ወደ ክልል ዕርዳታ ጭነው ከሄዱ ተሽከርካሪዎች ውስጥ 1,010 አልተመለሱም
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ተወካይ ካትሪን ሶሲ (ዶ/ር) ትግራይ ክልል የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ የተላኩ ተሽከርካሪዎች ባለመመለሳቸው፣ በኢትዮጵያ ለትግራይ ክልል ለሚያደርገው ድጋፍ የዕርዳታ ገንዘብ በማፈላለግ ፋንታ ለተሽከርካሪ መግዣ ገንዘብ እያፈላለገ እንደሆነ አስታወቁ፡፡
ከኅዳር 14 እስከ 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ባሉት ተከታታይ አሥር ቀናት ብቻ ወደ ትግራይ ከስምንት ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ጭነቶችን ይዘው የሄዱ 203 ተሸከርካሪዎች፣ በተላኩ በሦስት ቀናት ውስጥ መመለስ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም አንድም የጭነት ተሽከርካሪ አለመመለሱን አቶ ምትኩ አስረድተዋል፡፡
ይህ የተገለጸው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ተወካይ ካትሪን ሶሲ (ዶ/ር) ከአቶ ምትኩ ጋር በመሆን፣ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ስላለው አጠቃላይ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተደራሽነት ላይ ሐሙስ ኅዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች መግለጫ ሲሰጥ ነው፡፡
ተወካይዋ እንደገለጹት፣ በትግራይ ክልል ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች ዕርዳታ ጭኖ ለመላክ ክልሉን እንመራለን ከሚሉ የሕወሓት ሰዎችና መቀሌ አካባቢ ከሚገኙ አካላት ጋር ተሽከርካሪዎች እንዲመለሱ ለመጠየቅና ለመስማማት የተሞከረ ቢሆንም፣ ውጤቱ በተፈለገው ልክ ባለመሆኑ ተመድ ለዜጎች ዕርዳታ መግዣ ገንዘብ በማፈላለግ ፋንታ፣ የዕርዳታ እህል የሚጭኑ ተሽከርካዎችን መግዣ ገንዘብ እያፈላለገ መሆኑን ካትሪን (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ በበኩላቸው እንዳስታወቁት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል ከሕወሓት ታጣቂዎች ጋር ሲያደርግ የነበረውን ጦርነት በመግታት የተናጠል የተኩስ አቁም ካወጀ ወዲህ፣ ወደ ትግራይ ክልል ከተላኩ 1,317 ተሸከርካሪዎች ውስጥ ያልተመለሱት 1,010 መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ተሽከርካሪዎቻቸው በትግራይ ክልል ዕርዳታ ጭነው ከሄዱ በኋላ ያልተመለሱላቸው የተወሰኑ ባለንብረቶች ለትራንስፖርት ሚኒስቴር አቤት እያሉ እንደሆነ የገለጹት አቶ ምትኩ፣ ጉዳያቸው ካልተፈታ በቀጣይ ወደ ፍርድ ቤት የማይሄዱበት ምክንያት እደማይኖር አስታውቀዋል፡፡
መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ክልል ከመጣ ወዲህ ዕርዳታ ወደ ትግራይ ማመላለስ የነበረባቸው ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ ገብተው መመለስ ሲጠበቅባቸው ሕወሓት ለጦርነት የሚማግዳቸውን ወጣቶችና ወታደሮች ጭኖ ማመላለሻ ከማድረግ ባለፈ፣ የሕወሓት ታጣቂዎች በአማራና አፋር ክልሎች የሚያደርጉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ዘረፋ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ በዝምታ ማለፍን እንደመረጠ አቶ ምትኩ አክለው ተናግረዋል፡፡
ሕወሓት ምንም እንኳ የአፋር ሕዝብ ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ ቢያካሂድበትም የአፈር ክልልን አልፎ ወደ ትግራይ የሚሄደው ዕርዳታ ሲታይ፣ የአፋር ሕዝብና የፌደራል መንግሥቱ ምን ያህል ትዕግሥተኛና ለሰብዓዊነት ተቆርቋሪ እንደሆነ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡
በሰሜኑ ጦርነት የሰብዓዊ ዕርዳታ ድርጅቶች ከሚያደርሱት ዕርዳታ ውስጥ 80 በመቶ የሚሆነው በጦር ቀጣና ውስጥ በመሆኑ የፀጥታው ሁኔታ ከፍተኛ ስጋት እደሆነባቸው፣ በዚህም ላለፉት 12 ወራት 23 የረድኤት ሠራተኞች እንደተገደሉባቸው ካትሪን (ዶ/ር) አክለው ገልጸዋል፡፡
የኮምቦልቻ የዕርዳታ መጋዘን በሕወሓት ታጣቂዎች ከፍተኛ ዘረፋ እንደተፈጸመበት ጠቁመዋል፡፡
አቶ ምትኩ እንደተናገሩት በሕወሓት ትንኮሳ ሰበብ ባንኮች በትግራይ ሥራ በመቆማቸው በክልሉ ባጋጠመው የገንዘብ እጥረት ምክንያት፣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት የአውሮፕላን በረራ አማካይነት በሳምንት ሁለት ጊዜ በሚያደርገው በረራ 400 ሚሊዮን ብር ተልኳል፡፡
የተመድ የኢትዮጵያ ተወካይ እንደተናገሩት፣ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ 20 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ ዕርዳታ ያስፈልጋቸዋል፡፡