Saturday, June 10, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ቡና ባንክ 937 ሚሊዮን ብር ማትረፉንና የተበላሸ የብድር መጠኑን በግማሽ መቀነሱን አስታወቀ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተጠናቀቀው የ2013 የሒሳብ ዓመት የትርፍ ምጣኔያቸውን በከፍተኛ ደረጃ ካሳደጉ ጥቂት ባንኮች መካከል በቀዳሚነት የሚጠቀሰው ቡና ባንክ ዓመታዊ ትርፉን በ61 በመቶ በማሳደግ ከታክስ በፊት ከ937 ሚሊዮን ብር በላይ ሲያተርፍ፣ የተበላሸ የብድር መጠኑንም በግማሽ መቀነሱን አስታወቀ፡፡

ባንኩ እሑድ ታኅሳስ 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በ2013 ሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት ያገኘው የትርፍ መጠን ከቀዳሚው ዓመት የ355.3 ሚሊዮን ብር ብልጫ ያለው መሆኑን አስታውቋል፡፡

በ2012 የሒሳብ ዓመት ከታክስ በፊት አስመዝግቦት የነበረው የትርፍ መጠን 582 ሚሊዮን ብር እንደነበር ይታወሳል፡፡

ባንኩ በ2013 የሒሳብ ዓመት ያገኘው የትርፍ ዕድገት መጠን በኢንዱስትሪው ከፍተኛው የሚባል ሲሆን፣ እስካሁን ዓመታዊ ሪፖርታቸውን ያቀረቡ ባንኮች ዓመታዊ የትርፍ ምጣኔያቸው ዕድገት ከ50 በመቶ በታች ነው፡፡

የቡና ባንክን የ2013 የሒሳብ ዓመት አፈጻጸም በተመለከተ የባንኩ ዳይሬክተሮች ቦርድ ሊቀመንበር ሰውአለ አባተ (ዶ/ር) ባቀረቡት ጥቅል ሪፖርት፣ ዓለም አቀፋዊና አገራዊ ምክንያቶች በአጠቃላይ የባንኩ ኢንዱስትሪ ላይ ጫና ቢያሳድሩም የዳይሬክተሮች ቦርድና ማኔጅመንቱ አመራር የችግር ጊዜ አሠራሮችን በመዘርጋት ተፅዕኖውን ተቋቁሞ አጠቃላይ ገቢውን በማሳደግ ከቀደሙት ዓመታት የላቀ ትርፍ እንዲያስመዘግብ አስችለዋል ብለዋል፡፡

አፈጻጸሙ ከዓምናው በላቀ ደረጃ ላይ መገኘቱ የሚያበረታታ ውጤት መሆኑንም በሪፖርታቸው ያመለከቱት ዶ/ር ሰውአለ፣ ባንኩ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ካስመዘገበው የትርፍ ዕድገት ባሻገር ከፍተኛ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑንም በ47.5 በመቶ ማሳደጉ ተገልጿል፡፡

የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ መጠን በሒሳብ ዓመቱ መጨረሻ ላይ 20.46 ቢሊዮን ብር መድረሱን የሚያመለክተው የባንኩ መረጃ፣ ይህ አፈጻጸም ከቀዳሚው ዓመት በ6.58 ቢሊዮን ብር ዕድገት ያሳየ ስለመሆኑ አመልክቷል፡፡

የባንኩ የተቀማጭ ገንዘብ ጭማሪ በዓይነት ሲታይ የቁጠባ ተቀማጭ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ111.7 በመቶ ወይም የ2.9 ቢሊዮን ብር ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ የተንቀሳቃሽ ሒሳብ በብር 451 ሚሊዮን ወይም 254 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱም ተገልጿል፡፡

በዓመታዊ ሪፖርቱ ላይ እንደተመለከተውም፣ በአንድ ዓመት ውስጥ የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞቹን ቁጥር ከ576 ሺሕ በላይ ከፍ ማድረግ ችሏል፡፡ በዚህ የ71.5 በመቶ ዕድገት ማስመዝገብ የቻለ ሲሆን፣ ይህም አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 1.38 ሚሊዮን እንዲደርስ አስችሏል፡፡

በወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎቱ ረገድም በዋዲያና ቀረድ ከወለድ ነፃ ሒሳቦች በበጀት ዓመቱ ብቻ 45,672 ደንበኞችን በማፍራት አጠቃላይ የደንበኞቹን ቁጥር ከ576 ሺሕ በላይ አድርሷል ተብሏል፡፡

