Wednesday, May 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየጎዳናው ላይ ድጋፍ

የጎዳናው ላይ ድጋፍ

ቀን:

የፌዴራል መንግሥት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ከተባለው ከሕወሓት ታጣቂዎች ጋር እያካሄደ ባለውና ከአንድ ዓመት በላይ ባስቆጠረው የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት ከብዙ ሺሕ በላይ ዜጎች ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ ሕይወታቸውንም አጥተዋል፡፡

በተለይም ከፊት ለፊት የተደቀነውን ችግር ለመጋፈጥና የአገር ህልውናን ለማስከበር ቀን ከለሊት ደፋ ቀና በማለት ላይ የሚገኘው የአገር መከላከያ ሠራዊት ከመቼውም ጊዜ አሁን ላይ ፈተና ውስጥ ገብቷል፡፡ ይህንንም ፈተና ለማለፍ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከመከላከያው ጎን በመቆም በተለያየ መልኩ ድጋፋቸውን እያደረጉ ይገኛል፡፡

በአዲስ አበባ በሳሪስ ሠፈር፣ በ58፣ በሃና ማሪያም፣ በቦሌ፣ በሜክሲኮና በሌሎች ቦታዎች ላይ ደግሞ ለመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲውል መኮሮኒ፣ ፓስታ፣ ዱቄት፣ አልባሳት ዘይት እንዲሁም ሌሎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ነገሮችን በማሰባሰብ በጎ ተግባር ላይ የሚገኙ ወጣቶችን ሪፖርተር አይቷል፡፡

- Advertisement -

በወረዳ 11፣ 58 አካባቢ ለመከላከያ ሠራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲውል ድጋፍ እያሰባሰቡ መሆኑን የሚናገረው ወጣት ይድነቃቸው ብርሃኑ፣ ከ700 ሺሕ በላይ ገንዘብ የሚያወጡ ግብዓቶችን በመሰብሰብ ለሚመለከተው አካል እንዳስረከቡ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

የድጋፉ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ከታኅሣሥ 1 እስከ ታኅሣሥ 4 ቀን  2014 ዓ.ም. ድረስ ማከናወናቸውን የገለጸው ወጣት ይድነቃቸው፣ ለድጋፉም የማኅበረሰቡ ፍላጎትና ተነሳሽነት የጎላ በመሆኑ ከሚፈለገው በላይ ግብዓቶችን መሰብሰብ መቻላቸውን አስረድቷል፡፡

ከዚህ በፊትም ከቦረና አካባቢ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ ማድረጋቸውን ያስታወሰው ይድነቃቸው፣ የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በሚያከናውኑ ጊዜ ከወረዳ ፈቃድ እንደተሰጣቸውና ከፀጥታ አካላት ጋርም በቅንጅት እየሠሩ መሆኑን አክሏል፡፡

የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ በጣም አድካሚና አሰልች መሆኑን፣ ይሁን እንጂ በአካባቢ የሚገኙ ወጣቶች ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ከመከላከያ ሠራዊቱም ሆነ ከተፈናቀሉ ወገኖች ጎን በመቆም የበኩላቸውን ድርሻ እየተወጡ እንደሆነ ተናግሯል፡፡

እስካሁን ሁለት ጊዜ በማሰባሰብ ለወረዳ 11 እና ለቀይ መስቀል ማስረከባቸውን የሚናገረው ወጣት ይድነቃቸው፣ የመጀመርያ ዙር ባስረከቡ ጊዜ ምን ያህል እንደሆነ ተመን ባለማውጣቱ ምክንያት አካሄዱ ላይ መዘናጋት ታይቷል ብሏል፡፡

አሁን ላይ የተሰበሰበው ግብዓት ምን ላይ እንደደረሰ ለማወቅ እንዲሁም ደግሞ የመከላከያ ሠራዊቱንም ሆነ ለተፈናቀሉ ወገኖች አለኝታ ለመሆን ግንባር ድረስ መሄድ እንደሚፈልጉ ለሪፖርተር አስረድቷል፡፡

በቀጣይም የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብሩን ለማከናወንና ከማኅበረሰቡም ታማኝነትን ለማትረፍ የተሰበሰበው ግብዓት የት ደረሰ? የሚለውን መከታተል የግድ መሆኑን ጠቁሟል፡፡

የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ሰዓዳ ኑር መሐመድ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአገሪቱ ላይ የተጋረጠውን ፈተና ለመወጣትና ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ወረዳው የድርሻውን እየተወጣ ነው፡፡

ለመከላከያ ሠራዊቱ ተደራሽ የሚሆኑ ግብዓቶችን ከመምህራን፣ ከጤና ባለሙያዎች፣ ከባለሀብቶች እንዲሁም ከአካባቢውን ማኅበረሰብ በባለቤትነት የድጋፍ ማሰባሰብ መርሐ ግብር ማከናወኑን ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ተናግረዋል፡፡

