ከተመሠረተ አሥረኛ ዓመቱን የያዘውና በዋናነት በአምስት ባንኮች የተመሠረተው ፕሪሚየር ስዊች ሶሉውሽን (ፒኤስኤስ) ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ከ49 ቢሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ማንቀሳቀስ ሒደቶችን ማካሄድ መቻሉን ገለጸ፡፡
ኩባንያው የተመሠረተበትን አሥረኛ ዓመት የምሥረታ በዓልና የ2013 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸሙን በማስመልከት በሰጠው መግለጫ በዘጠኝ ዓመታት ውስጥ 49 ቢሊዮን ብር በኤቲኤም ማሽን በኩል ማንቀሳቀስ ችሏል፡፡
ፒኤስኤስ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት በአጠቃላይ የገንዘብ መጠናቸው ከ13.9 ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ 15.1 ሚሊዮን የገንዘብ ማንቀሳቀስ ሒደቶችን ያስተናገደ መሆኑን፣ የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ፀሐይ ሽፈራው ገልጸዋል፡፡ ይህም ፒኤስኤስ ሥራ ከጀመረበት ዓመት ጀምሮ ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ውስጥ በጥቅሉ ከ49 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ብዛታቸው ከ56 ሚሊዮን በላይ የገንዘብ ማውጣት ሒደቶችን በኤቲኤም አማካይነት ማስተናገድ ችሏል፡፡
የፒኤስኤስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዮሴፍ ክብረት በበኩላቸው፣ ከባንያው አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የፒኤስኤስአር የያዙ ካርዶች በማተምና ለአባል ባንኮች በማድረስ የባንኮቹን ፍላጎት ያማከለ አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ይህ ቁጥር ፒኤስኤስ ከተመሠረተበት ዓመት ጀምሮ ለገበያ ያሠራጫቸውን የክፍያ ካርዶች ብዛት 3.1 ሚሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉንም አመልክተዋል፡፡
በሞባይል ቀፎ አማካይነት በሚሰጥ ትዕዛዝ ከኤቲኤም ገንዘብ የማውጣት የካርድ አልባ አገልግሎት ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ በተያዘው በሒሳብ ዓመት ከ7.8 ሚሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸው ብዛታቸው 8,244 የሆኑ የገንዘብ ማውጣት ሒደቶችን ያሳለጠ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት የክፍያ መቀበያ ማሽኖችን በመጠቀም በአባል ባንኮችና በዓለም አቀፍ የክፍያ ካርዶች አማካይነት 147,321 የገንዘብ ማንቀሳቀስ ሒደቶችን ወይም ግምቱ 428 ሚሊዮን ብር በላይ የግዥ፣ እንዲሁም የገንዘብ ማውጣት ሒደቶችን ማከናወን ችሏል፡፡ ድርጅቱ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ የተፈጸሙ የፖዝ ትራንዛክሽኖች ቁጥር አበረታች ጭማሪ እያሳየ ቢመጣም፣ በአንፃሩ በኢትዮጵያ ውስጥ የክፍያ መቀበያ ማሽኖችን በመጠቀም የሚደረጉ ግብይቶች አሁንም በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡ ፒኤስኤስ የክፍያ መረቡን ከማስፋት አኳያ በሒሳብ ዓመቱ 67 ተጨማሪ ኤቲኤም ማሽኖች፣ እንዲሁም 771 የክፍያ መቀበያ ማሽኖች ከፒኤስኤስ ሥርዓት ጋር ተገናኝተው አገልግሎት መስጠት በመጀመራቸው፣ በአጠቃላይ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የኤቲኤም ማሽኖች ቁጥር 1,070፣ እንዲሁም የክፍያ መቀበያ ማሽኖች ቁጥር 2,565 አድርሶታል፡፡
ፒኤስኤስ ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር መመዘን ያለበት ከአገልግሎት ጥራትና ስፋት አንፃር ቢሆንም፣ በዚህ በጀት ዓመት ከመቼውም ጊዜ በተሻለ ያልተጣራ ትርፍ ሦስት ሚሊዮን ብር በላይ ያገኘ መሆኑን ኩባንያው አመልክቷል፡፡ ይህ የትርፍ መጠንም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 61.62 በመቶ ጭማሪ እንዳሳየም ገልጿል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ፒኤስኤስ በ2013 ሒሳብ ዓመት አቅዶ የነበረውን የትራንስፎርሜሽን ፕላን ቀረፃ ተግባራዊ በማድረግ ፒደብሊውሲ (PWC) የተባለ ዓለም አቀፍ አማካሪ በመቅጠር የድርጅቱን የአምስት ዓመት ስትራቴጂ ወይም የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በጥምር ሠርቶ ያጠናቀቀ ሲሆን፣ ይህ ስትራቴጂ ዕቅድ ለፒኤስኤስ ተስፋ ሰጪ የሆኑ ሥራዎችን በላቀ አፈጻጸም ተግባራዊ እንዲያደርግ ያግዘዋል ተብሏል፡፡
የፒኤስ ኤስ ዋነኛ ተጣማሪ ባንኮች አዋሽ፣ ንብ፣ ኅብረት፣ ብርሃን፣ አዲስ ኢንተርናሽናልና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮች ናቸው፡፡