Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ክቡር መስዋዕትነት!

ሰላም! ሰላም! ያው እንደ ወትሮዬ ከአገሬ የሚቀድም የለም ብዬ ላይ ታች እላለሁ። ታዲያ ሚዛን ካልጠበቃችሁ ላይ ታች ማለቱም እንደ ሎተሪ ዕጣ ብርቅ ነው። በአገር አጥፊው ሕወሓት ወረራ የተያዙብን ከተሞችና ቦታዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ሲያስፈነድቀኝ ቢሰነብትም፣ በሌላ በኩል ደግሞ በርካታ ጉዳዮች ከፊታችን እንዳሉ እያሰብኩ መራመድ ጀምሬአለሁ፡፡ መቼም በአደባባይ ጉዳያችን ለመነጋገር መሰለኝ ሳምንት ቆጥረን የምንገናኘው። አይደል እንዴ? ምን ይታወቃል? ታዲያ ለዚህ ለዚህም ሳይውል ሳያድር ሥራችን ሁሉ ዕቅድ ያስፈልገዋል በሉልኝ። ምነው ብቻዬን የምታስለፈልፉኝ? “ሼሪንግ ኢዝ ሃፒነስ” አላሉም እንዴ ፈረጆች? ፈረንጆች ስል ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፡፡ አቤት ውሸታቸው ብዛቱ፡፡ ወንበዴው ድል ሲቀናው ከበሮ እንዳልደለቁ፣ እኛ ስንደቁሰው ግን ዝም ጭጭ ብለዋል፡፡ ከፊታችን ስንቱን የተቆለፈ በር የመክፈት የቤት ሥራ እንዳለብን አስባችሁታል? ስንቱን እሳት የማጥፋት ሥራ እንዳለብን ይረሳችኋል? ይህ ሁሉ ፈተናስ ራስ አያምም? በጣም እንጂ፡፡ ድል በድል እየሆንን ጭቅጭቅ? በፍፁም አይታሰብም፡፡ አይሞከርም!

ለነገሩ ራሳችን የሚያዞረው ነገር በዛ መሰለኝ ራስ ምታት እንዴት እንደነበር የሚያስታውሰን ሳያስፈልገን አይቀርም። ዕድሜ ለጀግኖቻችን እንጂ እያደር ከፈረንጆች ዘንድ የምንሰማውና የምናየው ቁልቁል መውረድና ውርደት ያስገርማል። የእነሱ የቱ ትክክል የቱ ስህተት እንደሆነ መለየት እየተቸገርን ሰነበትን። እናም ከዚህ በላይ ጨርቃችንን ጥለን መሮጥ አለብን ትላላችሁ? አንድ ወዳጄ፣ ‹‹እንዲያውም የእኛ ሰው እኮ ታጋሽ ሆኖ ነው እንጂ የእነሱ ሥራ የሚያቀባብር አይደለም። እነሱን ለማሳመን ወይም እነሱ እኛን ለማሳመን መቸገር የለብንም፡፡ ሥራችንን በሚገባ አከናውነን ጀነን ማለት ነው ያለብን…›› ሲለኝ ነበር። ኋላ ለምሁሩ የባሻዬ ልጅ ስነግረው፣ ‹‹እውነቱን ነው፡፡ ባትሪው እንደ ሞተ መኪና በ‘ጃንፐር’ ተነስተው ከተጓዙም መልካም ነው፡፡ ነገር ግን እንደ ሰው ሳይሆን እንደ ‘ማሽን’ ለሚዘውረው ውሸታቸው መጫወቻ እንደማንሆን ማሳየታችን ለእኛ በቂ ነው። እኛ በቅኝ ተገዥነት የማንታወቅ የጀግኖቹ አያቶቻችን ልጆች መሆናችንንና ለአፍሪካውያን የነፃነት ትግል ፋና ወጊ መሆናችንን መቀጠላችንን በተግባር አሳይተን በአንድነት ስንቆም ያፍራሉ፡፡ ይህ ትውልድ ታሪክ መሥራት መጀመሩ በራሱ ታላቅ ጀብድ ነው…›› ብሎ አረጋጋኝ፡፡ እንዲህ ነው እንጂ!

ያለ ነገር ስለወሬና ወሬኞች ጎነታትዬ እንዳልጀመርኳችሁ ይገባችኋል። በአሉባልታ አዋክበው በአፍንጫችን ሊደፉን ያሴሩ ፈረንጆችና የእኛው ወንበዴዎች ልካቸውን ስናሳያቸው፣ በሌላ ዘዴና ፕሮፓጋንዳ ሊገጥሙን እንደሚሞክሩ ማሰብ ያስፈልጋል። ለዚህም ከፍተኛ ዝግጅት ማድረግ አለብን። በዚያ ሰሞን አንድ የታወቀ ወሬኛ ከፌስቡክና ከዩቲዩብ የቃረመውን የውሸት ወሬ እውነት አስመስሎ ሲያወራ፣ አንዲት ትንታግ ጎረቤታችን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መመርያ መሠረት በቁጥጥር ሥር መዋል አለበት ብላ የሠፈር ሮንዶችን ጠርታ አስረከበችው፡፡ እሱ የተናገረውን ሊክድ ቢሞክርም እኔ ምስክር ተቆጥሬ የሰማሁትን ያለ ይሉኝታ ዘክዝኬለት ዘብጥያ ወረደ፡፡ እዚያም ሄዶ ቢያርፍ ምን ነበረበት፡፡ ለምን ታሰርክ ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹የፖለቲካ እስረኛ ነኝ…›› ብሎ አረፈው፡፡ ውሸቱን መሆኑን የተረዱ ሌሎች ታሳሪዎች ‹‹ወንፊት›› ብለው ሰይመውት አንገቱን መድፋቱን ሰማሁ፡፡ ወያኔዎቹም እንዲህ አንገታቸውን ደፍተው ነው ‹‹ስትራቴጂካዊ ማፈግፈግ አደረግን›› ያሉት፡፡ ይህንን ጉድ የሰሙ የአራዳ ልጆች ምን ቢሉ ጥሩ ነው፣ ‹‹ስትራቴጂካዊ ክህደት››፡፡ ከሃዲ ሁሉ!

ያኔ አሜሪካ ኢራቅን የወረረች ጊዜ የሳዳም ሁሴን ቃል አቀባይ የነበረ ግለሰብ፣ አሜሪካኖቹ ዋና ከተማዋን ባግዳድን ለመቆጣጠር እየገሰገሱ በነበረበት ወቅት አስቂኝ ነገሮችን ይቀባጥር እንደነበር የነገረኝ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ሰውየው የፕሮፓጋንዳ ሹም ስለሆነ የሚቀባጥረው አለቃው የነገረውን ነው፡፡ ‹‹ኢራቅ የገቡት አሜሪካኖች በገዛ ደማቸው ውስጥ እየዋኙ ነው፡፡ አንድም የአሜሪካ ወታደር በሕይወት አይወጣም፡፡ የአሜሪካኖችን ቀብር በከፍተኛ ወኔ እያስፈጸምን ነው… እያለ ሲጮህ የአሜሪካ ወታደሮችና ታንኮች በአጠገቡ ሲያልፉ አይሰማቸውም ነበር…›› ያለኝ፡፡ ይህንን ጉዳይ ከወያኔው አፈቀላጤ ጋር እያነፃፀረ ሲያስረዳኝ፣ ይህኛውም ሰውዬ የኢራቁን ቃል አቀባይ አስታወሰኝ፡፡ ‹‹አንዴ እንደገና በመደራጀት የጦር ሥልቱን መቀየር ላይ ነን… ከተሞችን የለቀቅነው ከዋናው ዕቅዳችን ጋር የተጣጣመ በመሆኑ ነው… እያለ ካቲካላ እንዳሰከረው ሰው ሲቀባጥር የኢራቁን ኮሚክ ዓሊ አስታወሰኝ፡፡ አንዴ እኮ ዓብይን ሳዳም ሁሴን አያድነውም፣ እንጦጦ ደርሰን አራት ኪሎ ነው የምንገባው እያለ የነበረ ሰውዬ ከአለቃው ጋር ቆላ ተንቤን ቢገባም ከሲኦል አያመልጣትም…›› ነው ያለኝ የባሻዬ ልጅ፡፡ ብዙ ሺዎችን አስፈጅቶና አስማርኮ እንደ ጀብዱ ከሚያወራ ወፈፌ ጋር ነው እንግዲህ ትግል የገጠምነው፡፡ እስከ መጨረሻው ድረስ ተጉዘን አስተሳሰባቸውን ጭምር ነው መቅጨት ያለብን፡፡ ወፈፌ ሁላ!

‹‹አኖርሽ ነበረ በሬዬንም ሸጬ፣ አበላሽ ነበረ ወይፈኔን አርጄ፣ በምኔ ልቻልሽ በአንገቴ ተይዤ…›› እያሉ ያላዝኑ እንጂ ወይ ፍንክች ብለናል፡፡ ውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹አንበርብር ሰዎቹ ነጋ ጠባ እንደዚያ ሲቀደዱ ሁሉም ነገር ያለቀለት እየመሰለኝ ሲያሠጋኝ እኮ ነው መዝመት ያለብህ ብዬ የወሰንኩት…›› ብላ ስታስታውሰኝ የሠፈሬ ሮንድ ተቆጣጣሪነት ሥራዬን እንደ ዘመቻ አላየችውም እንዴ ብዬ ይቆረቁረኛል። እርግጥ ነው ተጠባባቂ ተብዬ ነው ይህንን ሥራ ደርቤ የማከናውነው፡፡ ማንጠግቦሽም ብትሆን ይህንን አታጣውም፡፡ አሁንም ከጦርነቱ ማግሥት ብርቱ አገራዊ ሥራ ስላለብን ጥሪት መያዝ ያስፈልጋል፡፡ ተፈናቃዮችን መልሶ ማቋቋምና የፈረሱትን መልሶ መጠገን የእኛው ዕዳ ነውና፡፡ ለዚህም የሥራ ሞራሌ ተነሳስቶ አንዳንድ ቦታዎች ልደውል ትኩረቴን ሰበሰብኩ። ማስታወሻዬን ገላለጥኩ። በእንጥልጥል የያዝኩትን ድለላ ካቆምኩበት ልቀጥል ስልኬን አንስቼ ልክ ልደውል ስል ይደወላል። ‹‹ሃሎ!›› ስል አንድ የማውቀው ድምፅ፣ ‹‹አንበርብር!›› ብሎ ይጮሃል። ‹‹አዎ ነኝ!›፣ ከማለቴ፣ ‹‹ምንድነው የምሰማው?›› ብሎ ይጠይቀኛል። ለዘመቻ ተጠባባቂ መሆኔን አስረድቼ ስለቀጣዩ ኃላፊነታችን አስረድቼ ስዘጋ ሌላ ስልክ መጣ። ‹‹ሃሎ!›› ስል አንዱ ደግሞ ሳትሰናበተኝ ልትዘምት ነው እንዴ ብሎ ይጮህብኛል፡፡ እሱንም እንዲሁ አባብዬ ሳስረዳ ሰዓቴ ነጎደ። ምን የማይነጉድ ነገር አለ? ዓባይ በከንቱ ሲፈስ የኖረው ወሬ ላይ ተጥደን መስሎኝ፡፡ አሁን ግን እንኳንስ ዓባይ በከንቱ ሲፈሱ የኖሩ ወንዞቻችን ይከተራሉ፣ ያልታረሰው ድልብ መሬታችን ላይ ትራክተርና ኮምባይነር ያጓራሉ፡፡ ወጣቶቻችን ጥራት ያለው ትምህርት እየተማሩ አገር ለማልማት ይዘጋጃሉ፡፡ ወሬ ቀርቶ ሥራ ይነግሣል፡፡ በቃ!

አሁን ከሚታየው የዓለም ሁኔታ አንፃር ግልጽነትና ተጠያቂነት ካልሰፈነ ሰላም አይኖርም እላለሁ። አሜሪካን የምታህል አገር፣ አውሮፓን የሚያህል አኅጉር፣ የተባበሩት መንግሥታትን የሚያህል ግዙፍ ድርጅትና ሌሎች በወሬ ፋብሪካ ተወረው እንዴት ሰላም ይኖራል። አንድ ሽብርተኛ ድርጅት መንግሥት ለማድረግ ብለው አገር ለማፍረስ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሱ፣ ነገ ምን ይዘው ሊመጡ እንደሚችሉ መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹አሜሪካም ሆነች ሌላው የሚያስቀድሙት ጥቅማቸውን ብቻ ነው፡፡ የእኛ የዘመናት ችግር ደግሞ ከብሔራዊ ጥቅማችን ይልቅ የመንደር ጥቅማችን ላይ እያተኮርን አገራችንን መጫወቻ ማድረጋችን ነው፡፡ ፈረንጅ የሚናገረው እውነት እየመሰለን፣ በፈረንጅ አፍ የሚያወሩ የእኛው ጉዶች እያታለሉን፣ ከጋራ ጥቅማችን ይልቅ የቡድን ጥቅም ላይ እየተራኮትን ነው የተበላነው፡፡ አሁን ግን እንንቃ፡፡ ከአገራችን ህልውና በላይ ምንም ነገር የለንም፡፡ አታይም እንዴ ስንት ጀግኖች ተሰውተው እኮ ነው ወያኔ አከርካሪው እየተሰበረ ያለው፡፡ ይህንን ክቡር መስዋዕትነት ማራከስ ወንጀል ነው…›› ሲለኝ ንግግሩ ደም ሥሬ ውስጥ የገባ ያህል ነው የተሰማኝ፡፡ ሁላችንም ይሰማን!

እጄ ላይ ምን የመሰለ የሚከራይ ቪላ ስለነበረ መደበኛ ሥራዬንና ቀጣናዬን የማረጋጋት ተግባሬን ለጊዜው አቆይቼ፣ ለመጨረሻ ውሳኔ ቤቱን አሳየን ወደ አሉኝ አዲስ ደንበኞቼ ከነፍኩ። እህትማማቾቹ ተከራዮች ቤቱን ዓይተው ጥቂት እርስ በርሳቸው ከተነጋገሩ በኋላ ትንሽ ተደራድረው እንደሚከራዩት አበሰሩን። አከራዩም እኔም ፈንድቀን፣ ‹እንኳን ለውሳኔ አበቃችሁ!› ብለን ሳናበቃ በማናውቀው ምክንያት፣ ‹ምን መሆንሽ ነው? ምን መሆንሽ ነው?› እየተባባሉ ወይዘሮዎቹ ፊታችን ቡጢ ቀረሽ ንትርክ ጀመሩ። የማላየው ነገር የለም መቼም! ቆየት ብዬ እንደተረዳሁት በአንድ ዓመት የሚበላለጡ እህትማማቾች ኖረዋል። የንትርኩ መንስዔ ታዲያ ምን ቢሆን ጥሩ ነው? ‹እኔ ነኝ መነጋገር ያለብኝ አንቺ አርፈሽ አዳምጪ! የለም አንቺ ምን ስለሆንሽ ነው እኔ ነኝ መናገር ያለብኝ› በሚል ግብግብ የተፀነሰ መሆኑ ነው። አገርን ያስቸገረው እንዲህ ያለው የጥጋበኞች ትንቅንቅ አይደለም እንዴ፡፡ አያችሁ ለጋራ ጉዳይ በእኩልነት መነጋገር ሲገባን ከአገር አጥፊዎች ጋር እየዋልን እርስ በርስ እንቧቀሳለን፡፡ አሁን ነቅተናል ማለት አለብን፡፡ መሀላችን እየገቡ በዘር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በመሳሰሉት የሚያናጅሱንን ዘወር በሉ ማለት ይኖርብናል፡፡ እስካሁን የተጫወቱብን ይበቃቸዋል፡፡ አንድ ስንሆን እንኳንስ እነሱን ጋላቢዎቻቸውን ልክ ማስገባት እንችላለን፡፡ ልክ ነዋ!

ለታዛቢ ቀላል ይምሰል እንጂ ለባለቤቶቹ ግን የልጅነት ትውስታን እያስመዘዘ ስንት መስማት የማይገባንን ገመና ያዘካዘከ ግጭት ነበር። ሁለቱንም አረጋግተን ጥቂት በሊቀመንበርነት ቦታው ማን ይቀመጥ የሚለውን እንዲነጋገሩ ፈቀቅ አልንላቸው። ‹‹ትልቅ ሰው ሲበላሽ ቅራሪ የለውም የሚባለው ለካ እውነት ነው?›› በማለት ለቤቱ ባለቤት ስነግረው እንደ ቀልድ፣ ‹‹ድሮስ የዚህች አገር የዘመናት ጥያቄ ይባስ ሲተበተብና ሲከር የኖረው በአዋቂው አይደል እንዴ?›› ብሎ ማኖ አስነካኝ። ቀይ ወይ ቢጫ በማላይበት ማኖ ብነካ ‘ኮሚሽኔን’ ሳልቀበል ንቅንቅ እላለሁ እንዴ? እሺ ብለን የምንጎትተው ነገር ብሷል እኮ እናንተ፡፡ እንዲያው ምንድነው ግን አንተ ቅደም እኔ ልከተል መባባልን የነሳን? በታላቅና በታናሽ መሀል ባሰ እኮ ጎበዝ፡፡ ምን ዓይነት መርዝ ነው የተረጨብን ያስብላል፡፡ ዳሩ ግን ከዚህም የምንላቀቅበት ጊዜ ተቃርቧል፡፡ የበለጠ እንዲቀርብ ግን ከድንዛዜያችን መንቃት አለብን፡፡ ድንዛዜ ይብቃ!

በሉ እንሰነባበት። ያከራየሁትን ቪላ ‘ኮሚሽን’ በተቀበልኩ አመሻሽ አዛውንቱ ባሻዬ ደወሉልኝ። የማርያም አራስ ሊጠይቁ ያለ እኔ አልሆንላቸው ብሎ ነበር የደወሉልኝ። ተያይዘን አራስ ጥየቃ። ሳያት የት እንደማውቃት ጠፋኝ እንጂ መልኳ አዲስ አልሆነብኝም። ባሻዬን ጠጋ ብዬ፣ ‹‹መቼ አገባች? አልሰማሁም ማግባቷን?›› አልኳቸው። ባሻዬ ደንግጠው፣ “ኧረ እባክህ ስለፈጠረህ ዝም በል። እኔ የወለደ እንጠይቅ አልኩህ እንጂ ስለጋብቻ እንመስክር ብዬ አመጣሁህ?” ብለው ሲቆጡኝ ነገሩ ገባኝ። የገባኝ መስዬ ባሻዬን ለመካስ፣ ‹‹እንዴት ነበር ታዲያ ምጡ? ጠናብሽ?›› ብዬ መጠየቅ። አፌ አያርፍም እኮ አንዳንዴ። ‹‹ማማጥ ድሮ ቀረ። ዕድሜ ለቀዶ ጥገና…›› አለችኝ። ባሻዬን ቀና ብዬ አላየሁም። ግድ ካልሆነ ባሻዬ በምንም ተዓምር በቀዶ ጥገና መገላገልን አይደግፉም። ስንቀለቀል መስማት የማይፈልጉትን ስላሰማኋቸው እንደሚቆጡኝ ገብቶኛል። ምኔ ሞኝ ነው ታዲያ? አውቄ ስልክ ተደወለልኝ አልኩና ‘ማርያም ጭንሽን ታሙቀው’ ብዬ ላጥ። ነገር ሲከር ዞር ማለትም ጥበብ ነው፡፡ የሰሞኑ ድል በከፍተኛ ማጥቃትና የድሮን ድብደባ ጭምር እንደሆነ መስማቴን አልረሳውም፡፡ አንዱ እንዲያውም፣ ‹‹ሰርጂካል ኦፕሬሽን›› ይባላል ያለውን ሳስታውስ የአገሬና የልጅቷ ምጥ ተነፃፀረብኝ፡፡ አንዳንዴ እኮ ያመራምረኛል!

ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር የተለመደችዋ ግሮሰሪ እንድንገናኝ ተቀጣጠርን። ስንገናኝ ግሮሰሪዋ በደንበኞች ጢም ብላለች፡፡ የእኛ ሰው ኮሮና ከእነ መፈጠሩ ረስቶት ተጠቅጥቋል፡፡ በዓይን ጠቀስ አድርጌው በረንዳ ላይ በጥግ በኩል ራቅ ብለን ተቀምጠን የሆነውን ሁሉ ነገርኩት። እንደ ወትሮው በአባቱ ወግ አጥባቂነት ዘና እያለ ያጫውተኛል ስል ኮስተር ብሎ፣ ‹‹በቃ አምጦ መውለድ ተረት ሊሆን ተቃረበ ማለት ነው?›› አለኝ። ‹‹አቤት?›› ስለው ባሻዬ የመጡ መስሎኝ ክው ብዬ፣ ‹‹አሳሳቢ የሆነ እክል ሊገጥም እስካልቻለ ድረስ ሰው ለምን አምጦ መውለድ እንደሚፈራ አልገባኝም። በምጥ የሚወለድ ልጅ እኮ ጤናማነቱና ጥንካሬው ሌላ ነው። እህ በአቋራጭ የመክበር፣ በአቋራጭ የመደለብ፣ በአቋራጭ ሥልጣን ላይ ፊጢጥ የማለት የዘመኑ ሰይጣናዊ አካሄድ ስንቱን ጤናማ ተፈጥሯዊ በረከት አበላሸው መሰለህ? ሕመም ፈርተን፣ ላብ ተፀይፈን፣ ሥራ ንቀን፣ ጎንበስ ማለት ጠልተን፣ በአጠቃላይ ምጥ ገሸሽ ብለን ያዋጣናል? ማቆራረጥና አጉል ዝላይ ዋጋ እንዳያስከፍሉን ፍራ…›› ሲለኝ ‹‹አልፈራም!›› አልኩት። እኔም በልቤ ከወላድ ምጥ በላይ አገርን ምጥ ያስያዘው ወንበዴ እንደ ጉም መበተኑ ሞራሌን ገንብቶታል፡፡ በጀግኖቹ ልጆቻችን መስዋዕትነት የተገኘው ድል አጀግኖኛል፡፡ ይህ ክቡር መስዋዕትነት በኢኮኖሚያዊ ልማቱም እንዲደገም መንደርደሪያ መሆን እንዳለበት ይሰማኛል፡፡ በመስዋዕትነት የተገኘው ድል መቼም ቢሆን የማንም መቀለጃ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከድህነት እንድትገላገል መሠረት ይሆናል እንጂ፡፡ መልካም ሰንበት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት