የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ባለአክሲዮኖች የባንኩን የተከፈለ ካፒታል በዕጥፍ በማሳደግ አሥር ቢሊዮን ብር እንዲሆን መወሰናቸው ተገለጸ፡፡ በ2013 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት 1.68 ቢሊዮን ብር ማትረፍ መቻሉም ታውቋል፡፡
ታኅሳስ 5 ቀን 2014 ዓ.ም. በተካሄደው የባንኩ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ በቀረበው ውሳኔ ሐሳብ መሠረት እስካሁን የነበረውን የአምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል ወደ አሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ባለአክሲዮኖቹ ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡
በዚህ ውሳኔ መሠረት ባንኩ ተጨማሪውን የአምስት ቢሊዮን ብር ካፒታል በአራት ዓመት ውስጥ አሥልቶ ለማጠናቀቅ ስምምነት መድረሱን የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ገነነ ሩጋ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ተጨማሪውን ካፒታል ለማሟላት አክሲዮን የሚሸጠውም ለባንኩ ባለአክሲዮኖች እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል፡፡ እንደ አቶ ገነነ ገለጻ፣ የባንኩ ባለአክሲዮኖች ካፒታሉ ወደ አሥር ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ውሳኔ ማሳለፋቸው ባንኩን የበለጠ ተወዳዳሪና ጠንካራ ለማድረግ ያግዘዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የባንኩ አጠቃላይ የተከፈለ ካፒታል፣ ያልተከፋፈለ ትርፍ፣ ሕጋዊና ልዩ ልዩ የመጠባበቂያ ሒሳቦችን ጨምሮ 7.0 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ውጤት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ1.2 ቢሊዮን ብር ወይም የ21.2 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ ወልደተንሳይ ወልደጊዮርጊስ እንደገለጹትም፣ የባንኩ የተከፈለ ካፒታል አጠቃላይ ከባንኩ ካፒታል ውስጥ 60.7 በመቶውን ድርሻ የያዘ መሆኑን ነው፡፡
ይህም ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ24.0 በመቶ ጭማሪ በማሳየት በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 4.3 ቢሊዮን ብር መድረሱን ገልጸዋል፡፡
ባንኩ ከካፒታል ማሳደግ ውሳኔው ቀደም ብሎ የ2013 የሒሳብ ዓመት የሥራ አፈጻጸሙን ይፋ ተደርጓል፡፡ በሪፖርቱ መሠረት ንብ ባንክ በሒሳብ ዓመቱ ከግብር በፊት 1.68 ቢሊዮን ብር ማትረፉንና ይህም የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት 24 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን ያሳያል፡፡
ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት አስመዝግቦ የነበረው የትርፍ መጠን 1.3 ቢሊዮን ብር እንደነበር የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ ከግብር በኋላ ያስመዘገበው የ2013 የሒሳብ ዓመት ትርፍ 1.2 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የንብ ባንክ አጠቃላይ ተቀማጭ ገንዘብ መጠኑን 43.5 ቢሊዮን ብር ማድረስ የቻለ ሲሆን፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ያሰባሰበው ተቀማጭ ገንዘብ 9.9 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት የ29.4 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡
የባንኩ አጠቃላይ አስቀማጭ ደንበኞች ቁጥርም በ466 ሺሕ 884 ወደ 1.68 ሚሊዮን ማድረስ ችሏል፡፡ ይህም የአስቀማጮቹ ቁጥር በ38.6 በመቶ ማደጉን የሚሳይ ነው፡፡
የባንኩ የ2013 ዓ.ም. አጠቃላይ ገቢ 5.8 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ1.3 ቢሊዮን ብር ወይም የ28.0 በመቶ ዕድገት አስመዝግቧል፡፡
ከዓለም አቀፍ የባንክ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ባንኩ 452.5 ሚሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱ ተገልጿል፡፡ ይህም ከባንኩ አጠቃላይ ገቢ 7.8 በመቶ የሚሆነውን ድርሻ የያዘ ሲሆን፣ ከዚህ ዘርፍ የተገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ60.9 ሚሊዮን ብር ወይም የ15.5 በመቶ ዕድገት እንዳሳየ ከቀረበው ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ ሀብት መጠኑ 54.2 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ይህም ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው 42.5 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ27.6 በመቶ ዕድገት አሳይቷል፡፡ ይህ ጠቅላላ የሀብት መጠን በባንኩ የተሰጠን የብድር ክምችት፣ በእጅ ያለን ጥሬ ገንዘብ፣ በአገር ውስጥና በውጭ አገር ባንኮች ያለን ተቀማጭ ገንዘብ፣ በብሔራዊ ባንክ የተቀመጠ መጠባበቂያ፣ የባንኩን ቋሚ ንብረቶች፣ እንዲሁም አክሲዮኖችና ቋሚ ንብረቶች ላይ የተደረጉ ኢንቨስትመንቶችን የሚያካትት እንደሆነም ተገልጿል፡፡
በ2013 ሒሳብ ዓመት መጨረሻ ላይ የባንኩ የብድር ክምችት 34.5 ቢሊዮን ብር የደረሰ ሲሆን፣ ካለፈው ሒሳብ ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ8.7 ቢሊዮን ብር ወይም 33.7 በመቶ ዕድገት እንደታየበት ተገልጿል፡፡ የባንኩ የተበዳሪዎች ቁጥርም ባለፈው በጀት ዓመት ከነበረው 15,541 ወደ 18,278 ከፍ ማለቱንም ሪፖርቱ አመልክቷል፡፡
በሌላ መልኩ ግን የብድር ውዝፍ ክምችት ምጣኔን ወይም የተበላሸ የብድር መጠኑ 3.61 በመቶ ስለመድረሱ ታውቋል፡፡ ይህም ካለፈው የሒሳብ ዓመት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ ጭማሪ ያሳየ መሆኑን ሪፖርቱ አመላክቷል፡፡ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ምጣኔ አንፃር ሲታይ የተሻለ ሆኖ መገኘቱንም ጠቅሷል፡፡
ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ በግንቦት 1991 ዓ.ም. በ717 ባለአክሲዮኖች በ27.6 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል የተቋቋመ ነው፡፡ ከ7,850 በላይ ሠራተኞች ያሉት ባንኩ የቅርንጫፎቹን ቁጥርም 380 አድርሷል፡፡