Friday, July 19, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

እኛ ኢትዮጵያውያን በጦርነት ያሳየነውን አንድነት በሥራም መድገም አለብን!

የሕወሓት ታጣቂ ቡድን ኢትዮጵያን ለመበተን የተጓዘበት ርቀት ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ ኢትዮጵያን ማፍረስ የማይችል ቢሆንም፣ ሙከራዎቹ ግን እንደ አገር ጎድቶናል፣ አድምቶናል፣ ሕይወት ቀጥፏል፣ ብዙ ንብረት ወድሟል፣ ዜጎችን አፈናቅሏል፡፡ ሕወሓት ተሸንፎ የወጣባቸውን አካባቢዎችም የኢትዮጵያ ኃይሎች እየተቆጣጠሩትና የመንግሥት አስተዳደር እየተጀመረባቸው ነው፡፡ ታጣቂ ቡድኑ በረገጣቸው አካባቢዎች ሁሉ የጥፋት እጁን አሳርፎባቸዋል፡፡ በወረራ ይዘዋቸው የነበሩ አካባቢዎች ላይ ያደረሰው ውድመት፣ የፈጸመው ኢሰብዓዊ የሆነ ድርጊት፣ ኢትዮጵያ በታሪክ በ‹‹ጥቁር መዝገብ›› የምታኖረው ዘግናኝ ድርጊት ነው፡፡ እኩይ ዓላማውን ለማሳካት የፈጸመው ግፍ መቼም አይረሳም፡፡ ጥሎት የሚያልፈውም ጠባሳ ሁሌም የሚታወስ ሲሆን፣ ለዚህ እኩይ ተግባሩ ግን እርሱንና አመለካከቱን በማጥፋት የመጨረሻውን የድል ዜና ማሰማት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ትግሉ ገና ነው፡፡ በመሃል ያሉ የቡድኑን ደጋፊዎች ማጥራት የማይቋረጥ ተግባር መሆን አለበት፡፡

አሁን ላይ የሕወሓት በሕይወት መኖር የዚህች አገር ጠንቅ መሆኑን ከመቼውም ጊዜ በላይ ተረድተናል፡፡ እወክለዋለሁ ለሚለው ሕዝብ ጭምር የማይጠቅም በመሆኑ፣ ኢትዮጵያውያን ዛሬ እየተገኙ ያሉት ድሎችን መቋጨት የሚኖርበት ሕወሓትን በማስቆምና ዳግም የኢትዮጵያ ሥጋት እንዳይሆን በማድረግ ጭምር ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን አሁን እንደጀመርነው አንድነታችንን የበለጠ በማጠናከር፣ ተደማምጠንና ተሳስበን ቀሪውን ትግላችንን በድል መደምደምና አገርን ወደ ማበልፀጉ ሥራ መግባት አለብን፡፡  

በጦር ግንባር የሚደረገው ትግል እንደተጠበቀ ሆኖ፣ በዚህ ቡድን በተፈጸመው ወረራ የወደሙ ከተሞቻችንን መገንባት፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን ወደ ቀዬአቸው መመለስና ኢኮኖሚችንንም ማከም ፊት ለፊት ከሚጠብቁን ብርቱ ሥራዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያን እንደ ጠላት ያዩና ወደፊት እንዳትራመድ ሴራ የጎነጎኑ የውጭ ኃይሎችን መታገል ሌላው ተጠባቂ ሥራችን ነው፡፡ በዲፕሎማሲው መስክ ከዚህ ቀደም የታዩ መዝረክረኮችንና መዘናጋቶችን መማሪያ በማድረግ ኢትዮጵያን እውነት ማስደመጥና ከአጥቂዎቿ መከላከልም ሌላው ብርቱ ሥራ ሆኖ መወሰድ አለበት፡፡

ጦርነቱ በተለይ ኢኮኖሚው ላይ የፈጠረው ተፅዕኖ ቀላል ካለመሆኑ አንፃር፣ እዚህ ላይ ብዙ መሥራት ይጠይቃል፡፡ በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ መገንባትና ሥራ ማስጀመር፣ የተስተጓጎሉ አምራች ኩባንያዎች በሙሉ አቅማቸው እንዲያመርቱ ማድረግ ከዛሬ የምንጀምራቸው ሥራዎች መሆን አለባቸው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ማግኛ የገበያ መዳረሻዎቻችንን ማስፋት፣ አዳዲስ ገበያዎችን ማፈላለግ፣ ምርት ማሳደግና ቢያንስ ስንዴና ዱቄት ከውጭ እንዳይገባ በርትቶ መሥራት የግድ ይለናል፡፡

