የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ተቋማት በድርጅቱ ቻርተር ስለመመራታቸው ጥርጣሬ እንዳለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
በአማራና በአፋር ክልሎች በሕወሓት ታጣቂዎች ውድመት የደረሰባቸው የጤና ተቋማትና በታጣቂዎች አደጋ የተጋረጠበትን የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያን እያዩ እንዳለዩ ማለፋቸው፣ እንዲሁም ሚሊዮኖች የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸው ጉዳዩ በዋነኝነት የሚመለከታቸው የተመድ ተቋማት ዝምታን መምረጣቸው፣ ‹‹ድርጅቱ በቻርተር ስለመመራቱ ያጠራጥረኛል፤›› ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ገልጸዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ (አምባሳደር) ማክሰኞ ታኅሳስ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ለዓለም የጤና አገልግሎት በግንባር ቀደምትነት መሟገት የነበረበት የዓለም ጤና ድርጅት፣ በአማራና በአፋር ክልሎች በርካታ የጤና ተቋማት ወድመው እንደማይመለከተው ዝም ማለቱ አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡
ዲና (አምባሳደር) አክለውም በሌላ አገር አንድ ጤና ኬላ ሲወድም ይጮህ የነበረና ዝም የማይል ድርጅት፣ ‹‹በኢትዮጵያ እየሆነ ያለውን ውድመት ዓይቶ በዝምታ ማለፉ ያስተዛዝባል፤›› ብለዋል፡፡
የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ድርጅትን ምዕራባውያን አገሮች ኢትዮጵያን በተመለከተ የራሳቸውን የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ እየተጠቀሙበት እንደሆነ ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ በቅርቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከባድ ችግር እንደተፈጠረና ‹‹አዲስ አበባ በሕወሓት ልትያዝ ነው›› በሚል ከአገር የወጡ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት፣ አሁን ግን ለገና በዓልና ለዕረፍት እንደሄዱ እንደሚገልጹ አንዳንዶቹም ወደ ኢትዮጵያ እየተመለሱ እንደሆነ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
‹‹እንዲህ ዓይነቱን ያልተፈጠረን ነገር እንደተፈጠረ የማስመሰል እንቅስቃሴ ይሁን ብሎ ማለፍ ነው፡፡ በዲፕሎማሲ ሥራ ውስጥ ትዕግሥት ያስፈልጋል፡፡ መስሏቸው በስህተት ሄዱ አሁን ደግሞ ተመለሱ፡፡ ስለሆነም በእነሱ ደረጃ ወርዶ መጨቃጨቅ አስፈለጊ መስሎ አይታየንም፤›› ብለዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙ ምዕራባውያን አገሮች ዕርዳታ ለመስጠት ዝግጁ እንዳልሆኑ፣ አገሪቱ ውስጥ እየተከናወነ ያለውንና በሕወሓት የተፈጸመውን ጭፈጨፋና ቀውስ ሄደው እንዲያዩ ቢነገራቸውም ለማየት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡
በተመሳሳይ ዜና በመላው ዓለም ከሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ውስጥ አንድ ሚሊዮን የዳያስፖራ አባላት ወደ አገር ቤት እንዲመጡ በቀረበው ጥሪ መሠረት ወደ አገር ቤት የሚመጡ እንግዶች የጉዞ ሁኔታ በበላይነት የሚመራ ኮሚቴ ስለመቋቋሙ የጠቀሱት ቃል አቀባዩ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማይበርባቸው አካባቢዎች ለሚኖሩ የዳያስፖራ አባላት የቻርተር በረራ የሚመጡበት እያመቻቸ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