ቅፅበታዊ የአየር ሁኔታን ለመተንበይ ያስችላሉ ተብሏል
ለአየር ሁኔታ መከታተያ የሚሆኑ ሦስት ራዳሮችን ከ400 ሚሊዮን በላይ በሆነ ወጪ ሊተክል መሆኑን፣ ብሔራዊ ሚቲዮሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ ኃይለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ከፊንላንድ መንግሥት ባገኘው የገንዘብ ድጋፍና ብድር የሚተከሉት እነዚህ ራዳሮች በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ሥራ ይጀምራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ እስካሁን አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው ራዳር አንድ ብቻ እንደሆነና ከሦስት ዓመታት በላይ በሥራ ላይ የሚገኝ መሆኑን፣ የአየር ሁኔታን ለመቆጣጠርና ከዚህ በፊት ለተሞከሩት የደመና ማበልፀግ ሥራዎች ማገልገሉን አስረድተዋል፡፡
ራዳሩ በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ሻውራ በተባለ ቦታ የሚገኝ እንደሆነና በ80 ሚሊዮን ብር ወጪ መገንባቱን የገለጹት ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ፣ በ150 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ክብ ውስጥ መረጃዎችን በውጤታማነት ማስተላለፍ የሚችል ቴክኖሎጂ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አሁን የሚተከሉት ራዳሮች እስከ 450 ኪሎ ሜትር ምሥል የማንሳት አቅም እንዳላቸው፣ እስከ 250 ኪሎ ሜትር በጥራትና በበቂ ሁኔታ መረጃ ማስተላለፍ እንደሚችሉ አክለዋል፡፡
የአየር ሁኔታ መከታተያ ራዳሮቹ በሦስት ቦታዎች የሚተከሉ ሲሆን፣ በመካከለኛው ኢትዮጵያ ክፍል በሰሜን ሸዋ ዞን እነዋሪ በተባለ ቦታ፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ መቆ በተባለ ቦታ፣ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ሃላባ ውስጥ እንደሆነ አቶ ክንፈ ገልጸዋል፡፡ በሰሜን ሸዋ ዞን እነዋሪ የሚተከለው የመጀመሪያው ራዳር መጪው ክረምት ከመግባቱ በፊት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡
‹‹የራዳሮቹ ዋጋ እንደ አካባቢው ይለያያል፣ እያንዳንዳቸው ከ2.5 እስከ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የሚያስወጡ ናቸው፤›› ሲሉ አቶ ክንፈ አስረድተዋል፡፡
ራዳሮቹን ለመትከል የሚያስፈልጉ መሣሪያዎች ፊንላንድ በሚገኙ ድርጅቶች በመመረት ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ ግብዓቶቹ ተመርተው እንዳለቁ በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ወደ አገር ውስጥ በማስመጣት ወደ ተከላ ሥራ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ክንፈ ገለጻ፣ አሁን ሽፋን ያስፈልጋቸዋል ተብለው የተለዩት አካባቢዎች በብዛት ዝናብ የሚገኝባቸውና ጎርፍ የሚከሰትባቸው ቦታዎችን ታሳቢ ያደረጉ ሲሆን፣ ራዳሮቹ በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖርን የአየር ሁኔታ በመከታተልና በመቆጣጠር የረዥም ጊዜ መረጃ ለመመዝገብ የሚያስችሉ ናቸው፡፡ እነዚህን መረጃዎች መሠረት በማድረግ ለግብርና፣ ለጤና፣ ለግንባታ ዘርፍ፣ ለግድቦችና ለሌሎችም ለከባቢ አየር ተጋላጭ የሆኑ ዘርፎች የዝናብ፣ የጎርፍ፣ የድርቅና የንፋስን በተሻለ ጥራት ለመተንበይና ለመመዝገብ ከፍተኛ ሚና ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡
ከዚህ በፊት የአየር ትንበያ የሚሠራው ከተለያዩ አገሮች ሳተላይቶች ከሚሰበሰቡ መረጃዎች መሆኑንና ከእያንዳንዱ ቦታ የአየር ሁኔታ መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ እንደሆነ የጠቀሱት፣ በብሔራዊ ሚትዮሮሎጂ ኤጀንሲ ተባባሪ ተመራማሪ አቶ ለታ በቀለ ሲሆኑ፣ የሚተከሉት ራዳሮች የተለዩ ቦታዎችን የአየር ሁኔታ በተሻለ ጥራት ለመተንበይ እንደሚያስችሉ ይናገራሉ፡፡ ‹‹እስካሁን የአጭር ጊዜ ትንበያ የሚባለው ቢያንስ የአንድ ቀን ነው፡፡ እነዚህ ራዳሮች ግን ከአምስት ደቂቃ ጀምሮ ያሉ ቅፅበታዊ የአየር ሁኔታ ትንበያ ለመሥራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ያላቸው ናቸው፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡
በአጠቃላይ በአገሪቱ የሚገኝ የአየር ሁኔታን በበቂ መጠን ለመከታተል 12 ራዳሮች እንደሚያስፈልጉ በጥናት መታወቁን የጠቆሙት የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ክንፈ፣ አሁን ያለውን ጨምሮ በሁለት ዓመት ተኩል የሚተከሉት ሦስት ራዳሮች ሲጠናቀቁ የተሻለ የአየር ሁኔታ ቁጥጥርና ክትትል አቅምን እንደሚፈጥሩ አስረድተዋል፡፡
ሌሎች ስምንት ራዳሮችን ለመትከል የሚያስፈልገው ፕሮጀክት ፕሮፖዛል መዘጋጀቱን የጠቆሙት አቶ ክንፈ፣ ‹‹ቴክኖሎጂው አዲስ ስለሆነ በአንድ ጊዜ ሁሉም ቢተከሉ ውጤታማ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ ባሉት እየተማርን ሌሎቹን ቀስ በቀስ እናስፋፋለን፤›› ብለዋል፡፡
በምሥጋው ፈንታው