Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኮንትሮባንድ ጭነው የሚያዙ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተገለጸ

ኮንትሮባንድ ጭነው የሚያዙ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው ተገለጸ

ቀን:

የኮንትሮባንድ ዕቃ ጭነው በተያዙ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጣለው ቅጣት፣ በማንኛውም ተሽከርካሪ ባለቤት ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ከተላለፈው ትዕዛዝ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ፣ አስፈጻሚዎች በተገለጸው ልክ ዕርምጃ ሊወስዱ እንደሚገባ ተገለጸ፡፡

በጉምሩክ ኮሚሽን የቃሊቲ ጉምሩክ የጽሕፈት ቤት ልዩ ረዳት አቶ ኃይሉ ሰብስቤ ፊርማ ወጪ የተደረገው ደብዳቤ እንደሚያሳያው፣ የጉምሩክ ኮሚሽን የሕግ ተገዥነት ዘርፍ  በቁጥር 7/0189/14 ኅዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በተጻፈ ደብዳቤ፣ ኮንትሮባንድ ጭነው በተያዙ የመንግሥት ተሽከርካሪዎች ላይ በአዋጅ 1160/2011 ላይ የተደነገገው አስተዳደራዊ ቅጣት የሚተላለፍባቸው መሆኑና አለመሆኑ በግልጽ ባለመደንገጉ፣ ለአፈጻጸም የተቸገሩ መሆኑን የሐዋሳ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በጥያቄ ገልጿል ይላል፡፡

የሐዋሳ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ለኮሚሽኑ በጻፈው ደብዳቤ፣ ኮንትሮባንድ ጭኖ የተገኘ ተሽከርካሪ ባለቤት፣ በወንጀሉ ተሳትፎ ቢኖረውም ባይኖረውም የተጫነውን የኮንትሮባንድ ዕቃ ዋጋ መቶ በመቶ፣ ወይም አንድ መቶ ሺሕ ብር ወይም ከሁለቱ አነስተኛውን የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል የሚለው የአዋጅ ቁጥር 1160/2011 ድንጋጌ፣ ጥፋቱ የፈጸመው በመንግሥት ተሽከርካሪ ከሆነ በተመሳሳይ ቅጣቱ ይተላለፍባቸዋል በማለት በግልጽ ስላልተደነገገ፣ ለአፈጻጸም ይረዳው ዘንድ አቅጣጫ እንዲሰጠው ጠይቋል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ኮሚሽኑ ይህንን ጥያቄ መሠረት በማድረግ ለሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በላከው ትዕዛዝ እንዳስታወቀው፣ የኮንትሮባንድ ዕቃ የጫነ ማጓጓዣ በማሻሻያ አዋጁ የተቀመጠው ቅጣት በማንኛውም የተሽከርካሪ ባለቤት ላይ ማለትም የተሽከርካሪው ባለቤት መንግሥትም ይሁን ግለሰብ፣ በተሽከርካሪው ላይ በተፈጸመ ጥፋት የሚጣለውን ቅጣት በማንኛውም አካል ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ያሳወቀ ሲሆን፣ ይህንንም ሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተፈጻሚ እንዲያደርጉት ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡

የጉምሩክ ኮሚሽን የሕግ ተገዥነት ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር አቶ ሙሉጌታ በየነ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ትዕዛዙ የጉምሩክ ሥነ ሥርዓት ለሚፈጸምባቸው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሙሉ የተላለፈው በተለየ መንገድ፣ በመንግሥት ተሽከርካሪዎች የሚፈጸም የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴ በዝቶ ሳይሆን፣ በተለያየ መልኩ የሚያጋጥም ተግባር በመሆኑ ነው፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ እንዳስታወቁት ለምሳሌ አንድ አምቡላንስ ኮንትሮባንድ ጭኖ ቢገኝ መኪናው የመንግሥት ነው፡፡ መንግሥት ደግሞ ኮንትሮባንድን የሚጭንበት ምክንያት የለም፡፡ በመሆኑም የድርጊቱ ፈጻሚ አሽከርካሪው አሊያም ተሽከርካሪውን እንዲቆጣጠር ኃላፊነት የተሰጠው ግለሰብ ነው፡፡ በመሆኑም ይህንን አካሄድ እንዴት ማስተዳደር ይቻላል የሚለው ጉዳይ ብዥታ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡

ኮሚሽኑ በደረሰበት ድምዳሜ መሠረት የተሽከርካሪ ባለቤቶች ተሽርካሪዎቻቸውን የመከታተል ኃላፊነትን ሕጉ ታሳቢ የሚያደርግ ስለሆነ፣ አሽከርካሪዎቹ የመከታተል ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የመንግሥት ንብረት የሆነን ተሽከርካሪ ለምን ዓይነት ግለሰብ ነው ተላልፎ የሚሰጠው? ተሽከርካሪው እንዴት ሄዶ ይመለሳል? የሚለውን ሕጉ ይመለከታል፡፡

ሕጉ ኮንትሮባድን በመከላከል፣ እንዲሁም ለሕዝብ አገልግሎት ተብሎ የወጣን ተሽከርካሪ ለሌላ ዓላማ እንዳይውል ለመቆጣጠር የሚያስችል ነው፡፡

በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ከሚታዩ ነገሮች አንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤት ስለሆነ፣ ሊጠየቅ አይገባም የሚል ሐሳብ እንዳለ የተናገሩት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ሕጉ ኃላፊነት የወሰደ አካል በአግባቡ ኃላፊነቱን ካልተወጣ ከዕርምጃ የማያመልጥ መሆኑን ለመሳየት የወጣ ነው፡፡

ኮሚሽኑ ለቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በጻፈው የአቅጣጫ ደብዳቤ ላይ እንዳስታወቀው፣ የአጓጓዥ ግዴታን ያለመወጣት የሚመለከተው የማሻሻያ አዋጁ፣ ቅጣት በማንኛውም የተሽርካሪ ባለቤት ላይ የመንግሥትም ጭምር ቢሆን በተሽከርካሪው ላይ በተፈጸመው ጥፋት የሚጣለው ቅጣት በየትኛውም አካል ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

ለሁሉም ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በተገለጸው ደብዳቤ መሠረት ተፈጻሚ እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተላልፈዋል ያሉት ምክትል ኮሚሽነሩ፣ ኮሚሽኑ ከሁሉም የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ኃላፊዎች ጋር በየሳምንቱ ውይይት አደርጎ ሥራዎችን እንደሚገመግመው ሁሉ፣ የዚህንም ጉዳይ አፈጻጸም የሚመለከት ይሆናል ብለዋል፡፡

ኮሚሽኑ ከዚህ ቀደም ከኮንትሮባንድ ጋር ተያይዞ ባደረገው ግምገማ፣ ከ2010 ዓ.ም. አስቀድሞ ኮንትሮባንድን የሚፈጽሙ ወንጀለኞች እንደማይያዙ መከታተሉን ገልጸው፣ በ2011 እና 2012 ዓ.ም. ለምንድነው ዕቃዎች ብቻ በቁጥጥር ሥር የሚውሉት የሚለውን ክፍተት በመለየት፣ ከፌዴራል ፖሊስ ጋር በጥምረት ሥራ እንደጀመረ አስረድተዋል፡፡

በ2013 ዓ.ም. የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወጥቶ የሚያዙትን ሳይጨምር 1,200 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች ከኮንትሮባንድ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ሥር እንደዋሉ የተናገሩት አቶ ሙሉጌታ፣ ባለፉት አምስት ወራት ውስጥ 400 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች ተይዘው በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ እየተደረገባቸው ነው፡፡ ኮሚሽኑ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ተጠርጣሪዎች ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን፣ መዝገብ ተደራጅቶ ወደ ዓቃቤ ሕግ መመራቱን፣ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ ፍርድ ቅጣት መተላለፉን የሚመለከት ሥራን፣ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰላማዊ የፖለቲካ ትግልና ፈተናው

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) የፖለቲካ ኦፊሰር የአቶ በቴ ኡርጌሳን...

አበጀህ ማንዴላ! አበጀሽ ደቡብ አፍሪካ!

በአየለ ት. የፍልስጤም ጉዳይ የዓለም አቀፍ ፖለቲካንም ሆነ የተባበሩት መንግሥታትን...

የውጭ ባለሀብቶች ለኢትዮጵያውያን ብቻ በተፈቀዱ የንግድ ዘርፎች እንዲገቡ የመወሰኑ ፋይዳና ሥጋቶች

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አዓመድ (ዶ/ር) የውጭ ኩባንያዎች በጅምላና ችርቻሮ...