በሰሜን ኢትዮጵያ በርካታ ቅርንጫፎችና ተበዳሪዎች ያሉት አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ዓመታዊ ትርፉ በ366 ሚሊዮን ብር መቀነሱን አስታወቀ፡፡ በርካታ ብድሮቹም ጤናማ ያልሆነ ምድብ ውስጥ ገብተውበታል፡፡
የባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት እንደሚያመላክተው በ2013 የሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ 414 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ይህ የትርፍ መጠን ካለፈው ዓመት ትርፍ ጋር ሲነፃፀር ከ366 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው ትርፍ 780.6 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡
የባንኩ የትርፍ ምጣኔ በዚህን ያህል መጠን የቀነሰው፣ ባንኩ ከሰጣቸው ብድሮች አብዛኞቹ በሰሜን ኢትዮጵያ በሚገኙ ቅርንጫፎች እንደሆነ ከባንኩ ዓመታዊ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡
የባንኩን የ2013 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸም በተመለከተ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ገብረ ሕይወት አገባ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በተለይ በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተፈጠረው ችግር በባንኩ ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል፡፡ የተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ለፋይናንስ ዘርፉ እጅግ ፈታኝ እንደነበር የገለጹት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የታዩ ኢኮኖሚያዊ ለውጦችና በሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተከሰተው ግጭት ከኮቪድ-19 ጋር ተዳምሮ ያስከተለው ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፈተና በአገሪቱ የባንክ ዘርፍ በተለይ ደግሞ በአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አፈጻጸም ላይ ጥላውን አጥልቶበት አልፏልም ብለዋል፡፡
የተራዘመው የኮቪድ ወረርሽኝ፣ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የከሰተው ግጭትና የዋጋ ግሽበት በባንኮች አፈጻጸም ላይ ቀላል የማይባል ተፅዕኖ ፈጥሯል ያሉት የቦርድ ሊቀመንበሩ፣ ተፅዕኖው በተለይም በተቀማጭ ገንዘብና በውጭ ምንዛሪ አሰባሰብ፣ በብድር አሰጣጥና አመላለስ፣ እንዲሁም በቅርንጫፍ ማስፋፊያ ሥራዎች ላይ ጎልቶ መታየቱን ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡
‹‹በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ብዛት ያላቸው ቅርንጫፎችና ደንበኞች ያሉት ባነካችን በርከት ባሉ ቅርንጫፎቹ ላይ ከተፈጸመው ዘረፋና የንብረት ውድመት በተጨማሪ፣ ሁሉም ቅርንጫፎቻችን ከሥራ ውጪ መሆናቸው አጠቃላይ እንቅስቃሴውን አዳክሞታል፤›› በማለት በባንኩ ላይ የፈጠረውን ተፅዕኖ አመላክተዋል፡፡ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ ተበዳሪ ደንበኞችም ብድራቸውን መክፈል ባለመቻላቸው፣ በርካታ ብድሮች እንዲበላሹ ወይም ጤነኛ ወዳልሆነ ብድር ምድብ ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ስለመሆናቸውም የቦርድ ሊመቀንበሩ ተናግረዋል፡፡ ይህም በመሆኑ በሒሳብ ዓመቱ የነበረው የባንኩን አፈጻጸም በእጅጉ እንደጎዳውም አስረድተዋል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ የመጀመርያ ሩብ ዓመት ባንኩ የነበረው አፈጻጸም በሁሉም መለኪያዎች የተሻለ የነበረ መሆኑን በመጥቀስ፣ ነገር ግን የተፈጠሩት ችግሮች ያስከተሉዋቸው ተያያዥ ጉዳቶች የነበረውን መልካም አፈጻጸም ለማስቀጠል አለመቻል ብቻ ሳይሆን፣ አፈጻጸሙ እንዲቀንስ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል፡፡
እንደ ቦርድ ሊቀመንበሩ ሪፖርት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንት የችግሩን ጥልቀት ግምት ውስጥ በማስገባት በተረጋገጡ ፈተናዎች ላይ ተከታታይ ውይይቶችና ግምገማዎች በማካሄድ፣ ተግዳሮቶቹን ተቋቁሞ ለማለፍ የሚያስችሉ የተለያዩ የአጭርና የረዥም ጊዜ ስትራቴጂዎችና የማስፈጸሚያ ሥልቶችን በመንደፍና ለተግባራዊነታቸው አበክረው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡ በዋናነትም የባንኩን ተቀማጭ ገንዘብና የውጭ ምንዛሪ ግኝት ለማሳደግ የሚያስችሉ ስትራቴጂዎች፣ እንዲሁም በተበዳሪ ደንበኞች ላይ የተፈጠረውን ጫና ለማቃለል የተወሰዱ ዕርምጃዎችን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
ከወቅታዊ ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ አንዳንድ ግለሰቦች በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት የባንኩ መልካም ስም ለማጠልሸት ያደረጉት መሠረተ ቢስ ሙከራ፣ በባንኩ እንቅስቃሴ ላይ ጥላውን ያሳረፈ እንደነበርም የቦርድ ሊቀመንበሩ ጠቁመዋል፡፡
‹‹እውነታው የሚያሳየው አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ በፈታኝ ሁኔታዎች ውስጥም ሆኖ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለሚያወጣቸው መመርያዎች፣ ለአገር ሕጎችና ለመመሥረቻ ደንቦቹ ተገዥ በመሆን የሚሠራ ባንክ ነው፤›› ብለዋል፡፡
እንዲህ ያሉ ጫናዎች የገጠሙት ቢሆንም ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ ከታክስ በፊት ያስመዘገበው 414 ሚሊዮን ብር ትርፍ፣ ከነበሩት ፈታኝ ሁኔታዎች አኳያ ሲታይ አበረታች ሊባል የሚችል እንደሆነም የቦርድ ሊቀመንበሩ ገልጸዋል፡፡
በ2013 የሒሳብ ዓመት የባንኩ ሌሎች አፈጻጸሞች ላይ በሪፖርቱ እንደተመለከተው፣ አገልግሎት እየሰጡ ባሉ ቅርንጫፎች አማካይነት ተቀማጭ ገንዘብ ለማሰባሰብ የተደረገው ጥረት ፈታኝ የነበረ ቢሆንም፣ አጠቃላይ ተቀማጭ የገንዘብ መጠኑ 26 ቢሊዮን ብር ማድረስ መቻሉን ተገልጿል፡፡ ይህ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን አፈጻጸም ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ0.5 በመቶ ዝቅ ያለው መሆኑም ተመልክቷል፡፡፡ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት መጠን 32.2 ቢሊዮን ብር የደረሰ መሆኑን፣ ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ13 በመቶ ዕድገት ማሳየቱ፣ እንዲሁም የባንኩ መጠባበቂያ ካፒታል 3.6 ቢሊዮን ብር መድረሱ በሪፖርቱ ተካቷል፡፡ የባንኩ መጠባበቂያና ካፒታል መጠን በሒሳብ ዓመቱ የ4.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ ባንኩ 5.4 ቢሊዮን ብር ብድር በመስጠት፣ አጠቃላይ የብድር ክምችቱን መጠን ወደ 21.8 ቢሊዮን ማሳደግ መቻሉ በሪፖርቱ ተገልጿል፡፡ ይህም ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ14.4 በመቶ ጭማሪ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡ ‹‹በበጀት ዓመቱ በደንበኞቻችን ላይ የተከሰተው የንግድና ኢንቨስትመንት መቀዛቀዝ በተበዳሪ ደንበኞቻችን የብድር መመለስ አቅም ላይ ጫና በማሳደሩ፣ የብድር ተመላሽ ገንዘብ በማሰባሰብ ሒደት ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል፤›› ሲሉ የቦርድ ሊቀመንበሩ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ ‹‹በዚህም ምክንያት በርካታ ብድሮች ጤናማ ወዳልሆኑ ምድብ ገብተዋል፤›› ብለዋል፡፡ ይህም የባንኩ ጤናማ ያልሆኑ ብድሮችን መጠን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው ጣሪያ በላይ የሚሆኑበት ሁኔታ መፍጠሩንም ጠቅሰዋል፡፡ ባንኩ እነዚህን ችግሮች ለመወጣት በቀጣይ የተለያዩ ዕርምጃዎችን የሚወስድ መሆኑን፣ ካፒታሉን ወደ አምስት ቢሊዮን ብር ለማሳደግም ያላሰለሰ ጥረት እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡
ማኅበራዊ ኃላፊነት ከመወጣት አኳያ ባንኩ በሒሳብ ዓመቱ 21 ሚሊዮን ብር ወጪ ያደረገ መሆኑን የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ ከዚህ ወጪ ውስጥ አሥር ሚሊዮን ብር ገበታ ለአገር ፕሮጀክት፣ አምስት ሚሊዮን ብር ለአገር መከላከያ ሠራዊት፣ አምስት ሚሊዮን ብር ለአንበጣ መከላከያ፣ እንዲሁም አንድ ሚሊዮን ብር ለአዲስ አበባ የተማሪዎች ምገባ ፕሮጀክት የተሰጠ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
በሒሳብ ዓመቱ 13 ቅርንጫፎችን የከፈተው አንበሳ ባንክ፣ በዓመቱ መጨረሻ አጠቃላይ የባንኩ ቅርንጫፎች ቁጥር 276 ማድረስ መቻሉን አስታውቋል፡፡ ባንኩ በአሁኑ ወቅት 253,227 የሞባይል ባንኪንግ፣ 175,042 የካርድ ባንኪንግና 31,645 የኢንተርኔት ባንኪንግ አገልግሎት ተጠቃሚ ደንበኞች እንዳሉት፣ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ የተከፈለ ካፒታል 2.53 ቢሊዮን ብር መድረሱ በሪፖርቱ ውስጥ ተመልክቷል፡፡