አሁን ከወረራ ከተለቀቁ ከተሞቻችን አንፃር በቀዳሚነት ግን እንደ ኤሌክትሪክና መሰል የወደሙ መሠረተ ልማቶችን ማበጀትና ለሥራ ማብቃት ይኖባቸዋል፡፡ የሽብርተኛው ቡድን መውጣትን ተከትሎ የወደሙ የኤሌክትሪክና የስልክ አገልግሎቶችን እንዲጀመሩ እየተሠራ ያለው ሥራ ግን እንደ መልካም የሚወሰድ ነው፡፡ እንዲሁ በሁሉም የተጎዱ አካባቢዎች ከሥር ከሥር ሥራዎችን መሥራት ብዙ ነገሮችን ያቀላል፡፡ በአጠቃላይ ግን እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ለመሥራት ኢትዮጵያ ትልቅ አቅም ያስፈልጋታል፡፡ ዋነኛው ገንዘብ ነው፡፡ የውጭ ምንዛሪ ፍላጎታችንም በእጅጉ የሚጨምር ስለሆነ፣ የውጭ ምንዛሪ ግኝታችንን ልናሰፋ የምንችልባቸው የተለያዩ አማራጮችን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንፃር በኢትዮጵያ ችግር ወቅት አለኝታነታቸውን ያሳዩ የኢትዮጵያ ድምፅ ለዓለም እያሰሙ ያሉ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያን ጅምር ጠንክሮ መቀጠል አለበት፡፡ ከዚህ በኋላ በምትቀጥለው ኢትዮጵያ ውስጥ ዳያስፖራዎች የሚኖራቸው ሚና በገንዘብ በመደገፍና የውጭ ምንዛሪን በትክክለኛው መንገድ ከማስገባት በላይ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና ያለው መሆኑን በማሰብ የኢኮኖሚያዊ ክንውኖቻችንን ከዚሁ ተግባር ጋር ማቆራኘት ያስፈልጋል፡፡

ለዚህ ደግሞ የገና በዓልን አስመልክቶ ወደ አገር ቤት የሚመጡ ዳያስፖራዎች የኢትዮጵያ ጉዞ እንደ ትልቅና መልካም ዕድል መወሰድ አለበት፡፡ ዳያስፖራዎች በነገዋ ኢትዮጵያ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ በቂ መረጃ የሚይዙበት፣ በቶሎም እንዲተገበሩ ለማስቻል ይህንን አጋጣሚ በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በአግባቡ ኢንቨስት ለሚያደርጉት ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተመቻቸ ፖሊሲ ማዘጋጀት አንዱ መንገድ ነው፡፡

አሁን ካለንበት ችግር አንፃር ዳያስፖራዎች ላይ የተጣለው አደራ እንዲህ በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ትልቅ አቅም አላቸው ተብሎ ስለሚታሰብ ይህንን አቅም በጋራና በተናጠል ሆነው በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ አጋጣሚውን መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ከመንግሥት ይጠበቃል፡፡

ወደ አገር ቤት ለሚመጡ ዳያስፖራዎች የኢንቨስትመንት አማራጮች ስለመኖራቸው የምናሳይበት ጥሩ አጋጣሚ ነውና በቀጥታ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት አዋጭ የሚባሉ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን በማቅረብ ዳያስፖራው የአገሩን ኢኮኖሚ በማሳደጉ ረገድ የበለጠ ሚና እንዲኖረው ማድረግ ይገባል፡፡ የግል ተቋማትም ቢሆኑ አዋጭ ቢዝነሶችን በመቅረፅ ከዳያስፖራው ጋር የሚሠሩበትን አግባብ ሊያመቻቹ ይገባል፡፡

ዳያስፖራው ለራሱም ሆነ አገሩን ለዘለቄታው ለመጥቀምም ቀዳሚው ተግባር መሆን ያለበት ባለው አቅም ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ መሠማራት ስለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ስለዚህ ወደ አገር ቤት የሚደረገው ጉዞ ኢንቨስት አደርጋለሁ ብሎ ጭምር እንዲያስብ ማድረግ፣ መንግሥትም እንዲህ ያሉ ኢንቨስትመንቶች ላይ ብትሳትፉ ብሎ የሚያቀርበው ፕሮጀክት ሊኖረው ይገባል፡፡ በአጭሩ ዳያስፖራዎቻችን ኢንቨስተርም ይሆኑ ዘንድ እናበረታታቸው፣ ሁኔታዎችንም እናመቻችላቸው፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት