Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየከተሜው ሕይወት በከተማ ግብርና

የከተሜው ሕይወት በከተማ ግብርና

ቀን:

በአዲስ አበባ ከተማ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የከተማ ግብርና እየታየ መጥቷል፡፡ ይህንኑ የሚከታተልም ጽሕፈት ቤትም የከተማዋ አስተዳደር አቋቁሟል፡፡ ከተሜው በየመኖሪያው ከጓሮው ባለው ክፍት ቦታ የቻለውን ያህል የአትክልትና ፍራፍሬ የማልማት፣ እንዲሁም ዶሮ ዕርባታን እያከናወነ መሆኑ ይታወቃል፡፡

በአዲስ አበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶ አደሮች ለከተማዪቱ የሚያቀርቡት የእርሻ ውጤቶች እንዳሉ ሆነው፣ በተለያዩ ክፍላተ ከተማ የሚገኙ አባወራዎችም ለየአካባቢዎቻቸው የምርት ውጤቶቻቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ፡፡

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ዱላ ማርያም አካባቢ ነዋሪ የሆኑት አቶ በቀለ ደሜ፣ ቲማቲምና ሽንኩርት፣ ጤፍና ሌሎችንም በማምረት ከራሳቸው አልፈው ወገኖቻቸውን እየጠቀሙ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ በግብርና ሥራ ከተሰማሩ ከሃያ ዓመት በላይ እንደሆናቸው የሚናገሩት አቶ በቀለ፣ ከዚህ በፊት ከመንግሥት በኩል የሚቀርብላቸው ድጋፍ ባለመኖሩ ምክንያት የፈለጉትን ያህል ምርት ሊያመርቱ እንዳልቻሉ፣ ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት ግን ይህ ሁሉ ችግር ተቀርፎ በቂ ምርት እያመረቱ እንደሆነ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ለሚያመርቱት ምርት የሚሆን ዘርና ማዳበሪያ ለማግኘት ሩቅ ቦታ እንደሚጓዙ ያስታወሱት አቶ በቀለ፣ አሁን ላይ እስከ ደጃፋቸው ድረስ በግብርና ባለሙያ ተጭኖ እንደሚመጣላቸው አብራርተዋል፡፡ አካባቢው ለግብርና ለምና ምቹ በመሆኑም በዓመት ሁለት ጊዜ በመስኖ ልማት የተለያዩ ምርቶችን እንደሚያመርቱና ከዚህ በፊት ከሚያስገቡት ምርት በላይ እያስገቡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከአሥር ኩንታል ጀምሮ ምርት እንደሚያስገቡ የገለጹት አቶ በቀለ፣ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቶ ባደረገላቸው ድጋፍ አማካይነት ከ50 እስከ 60 ኩንታል ሊያስገቡ መቻላቸውን አስታውሰዋል፡፡

ከዚህ ቀደም መሬታቸው ሊወሰድ እንደነበር ያስታወሱት አቶ በቀለ፣ ከረዥም ጊዜ በኋላ በቂ የሆነ ምርቶችን በማምረትና ለማኅበረሰቡ በትክክለኛው መንገድ በመሸጥ ልጆቻቸውን እያሳደጉ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት አቅማቸው እየደከመ መምጣቱን የግብርና ሥራውንም ልጆቻቸው እያገዟቸው እንደሆነ፣ የዘንድሮ ምርትን ለመሰብሰብ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በሰሜኑ ክፍል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት ሁለት ልጆቻቸው ከመከላከያ ጎን በመሆን የአገር ህልውናን ለመወጣት መዝመታቸውን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ሌላኛው ሽንኩርት፣ ጎመንና ቲማቲም በማምረት ተጠቃሚ የሆነው አቶ ሲሳይ ሐሰን በዚህ ሥራ ከተሰማራ 12 ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ከሁለት ጓደኞቹ ጋር ሆኖ መሬት እየተከራየ አትክልትን በማምረትም ሦስት ኤፍኤስአር መኪና ሙሉ ቲማቲምና ሽንኩርት እንደሚያመርት ገልጿል፡፡

ምርቶቹን ለማምረት የመስኖ ውኃ የሚጠቀመው አቶ ሲሳይ የጎመን ምርት ዘንድሮ እንደጀመረና ከፈጣሪ ጋርም ከፍተኛ የሆነ ምርት ለማስገባት ዕቅድ እንደያዘ ይናገራል፡፡

የከተማ ግብርና ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከመንግሥት ምንም ዓይነት ድጋፍ እያገኘ አለመሆኑን የሚናገረው ሲሳይ፣ ይህንንም በመረዳት ምርት ለማምረት የሚገለገልበት መሬት መንግሥት እንዲሰጠው በአጽንኦት ጠይቋል፡፡

እስካሁን በተለያዩ ቦታዎች ላይ በመዘዋወር ተከራይቶ እንደሚሠራ፣ ለኪራይ ከአሥር ሺሕ ብር በላይ ማውጣቱንና ይህም ‹‹አተርፍ ባይ አጉዳይ›› እንዳደረገው ተናግሯል፡፡

በዓመት ሦስት ጊዜ ምርት እንደሚያመርት ለምርቱ የሚሆነውን ዘር ከተለያዩ ቦታዎች ላይ እንደሚያመጣ አስታውሷል፡፡

የአርሶ አደርና የከተማ ግብርና ምክትል ኮሚሽነር አቶ መሐመድ ልጋኒ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በከተማዋ ከ20 ሺሕ በላይ አርሶ አደሮች እንዳሉ፣ እነዚህም አርሶ አደሮች የተለያዩ ምርቶችን በማምረት ተጠቃሚ እየሆኑ ይገኛል፡፡

በከተማ ግብርና የተሰማሩ አርሶ አደሮችም ባለፉት ዓመታት ከከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ በነበሩ ችግሮች ሙሉ ለሙሉ በሚባል መልኩ አቅማቸውን መጠቀም እንዳልቻሉ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩም ከ20 ሺሕ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ግዥ በመፈጸም አርሶ አደሩ ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረጉን የገለጹት አቶ መሐመድ፣ ከዚህ በፊትም አርሶ አደሩ ይጠቀምባቸው የነበሩ ዘሮችን ለምርታቸው ጥሩ የተባለ ዘር እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በፊት ይጠቀሟቸው የነበሩ ዘሮች ለምርቶቻቸው ማነቆ እንደነበሩ፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ ከአምስት ሺሕ ኩንታል በላይ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የገብስና የእህል ዘሮች በነፃ ግዥ በመፈጸም ለአርሶ አደሩ ተደራሽ መደረጉን ጠቁመዋል፡፡

ከከተማ አስተዳደሩም በኩል ስድስት ትራክተሮች ለአርሶ አደሮች በመስጠት አርሶ አደሩ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡

የከተማ ግብርና ላይ ተሳታፊ የሆኑ አርሶ አደሮች በቂ የሆነ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በተለያዩ መድረኮች ውይይት ማድረጋቸውን፣ በተለይም በከተማዋ እየታየ ያለውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ትልቁን ድርሻ መወጣት ስለሚኖርባቸው የተለያዩ ድጋፍ እየተሰጣቸው መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዘንድሮ የተገኘውን ምርት ለመሰብሰብ ልጆቻቸው ወደ ግንባር ያቀኑ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ በስድስት ክፍላተ ከተማ በጎ ፈቃደኞችና የመንግሥት ሠራተኞች በማሰማራት የሰብል ምርት እየተሰበሰበ ይገኛል፡፡

በከተማዋ የሚታየውን የዋጋ ንረት ለመቀነስ የከተማ ግብርና ትልቅ መፍትሔ መሆኑን የሚናገሩት አቶ መሐመድ፣ ይህ አምራቹን ከሸማቹ ጋር በቀጥታ በማገናኘት የገበያ ሰንሰለቱን ለማካሄድ ይረዳል ሲሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...