ዛሬ የጉዞ አቅጣጫችን ከሜክሲኮ ወደ ቄራ ነው። እንደተለመደው ሁሉ ዛሬም በታክሲያችን ሰው ሠራሽ ጣርያ ሥር ተሰብስበናል። ማንም ቢሆን ከታክሲ ጣርያ ሥር ባይገኝም፣ ከሕግ ጣርያ በታች መሆኑ ግን አይቀርም። በተለይ ደግሞ ሕዝብ የገደሉ፣ ንብረቱን የዘረፉና ያወደሙ መጨረሻቸው ሕግ ፊት መቅረብ ነው። ጉልበተኞች እየፈነጩ በነበረበት ጊዜ ስንቱ በሕግ ተማምኖ ሲኖር ተሰቃይቶ ይሆን? የሕግ የበላይነትን ተማምነን መኖር ካልቻልን ፈተናችን ብዙ ይሆናል፡፡ ‹‹ዜጎች በሕግ ፊት እኩልነታቸው ካልተጠበቀና ፍትሕ ሁሉንም ዜጋ በእኩልነት ካላየች አቤት ማለት አለብን፡፡ ፍትሕ እንዳይዛባ ድምፃችንን ከፍ ማድረግ አለብን፡፡ አገር ሊያፈርሱ የነበሩ ወንበዴዎች ሕግ ፊት ቀርበው ቅጣታቸውን ካልተቀበሉ፣ እንዴት ሆኖ ነው ስለሕግ የበላይነት የምንነጋገረው…›› የሚል የምሬት ድምፅ ይሰማል፡፡ ዘንድሮ ሰው ሁሉ አምርሯል፡፡
ታክሲያችን ሜክሲኮ አደባባዩን እየዞረች ነው። ‹‹አሁንስ የቢል ቦርድ መዓት ተገጥግጦ ዓይናችንን እያጭበረበረው ሊያጠፋው እኮ ነው…›› አለ አንዱ ተሳፋሪ። ሌላኛውም ቀጠለ። ‹‹እኔ እኮ የምለው ለዓለም አየር ንብረት ለውጥ ችግር መፍትሔ ይሆን ዘንድ ችግኝ ነው እንጂ ትከሉ የተባለው ቢል ቦርድ ነው እንዴ?›› አለ። ሌላኛዋ ወጣት ተሳፈሪ፣ ‹‹ምን ችግር አለው? ብቻ ቢል ቦርዱ ልማታዊ ከሆነ እንደ ችግኝ መቁጠር ቀላል ነው…›› ስትል ወዲያው አንዱ ከአፏ ነጥቆ፣ ‹‹አንቺ ኧረ እንደ እሱ አይባልም፣ አሁን እኮ ቢል ቦርዱም፣ ኪነ ጥበቡም፣ ውይይታችንም አገር አገር ማለት ነው ያለባቸው›› በማለት ማስተካከያ ሰጠ። ‹‹ተወኝ እባክህ ከዚህ በላይ ምን እንዳንሆን ነው?›› ብላ ትካዜ ውስጥ ጭልጥ አለች። ምን ሆነሽ ነው ማለቱን መርሳቱ ሳይሻል አይቀርም። በአሁኑ ጊዜ ምንስ ባይኮን ምን እንደሆንን አጥተነው ነው? ምን ሆናችሁ እያልን የምንጠያየቀው? ሆድ ይፍጀው ብቻ!
በዚህ ጊዜ ሾፌሩ፣ ‹‹ኧረ ዞር በል…›› እያለ ከማይሰማው መንገደኛ ጋር ይጯጯኋል። ‹‹እንዴ እኔ የምለው እንዴት ነው ሰው ትርፍ ሕይወት አለው እንዴ እንዲህ መኪና የሚዳፈረው?›› አለና ጠየቀ። ማንን እንደሚጠይቅ ግልጽ አላደረገልንም፡፡ ወያላውን እስካሁን ድምፁን አልሰማነውም። ሲያዩት ዝምተኛ ይመስላል። ‹‹ነው ብለህ ነው? ሰው ምን ትርፍ ነፍስ ቢኖረው እንዴት በገዛ እጁ ሕይወቱን ያጠፋል?›› ብሎ ጥያቄውን በጥያቄ መልሶለት አረፈው። ሾፌሩ ትንሽ ዝም ብሎ ቆይቶ፣ ‹‹እኔ መቼም ሕይወታቸውን ለአገራቸው አንዴ አይደለም ሚሊዮን ጊዜ ለመስጠት የቆረጡ የዘመኑን ጀግኖች ሳይ በጣም ነው የምፅናናው…›› አለው፡፡ ‹‹ወዳጄ ልክ ብለሃል፡፡ እኔ ደግሞ በሌላ በኩል አገር ለማፍረስና ሕዝባችንን ለመፍጀት ተነስተው ያሰቡት ያልተሳካላቸውን ወንበዴዎች ሳስብ ውስጤ እንደ እሳት ይነዳል…›› የሚለው ወያላው ነው። ውይይቱ እየተጋጋለ ነው!
ሾፌሩ ሙዚቃውን ከፍ አድርጎ ከፍቶ ውይይቱን ሊገታ ሲፈልግ፣ ‹‹ኧረ ሾፌር ቀነስ አድርገው እባክህ?›› አሉ አንድ አዛውንት። ወያላው፣ ‹‹እንዴ ፋዘር ስንት የጨመረ ነገር እያለ ካልጠፋ ነገር ደመላሽን ቀንሰው ይላሉ?›› አላቸው። ይኼኔ ሰውዬው እንደ መቆጣት እያደረጋቸው፣ ‹‹መቼ እሱን አጣሁትና ነው? እዚህ አንተ እየጮህክብን ተቸገርን እንጂ…›› አሉት። ይኼኔ ወያላው፣ ‹‹አይ ፋዘር ነዳጅ መጨመሩን አልሰሙም ማለት ነው?›› አላቸው። ‹‹እውነትህን እንዳይሆን ብቻ?›› ሲሉት፣ ‹‹ምን ያስዋሸኛል ታዲያ?›› አላቸው ለብዙ ጊዜ እንደሚያውቃቸው ሆኖ። ‹‹ኧረ ጎበዝ እናት አገርን ለመደገፍ ሲባል እንኳንስ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በሕይወታችን ክፈሉ ብንባል ልንከፋ ነው እንዴ?›› ብለው ዙሪያቸውን ቃኘት አደረጉ። መልስ ሲያጡ ቀጠል አደረጉና፣ ‹‹እኔ የምለው ጎበዝ ለአገራችን ህልውና ሲባል በትንሹ መጎዳት ያስከፋ እንዴ?›› ሲሉ የታክሲው ተሳፋሪዎች በአንድ ድምፅ ‹አያስከፋም!› አሉ። ‹‹እንዲህ ነው እንጂ የአገር ፍቅር፡፡ ቅጠል በልተንም ቢሆን አገራችንን ከገባችበት መከራ ውስጥ መንጥቀን እናወጣታለን…›› ሲሉ ጭብጨባ ጎረፈላቸው፡፡ ይኸው ነው!
‹‹የአገሬ ጉዳይ ያንገበግበኛል፣ የወገኔ ብሶት ያንዘረዝረኛል…›› የሚለው የጀግንነት ሙዚቃ በሰፊው ተከፍቶ እስክስታና ጭብጨባው ቀጠለ፡፡ ይኼኔ አንዲት እናት፣ ‹‹ለአገር ምን ያልተዘፈነ ነገር አለ ብላችሁ ነው፡፡ ዋናው ቁምነገር አገር መውደድ ማለት ምንድነው ትርጉሙ የሚለውን ጥያቄያዊ ሙዚቃ ስሰማ ያደግኩ ስለሆንኩ፣ በእኔና በአገሬ መካከል ያለው ቅርበት ልክ ከእናንተ ጋር አሁን አንድ ታክሲ ጣሪያ ውስጥ ያለሁ ነው የሚመስለው፡፡ ያኔ ከአርባ ምናምን ዓመታት በፊት ሶማሊያ ኢትዮጵያን ስትወር የወዛደር ዘማች ሆኜ ክላሽኔን ይዤ የተፋለምኩ ነኝ፡፡ ከዚህ ከአቃቂ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ነበር የዘመትኩት፡፡ ከስንቶች ጀግና እህቶቼ ጋር የዚያድ ባሬን ወራሪ ሠራዊት አባረን ድንበር ላይ ስንቆም፣ ከእኔና ጥቂት እህቶቼ በስተቀር በርካቶች ተሰውተው ነበር፡፡ ያ ዘመን አልፎ ዛሬ ሌሎች ጀግኖች ሴቶችን በዓይኔ በብረቱ ማየቴ ያፅናናኛል፡፡ አገር እንዲህ ነው የምትነዝረው…›› ሲሉን በአድናቆት አጨበጨብንላቸው፡፡ ወይ ጀግንነት!
ዘፈኑ እንዳለቀ አንድ ግጥም ሲነበብ ሰማን። ግጥሙ ‹‹እስኪ ቀን እንግደል›› የሚል ነው። ልክ ግጥሙን ሰምተን እንዳበቃን ‹‹ፓ አይ ግጥም፣ ኧረ ገጣሚ ይኑር። እውነተኛ የልብን የሚናገር ቢኖር እኮ ገጣሚ ነው…›› አለ አንድ ጎልማሳ ተሳፋሪ። የፂሙ መጎፈር እሱ ራሱን ገጣሚ አስመስሎታል፡፡ ‹‹አይ አንተ እኛ መቼ የልብ የሚናገር ጠፋን? የልብ አድራሽ ነው እንጂ…›› አለው ሌላኛው ተሳፋሪ። ትንሽ ዝም ካለና ጉሮሮውን ከጠራረገ በኋላ፣ ‹‹እነዚህ የሕወሓት ወንበዴዎች አገር ለማጥፋት ተነስተው በጀግኖቻችን ተጠራርገው ሲደመሰሱና ሲሸሹ የእነሱም የውንብድና ታሪክ በግጥም ይቀርብልናል፡፡ የልጅ ልጆቻቸው የሚያፍሩበት ታሪክ ይሰነዳል…›› እያለ ተነተነልን። ‹‹እውነት ነው ለማንም ሰው ሊመሰክርለት የሚገባው ሥራው ነው። መጀመርያ ነበር ሁሉን ነገር አስቦ መፈጸም የሚያስፈልገው። ኋላ ከሚመጣ የህሊና ክስ ለመሸሽ ሕዝብን በቀናነት ማገልገል፡፡ ሄግ ከሚገኘው ፍርድ ቤት ተወንጅሎ ላለመቅረብ አስተውሎ መራመድ ያሻል። ‹ሳይቃጠል በቅጠል› የተባለው ያለ አንዳች ይመስላችኋል? የድሮ ጊዜ መልካም ነበር፡፡ ምክንያቱም በድሮ ጊዜ ሄግ፣ ኔቶ ምናምን የሉም ነበር፡፡ አሁን ግን ይብላኝለት ለተጠያቂ፡፡ ‹ብልህ ከሰው ስህተት ሲማር ሞኝ ከራሱ ጥፋትም አይማርም› እንዳንባል…›› የሚለን ሌላ ጎልማሳ ነው፡፡ እውነት ነው!
በዚህ መሀል ስለኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ድንገት አንዱ አንስቶ ‹‹እኔ የምለው ግን እሳቸው ሰውዬ ስለወንበዴው ቡድን ሲነግሩን የነበረው ሁሉ ደረሰ አይደል?›› ብሎ ጠየቀ፡፡ ‹‹አሁን አሪፍ ጥያቄ ነው የቀረበው…›› አለው አብሮት የተቀመጠው። ሁሉንም ለአፍታ ቃኘት ካደረገ በኋላ፣ ‹‹እሳቸው እኮ ሲታገሉ የነበሩት ከወንበዴው ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከአሜሪካ መራሹ ዓለም አቀፍ ኢምፔሪያሊዝም ጋር ነበር፡፡ አሁን የገጠመን ጠላትም ተመሳሳይ ነው፡፡ ድሮም ወንበዴዎቹ ሲደገፉ የነበሩት በእነ አሜሪካና ምዕራባውያን ነበር፡፡ አሁንም ያየነው ታሪክ ራሱን ሲደግም ነው፡፡ መንጌን ያኔ በራሳችን ስንፍና አልሰማናቸውም እንጂ ይህንን ታሪክ ነበር የነገሩን…›› ብሎ በቁጭት ጣሪያ ጣሪያውን እያየ ሲናደድ ሁላችንም ተከፋን፡፡ ቆጨን ማለት ይቀላል!
ታክሲያችን ቄራ መዳረሻ ላይ ናት፡፡ ወያላው የሚቀጥለውን ጉዞ መጣራት ጀመረ፡፡ አጭሩ መንገድ ተራዝሟል ማለት ነው፡፡ ሁለት ሰዎች ወርደው ሌሎች ተተኩ፡፡ ወንድና ሴት ናቸው፡፡ የሴቷ ማስቲካ እንደ አውቶማቲክ ጠመንጃ ይንጣጣል፡፡ ወንድየው ከደጅ የጀመረውን የስልክ ወሬ በረጅሙ ቀጥሏል፡፡ ‹‹በቃ እኔ ገዛዋለሁ፡፡ አምስት መቶ ሺሕ ብር ወዲያውኑ በካሽ እከፍላለሁ፡፡ ችግር የለም እጅ በእጅ ነው…›› እያለ በኩራት ሲናገር ብዙዎቻችን በመገረም ዞር ዞር እያልን አየነው፡፡ ስልኩን በያዘበት እጁ ላይ ያሉት አራት ጣቶች በወርቅ ተንቆጥቁጠዋል፡፡ ሁለት ቁልፎቹ የተፈቱበት ሸሚዙ የግለሰቡን ደረት ግልብጥ አድርጎ ያሳያል፡፡ ደረቱ ላይ እንደ ዘንዶ የተጠመጠመበት የወርቅ ሀብል የአንበሳ ማሰሪያ ሰንሰለትን ምሥጋና ያሳጣል፡፡ አጠገቤ የተቀመጡት አዛውንት ሰውዬውን በመጠራጠር እያዩ አፋቸውን ጆሮዬ ላይ ለጥፈው፣ ‹‹እንዴት ነው ከኢንቨስተር ጋር ነው ወይስ ከባለሥልጣን ጋር ነው ያለነው?›› አሉኝ፡፡ ከሁለት አንዱ ነው እንዳልል እኔም አልገባኝም ስቄ ዝም አልኩ፡፡ አንዱ ወጣት ግን፣ ‹‹ሕገወጥ ቢሆን ነው እንጂ ይህንን ያህል ገንዘብ እጅ በእጅ መንቀሳቀስ የተከለከለ ነው…›› ሲል ሰማነው፡፡ እንዲህ ያለ ጓደኛም አለ!
ሰውዬው ስልኩን ከዘጋ በኋላ ወዲያው ተደወለለት፡፡ ጥቂት ሰላምታ ተለዋውጦ፣ ‹‹ጉዳዩን በሕግ ስለያዝኩት ድርድር አልፈልግም…›› ብሎ ዘጋው፡፡ ጥቂት ቆይቶ ተደወለ፣ እንደተለመደው ከሰላምታ በኋላ ትንሽ ቆይቶ፣ ‹‹ይጠብቀኝ አሳየዋለሁ፣ ማን እንደሆንኩ አያውቀኝም፣ ታፋውን ገንጥዬ ስጥልለት ማን እንደሆንኩ ያውቃል…›› ሲል ሁላችንም ደነገጥን፡፡ ትንሽ ቆይቶ ማስቲካዋን ያለ ኃፍረት ከምታንጣጣው ሴት ጋር ወራጅ ብለው ወረዱ፡፡ በዝምታ ሞልታ ልትፈነዳ የተቃረበችው ታክሲያችን ተነፈሰች፡፡ ሁላችንንም ቀለል አለን፡፡ ውስጣችንን ፍርኃት ሲንጠው ቆይቶ ተገላገልነው፡፡ ለካ ሌሎች ወንበዴዎችም ወደፊት የቤት ሥራዎቻችን ናቸው ማለት ነው፡፡ ብዙ ሥራ አለብን!
አዛውንቱ በመገረም፣ ‹‹እንዴት ነው ነገሩ? አንዴ ስለባለፀጋነቱ ያወራል፡፡ ሌላ ጊዜ በሕጋዊ መንገድ እንደሚራመድ ያብራራል፡፡ ሲለው ደግሞ ቋንጃ እሰብራለሁ ይላል፡፡ ይህንን ሰው ማን እንበለው?›› ሲሉ ሁላችንም ፈገግ አልን፡፡ ያ ነገረኛ ወያላ ሳቅ እያለ፣ ‹‹አባባ እንደልቡ ብንለው ጥሩ ነበር፡፡ ይህ ሰው እንደዚያ ሳይሆን መጠራት ያለበት…›› አለና ዝም አለ፡፡ አዛውንቱ ጓጉተው ስለነበር፣ ‹‹ምን እንበለው?›› ሲሉ፣ ወያላው፣ ‹‹ዕብሪተኛው ወንበዴ›› እያለ ሲስቅ ወራጅ አለ አልን፡፡ እየወረድን ሳለ አዛውንቱ እየሳቁ፣ ‹‹ዕብሪትና ትዕቢት ተጋግዘው የሰፈሩበት ጭንቅላት ባዶ ነው…›› ብለውን ተለያየን፡፡ መልካም ጉዞ!