የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በካሜሩን የሚያደርገውን ተሳትፎ ምክንያት በማድረግ ቡድኑን ለመደገፍ ወደ ሥፍራው የሚያቀኑ ተመልካቾችን ጉዞ የሚያመቻቹ ተቋማት ዝግጅታቸውን መጀመራቸውን አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከዚህ ቀደም ከሲሳይ አድሬስ ፕሮሞሽን ጋር በጋራ ሆኖ ከ500 በላይ ተመልካቾችንና 25 ጋዜጠኞችን ይዞ ወደ ሥፍራው ለመጓዝ ቅድመ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን መግለጹ አይዘነጋም፡፡
ሲሳይ አድሬስ ፕሮሞሽን የደርሶ መልስ ትኬት፣ የሆቴል፣ የምግብ፣ የጉብኝት፣ የቲሸርት፣ የስታዲየም መግቢያ፣ ከቦታ ቦታ የሚያንቀሳቅስ የትራንስፖርትና የመጨረሻ ጨዋታ ትራንስፖርትን ጨምሮ በ68,223 ብር ክፍያ ማንኛውም ተመልካች መጓዝ እንደሚችል ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ እስካሁን ከ100 በላይ ተመልካቾችን መመዝገቡን የፕሮሞሽኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ አድሬስ ለሪፖርተር አስታውቀዋል፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከሲሳይ አድሬስ ፕሮሞሽን ጋር በጋራ ሆነው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 25 የሚዲያ አካላትንም ወደ ሥፍራው ይዘው እንደሚጓዙ ማብራራታቸው ይታወሳል፡፡
በሌላ በኩል ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር ባለፈው መስከረም ለአራት ዓመት የሚቆይ የ15 ሚሊዮን ብር ስፖንሰርሺፕ የተፈራረመው ኤልኔት ግሩፕ፣ ወደ ካሜሩን የሚያመሩ ተመልካቾች ይዞ የመጓዝ ዕቅዱን ማጠናቀቁን አስታውቋል፡፡
ማክሰኞ ታኅሣሥ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጋር በጋራ ሆኖ ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጠው ተቋሙ ከጥር 1 ጀምሮ የካሜሩኑን የአፍሪካ ዋንጫ ለመመልከት ወደ ሥፍራው የሚያመሩ ተመልካቾችን ለመውሰድ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢቲ ሆሊደይስ ጋር በመሆን ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ ለ17 ቀናት የሚቆይ የጉዞ መሰናዶ የተመረጠ የሆቴል ቆይታ፣ የምግብ፣ የጉብኝት፣ የመዝናኛ ፕሮግራሞች ወጪን፣ የትኬት፣ የቪዛ፣ የኢንሹራንስና የኮቪድ ምርመራ ወጪን ጨምሮ 135 ሺሕ ብር ማግኘት እንደሚቻል በጋዜጣዊ መግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ተቋሙ የሚዲያ አካላትንም ሙሉ ወጪ ችሎ ወደ ሥፍራው እንደሚጓዝ ያብራራ ሲሆን፣ ሚዲያዎቹን መርጦ የሚያቀርበው ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እንደሆነ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ጥላሁን አስረድተዋል፡፡