Friday, May 24, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የዋጋ ግሽበትን የሚያባብሰው የግብይት ሥርዓት ይታሰብበት!

ዜጎች ምርር ያለ የኑሮ ውድነት ሲገጥማቸው መንግሥት ሊወስዳቸው ከሚገቡ ዕርምጃዎች መካከል አንዱ፣ የግብይት ሥርዓቱን ጤንነት በመመርመር ፈጣን ማስተካከያ ማድረግ ነው፡፡ ምንም እንኳ ከዛሬ 30 ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ገበያ መር በሚባለው የኢኮኖሚ ሥርዓት እንድትመራ ብትደረግም፣ የግብይት ሥርዓቱ ግን ለዘራፊዎች መረን የተለቀቀ በመሆኑ ጤናማና የተረጋጋ ገበያ ማስፈን አልተቻለም፡፡ የግብይት ሥርዓቱ የአቅርቦት ሰንሰለት በጣም ረዥምና በርካታ ሕገወጥ ተዋንያን የሚተራመሱበት ስለሆነ፣ ሕጋዊ ነጋዴዎችና ሸማቾች በአግባቡ ሊገበያዩ የሚችሉበት ዓውድ መፍጠር አዳጋች ሆኗል፡፡ የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት መንግሥታዊ አካልም ሆነ ሌሎች ባለድርሻ አካላት የእሳት ማጥፋት ዓይነት ሩጫ ስለሚያበዙ፣ በተጠና መንገድ የግብይት ሥርዓቱን ፈር የሚያሲዝ መሠረት ለመጣል አልተቻለም፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ሰርገው የገቡ ኃይሎች ምርቶችን በመደበቅ፣ በአድማ ዋጋ በመተመን፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን አንቀው በመያዝና ተቆጣጣሪ አካላትን በቁጥጥራቸው ሥር በማዋል ከፍተኛ ደባ ይፈጽማሉ፡፡ የዋጋ ግሽበት ጉዳይ ሲነሳ የግብይት ሥርዓቱ ጤንነት በሚገባ ካልተመረመረ ልፋቱ ሁሉ ከንቱ ነው፡፡ ከአህል በረንዳ ጀምሮ እስከ ተለያዩ ሸቀጦችና ምርቶች ድረስ ያለው የደላላ ሠራዊት ትርምስ፣ ለኑሮ ውድነቱ የሚያበረክተው አሉታዊ ተፅዕኖ መፍትሔ ካልተገኘለት ሌላው ጥረት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡

በአንድ አገር ውስጥ የዋጋ ግሽበት ማኅበራዊ ቀውስ እንዳይፈጥር የማረጋጋት ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው፡፡ መንግሥት የማረጋጋት ዕርምጃ ሲወስድ በዋነኝነት የሚነሳው በፊስካልና በገንዘብ ፖሊሲ ላይ ማሻሻያዎችና ክለሳዎች ማድረግ ነው፡፡ በቅርቡ በብሔራዊ ባንክ አማካይነት የተወሰዱ የባንክ ብድርን ለጊዜው ገታ ማድረግና የገንዘብ ዝውውር መጠንን መቀነስ ለተወሰነ ጊዜ ቢረዱም፣ ነገር ግን የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ከመጠን ያለፈ ወጪ አደብ ማስገዛት መጠነኛ ዕፎይታ ይሰጣል፡፡ መንግሥት ወጪው ሲቀንስ ከብሔራዊ ባንክ እየተበደረ ገበያው ውስጥ የሚረጨው ገንዘብ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ ይሁንና አሁንም ብርቱ ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ከፍላጎት ጋር መጣጣም ያቃተውን አቅርቦት ማጠናከር ነው፡፡ በኅዳር ወር የተመዘገበውን 33 በመቶ የዋጋ ግሽበት ማርገብ የሚቻለው ግን የምግብ ምርቶችንና የሌሎች ሸቀጦችን አቅርቦት በማሳደግ ነው፡፡ የአቅርቦት ሰንሰለቱ እጅግ የተራዘመና ብዙ ተዋንያን የሚሳተፉበት ስለሆነ፣ አጠር ባለ ሰንሰለትና በጤናማ አሠራር የአቅርቦት መስመሩን ማስተካከል ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በተለይ የሚመለከታቸው መንግሥታዊና ባለድርሻ አካላት ጠንካራ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የግብይት ሥርዓቱን አንቀው የያዙት ጥቂት ጉልበተኞች እስካልተወገዱ ድረስ፣ የዋጋ ግሽበቱን ነጠላ አኃዝ ለማድረግ የተያዘው ዕቅድ ሕልም ነው የሚሆነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ከማፍያዎች መላቀቅ አለበት፡፡ 

ኢትዮጵያ ከአንድ ዓመት በላይ የቆየ ጦርነት ውስጥ ሆና የዋጋ ግሽበት ማጋጠሙ አይቀሬ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡ የዋጋ ግሽበቱ ምክንያታዊነት ሳይኖረው በዘፈቀደ የዜጎችን የኑሮ ዋስትና ሲገዳደር ግን፣ በተቻለ መጠን መንስዔውን ተረድቶ ዕርምጃ ለመውሰድ መወሰን ተገቢ ነው፡፡ የአገሪቱ የግብይት ሥርዓት ፈር ባለመያዙ ምክንያት በመንግሥት፣ በሸማቾችና በነጋዴዎች መካከል ሊኖር የሚገባው መስተጋብር የተዛባ ነው፡፡ መንግሥት ነፃ ገበያ በሚባለው የኢኮኖሚ ሥርዓት አማካይነት የተቆጣጣሪነት ሚናውን ሲረሳው፣ ነጋዴው አጋጣሚውን ከመጠን በላይ ትርፍ ለማጋበስ ሲጠቀምበት ዋነኛው ተጎጂ ሸማቹ ነው፡፡ እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት ጉዳይ መንግሥት ነፃ ገበያ ነው ብሎ ገበያውን ለሥርዓተ አልበኞች መልቀቅ የለበትም፡፡ ነጋዴውም የሚቆጣጠረውን አካል ችላ ባይነት ተገን አድርጎ ዘረፋ ውስጥ መሰማራት አይኖርበትም፡፡ መንግሥት የተለያዩ ምርቶች አቅርቦት በሕገወጦች እንዳይታነቅ መከላከል ይኖርበታል፡፡ የንግድ ማኅበረሰቡም ምርቶችን ከመደበቅና ዋጋ ከመቆለል መታቀብ አለበት፡፡ ይልቁንም ጤናማ የንግድ ፉክክር እንዲኖር ሕገወጥ ተዋንያን ከግብይት ሥርዓቱ ውስጥ እንዲወጡ መታገል ይጠበቅበታል፡፡ የምርቶች ሥርጭት በእነሱ ሲጠለፍ የንግድ ፉክክሩም ጤና ያጣል፡፡ 

በተለያዩ ጊዜያት ለመጠቆም እንደተሞከረው የግብይት ሥርዓቱ ሥር ነቀል ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡ የመጀመሪያው የግብይት ሥርዓቱ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካል ተቋማዊ አደረጃጀቱን ማጠናከር፣ በባለሙያዎችና በጠንካራ አመራሮች ራሱን ዝግጁ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ የዘመኑን ቴክኖሎጂዎች በመታጠቅ ዓለም የደረሰበትን የቁጥጥር ሥርዓት ልምድ መቅሰም ይጠበቅበታል፡፡ ቁጥጥሩም ሆነ ክትትሉ ንግድን የማያደናቅፍና የበለጠ ረብሻ የሚፈጥር ሳይሆን፣ የግብይት ሥርዓቱ ውጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆን ማገዝ ይኖርበታል፡፡ ከዘመኑ ጋር የማይራመድ በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ የቁጥጥር ሥርዓትን በማስወገድ፣ አሳማኝና ውጤታማ ሥራ ለማሳየት ብቁ መሆኑን ማስመስከር አለበት፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን የሸማቾችን መብት ለማስጠበቅ የተመሠረቱ ቡድኖችም ሆኑ ስብስቦች በብሔራዊ ደረጃም ሆነ በክልል ራሳቸውን በማጠናከር፣ ከዘመኑ ጋር እኩል ለመራመድ የሚያስችል ዕውቀት ጨብጠው ኃላፊነታቸውን ለመወጣት መዘጋጀት ይኖርባቸዋል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ረቀቅ ያሉና አደገኛ ሥውር ተዋንያን የሚሳተፉበት ስለሆነ፣ የእነሱን ኔትወርክ መበጣጠስ የሚቻለው ላቅ ባለ ትጋትና በሀቅ ላይ የተመሠረተ አሠራር በማስፈን ነው፡፡ መንግሥትን፣ ሸማቾችንና ነጋዴዎችን በእኩልነት ማገናኘት የሚያስችል አሠራር ሲሰፍን የፖሊሲ ለውጥም ሆነ ማሻሻያ ሲኖር ግርታ አይፈጠርም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል እንደማይቻል መተማመን ይገባል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ ለዋጋ ግሽበት መባባስ ምክንያት የሆኑ ሕገወጥ ድርጊቶች በመብዛታቸው፣ ሸማቾች ለመብታቸው የሚቆምላቸው ጠንካራ ተቋም ባለመኖሩ አቅመ ቢስ ሆነዋል፡፡ ሌላው ቀርቶ በሚዛን ሲጭበረበሩና ጥራታቸው የተጓደለ ምርቶች ሲቀርቡላቸው፣ እኔ አለሁ ብሎ መብታቸውን ለማስከበር ኃላፊነት የሚወስድ የለም፡፡ የፍጆታ ምርቶችና ሸቀጦች ከተመረቱበት ወይም ከመጡበት ሥፍራ ጀምሮ ሸማቹ እጅ እስኪገቡ ድረስ፣ የሚያልፉበት የአቅርቦት ሰንሰለት ተመልካች የለውም፡፡ መርዛማ የሆኑ ባዕድ ነገሮች የታከሉባቸው ምርቶች ገበያውን ሲያጥለቀልቁት በየትኛው ኬላ እንደገቡ እንኳን የሚያውቅ የለም፡፡ የግብይት ሥርዓቱ በዚህ መጠን የተበላሸ በመሆኑ የተቆጣጣሪ ያለህ እያለ ነው፡፡ የግብይት ሥርዓቱ መሠረታዊ ለውጥ የሚያስፈልገው የዋጋ ግሽበትን ከመቆጣጠር በላይ፣ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ቀውስ ውስጥ እንዳይገባ ለመታደግ ጭምር ነው፡፡ የተመረተው በአግባቡ ሸማቾች ዘንድ በተመጣጣኝ ዋጋ እንዳይቀርብ ከሚፈጸመው አሻጥር በተጨማሪ፣ የሚመለከተው መንግሥታዊ አካልም ሥራውን በአግባቡ ለመወጣት አለመቻሉ ከፍተኛ ትኩረት ያስፈልገዋል፡፡ በልማዳዊ አሠራር የተተበተበው የንግድ ሥራ ቁጥጥር በዘመናዊ አሠራር ካልተተካ፣ የግብይት ሥርዓቱ የሕገወጦች መፈንጫ ሆኖ መቀጠሉ አይቀርም፡፡ ሁሉንም ችግር በነጋዴው ላይ እያሳበቡ ኃላፊነትን ከመዘንጋት፣ ዘመናዊ አሠራር ማስፈን ችግሮችን ለመቅረፍ ይረዳል፡፡ 

የንግድ ማኅበረሰቡም ቢሆን በንግድ ምክር ቤቶቹም ሆነ በማኅበራቱ አማካይነት ከሕገወጥ ድርጊቶች መራቅ ይኖርበታል፡፡ አገር ጦርነት ውስጥ ሆና ኢኮኖሚው ከፍተኛ የሆነ ጫና ውስጥ ባለበት ጊዜ፣ የነዳጅ ዋጋ ሲጨምርም ሆነ ሌሎች ጭማሪዎች ሲያጋጥሙ ሁሉንም ነገር ወደ ሸማቾች ማስተላለፍ አስተዛዛቢ ነው፡፡ በአንድ ሊትር ቤንዚን ላይ 5.90 ብር ጭማሪ ሲደረግ ከዚህ ውስጥ የራስን ድርሻም ማንሳት ይገባል፡፡ ጭማሪዎች ሲኖሩ ራስን አላስነካም ማለት ስግብግብነት ነው፡፡ ዜጎች ገቢያቸው ሳይጨምር የመጣውን ጭማሪ ሁሉ ተሸከሙ ማለት ከወገን የሚጠበቅ አይደለም፡፡ መንግሥትም ቢሆን ከቁጥጥር ሥራዎቹ መሀል የዘነጋው አንድ መሠረታዊ ነገር አለ፡፡ ይህም የትርፍ ህዳግ ይባላል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የትርፍ ህዳግ በመቶኛ ተሠልቶ ቢወሰን ኖሮ፣ ነጋዴው አሥርና ሃያ ዕጥፍ ከአንድ ምርት ላይ እያተረፈ የዋጋ ግሽበቱ ጣሪያ አይነካም ነበር፡፡ ከመነሻው ሁሉንም ነገር ችሎ ነጋዴው እጅ ላይ በመቶ ብር የደረሰ አንድ ምርት የትርፍ ህዳግ ባለመኖሩ ምክንያት፣ ለሸማቹ በአንድ ሺሕ ብር እየተሸጠ የዋጋ ግሽበቱ ጀርባውን ያጎብጠዋል፡፡ የግብይት ሥርዓቱ ብልሽት ይህንን ይመስላል፡፡ የዋጋ ግሽበትን የሚያባብሰው የግብይት ሥርዓት ከፍተኛ ትኩረት ይሻል!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...

ያልነቃ ህሊና!

ከሽሮሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፖለቲካውም ሆነ ዲፕሎማሲው ብልኃትና ብልጠት አይጉደለው!

ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር የሁለቱን አገሮች የ120 ዓመታት የዲፕሎማቲክ ግንኙነት አስመልክቶ ያደረጉት የፖሊሲ ንግግር፣ በመንግሥት በኩል ቁጣ አዘል ምላሽ ነበር ያገኘው፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያና...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት ብትችል፣ ከበርካታ ታዳጊ አገሮች የተሻለ በዕድገት ጎዳና የመገስገስ እምቅ አቅም እንዳላት የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ ይህንን የመሰለ...

የመግባቢያ አማራጮችን ተባብሮ መፈለግ ከጥፋት ይታደጋል!

በአሁኑ ጊዜ ሕዝብና አገርን ጤና የሚነሱ በርካታ ችግሮች በየቦታው እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ችግሮቹ ከመጠን በላይ እየተለጠጡ ቅራኔዎች ሲበረክቱ ሰከን ብሎ ከመነጋገር ይልቅ፣ የጉልበት አማራጭ...