በዓመቱ ውስጥ 400 ሚሊዮን ብር ከወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ በመሰብሰብ አጠቃላይ የወለድ ነፃ ተቀማጭ ገንዘብ 576,026 ማድረሱ በቀረበው ሪፖርት ላይ ተመልክቷል፡፡

ባንኩ ጥሩ አፈጻጸም ያሳየበት ዘርፍ ተብሎ የተገለጸው ክዋኔ ለደንበኞቹ የሰጠው የብድር መጠን ዕድገት ነው፡፡ ከባንኩ መረጃ መረዳት እንደተቻለው፣ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ለተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች የሰጠው አጠቃላይ የብድር መጠን 6.73 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ ይህም በቀዳሚው ዓመት ከሰጠው 58.1 በመቶ ጭማሪ በማሳየቱ በዓመቱ መጨረሻ ላይ አጠቃላይ የብድር ክምችቱ 18.29 ቢሊዮን ሊደርስ ችሏል፡፡

ከባንኩ የብድር አሰጣጥና አመላለስ ጋር በተያያዘ፣ በሒሳብ ዓመቱ የመክፈያ ጊዜ ያለፈባቸው የተበላሸ የብድር መጠን ከጠቅላላው ብድር ያላቸው ምጣኔ በግማሽ መቀነሱ ነው፡፡

ባንኩ በ2012 የሒሳብ ዓመት የተበላሸ የብድር መጠኑ 4.64 በመቶ የነበረ ሲሆን በ2013 የሒሳብ ዓመት ግን ወደ 2.4 በመቶ መውረድ ችሏል፡፡ ይህም መጠን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ካስቀመጠው የአምስት በመቶ ጣሪያ ያነሰ መሆኑን ጠቅሰው፣ ለዚህ ከፍተኛ ውጤት መገኘት የባንኩ ማኔጅመንትና የዳይሬክተሮች ቦርድ የብድር አስተዳደር ሥርዓቱን ጥንቃቄ የተሞላበት እንዲሆን የወሰዷቸው ዕርምጃዎች እንደሚጠቀሱ የቦርድ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

የዓለም አቀፍ ባንክ አገልግሎትን በተመለከተ ቡና ባንክ በተጠናቀቀው የሒሳብ ዓመት ያሰባሰበው የውጭ ምንዛሪ መጠን 163.97 ሚሊዮን ዶላር ነው፡፡ ይህም ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ2.7 በመቶ ወይም 4.4 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አሳይቷል፡፡

ምንም እንኳን የውጭ ምንዛሪ ግኝቱ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር መጠነኛ ብልጫ ቢያሳይም፣ ኮቪድ-19 በዘርፉ ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ ግን አሁንም በውጭ ምንዛሪ ግኝት በኩል ባንኩ በሚፈልገው መንገድ እንዳይጓዝ እንቅፋት ሆኖ ስለመቀጠሉ የቦርድ ሊቀመንበሩ ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

ባንኩ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ግንባታ ዕቅዱን ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካገኘው 1043 ካሬ ሜትር ቦታ በተጨማሪ ሰፋ ያለ ቦታ በአዲስ አበባ እንዲሰጠው ጥያቄ አቅርቦ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኝ ስፋቱ 4570 ካሬ ሜትር ቦታ ተዘጋጅቶ ለባንኩ እንዲሰጥ ውሳኔ የተላለፈ መሆኑን አመልክቷል፡፡

ይህንን ውሳኔ ተግባራዊ ለማድረግም ልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የሚለማ ቦታ እያዘጋጀ ስለሚገኝ ለተዘጋጀው ቦታ በከተማው መሬት ልማትና ማደስ ኤጀንሲ ሲፀድቅ ባንኩ የይዞታ ባለቤትነት ካርታ ለመቀበልና ቦታውን ለመረከብ በሒደት ላይ እንደሚገኝም ተገልጿል፡፡

የቡና ባንክ ጠቅላላ የካፒታል መጠኑ በ706.2 ሚሊዮን ብር ዕድገት አሳይቶ 3.81 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ በሒሳብ ዓመቱ 43 ቅርንጫፎችን በመክፈት አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥር 285 ማድረስ ችሏል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች