- በሰሜኑ አካባቢ የተስፋፋው ጦርነት ያደረሰው ጉዳት የጎበኛችሁትን ይመስላል፣ ለትውልድ የሚሻገር ጉዳትን ለማድረስ ከማቀድና ከመፈጸም የሚበልጥ ክፋት ምን ሊኖር ይችላል?
- ክቡር ሚኒስትር እኔ ወገን በወገኑ ላይ በዚህ ደረጃ ይጨክናል ብዬ አስቤ አላውቅም፣ ዓላማው ግን ነው።
- ምንድነው ዓላማው?
- በጦርነቱ ብንሸነፍ እንኳን መንግሥት ተረጋግቶ እንዳይቀጥል የዓመታት የቤት ሥራ እንስጠው ብለው ዕቅድ አውጥተው የተገበሩት ሰይጣናዊ ሥራ ነው፣ ጦርነቱን ብንሸነፍም በቀጣይ ሕዝቡ በኢኮኖሚ ችግርና በሕክምና ዕጦት ተማርሮ መንግሥት ላይ እንዲነሳ እናደርገዋለን ብለው አቅደው የፈጸሙት ክፋት ነው የሚመስለኝ።
- ክቡር ሚኒስትር እኔም በዚህ ሐሳብ እስማማለሁ፣ እንዴት የሰው ልጅ ሆን ብሎ የጤና ተቋማትን እየለየ ያወድማል? ማንን ለመጉዳት ነው? ከአምስት ሺሕ በላይ የጤና ተቋማትን እኮ ነው ያወደሙት?
- ክቡር ሚኒስትር ልክ ነው፣ በዕቅድ የተፈጸመ መሆኑን እንዳምን ያደረገኝ ደግሞ አንድም የወደመ የጤና ተቋም በSSA ላይ ተመዝግቦ አለማየቴ ነው።
- ምንድነው SSA ያልከው?
- Surveillance system for attacks on health care (SSA) ይባላል፣ የዓለም ጤና ድርጅት በየአገሩ በጤና ተቋማት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች እንዲመዘገቡ ብሎ በሥራ ላይ ያዋለው መተግበሪያ ነው።
- እህ…
- ይህ መተግበሪያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ዕውቅና የተሰጠውና ጥቃት ያደረሱ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ የሚረዳ ነው፣ በየአገሩ በጤና ተቋማትና ባለሙያዎች ላይ የተፈጸሙ ጥቃቶችን ያሳያል፣ የየአገሩን ስም መተግበሪያው ላይ በማስገባት የደረሱ ጉዳቶችን መረጃ ማግኘት ይቻላል።
- በኢትዮጵያ የደረሰው ጉዳትም ተመዝግቧል?
- የሚገርመው እኮ እሱ ነው ክቡር ሚኒስትር፣ የኢትዮጵያን ስም ሲያስገቡ ዜሮ ነው የሚመጣው፣ መረጃው ምንም ጉዳት ወይም ጥቃት የለም ነው የሚለው።
- እንዴት ሊሆን ይችላል? ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ተቋማት ጭምር የሚያውቁት መረጃ አይደለም እንዴ?
- ክቡር ሚኒስትር ነገሩን መመርመር ያለብን ይመስለኛል፣ ሆን ተብሎ ለማድበስበስ የተሴረ ይመስላል፣ ምክንያቱም…
- ምክንያቱም ድርጅቱ የሚመራው በእነሱ ወገን ነው።
- እነሱ ማለት?
- የጤና ተቋማቱን ባወደሙት፡፡
- አሃ… አሃ… የጤና ድርጅቱን የሚመራው ሰው?
- ትክክል።
- ጥሩ መረጃ ነው!
[ክቡር ሚኒስትሩ ሥራ አመሻሽተው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ባለቤታቸው የቴሌቪዥኑን ቻናል እየቀያየሩ ሲመለከቱ አገኟቸው]
- ምንድነው የምትፈልጊው? አንዱ ቻናል ላይ አትረጊም እንዴ?
- እንዴት ብዬ ልረጋጋ? እነሱ እየተቅበዘበዙ አይደለም እንዴ?
- እነማንን ነው የምትይው?
- ማፈግፈግ አይደለም፣ ሥልታዊ የቦታ ለውጥ ነው ያሉትን ማለቴ ነዋ፡፡
- አይ አንቺ…
- እንዲያውም ቴሌቪዥኑ ይቅርብኝና አንተ ንገረኝ እስኪ?
- ምን ልንገርሽ?
- የት እንደ ደረሱ?
- ጋሸናንና ላሊበላን ለመያዝ እየተዋጉ ነው።
- ጋሸናና ላሊበላ?
- አዎ።
- እንደገና?
- እንደገና ማለት?
- የቦታ ለውጥ አደረግን ያሉት ከላሊበላና ከጋሸና አልነበረም እንዴ?
- አዎ፣ ከጋሸናና ከካሳጊታ ሲለቁ ነበር እንደዚያ ያሉት፣ ጎበዝ ነሽ አትዘነጊም… እ?
- እና ላሊበላን ድጋሚ ለመያዝ እየተዋጉ ነው? ከምርህ ነው?
- ስነግርሽ? አዎ።
- ውይ… ተምታቶባቸው እንዳይሆን?
- ምኑ?
- ላሊበላ ላይ ያተኮሩበት ምክንያት፡፡
- እንዴት?
- በቃ ተምታቶባቸው ነው የሚሆነው… አይ…
- ምኑ ተምታቶባቸው?
- ቤተ ጊዮርጊስ ተምታቶባቸው ሳይሆን አይቀርም፡፡
- ላሊበላ ቤተ ጊዮርጊስ?
- አዎ…
- ከምን ሊምታታባቸው ይችላል?
- ከቤተ መንግሥት?
- ምን…?
- ያገኛችሁትን ቤተ መንግሥት ያዙ ተብለው ነው… ደጋግመው ወደ እዚያ የሚሄዱት፡፡
- ወዴት?
- ወደ ቤተ ጊዮርጊስ!
- አይ አንቺ…!