Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የገና ባዛር የዋጋ ቅናሽ ተደርጎበት በራሱ በኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚዘጋጅ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • በዚህ ባዛር ጥሩ ውጤት ከተገኘ ለሌሎች ባዛሮች ጨረታ ላይወጣ ይችላል ተብሏል

ከመጪው ቅዳሜ ታኅሳስ 9 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ በኤግዚቢሽን ማዕከል የሚካሄደው የገና ባዛር፣ የምርት ማሳያ ቦታ ኪራይና የደንበኞች መግቢያ ዋጋ ላይ ቅናሽ ተደርጎ፣ በኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት ድርጅት እንደሚዘጋጅ ተገለጸ፡፡ ከዚህ በፊት የሁነት አዘጋጆችን በጨረታ አወዳድሮ ባዛሮችን እንዲዘጋጁ ሲያደርግ የነበረው ድርጅቱ፣ ባዛሩን በራሱ ለማዘጋጀት የወሰነው ጨረታውን አሸንፎ የነበረው ‹‹ቤታሆን›› የተሰኘ የሁነት አዘጋጅ በተሰጠው ጊዜ ውስጥ ክፍያ ባለመፈጸሙ መሆኑ ታውቋል፡፡

የኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት ድርጅት ማክሰኞ ታኅሳስ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ እስካሁን ከ350 በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ነጋዴዎች በባዛሩ ላይ የሽያጭ ቦታ ለመከራየት ተመዝግበዋል፡፡ እንደ ድርጅቱ ገለጻ፣ የቦታው ኪራይ ላይ ከዚህ በፊት ከነበረው ዋጋ እስከ 20 በመቶ ቅናሽ ተደርጓል፡፡ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥላሁን ታደሰ፣ ‹‹በ90 ሺሕ ብር ሲከራዩ የነበሩ ቦታዎችን በ60 እና በ65 ሺሕ ብር እያከራየን ነው፤›› ብለዋል፡፡

የገበያተኞች የመግቢያ ዋጋ ላይም ‹‹ከፍተኛ›› ቅናሽ እንደተደረገ የተገለጸ ሲሆን፣ ከዚህ በፊት ከሃምሳ እስከ አንድ መቶ ብር የነበረው የመግቢያ ዋጋ መነሻውን ሰላሳ ብር አድርጎ በባዛሩ የመጨረሻ ቀናት 50 ብር እንዲሆን መወሰኑ ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ ይኼንን የዋጋ ቅናሽ በማድረጉ በባዛሩ ለገበያ የሚቀርቡ ምርቶች ላይ ቅናሽ እንዲኖር ያደርጋል የሚል እምነት እንዳለው ያስታወቀ ሲሆን፣ በጨረታ ቀርቦለት የነበረውን ገንዘብ በራሱ የማግኘት ዕቅድ እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡

ባዛሩን 500 ሺሕ ያህል ሰዎች ይጎበኙታል ተብሎ እንደሚጠበቅ ያስታወቀው ድርጅቱ፣ ከ500 በላይ ነጋዴዎች ይሳተፉሉ የሚል ግምትን አስቀምጧል፡፡ ይሁንና እስካሁን የተመዘገቡት ሰዎች ከ350 እስከ 400 ያህል መሆናቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጁ፣ ‹‹ከዚህ በፊትም ባለው አሠራር ቀሪዎቹ ነጋዴዎች የሚሞሉት ገበያው እየደመቀ ሲመጣ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የገና ባዛርን ለማዘጋጀት የገባው ውል የተሰዘረበት ‹‹ቤታሆን›› ጨረታውን ያሸነፈው 68 ሚሊዮን ብር በማቅረብ ሲሆን ይህ ዋጋ በሁለተኛ ደረጃ ከቀረበው ዋጋ የ30 ሚሊዮን ብር ልዩነት እንዳለው ተገልጿል፡፡ ‹‹ቤታሆን›› የፋሲካ ባዛርንም ለማዘጋጀት ጨረታውን አሸንፎ የነበረ ሲሆን፣ ለሁለቱ ባዛሮች ያቀረበው 111 ሚሊዮን ብር ከዚህ በፊት ባዛር ለማዘጋጀት ከቀረቡት ዋጋዎች ከፍተኛው ነው፡፡

‹‹ቤታሆን›› ያቀረበውን የጨረታ ዋጋ 20 በመቶ ውሉን ካገኘ ከሦስት እስከ አምስት ባሉት ቀናት ውስጥ የመክፈል ግዴታ የነበረበት ቢሆንም፣ በጊዜው ከወጣው የብሔራዊ ባንክ መመርያ ጋር በተያያዘ የክፍያ መፈጸሚያ ጊዜው ወደ አንድ ወር ተራዝሞለት ነበር፡፡ ይኼ ውሳኔ የተወሰነው አዘጋጁ ያቀረበው ዋጋ ከፍተኛ በመሆኑ ላለማጣትና ባዛር በማዘጋጀት ‹‹ብዙም ልምድ የሌለው በመሆኑ›› ድጋፍ ለማድረግ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ይሁንና ‹‹ቤታሆን›› እስካለፈው ሳምንት ሐሙስ ኅዳር 30 ቀን 2014 ዓ.ም. ድረስ ክፍያ ባለመፈጸሙ ጨረታው እንዲሰረዝ መወሰኑን ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ ጥላሁን ተናግረዋል፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ የባዛር ፈቃድ ማግኘት አስቸጋሪ እንደነበር የተገለጸ ሲሆን፣ ከከተማ አስተዳደሩ ጋር ከተደረገ ንግግር በኋላ ፈቃዱ የተገኘው ባለፈው ሳምንት መሆኑ ታውቋል፡፡

ጨረታውን አሸንፎ በነበረው ‹‹ቤታሆን›› ሥር የተመዘገቡ ነጋዴዎች መኖራቸውን የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ ‹‹ቤታሆን›› ነጋዴዎቹ የከፈሉትን ገንዘብ ወደ ኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት ድርጅት እንዲያዞር አልያም እንዲመለስላቸው ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ገንዘባቸው የተመለሰላቸው ነጋዴዎች በድርጅቱ በድጋሚ እየተመዘገቡ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

‹‹ቤታሆን›› የተሰረዘበት ውል የፋሲካ ባዛርንም የሚያካትት በመሆኑ፣ ድርጅቱ የፋሲካ ባዛርንም እንደሚያዘጋጅ አስታውቋል፡፡ ‹‹በአዲስ ዓመት በዓል ባዛር ላይ የተሳተፉት ነጋዴዎችን የመመዝገብ ሥራ አስቀድሞ ተሠርቶ ነበር፤›› ያሉት አቶ ጥላሁን፣ ድርጅቱ ካለው ልምድ እንፃር ባዛሩን ‹‹ውጤታማ›› ማድረግ ይችላል በማለት ተናግረዋል፡፡ በዚህ ባዛር ላይ የሚገኘው ውጤት ‹‹ጥሩ›› ከሆነም ከዚህ በኋላ ለሚዘጋጁ ባዛሮች ጨረታ ላይወጣ እንደሚችልም ዋና ሥራ አስኪያጁ ጠቁመዋል፡፡ ይኼም በመሸጫ ቦታ ኪራይ ዋጋ ላይ በተደጋጋሚ ይነሳ የነበረውን ቅሬታ ይፈታል የሚል ሐሳብ ተነስቷል፡፡

የኤግዚቢሽን ማዕከልና ገበያ ልማት ድርጅት ከከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ የሚያገኝ ከሆነ፣ በገና ባዛር ላይ የተለያዩ ኮንሰርቶችን የማዘጋጀት ዕቅድ እንዳለው ያስታወቀ ሲሆን፣ ለገና በዓል እንደሚመጡ የሚጠበቁት አንድ ሚሊዮን ዳያስፖራዎች ተሳታፊ ይሆናሉ የሚል እምነትም አለው፡፡

ድርጅቱ የመስቀል አደባባይ ፕሮጀክትንም የሚያስተዳድር በመሆኑ፣ ዕድሳት የተደረገለት የመስቀል አደባባይና ዘመናዊ የመኪና ማቆሚያው በዳያስፖራዎች ይጎበኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጿል፡፡ የተለያዩ ባንኮች ማዕከሉ ውስጥ የምንዛሪ አገልግሎት እንዲሰጡ የማድረግ ሥራም እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች