Friday, September 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አይሲቲ ፓርክ ለተመሠረተበት ዓላማ እየዋለ አይደለም የሚል ቅሬታ ተነሳበት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በፓርኩ ላይ “የአስተዳዳሪነት ጥያቄ” አለኝ ብሏል

በአዲስ አበባ ከተማ ከጎሮ አደባባይ ወደ ቱሉ ዲምቱ በሚወስደው መንገድ ላይ የሚገኘው አይሲቲ ፓርክ ሲመሠረት የነበረውን የቴክኖሎጂ ዘርፍን የማሳደግ ዓላማ በሚያሳካ መንገድ እየሠራ አይደለም የሚል ቅሬታ ቀረበበት፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ፓርኩ ሲመሠረት ይቀርባሉ ተብለው የነበሩ ግልጋሎቶች ቃል በተገባው መጠን አለመቅረባቸውን፣ እንዲሁም ወደ ፓርኩ ለመግባት ዓመታትን ለመጠበቅ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያን በአፍሪካ ቀዳሚ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ማዕከል የማድረግ ራዕይ ይዞ በ2003 ዓ.ም. አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአይሲቲ ፓርክ፣ በቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ 30 ተቋማትን በውስጡ ይዟል፡፡ ፓርኩ የተመሠረተበት አንዱ ምክንያት መንግሥት በዘርፉ ለተሰማሩ ኩባንያዎች የሚያስፈልጉትን ያልተቆራረጠ ኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ ኃይል በአንድ ቦታ በሚያስፈልግ መጠን እንዲያቀርብ ለማድረግ ነው፡፡

ይሁንና እነዚህ መሠረተ ልማቶች አሁንም ድረስ ቃል በተገባው ልክ እየቀረቡ እንዳልሆነ፣ ሪፖርተር ያነጋገራቸውና በፓርኩ ውስጥ የሚገኘው “አፍሪኮም ቴክኖሎጂስ” ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ባህሩ ዘይኑ ገልጸዋል፡፡ ኩባንያቸው ከአምስት ዓመት በፊት ወደ አይሲቲ ፓርክ እንደገባ ያስረዱት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ቃል የተገቡላቸው ጥቅማ ጥቅሞች ካለመከበራቸውም በላይ የሚያገኙት ኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ ኃይል የሚቆራረጥና ዋጋውም ያልቀነሰ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ‹‹የታሰበው ለተወሰነ ዓመት ታክስ ሳንከፍል በምትኩ የሥራ ዕድል በመፍጠር እንድናካክስ ነበር፤›› ያሉት አቶ ባህሩ፣ ፓርኩ ውስጥ ሲገቡ እንደ ኮምፒዩተር ያሉ ለሥራ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ከቀረጥ ነፃ ማስገባት እንደሚችሉ ተነግሯቸው የነበረ ቢሆንም፣ ተፈጻሚ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹የእነዚህ ችግሮች አንዱ ምንጭ ፓርኩ የቴክኖሎጂ ዘርፉን ከመደገፍ ይልቅ፣ ቦታና ሼዶችን በማከራየት የሚያገኘው ገቢ ላይ ማተኮሩ ነው፤›› የሚል አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡

ወደ አይሲቲ ፓርክ ለመግባት ጥያቄ ያቀረቡ ኩባንያዎችም ወደ ፓርኩ ለመግባት አለመቻላቸውን ገልጸው፣ ጥያቄያቸው ምላሽ አለማግኘቱ ላለመግባታቸው አንዱ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የ“ኤክሰለረንት ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ” ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ መላኩ በሻህ፣ ኩባንያቸው በ2011 ዓ.ም. ሥራ የጀመረው “ቀጥታ ወደ ፓርኩ ትገባላችሁ” የሚል ቃል ተገብቶላቸው መሆኑን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ ይሁንና “በሰዎች መቀያየርና በፋይል መጥፋት” ምክንያት እስካሁን ወደ ፓርኩ እንዳልገቡ አስረድተዋል፡፡

ሌላው ወደ ፓርኩ መግባት አለመቻሉን የገለጸው “ኤምኤምሲዋይ ቴክ” የተባለ ኩባንያ ሲሆን፣ የኩባንያው ዋና የቴክኖሎጂ ኃላፊ አቶ ታዲዮስ ተፈራ ወደ ፓርኩ ለመግባት ለመጀመርያ ጊዜ ጥያቄ ያቀረቡት ከአምስት ዓመት በፊት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ “በጊዜው በቂ የኢንተርኔትና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የለም” የሚል ምላሽ እንዳገኙ ገልጸው፣ አሁንም ቢሆን ለኩባንያቸው የሚሆን መሠረተ ልማት ባለመዘርጋቱ ወደ ፓርኩ አለመግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

ኩባንያዎቹ እንደሚገልጹት በከተማዋ ውስጥ ሰፊ የሥራ ቦታ ማግኘት ባለመቻላቸው ቢሮዎቻቸውን ከአንድ በላይ የሆኑ ሕንፃዎችን በውድ ዋጋ በመከራየት እንዲከፍቱ ተገደዋል፡፡ 200 ሔክታር መሬት ላይ ወዳረፈው አይሲቲ ፓርክ መግባት በከተማዋ ውስጥ ለማግኘት ያልቻሉትን ሰፊ የሥራ ቦታ በርካሽ ለማግኘት እንደሚረዳቸው ያምናሉ፡፡

ፓርኩ ለአገር ውስጥ ኩባንያዎች አንድ ካሬ ሜትር በ4.7 ዶላር፣ ለውጭ አገር ኩባንያዎች ደግሞ በ5.1 ዶላር ወርኃዊ ክፍያ ያከራያል፡፡ ይሁንና በፓርኩ ውስጥ ያለው የኪራይ ዋጋ ከፍተኛ ነው የሚል ቅሬታም ተነስቷል፡፡

የ“ኤክሰለረንት ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ” ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ መላኩ፣  ይህ ዋጋ አሁን ቢሮ ለከፈቱባቸው ሕንፃዎች ከሚከፍሉት ጋር ተቀራራቢ እንደሆነ ተናግረው፣ ፓርኩ ከከተማ ካለው ርቀት ጋር ተዳምሮ ይኼ ዋጋ አዋጭ አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡ ‹‹ደንበኞቻችን በውጭ አገሮች የሚገኙ ኩባንያዎች በመሆናቸው ዝቅተኛ ዋጋ በማቅረብ የዓለም ገበያ ላይ መወዳደር አለብን፤›› የሚሉት ዳይሬክተሩ፣ ለዚህም ሲባል እንደ ኪራይ ያሉ ወጪዎችን መቀነስ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሁለት ሺሕ ካሬ ብንፈልግ በወር 500 ሺሕ ብር ገደማ በየወሩ መክፈል አለብን፣ ከተማ ውስጥ ከዚህ ያነሰ ዋጋ ሕንፃ መከራየት እንችላለን፤›› በማለት አክለዋል፡፡

ዳይሬክተሩ ኩባንያቸው ወደ ፓርኩ ለመግባት በሒደት ላይ መሆኑን ገልጸው፣ ‹‹መግባት አለመግባታችን ግን በሚያቀርቡልን ዋጋ ላይ ይወሰናል፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የአይሲቲ ፓርክ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሱራፌል ሽመልስ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ ገለጻ፣ ፓርኩ በየሁለት ዓመቱ የዋጋ ጭማሪ ማድረግ ቢኖርበትም ለሰባት ዓመታት የኪራይ ዋጋን ሳይጨምር አንድ ካሬ ሜትር በአንድ ዶላር ሲያከራይ ቆይቷል፡፡ የዋጋ ጭማሪ ከመደረጉ በፊት ለሁለት ዓመታት ጥናት መካሄዱንና በአሠራሩ መሠረት 12 ዶላር መሆን የነበረበት የኪራይ ዋጋ በአምስት ዶላር ገደማ እየቀረበ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ዋጋ የተስማሙ ሦስት ኩባንያዎች በቅርቡ በአይሲቲ ፓርክ ውስጥ ሥራ መጀመራቸውንም ገልጸዋል፡፡

አቶ ሱራፌል 12 ኩባንያዎች ለመግባት ያቀረቡት ጥያቄ እየታየ መሆኑን ጠቁመው፣ ወደ ፓርኩ ለመግባት ብዙ ግዜ እንደፈጀባቸው የገለጹ፣ ኩባንያዎች ከዚህ በፊት በነበረው የፓርኩ አስተዳዳሪ ተቋም ጊዜ ያመለከቱ ሊሆኑ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

በፓርኩ ውስጥ የጎደሉ መሠረተ ልማቶችን ለማሟላትም የኢንተርኔት መስመር ዝርጋታና የኤሌክትሪክ ኃይል ማከፋፈያ ግንባታ፣ እንዲሁም የሦስት የውኃ ጉድጓዶች ቁፋሮ እየተጠናቀቀ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ፓርኩ ከከተማ ያለውን ርቀት የሚያጠቡ ሁለት መንገዶች ግንባታ እየተከናወነ እንዳለ ገልጸው፣ እነዚህም መሠረተ ልማቶችን በአንድ ዓመት ከሦስት ወር ውስጥ ሠርቶ የማጠናቀቅ ዕቅድ እንዳለ አክለዋል፡፡

አይሲቲ ፓርክ በ2003 ዓ.ም. አገልግሎት ሲጀምር በቀድሞው የኢትዮጵያ ኢንፎርሚሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ሥር ይተዳደር የነበር ሲሆን፣ ከሰኔ 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ደግሞ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥር እየተዳደረ ነው፡፡

በፓርኩ ውስጥ ያሉና ወደ ፓርኩ መግባት የሚፈልጉ ኩባንያዎች አይሲቲ ፓርክ  በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥራ መተዳደሩ ለዘርፉ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ፣ የሚያገኘው ገቢ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ምክንያት ሆኗል ይላሉ፡፡ ይህም ፓርኩ ከተመሠረተበት ዓላማ ጋር አብሮ አይሄድም የሚል ሐሳብ አንስተዋል፡፡ ኢንዱስትሪ ፓርኩ መሠረተ ልማትን በቅናሽ ዋጋ ለኩባንያዎቹ ቢያቀርብ ኩባንያዎቹ ፓርኩ አሁን ላይ በኪራይ ከሚያገኘው ገቢ በላይ የሚሆን ታክስ ለመንግሥት ማስገባት እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሱራፌል በበኩላቸው አይሲቲ ፓርክ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ሥር በመሆኑ፣ ‹‹ዓላማው አቅም ያላቸው ኩባንያዎችን መሳብ ነው፤›› ብለዋል፡፡ አይሲቲ ፓርክ እንደ ሌሎች የኢንዱስትሪ ፓርኮች እንደሚታይ የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ፓርኩ እስካሁን የወጣበትን ወጪ እንዳልመለሰም ተናግረዋል፡፡

የቴክኖሎጂ ዘርፉን የሚመራው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ አብዛኛዎቹ በፓርኩ ውስጥ የሚሠሩ ሥራዎች ሚኒስቴሩን የሚመለከቱ መሆኑን ገልጾ የአስተዳዳሪነት ጥያቄ እንዳለው አስታውቋል፡፡ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሚኒስቴሩ የሚዲያና የፕሬስ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ አለምነህ፣ ‹‹ፓርክ ስለሆነ ብቻ በኢንዱስትሪ ፓርክ ሥር ማድረግ ልክ አይደለም፤›› ብለው፣ ፓርኩ በሚኒስቴሩ ሥር እንዴት ይተዳደር የሚለውን በተመለከተ የመዋቅር ጥናት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የመዋቅር ጥናት እየተደረገ መሆኑ አይሲቲ ፓርክ በሚኒስቴሩ ሥር እንደሚሆን እንደሚችል የሚጠቁም መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና “የሚመለከተው አካል” ተቋማት ላይ ማሻሻያ ለማድረግ እየሠራ በመሆኑ፣ የመንግሥትን ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑን ተናግረው፣ የፓርኩን የአስተዳዳሪነት ጥያቄ ለመመለስ መመርያ መውጣት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

በ2002 ዓ.ም. የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ኮርፖሬሽንን ለማቋቋም የወጣው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ፣ የፓርኩን የተቆጣጣሪነት ሥልጣንን ለቀድሞው የኢትዮጵያ ኢንፎርሜሽን ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ልማት ኤጀንሲ ሰጥቶ እንደነበር ይታወሳል፡፡  

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች