Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናፓርላማው የተቋማቸውን ሪፖርት የማያቀርቡ ባለሥልጣናትን አስጠነቀቀ

ፓርላማው የተቋማቸውን ሪፖርት የማያቀርቡ ባለሥልጣናትን አስጠነቀቀ

ቀን:

ከተጠሩ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች አንድም ሚኒስትር አልተገኘም

የሚመሩትን ተቋም የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት በግንባር ቀርበው ለምክር ቤቱ የማያቀርቡ ሚኒስትሮችንና ሌሎች የመንግሥት ተቋማትን በበላይነት የሚመሩ ኃላፊዎች አሠራራቸውን እንዲያስተካክሉ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አስጠነቀቀ፡፡

ቋሚ ኮሚቴው ኃላፊዎቹን ያስጠነቀቀው 2014 በጀት ዓመት የባለድርሻ አካላት የጋራ ፎረም ዕቅድ ላይ ኅዳር 29 ቀን 2014 .ም. ውይይት ባካሄዱበት ወቅት ነው፡፡

- Advertisement -

በውይይቱ ከአሥር በላይ ተቋማት በተለይም የገንዘብ ሚኒስቴር፣ የገቢዎች ሚኒስቴር፣ የፕላንና ልማት ሚኒስቴር፣ የትምህት ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን፣ የጉምሩክ ኮሚሽን፣ ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት፣ የግዥ አገልግሎትና ንብረት አስተዳደር ኤጄንሲ ተጋብዘዋል፡፡

በፓርላማው ደንብና አሠራር መሠረት በውይይቱ የተጋበዙ ተቋማት ሚኒስትሮችና የበላይ ኃላፊዎች በአካል ቀርበው ዕቅዳቸውን ማቅረብ ቢጠበቅባቸውም፣ ከአራቱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተገኘ አንድም ሚኒስትር አልነበረም፡፡

አቶ ከድር እድሪስ የተባሉ የቋሚ ኮሚቴው አባል፣ ‹‹እኛ በምክር ቤት ደረጃ የሾምነው ሚኒስትሮችን ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ወሳኝ በሆነ የሕዝብ ጉዳይ መገኘት ነበረባቸው፤›› ብለዋል፡፡

የምክር ቤት አባሉ በውይይቱ ዋዜማ ቋሚ ኮሚቴው ‹‹ሁሉም ሚኒስትሮች መገኘት እንዳለባቸው የተገለጸ ቢሆንም የተገኘ የለም›› በማለት ይህ ለምን ሆነ ሲሉ የጠየቁ ሲሆን፣ ለእንዲህ ዓይነት አካሄድ ቋሚ ኮሚቴው ጠንከር ያለ አቅጣጫ ማስቀመጥ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

ወ/ሮ መዓዛ የተባሉ ሌላ የምክር ቤት አባል የመንግሥት ወጪ አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ሲቋቋም፣ አገሪቱ አሁን ካለችበት ውስብስብ ችግር ለመሻገር በትንሽ ወጪ ተሻጋሪና ከፍተኛ ሥራዎች መከናወን እንዳለባቸው በመታመኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

ለተከታታይ 30 ዓመታት የፈጻሚ አካላት ሥልጣን ለሀብት ማግበስበሻነት ይውል የነበረ በመሆኑና የተፈጠረው ሌብነት ለእርስ በርስ ጦርነት አገሪቱን እንደዳረጋት የገለጹት የምክር ቤት አባል፣ አሁን የመንግሥት ለውጥ ተካሂዶ የነበረው አሠራር እንዳይቀጥል ፈጻሚ አካሉ ከቋሚ ኮሚቴው ጋር ተናቦ መሥራት እንደሚገባው አስገንዘበዋል፡፡

‹‹በዛሬው ስብሰባ ምክር ቤቱ የሕዝብ ድምፅ የተሸከመና ትልቅ ኃላፊነት ይዞ የመጣ በመሆኑ፣ ዛሬ የጠበቅኩት ሚኒስትሮች ይመጣሉ ብዬ ነበር፡፡ ነገር ግን የመጡት ተወካዮች በዳይሬክተርና በተለያዩ ደረጃዎች ያሉ የሥራ ኃላፊዎች ናቸው፡፡ የእነሱን መምጣት በማከብር ቢሆንም ችግርን ከሥሩ ለመንቀልና ለቀጣይ ሥራ  ያሳስበኛል፤›› ብለዋል፡፡

ወ/ሮ መዓዛ  መሠረታዊ ለውጥ ሊመጣ የሚችለው ዕቅዶችን የጋራ በማድረግ በመሆኑ፣ ‹‹ቋሚ ኮሚቴው ሚኒስትሮችን እንደገና በመጥራትና በማነጋገር መሠራት ያለበት መከናወን ይኖርበታል›› ብለዋል፡፡ ያ ካልሆነ ግን አሁን በመጀመርያው የትውውቅ መድረክ ካልተገኙ ነገ ተናቦ ለመሥራት አስቸጋሪ እንደሚሆነ ተናግረዋል፡፡

በጦርነቱ ምክንያት በርካታ መሠረተ ልማቶች በመውደማቸውና በአነስተኛ ወጪ መልሶ ለመገንባት ለመወሰን፣ የተቋማት የበላይ ኃላፊዎች መገኘት አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በሌላ በኩል ቋሚ ኮሚቴው ተቋቁሞና የሥራ ርክክብ አድርጎ ሥራ ከጀመረ ጀምሮ፣ የኃላፊዎች አለመገኘት መቀጠሉንና ሥራ ለመሥራት አስቸጋሪ እንደሆነባቸው የተናገሩት ሌላኛዋ የምክር ቤት አባል ወ/ሮ ዘሐራ መሐመድ  ናቸው፡፡

‹‹በአምስተኛው የፓርላማ ዘመን ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት የተቋማትን የኦዲት ግኝት ለማስተካከል፣ አጥፊዎችን ወደ ሕግ ለመውሰድ፣ እንዲሁም ቋሚ ኮሚቴው ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ሲጠራ ኃላፊዎች የመሥሪያ ቤታቸውን ክፍተት ወይም አፈጻጸም ራሳቸው ቀርበው ከማቅረብ ይልቅ፣ በታችኛው እርከን ያሉ ኃላፊዎችን በተደጋጋሚ የመላክ ችግር እንደነበር መረጃ ደርሶናል፤›› ብለዋል፡፡

ነገር ግን ይህ ችግር አሁን እየቀጠለ እንደሆነ፣ የበላይ ኃላፊዎች ለስብሰባ ካለመገኘታቸው በተጨማሪ ለስብሰባ መነሻ ዕቅድ አላላካቸው ሲታይ፣ ባለሙያው ከኃላፊው ጋር ተነጋግሮና ተወያይቶ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት ዕቅዱን መላክ ሲገባው፣ አንዳንዶቹ ካለፈው ዓመት ዕቅድ ገልብጠው (Copy Paste) መላክና መሥሪያ ቤቱ ስሙ ተቀይሮ ሳለ ቀድሞ የነበረውን ስም እንዳለ ይዞ ማምጣት የኃላፊዎች ትኩረት ማነስ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

‹‹በመሆኑም አገሪቱ አሁን ካለችበት ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ አኳያ እንዲህ ዓይነት ዝርክርክነት ያዋጣናል ወይ?›› በማለት ጥያቄ አቅርበው፣ ለጉዳዩ ትኩረት በማድረግ ኃላፊዎቹ እንዲህ ዓይነት አካሄዳቸው ስለማያዋጣ እንዲያስተካክሉ ጠይቀዋል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ምክትል ዋና  ኦዲተር ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ በበኩላቸው፣ በቀደመው የፓርላማ ዘመን በነበሩ ውይይቶች የተቋማት የተወሰኑ ኃላፊዎች ብቻ እንደሚገኙ፣ የሚመጡት ኃላፊዎችም ከምክር ቤቱና ከዋና ኦዲተር የሚሰጣቸውን አስተያየትና ግብረ መልስ ከኃላፊዎች ጋር ተነጋግረው ማስተካከያ ሲወስዱ እምብዛም  አለመታየቱን ገልጸዋል፡፡

ማስተካከያ ያለማድረግ ችግር ደግሞ በዋነኝነት የተቋማቱ ኃላፊዎች በውይይቱ በኣካል ስለማይገኙ እንደሆነ፣ አንዳንዴም ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሰዎች እንደሚላኩ አስረድተዋል፡፡

ምክትል ዋና ኦዲተሯ በቀጣይ የኦዲተር መሥሪያ ቤት የኦዲት ሪፖርት ሲቀርብ፣ በቀጥታ የቴሌቪዥን ሥርጭት ለሕዝብ እንዲተላለፍ ለቋሚ ኮሚቴው ጥያቄ አቅርበዋል፡፡

‹‹በሹመት ወቅት ፓርላማ ቀርቦ በፓርላማ አባላቱ ፊት ቃለ መሃላ የፈጸመው ምክትሉ ወይም ዳይሬክተሩ ሳይሆን ሚኒስትሩ በመሆኑ፣ እኛ መጠየቅ የምንችለው ሚኒስትሩን እንጂ ዳይሬክተር ወይም ኃላፊ አይደለም፤›› ያሉት ደግሞ  የቋሚ ኮሚቴው ምክትል ሰብሳቢ ወ/ሮ አራሬ ሞሲሳ ናቸው፡፡

ከቀናት በፊት ለዚህ ውይይት ተቋማቱ ሲጠሩ በተላከው የመጥሪያ ደብዳቤ የየመሥሪያ ቤቱ ኃላፊዎች ብቻ እንዲገኙ የተባለ ቢሆንም፣ አለመገኘታቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹ሥራውን የምትሠሩት ምክትሎች ወይም ዳይሬክተሮች ብትሆንም፣ ተጠያቂነትን ለማስፈን ሚኒስትሮች መገኘት ነበረባቸው፤›› ብለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ክርስቲያን ታደለ፣ ቋሚ ኮሚቴው  ሊጠይቅ የሚችለው የተቋማት የበላይ ኃላፊዎችን በመሆኑ፣ እንዲህ ዓይነት አሠራር ምክር ቤቱ ካለው ግርማ ሞገስ አኳያ ሊደገም የማይገባና በአንክሮ እንዲታይ አሳስበዋል፡፡

‹‹ይህ ጉዳይ ከአሁኑ ሊቀረፍና ሊስተካካል ይገባል፡፡ ከዚህ በፊት የነበረው የድሮ አሠራር ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ እንደ አዲስ የተቋቋመ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመሆኑ፣ ሕዝቡ ከሕግ አውጭው፣ ከአስፈጻሚውና ከሕግ ተርጓሚው የሚፈልገውን ነገር ማግኘት ስለሚጠበቅበት ወደፊት መደገም የለበትም፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...