Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ‹‹የመጨረሻው ዕርምጃ›› ከመውሰዱ በፊት ታጣቂዎች እጅ እንዲሰጡ አሳሰበ

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ‹‹የመጨረሻው ዕርምጃ›› ከመውሰዱ በፊት ታጣቂዎች እጅ እንዲሰጡ አሳሰበ

ቀን:

  • የክልሉ ኮማንድ ፖስት ዋና አስተባባሪ በሌላ ኃላፊ መተካታቸው ተገልጿል

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመጨረሻ ያለውን ዕርምጃ መውሰድ ከመጀመሩ በፊት በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅ እንዲሰጡ አሳሰበ፡፡ ያለፈው የክረምት ወቅት በክልሉ ኦፕሬሽን ለማድረግ አስቸጋሪ ሁኔታ ይፈጠር እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን ‹‹የበቀሉት ሳሮች እንዲቃጠሉ እየተደረገ በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ የመጨረሻው ዕርምጃ ይወሰዳል፤›› ተብሏል፡፡

የክልሉ መንግሥት ታጣቂዎቹ እጅ እንዲሰጡ ያሳሰበው በክልሉ በሚገኘው ኮማንድ ፖስት መሪነት፣ ከፌዴራል ፖሊስና የተለያዩ ክልሎች ልዩ ኃይሎች ጋር በመሆን ኦፕሬሽን ለማድረግ ዝግጅት እያደረገ በመሆኑን ነው፡፡ ጥሪው የቀረበው ከኅዳር ወር መጨረሻ ጀምሮ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ የክልሉ ባለሥልጣናት ከሰሞኑ በየወረዳዎቹ በመገኘት ነዋሪዎችን እያወያዩና ለታጣቂዎቹ የሚደረገውን ጥሪ እያቀረቡ መሆኑም ታውቋል፡፡

በቅርብ ጊዜ ይወሰዳል የተባለውን ‹‹የመጨረሻ ዕርምጃ›› በዋናነት የሚመራውን መከላከያ ሠራዊት የሚያስተባብሩና የሚመሩት የኮማንድ ፖስቱ ዋና አስተባባሪ ሌተና ጄኔራል ሀሰን ኢብራሂም መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ዋና አስተባባሪው ከኅዳር ጀምሮ ወደ ኃላፊነቱ የመጡት የቀድሞውን የኮማንድ ፖስት ዋና አስተባባሪ ሌተና ጄኔራል አሥራት ዲኔሮ በመተካት መሆኑን፣ የክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽ ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለፉት ዓመታት በመተከልና ካማሺ ዞኖች፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአሶሳ ዞን ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በንፁኃን ላይ ጥቃትና ግድያ ሲፈጽሙ ቆይተዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት በመተከልና ካማሺ ዞኖች የሚንቀሳቀሱት የጉሙዝ ሕዝብ ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ (ጉሕዴን) ታጣቂዎች መሆናቸውን ያስታወቀ ሲሆን፣ በአሶሳ ዞን የሚንቀሳቀሱት ‹‹የሱዳንና ግብፅ ቅጥረኞች›› የሆኑ ታጣቂዎች መሆናቸውን ገልጿል፡፡

መተከልና ካማሺ ዞኖች ካለፈው አንድ ዓመት ወዲህ በኮማንድ ፖስት ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ በተለይ መተከል ላይ እጅ የሰጡ 2,500 ያህል ታጣቂዎች የተሃድሶ ሥልጠና ሲሰጣቸው ነበር፡፡ ኃላፊው እንዳስታወቁት እጅ ሰጥተው የነበሩት ታጣቂዎች እንዲሟሉላቸው ሁለት ጥያቄዎችን አቅርበው ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጥያቄ የፖለቲካ ሥልጣንን የሚመለከት እንደነበር የተናገሩት አቶ መለሰ ‹‹የክልሉ መንግሥት ይኼንን ለመመለስ በሚያስችል ደረጃ እየተንቀሳቀሰ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ሁለተኛው ጥያቄ ‹‹በማኅበር ተደራጅተን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችን ይረጋገጥ›› የሚል እንደሆነ ያስታወሱት ኃላፊው፣ ይኼንን የሚከታተል ጽሕፈት ቤት ተቋቁሞ ሥራ ሊጀመር እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይሁንና ሰኔ ወር ላይ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕወሓት ታጣቂ ቡድን በአማራና በአፋር ክልሎች ጥቃት ሲከፍት እጅ ሰጥተው ተሃድሶ የተሰጣቸው ታጣቂዎች ስምምነቱን ሽረው ወደ ጥቃት መግባታቸውን አስታውቀዋል፡፡

የጉህዴን ታጣቂ የሚንቀሳቀስበት የካማሺ ዞን ከኦሮሚያ ክልል ጋር አዋሳኝ በመሆኑ፣ በአሸባሪነት ከተፈረጀው ሸኔ ጋር ጥምረት መፍጠሩን የተናገሩት ኃላፊው፣ በመተከል ዞን ድባጤ ወረዳም ከዚሁ ቡድን ጋር በመሆን ጥቃት ማድረሱን ገልጸዋል፡፡

አቶ መለሰ ይኼንን ተከትሎ የክልሉ መንግሥትና ኮማንድ ፖስቱ ከዚህ በኋላ ድርድር ላለማድረግ መወሰኑን የተናገሩ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ ትጥቅ ፈተው እጅ የሚሰጡ ታጣቂዎችን ብቻ እንደሚቀበል ተናግረዋል፡፡ ነገር ግን እጅ የሚሰጡት ታጣቂዎች ጭፍጨፋ የፈጸሙ ወይም ያስተባበሩ ከሆነ ተጠያቂነት እንደማይቀር ገልጸዋል፡፡

አሶሳ ዞን ያሉት ታጣቂዎች ላይ የተወሰደው ዕርምጃ ከዚህ በኋላ ታጣቂዎቹ ሥጋት እንዳይሆኑ ማድረግ አስችሏል የተባለ ሲሆን፣ የብዙ ታጣቂዎችና መሳርያ መማረኩን ተናግረዋል፡፡ ይሁንና በክልሉ ሁሉም ቦታ ሰላምና ፀጥታ እስኪረጋገጥ ድርስ ዕርምጃው እንደማይቆም አቶ መለሰ አክለዋል፡፡

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲሊ ሀሰን ኅዳር 4 ቀን 2014 ዓ.ም. ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ታጣቂ ቡድኑ ‹‹ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ›› ለአገር መከላከያራዊትና ለፀጥታ ኃይል እጁን እንዲሰጥ ተጠይቋል።

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...