመጡት ሌሎች ምርቶች ደግሞ ፋርማሲዩቲካል ምርቶች ሲሆኑ፣ እነሱም የላቦራቶሪ መሣሪያዎች፣ የሕክምና መሣሪያዎችና መገልገያዎች፣ የአምራች ኢንዱስትሪዎች፣ የማሽነሪ ማምረቻ ማሽኖች መሣሪያዎች፣ መለዋወጫዎችና ተጓዳኝ ዕቃዎችና የግዥ ጥያቄዎች መሆናቸውን ያመለክታል፡፡ በንጥረ ምግብ የበለፀጉ የሕፃናት ምግቦች በሦስተኛ ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጠው ነው፡፡ መጠናቸው ከ50,000 ዶላር ያልበለጠ የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ለራሳቸው ማሽነሪዎችና መሣሪያዎች መለዋወጫ መሣሪያዎች የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ፣ እንዲሁም የመማሪያ ደብተሮች፣ እስክርቢቶዎች፣ እርሳስሶችና የኅትመት ወረቀቶችም በዚሁ ምድብ ሥር ናቸው፡፡
መመርያው የውጭ ምንዛሪ የሚጠይቁ የትርፍ ክፍፍል ክፍያንም በዚሁ ምድብ ያስቀመጠ ሲሆን፣ በመመርያው የንግድ ሥራ ትርፍና የትርፍ ክፍፍል (ዲቪደንድ) ገንዘብ ዝውውር፣ በሚል ተገልጿል፡፡ የውጭ አገር አየር መንገዶች ተጨማሪ ሽያጭ ገንዘብ ዝውውር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ድርጅቶች የአክሲዮን ድርሻ ሽያጭም በሦስተኛው ምድብ ሥር ናቸው፡፡ እንዲህ ባለው መልክ የተቀመጠው የውጭ ምንዛሪ፣ አጠቃቀምና ለዚህ የገቢ ንግድ ዕቃዎች በባንክ የሚመደበው የውጭ ምንዛሪ መጠን በማንኛውም ጊዜ ለምርትና አገልግሎቶች ገቢ ንግድ ከሚመደበው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ መጠን ከሃምሳ በመቶ ያነሰ መሆን እንደማይገባውም በመመርያው ተደንግጓል፡፡ ይኼው የተመደበው ሃምሳ በመቶ የውጭ ምንዛሪ ውስጥ አሥራ አምስት በመቶ ለመጀመርያው አንደኛ ደረጃ ቀዳሚዎች፣ አርባ አምስት በመቶው በሁለተኛ ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጣቸው ምርቶች፣ እንዲሁም አርባ በመቶው ለቀጣይ ሦስተኛ ደረጃ ቀዳሚዎች የሚከፋፈል መሆኑን መመርያው ያመለክታል፡፡
የገቢ ንግድ ዕቃዎች የተመደበው በማንኛውም ጊዜ ለገቢ ምርትና አገልግሎት ከሚመደበው አጠቃላይ መጠን ሃምሳ በመቶ የማያንስ ሆኖ ቢገኝ ግን፣ በቀጣዩ ወር አምስት የሥራ ቀናት ውስጥ ባንኩ ልዩነቱን ለብሔራዊ ባንክ ፈሰስ እንዲያደርግ ማድረግ ግዴታ መሆኑን ይኼው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመርያ ያመለክታል፡፡
ከዚህም ሌላ ከተመደበው የውጭ ምንዛሪ ጥቅም ላይ የዋለው መጠን በማንኛውም ጊዜ ለገቢ ምርትና አገልግሎቶች የዋለው መጠን በማንኛውም ጊዜ ለገቢ ምርትና አገልግሎቶች የጠቅላላ መጠን ከሃምሳ በመቶ ያነሰ ሆኖ ቢገኝ፣ ልዩነቱን በየስድስት ወራት ባንኮቹ ለብሔራዊ ባንክ ፈሰስ እንዲያደርጉ ያስገድዳል፡፡ ይህንን ፈሰስ የተደረገ ገንዘብ ብሔራዊ ባንክ በወቅቱ አማካይ የምንዛሪ ተመን ተመጣጣኝ የብር መጠን ክፍያውን ወደ ባንኩ ተቀማጭ ሒሳብ ገቢ የሚያደርገው መሆኑንም በመመርያው ተጠቅሷል፡፡
በዚህ መመርያ ውስጥ የተከለከለው ከተቀመጡ አንቀጾች ውስጥ የባንክ ሥራ አስፈጻሚዎች በተለየ ውሳኔ ሊሰጡባቸው ይችላሉ የተባሉ ጉዳዮች መጠቀሳቸው ነው፡፡ ለአብነትም ያህል በማምረቻ ማሽነሪዎች አካላት ወይም መሣሪያዎች አካላት ላይ በተከሰተ ጉዳት፣ እንዲሁም አነስተኛ የገንዘብ መጠን ባላቸው ወሳኝ ግብዓቶች ምክንያት የምርት መስተጓጉል እንዳይፈጠር፣ የባንኩ ከፍተኛ ሥራ አስፈጻሚ (ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ኦፊሰር) ከማኑፋክቸሪንግ ወይም ከግብርና መስክ የሚቀርቡ የመለዋወጫ መሣሪያዎች ከውጭ የማስገባት ጥያቄ የመፍቀድ ሥልጣን የተሰጠው መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
በብሔራዊ ባንክ የገንዘብ (ሞኒተሪ) ዘርፍ ገዥ ወይም ምክትል ገዥ ለፋይናንስ ተቋማት፣ ለፌዴራል መንግሥትና የክልል መንግሥት፣ እንዲሁም የከተማ አስተዳደሮችን ጥያቄዎች እንደተናጠል ጉዳዮቻቸው ልዩ ቅድሚያ ፈቃድ ሊሰጥ እንደሚችልም ይህ መመርያ ይደነግጋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፣ የባንክ የቦርድ አመራሮችና ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በዚህ መመርያ መሠረት በየደረጃቸው ተጠያቂ የሚሆኑበትን አሠራር ያመለካተ ሲሆን፣ የውስጥ ኦዲተርም የራሱ ኃላፊነት ተሰጥቶቷል፡፡ የየባንኩ የውስጥ ቁጥጥር ኦዲት ሥራ ቢያንስ በስድስት ወራት አንድ ጊዜ እንደ አስፈላጊነቱ ድንገተኛ ፍሻዎችን በማድረግ፣ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥራዎች ከመመርያዎች ጋር የተጣጣሙ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል፡፡
የኦዲት ግኝቶቹም ለሚመለከተው የባንኩ አመራር ቦርድ፣ እንዲሁም የበላይ ኃላፊዎች መቅረብ ያለበት ሲሆን፣ የውስጥ ኦዲት ሪፖርት ቅንጅትም ለአመራር ቦርዱ በቀረበበት ተመሳሳይ ጊዜ በብሔራዊ ባንክ ለውጭ ምንዛሪ ግብይትና ተቀማጭ አስተዳደር መላክ እንደሚኖርበት ያመለክታል፡፡
በዚህ መመርያ የቀረበውን የትኛውንም መሥፈርት በምንም ዓይነት መልኩ የተላለፈ ማንኛውም ባንክ፣ በእያንዳንዱ መመርያ የሕግ ጥሰቱ አምስት ሺሕ ዶላር ቅጣት የሚቀጣ ስለመሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ከዚህ ቅጣት ሌላ ይህንን መመርያ በሚፃረር መልኩ ማንኛውም ባንክ በመመርያው የተገለጹትን ሁሉ ተግባራዊ ያላደረገ ወይም በሌላ በምንም ዓይነት መልኩ ተነሳስቶ መመርያውን የተላለፈ ወይም ተግባራዊነቱንም ያስተጓጎለም በብሔራዊ ባንክ መቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ተጠያቂ እንደሚሆንም አመልክቷል፡፡