በበጎ ፈቃደኞችም ሆነ በተለያዩ ድርጅቶች የሚደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ ሥራ ላይ ሕገወጥ የሆነ ድርጊት እንዳይፈጸም ኮሚቴ መዋቀሩን የገለጹት ወ/ሮ ሰዓዳ፣ የርክክብ ሒደቱ ሲፈጸም ሆነ ወደ ግንባር ድረስ ሲሄድ የፋይናንስ ሥርዓትና መመርያን በጠበቀ መልኩ እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የሀብት ማሰባሰቢያ ሒደቱ ለአራተኛ ጊዜ መከናወኑን፣ ዓምናም በሁለት ዙር በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ላይ በዓይነትም በገንዘብም ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡

በሰሜኑ ክፍል በተነሳ ጦርነት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖችና መከላከያ ሠራዊቱን መልሶ ለማቋቋም በሦስተኛው ዙር በገንዘብም በዓይነትም እስከ አምስት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ግብዓቶችን መሰብሰብ መቻሉን አክለዋል፡፡

የድጋፍ ማሰባሰብ መርሐ ግብሩ ቀጣይነት ያለው ነው ያሉት ወ/ሮ ሰዓዳ፣ በወረዳው በኩልም ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው እየተንቀሳቀሱ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞች የራሳቸውን አስተዋጽኦ እየተወጡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በጎ ፈቃደኞቹ በዓይነት ከ700 ሺሕ በላይ የሚያወጡ ግብዓቶችን መሰብሰብ እንደቻሉ ከአምስት ሺሕ በላይ የሚሆኑ ወጣቶችም በወረዳ ሥር ሥልጠና ወስደው የአካባቢውን ፀጥታ እያስጠበቁ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የእምነት ተቋማትም በራሳቸው ተነሳሽነት ገንዘብ በማሰባሰብ ድጋፍ ማድረጋቸውን በቅርቡም አያንቱና ዋቅ የሚባሉ ቤተ እምነቶች 27 በሬዎችን ስምንት ሺሕ እሽግ ውኃ ለከተማ አስተዳደሩ ማስረከባቸውን አስታውሰዋል፡፡

በተለይም ለመከላከያ ሠራዊቱና ለተፈናቀሉ ዜጎች የጀርባ አጥንት በመሆን ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ አርሶ አደሮች ከ500 ሺሕ ብር በላይ ገቢ ማድረጋቸውን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከፊቷ የተደቀነባትን ፈተና ለማለፍ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንዳለበት እንዲሁም በበጎ ፈቃደኝነት ተሰማርተው የየአካባቢውን ፀጥታ የሚያስከብሩ ወጣቶች ምስጋና እንደሚገባቸው አስታውሰዋል፡፡

ከየካ ክፍለ ከተማ ከወረዳ ሰባት፣ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ከወረዳ ሦስትና ከሌሎች ወረዳዎች ጋር በቅንጅት እየሠራ የሚገኘው የዓለም ሽሮና ገበታ ሬስቶራንት ባለቤት  አቶ ፀጋ ፍቃዱ ለሪፖርተር እንደተናገረው፣ ጆርካ ኢቨንት ባዘጋጀው የአስቤዛ ባዛር ላይ ለመከላከያ ሠራዊቱ ድጋፍ በማሰባሰብ ተደራሽ ማድረግ ችለዋል፡፡   

 ድጋፉንም ከጆርካ ኢቨንት ከሰጣቸው ቦታ በተጨማሪ በአራት ቦታዎች ማለትም ፒያሳ አካባቢ በሚገኘው ጋዜጠኞች ሕንፃ፣ በ22፣ በሆሊዴይ ሆቴል አካባቢና ከአውሮፓ ኅብረት አጠገብ በሚገኘው እራካን ሕንፃ ድንኳኖችን በመጣል የአልባሳትና የአስቤዛ ድጋፍ እያሰባሰበ መሆኑን ተናግሯል፡፡

የጆርካ ኢቨንት ባዘጋጀው ባዛር ላይ ሸምተውና ተገበያይተው የሚሄዱ ሸማቾች ለመከላከያ ሠራዊቱና ለተፈናቀሉ ወገኖች ባላቸው አቅም ድጋፍ እንዲያደርጉ መደረጉን አቶ ፀጋዬ ገልጸዋል፡፡

በተለይም እንደ ከባድ ችግር እየታየ ያለው የሴቶች ንፅህና መጠበቂያ መሆኑን ይኼንንም ተደራሽ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን ገልጸው፣ ከማኅበረሰቡም የሚደረገው የድጋፍ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር ላይ በዓይነት ብቻ ተቀብለው እያስረከቡ እንደሚገኝ አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የማዳበሪያ አቅርቦትና ውጣ ውረዱ

በቅፅል ስሙ “The Father of Chemical Warfare” እየተባለ የሚጠራው...

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ የትርፍ ምጣኔውን ከ70 በመቶ በላይ አሳደገ

ከሁለቱ መንግሥታዊ ባንኮች መካከል አንዱ የሆነው የኢትዮጵያ ልማት ባንክ...