Monday, May 29, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ዓባይ ኢንሹራንስ ከታክስ በፊት ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ ማትረፉን ገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በ2013 የሒሳብ ዓመት በአጠቃላይ 362.02 ሚሊዮን ብር ዓረቦን ማሰባሰብ የቻለው ዓባይ ኢንሹራንስ ከታክስ በፊት 75.5 ሚሊዮን ብር ማትረፉን አስታወቀ፡፡

ኩባንያው ቅዳሜ ታኅሳስ 2 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንዳስታወቀው በሒሳብ ዓመቱ ካሰባሰበው ዓረቦን ውስጥ 350.15 ሚሊዮን ብር የሚሆነው የጠቅላላ መድን ድርሻ ሲሆን፣ ቀሪው 11.8 ሚሊዮን ብር ደግሞ ከሕይወት መድን የተገኘ ነው፡፡

አፈጻጸሙ ከዕቅዱ አንፃር 14 በመቶ ብልጫ ያለው ነው፡፡  ዓባይ ኢንሹራንስ በሒሳብ ዓመቱ አሰባስባለሁ ብሎ ያቀደው 325.5 ሚሊዮን ብር እንደነበር ታውቋል፡፡ ከአምናው አንፃር ሲታይ ግን 33.8 በመቶ ዕድገት የታየበት የዓረቦን ገቢ ማስገኘቱን የኩባንያው መረጃ ያመለክታል፡፡

ይህ ዓመታዊ የዓረቦን ዕድገት መጠን በኢንዱስትሪው ከተመዘገበው 24.8 በመቶ አማካይ ዕድገት ጋር ሲነጻፀር ዘጠኝ በመቶ ከፍ ያለ መሆኑንም የዓባይ ኢንሹራንስ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር አቶ አባተ ስጦታው ተናግረዋል፡፡ 

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከጠቅላላ የመድን ዋስትና ብቻ 197.7 ሚሊዮን ብር የተጣራ ዓረቦን ማስዝገቡንና ከዓምና አፈጻጸም 171.3 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር የ15.4 በመቶ ዕድገት እንደታየበት አመልክተዋል፡፡

ዓምና ከሕይወት ኢንሹራንስ ተገኝቶ ከነበረው 10.8 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 9.9 በመቶ ዕድገት የታየበት መሆኑም ተጠቅሷል፡፡

የካሳ ክፍያን በተመለከተ ከጠቅላላ መድን ዋስትና ጋር በተያያዘ በኩባንያው የተከፈለው የተጣራ የካሳ ክፍያ መጠን ብር 91 ሚሊዮን እንደሆነና ይህ የካሳ ክፍያ ሊከፈል ይችላል ተብሎ ከታቀደው ብር 96 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 5.2 በመቶ ቅናሽ እንዳለው ታውቋል፡፡

በሒሳብ ዓመቱ የተከፈለው ካሳ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር 2.4 በመቶ ብልጫ እንዳለውም ለማወቅ ተችሏል፡፡

በኩባንያው የተመዘገበው የተጣራ የካሳ ወጪ ጥያቄ መጠን ግን 113.2 ሚሊዮን ብር መሆኑን የሚያመለክተው የኩባንያው መረጃ፣ ይህም በዕቅድ ከተያዘው 128.1 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 11.6 በመቶ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ 22 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ነው፡፡

እንደ ሌሎች የአገሪቱ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሁሉ ዓባይ ኢንሹራንስ በአጠቃላይ ከተመዘገበው የካሳ ወጪ ውስጥ የተሽከርካሪ ዋስትና 87.4 በመቶ የሚሆነውን ከፍተኛ ድርሻ የያዘ ሆኗል፡፡

ኩባንያው በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት 46.6 ሚሊዮን ብር ገቢ ከኢንቨስትመንት ያገኘ ሲሆን፣ ይህም ከዓምናው ተመሳሳይ ወቅት ብር 40 ሚሊዮን ጋር ሲነፃፀር የ16.4 በመቶ ዕድገት ያሳየ መሆኑ ተገልጿል፡፡  

በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ከጠቅላላ መድን ዋስትና ብቻ ከታክስ በፊት 75.5 ሚሊዮን ብር ትርፍ አስመዝግቧል፡፡ ይህም ከቀደመው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት አትርፎ ከነበረው 68.1 ሚሊዮን ብር ጋር ሲነፃፀር 10.8 በመቶ ብልጫ አለው፡፡

አተርፋለሁ ብሎ ያቀደው 82.37 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ በ2013 ሒሳብ ዓመት ያገኘው ትርፍ ከዕቅዱ አንፃር የ8.3 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች