የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን ከሦስት ዓመት በፊት በተካሄደው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕጣ የወጣላቸውና በተለያዩ ምክንያቶች የጋራ መኖሪያ ቤቶች ባለቤት የሆኑ ነዋሪዎችን ቤት በሚቀጥለው ወር ሙሉ ለሙሉ ለማስረከብ እየሠራ መሆኑን ገለጸ፡፡
በሚቀጥለው ወር ወደ ቤታቸው ይገባሉ የተባሉት ከ63 ሺሕ በላይ የቤት ባለቤቶች ሲሆኑ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ በ16 ሳይቶች የሚገኙ መሆናቸው ታውቋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አውራሪስ ከበደ፣ የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ ላይ ቅድመ ርክክብ ቢደረግም፣ የመሠረተ ልማት ሥራዎች ባለመጠናቀቃቸው የቤት ባለቤቶች ሙሉ ለሙሉ ተረክበውና አፅድተው አለመግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡
እነዚህ የቤት ባለቤቶች በ13ተኛው ዙር የ20/80 ዕጣ፣ በሁለተኛው ዙር የ40/80 ዕጣ፣ እንዲሁም እንደ የልማት ተነሺነት ባሉ ልዩ ልዩ ምክንያቶች የቤት ባለቤት የሆኑ ናቸው፡፡ በ2011 ዓ.ም. በወጣው ዕጣ 52 ሺሕ ቤቶች ለባለዕድለኞች የተሰጡ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 47 ሺሕ የሚሆኑት የቤት ባለቤቶች ውል መፈጽማቸው ተገልጿል፡፡
የቤት ባለቤት ከሆኑት ውስጥ እያፀዱ ያሉና መኖር የጀመሩ እንዳሉ የተናገሩት አቶ አውራሪስ፣ ብዙዎቹ ግን ቤታቸውን ሙሉ ለሙሉ አለመረከባቸውን አስታውቀዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ቤቶቹን ላለመረከባቸው ምክንያት የሆነው ቤቶቹ ሙሉ ለሙሉ ተገንብተው አለማለቃቸው ብቻ ሳይሆን እንደ ውኃ፣ መብራትና መንገድ ያሉ የመሠረተ ልማት አቅርቦቶች አለመዘርጋታቸው እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
እነዚህን ቀሪ ሥራዎች አጠናቆ ነዋሪዎች ወደ ቤታቸው እንዲገቡ ማድረግ በኮርፖሬሽኑ የ100 ቀናት ዕቅድ ውስጥ ያለ መሆኑ ያስረዱት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ 100 ቀናት የሚጠናቀቀው ጥር 10 ቀን 2014 ዓ.ም. እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
የነዋሪዎቹን የቤት መረከቢያ ጊዜ ያስረዘሙ ምክንያቶች ለብዙ ጊዜያት የተከማቹ ናቸው የተባለ ሲሆን፣ የፕሮጀክት አፈጻጸም ማነስ፣ ፋይናንስ እጥረትና ከመሠረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ጋር በቅንጅት አለመሥራት ተጠቃሽ ናቸው፡፡