Monday, February 26, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የወተት ፋብሪካዎች በፋይናንስ እጥረትና በኢመደበኛ ንግድ ምክንያት አደጋ ውስጥ ወድቀናል አሉ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ልማት ባንክ ድርጅቶችን ለማዳን ማሻሻያ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል

በሥራ ማስኬጃ ፋይናንስ እጥረትና የኢመደበኛ ገበያ በመስፋፋቱ የወተት ፋብሪካዎች አደጋ ላይ መውደቃቸውን ተናገሩ።

ባለፉት አምስት ዓመታት የሊዝ ፋይናንስ አቅርቦት በመስፋፋቱ ምክንያት፣ አዳዲስ የወተት ፋብሪካዎች በከፍተኛ ቁጥር ጨምሮ ከ30 በላይ ቢደርሱም፣ ለዓመታት የነበሩ ችግሮች ባለመፈታታቸው ድርጅቶቹን እየተፈታተነ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በተለይም የወተት ዘርፉን የግብይት ሥርዓት የሚመራ ሕግ በአገር አቀፍ ደረጃ ባለመኖሩና በአንዳንድ ክልሎች በሥራ ላይ ያሉ መመርያዎች በሚገባ በመሬት ላይ አለመውረዳቸው፣ ከኮቪድ-19 እና ከአገሪቱ ሰላም መደፍረስ ጋር ተዳምሮ ለከፋ ቀውስ እንደዳረጋቸው የዘርፉ ተዋናዮች አስረድተዋል።

በደብረ ብርሃን ከተማ የሃፒ ወተት ፋብሪካ ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰለሞን ፋንቱ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ወተት ከገበሬዎች መሰብሰብ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከባድ እየሆነ መምጣቱትን በመግለጽ፣ ለዚህም ተጠያቂ ያደረጉት በኢመደበኛ ዘርፍ ያሉ ነጋዴዎችን ነው።

ፋብሪካዎች እስከ 50 ኪሎ ሜትር ዙሪያ (ራዲየስ) በመጓዝ ወተት ከገበሬዎች መግዛት ቢችሉም፣ የኢመደበኛ ገበሬዎች የተሻለ ዋጋ በመስጠት ምርቱን እየወሰዱ ፓስቸራይዝ ሳያደርጉ ይሸጣሉ ያሉት አቶ ሰለሞን፣ ይህን ዓይነት ድርጊት መፈጸም በሕግ የተከለከለ ቢሆንም፣ ሕጉ በትክክል ስለማይፈጸም ሕጋዊ አምራቾችን ከገበያ ውጭ አያደረገ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ሾላና ማማ ወተት በሥራው ላይ የቆዩ የዘርፉ ተዋናያኖች የተሻለ የገንዘብ ፍሰት ለዓመታት ስላላቸው ችግሩን መቋቋም ቢችሉም፣ አዳዲስ ፋብሪካዎች የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ማግኘት ባለመቻላቸው አደጋ ውስጥ መውደቃቸውን ያወሳሉ።

በዚህም የተነሳ የማምረት አቅማቸውን አሥር በመቶ እንኳን መጠቀም አለመቻላቸውን የሚያነሱት የአዳማ ወተት ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ንጋቱ፣ ለባለፉት ሁለት ዓመት ኪሳራ ማስመዝገባቸውን በምሬት ይናገራሉ።

የአዳማ ወተት ፋብሪካ የማምረት አቅሙ 1,500 ሊትር ወተት በሰዓት ቢሆንም፣ አሁን እያመረተ የሚገኘው በቀን 2000 ሊትር መሆኑን አቶ እንዳልካቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል። ለዚህ በዋነኝነት ያነሱት የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ማግኘት አለመቻላቸውን ሲሆን፣ ለዚህም ተጠያቂ ያደረጉት የኢትዮጵያ ልማት ባንክን የብድር መመርያን ነው።

‹‹የሥራ ማስኬጃ ብድር ከባንኩ ማግኘት የማይታሰብ›› ነው ያሉት አቶ እንዳልካቸው፣ ይህንንም ከሌሎች የፋይናንስ ተቋማት ለማግኘት ቢሞክሩም የብድር ታሪካቸው በመበላሸቱ ይህንን ማድረግ አለመቻላቸውን ዋና ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል። 

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዮሐንስ አያሌው (ዶ/ር) በበኩላቸው ባንካቸው ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑን፣ የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ለወተት ፋብሪካዎች ለማቅረብ መታቀዱን ይፋ አድርገዋል። ባንኩም ችግሮቻቸውን በመረዳት ማሻሻያዎችን እንደሚያደርግ ለሪፖርተር ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በነፍስ ወከፍ እያንዳንዱ ዜጋ በዓመት 19 ሊትር ወተት ይውስዳሉ ተብሎ የሚታመን ሲሆን፣ ከኬንያ ጋር ሲነፃፀር በስድስት እጥፍ ያነሰ ነው። በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ ከ5,000 በላይ ገበሬዎች በዓመት ከ35 ሚሊዮን ሊትር በላይ ወተት ለአዲስ አበባ ገበያ ብቻ ያቀርባሉ ተብሎ ቢታመንም፣ ከዚህ ውስጥ 73 በመቶ የሚሆነው በቀጥታ ለሸማቾችና ለፋብሪካዎች ይቀርባል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ባለፈው ዓመት 4.6 ቢሊዮን ሊትር ወተት በ57 ሺሕ ገበሬዎች መታለቡን የማዕከላዊ ስታስቲክስ አገልግሎት (የቀድሞ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ) መረጃ ያሳያል። ምንም እንኳን ቁጥሩ በየዓመቱ ዕድገት ቢያሳይም፣ ፋብሪካዎች ጋር ገበሬዎች ባለመቆራኘታቸው ሸማቾች ጋር የሚደርሰው አነስተኛ መሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል። በዚህ የተነሳ እንዲሁም በፋይናንስ እጥረትና ወተት መሰብሰብ ባለመቻላቸው፣ እንደ በቆጂ ወተት ፋብሪካ ያሉ ቀደምት ድርጅቶች በቅርቡ ተዘግተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች