Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የመኪና ታርጋ ለማውጣት ተቀምጦ የነበረው ቅድመ ሁኔታ እንዲቀር ተደረገ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ሰሌዳ (ታርጋ) ለማግኘት የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ማስገጠምና በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት መገጠሙን የሚያረጋግጥ ቅድመ መስፈርት ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ በጊዜያዊነት መነሳቱን ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ ይኼንን ቅድመ ሁኔታ ያነሳው የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ አገጣጠም ላይ ያሉ ችግሮችን የሚፈታ ጥናት ማድረግ በማስፈለጉ መሆኑን አስታውቋል፡፡

ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ በማሽከርከር የሚከሰት የትራፊክ አደጋ ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ፣ በ2011 ዓ.ም. የተሽከርካሪዎች የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ መግጠምና ማስተዳደርን የተመለከተ መመርያ የወጣ ሲሆን፣ ከመመርያው መውጣት በኋላ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች፣ የመኪና ታርጋ ከማግኘታቸው በፊት የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያን ማስገጠማቸውን የማረጋገጥ ግዴታ ነበረባቸው፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሚኒስቴሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ አቶ አብዱልበር ሸምሱ፣ ሚኒስቴሩ ይኼንን ውሳኔ ያሳለፈው ቅድመ ሁኔታው አዲስ ተሽከርካሪ የሚያስገቡ ባለንብረቶች ላይ ያስከተለውን ‹‹አላስፈላጊ›› ቢሮክራሲን ለመቀነስ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ኃላፊው ይኼንን የተመለከተ የአሠራር ማሻሻያ ለማድረግ ጥናት እየተደረገ መሆኑ የገለጹ ሲሆን፣ ከጥናቱ መጠናቀቅ በኋላ አሠራሩ ሙሉ ለሙሉ ወደነበረበት ሊመለስ አልያም በተሻለ መንገድ መተግበር ሊቀጥል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም. በወጣው መመርያ መሠረት የፍጥነት መገደቢያው የሚገጠምላቸው ተሽከርካሪዎች የምርት ዘመናቸው እ.ኤ.አ. 2000 እና ከዚያ በኋላ የተመረቱ ተሽከርካሪዎች ናቸው። የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር እያደረገ ባለው ጥናት የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ሊገጠምባቸው የሚገባቸውን ተሽከርካሪዎች ዓይነትን ለመለየት እንዳሰበ ገልጿል፡፡

 ‹‹መመርያው መሣሪያው ሚገጠምላቸው ተሽከርካሪዎች የምርት ዘመን ላይ ልዩነት ቢያስቀምጥም፣ ማንኛውም ዓይነት ተሽከርካሪ የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ እንዲገጥም ያዛል፤›› ያሉት አቶ አብዱልበር፣ እንደ አገር ሁሉም ተሽከርካሪ ላይ ገጠማ የማድረግ ሥራ ከመሥራት ቅድሚያ የሚሰጣቸውን መለየት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ በዚህም መሠረት አዲሱ አሠራር ተፈጻሚ መሆን ሲጀምር ገጠማው መኪናዎቹ በሚያደርሱት የአደጋ መጠን እንደሚለያቸው ገልጸው ‹‹አደጋን ከመቀነስ አንፃር ሁለት ሰው የሚጭን መኪና ላይ ከመግጠም የሕዝብ ተሽከርካሪ ላይ በቅድሚያ ማድረግ የተሻለ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከዚህም ባሻገር በአተገባበሩ ላይ ብልሹ አሠራርና የመልካም አስተዳደር ችግሮች መታየቱ ተገልጿል፡፡ አቶ አብዱልበር የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ገጠማው ላይ የሚሳተፉ አካላት ብዙ መሆናቸውን የተናግረው፣ ይኼም ሥራው በተፈለገው መልኩ እየተፈጸመ መሆኑን ለማረጋገጥ የማያስችል ክፍተት እንደፈጠረ አስታውቀዋል፡፡ አሁን እየተደረገ ባለው ጥናት ይኼንን ክፍተት ለመድፈን የታሰበ ሲሆን፣ ጥናቱ ማሻሻያ የሚያስፈልገው ‹‹መመርያው ላይ ነው ወይስ ሒደቱ ላይ የሚለውን ይለያል፤›› ተብሏል፡፡

በሚኒስቴሩ አዲስ ማሻሻያ መሠረት ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ አዳዲስ መኪናዎች፣ የመኪና ታርጋ ለማግኘት ፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ ማስገጠም ቅድመ ሁኔታ መሆኑ ለጊዜው ቢቀርም፣ መሣሪያውን ማስገጠም ግን አለመቅረቱ ተገልጿል፡፡ ተሽከርካሪ የሚያስገቡ ባለ ንብረቶች በማንኛውም ጊዜ ተሽከርካሪዎቻቸው ላይ መገደቢያውን ማስገጠም እንዳለባቸው የሚገልጽ የግዴታ ስምምነት መፈረም እንዳለባቸው ታውቋል፡፡ በግዴታ ስምምነቱ መሠረትም ቀጣይ ሚኒስቴሩ የማጣራት ሥራ እንደሚሠራ አቶ አብዱልበር ተናግረዋል፡፡

የፍጥነት መገደቢያ መሣሪያ መግጠም ግዴታ ሆኖ መተግበር የጀመረው ከ2012 ዓ.ም. መጨረሻ ጀምሮ ሲሆን፣ እስካሁን ከ32 ሺሕ በላይ ተሽርካሪዎች የመገደቢያ መሣሪያ እንደተገጠመላቸው ታውቋል፡፡ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር አሠራሩን ለማሻሻል የሚያደርገውን ጥናት በአንድ ወይም በሁለት ወር ውስጥ ለማጠናቀቅ እየሠራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች