ሰላም! ሰላም! ሰላም ለአገራችን፣ ሰላም ለሕዝባችን ብለን ወጋችንን ብንጀምር መልካም ነው፡፡ ሰላም ከአልማዝና ከወርቅ በላይ በሆነበት በዚህ ዘመን፣ ሰላም ለሁላችንም ይሰፍን ዘንድ ፈጣሪ ይርዳን እላለሁ፡፡ ውዷ ባለቤቴ፣ “አልበር እንደ አሞራ ሰው አድርጎ ፈጥሮኝ…” እያለች ከጓዳዋ ሆና ታንጎራጉራለች፡፡ “ኧረ ማንጠግቦሽ ወፎች ረገፉ…” ብዬ መልሷን መጠበቅ ያዝኩ። አለ አይደል መዝፈንና መታወቅ፣ እልፍ ሲልም ቱጃር መሆን አሁን ቀላል እየሆነ ነው። አወይ የነፍስ ጥሪን አለማወቅ፡፡ እናንተዬ በደህናው የወጣትነት ድምፃችን የሠፈሩን ኮረዶችና ኮበሌዎች ‘ነይ!’ ‘ና!’ እያልን በጉልቤ ቅላጼ መውጫ መግቢያ ከምናሳጣ፣ ዘፍነን ቢሆን ኖሮ ዛሬ የት በደረስን ነበር? ለነገሩ አሁንም አልመሸም። አንዳንዶቹ እንደሚሉት ድምፅ ሳይሆን ድፍረት ሆኗል መታወቂያው። እኔ የምለው ቀደም ሲል የተዘፈነውን ዘፈን “ሪሳይክል” ማድረግ እስኪ አሁን ምን የሚሉት ነገር ነው? እንዴ እኔ የማውቀው የወዳደቁ ቆሻሻዎችን “ሪሳይክል” ማድረግን ነበር። ቆሻሻን እንደገና ለመጠቀምና ገንዘብ አመንጪ ለማድረግም ገና አሁን አይደል ዳዴ እየተባለ ያለው? አንዳንዱማ ዓይኑን በጨው እጥብ አድርጎ ራሷኑ ዘፈኑዋን እንደ ወረደች ይደግምና ግጥምና ዜማ የራሴው ይለናል። ብቻ ተውት፡፡ የእኔ አለመዝፈን ቁጭት የሚፈጥረው፣ “እኔ ነፍስ ሳውቅ ገንዘቤ ሲያልቅ’’ ብሎ ራሱ ላይ እንደ ተረተው ዓይነት ሲሆን ነው። ፀፀት እንዳይወርሰን ለየዕለቱ ክንዋኔያችን ዋጋ እየሰጠን እላለሁ። ሰላምም እንዲሁ!
“ምን ላድርግ እኔም ወግ አልደርሰኝ ሲል አሞራ መሆን አማረኝና ነው ያንጎራጎርኩት…’’ ብላ ማንጠግቦሽ መለሰችልኝ፡፡ ምን ለማለት ይሆን? እኔ እኮ ይህን ዳር ዳር መዞር ከማን እንደተማረች ሊገባኝ አልቻለም። ይገርማችኋል ብዙዎቹ የአገር መሪዎች በጥያቄው ወይም በጉዳዩ ላይ ማተኮራቸውን ትተው ጥግ ጥጉን ይዞራሉ ሲባል እሰማ ነበር። አሁን ቤቴ ድረስ ተከተለኝ እንዴ? ይህን አሰብኩና የማንጠግቦሽን ውሎ ማጥናት እንደሚኖርብኝ ማሰብ ጀመርኩ። ባልና ሚስት በፖለቲካ አመለካከት ሳቢያ የማይተማመኑበት ጊዜ ተመልሶ መጣ እንዴ ጎበዝ? ይህን ላነሳባት አሰኘኝና “ጠብ የሻተው መኮንን የዶሮ ሻኛ አምጡልኝ” ይላል ሲሆንብኝ ጊዜ ተውኩት። ሆ…ሆ… ደግሞ በገዛ እጄ ሰላሜን ልጣ? ኑሮአችን ውስጥ እንኳን ፖለቲካ ተጨምሮበት እንዲሁም ሆድ ያስብሳል፡፡ ሰላም ሁኑ!
“ማንጠግቦሽ ለምን አትዘረግፊውምና አትገላገይውም?” አልኳት ዙሪያውን መመላለስ ሰልችቶኝ፡፡ ”መብረር አማረኝ ነው የምልህ። እኔም በአውሮፕላን መንሸራሸር አማረኝ…” ብላኝ እርፍ አትል መሰላችሁ? ታየኝ እኮ አሁን ለእሷ የአውሮፕላን ቲኬት ስገዛና ሳዝናናት። አሁን በፈጠራችሁ በዚህ የኑሮ ውድነት በአውሮፕላን መብረር አማረኝ ብላ አንድ የደላላ ሚስት አስታወቀች ተብሎ ቢነገር፣ ሕዝባችን በዚህ ለአገር ስንት መስዋዕትነት በሚከፈልበት ጊዜ በማለት ሆ ብሎ ወደ ቤቴ ይዘምት እንደነበር በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። አሁንስ የማንጠግቦሽ ምኞት ነው ማቆሚያ መቀመጫ የነሳኝ። አንዱ ሐሜተኛ የነገር ጩቤውን እየመዘዘ፣ “እንኳን በአውሮፕላን በመንኮራኩር ወደ ጨረቃ ብትመጥቅ ምን ችግር አለባት? ባሏ እንደሆነ የሚውለው ሚሊዮኖችን ከሚያገላብጡ ዲታዎች ጋር ነው…” ይለኛል፡፡ እኔ የአገሩን መሬት በሙሉ የሸጥኩ ይመስል፡፡ እኔ አንበርብር ምንተስኖት ባልዋልኩበትና ባልፈጸምኩት አጉል ድርጊት በሐሜት ስሜ ሲጠፋ ታየኝ፡፡ ውስጡ ገብተው የሚዳክሩት ግን አይሰማቸውም፡፡ ያውም ለአረንጓዴ ሥፍራ የተከለለ መሬት በጠራራ ፀሐይ እየቸበቸቡ፡፡ ሰላም ጠፋ እኮ!
የአምሮቷን መነሻና ከበስተጀርባ ያለውን ፍላጎት ሳጠና ምናልባት በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ የሚያንዣብበውን ቦይንግ 787 ድሪምላይነር አውሮፕላን እንደሆነ ጠረጠርኩ። አዎ ያስጎመጃል፡፡ እንዲያውም ከዚህ ጋር አያይዘው አዛውንቱ ባሻዬ አንድ ጨዋታ አጫውተውኝ ነበር። ምን አሉኝ መሰላችሁ? “ኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ አውሮፕላን ሲበር የታየው ነሐሴ 12 ቀን 1921 ዓ.ም. ነበር። ይገርምሃል አባቴ ሲያጫውተኝ ከአሥር ዓመት በፊት ልዩ ልዩ ክፍሉ ተበታትኖ መጥቶ ሊገጣጠም ቢታሰብም፣ ወቅቱ ስላልፈቀደ ሳይሆን ቀርቷል…” እያሉኝ አባታቸው በልጅነታቸው ስላጫወቷቸው ትውስታዎች አወጉኝ። አቤት የዱሮ ሰው መቼም ጨዋታ አዋቂ እኮ ነው። የአየር መንገዳችን ትጋት ግን የሚደነቅ ነውና እኔ ደላላው አንበርብር ይህችን የነተበች ባርኔጣዬን አውልቄ እጅ ልነሳው እሻለሁ። በእንዲህ ዓይነቱ ታላቅ ግስጋሴ ላይ ያለው አየር መንዳችን የስኬቱና የዕድገቱ የጀርባ አጥንት ለሆኑት ሠራተኞችም የልፋታቸውን ያህል ያስብላቸው ዘንድ እንዲያስብበት ማሳሰብም ደግ ነው፡፡ የሥራ ሰላም ባለበት ነው ስኬት የሚኖረው!
እናም ቀስ አልኩና ከቤቴ ሾልኬ ወጣሁ፡፡ አምላኬ የማንጠግቦሽን ልብ እንዲጠብቅ ላሳስበው በማሰብ ከአቅራቢያችን ቤተ ክርስቲያን ጎራ አልኩ። ለካስ ሳላስበው ከሐዘንተኛ ሰዎች ጋር ተቀላቅዬላችኋለሁ፡፡ መቼም ሰው እያለቀሰ ዝም አይባል። እኔም አስነካው ጀመር። “ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው’’ እንደሚባለው ለማላውቀው ሟች ሆዴ እስኪገለባበጥ አነባሁ፡፡ ያዝ እንግዲህ ዋይ! ዋይ! በዚያውም ውስጤ የተከማቸውን ብሶት ዘረገፍኩት፡፡ አንዳንዴ እኮ በውስጣችን የታመቀው ቁጣና ብስጭት በእንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ መብረድ አለበት፡፡ ‹‹ሳቅ የደስታ ምንጭ ነው›› የሚባለው ስህተት እንደ መሆኑ መጠን፣ ለቅሶ የሐዘን መገለጫ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ለዚህ ነው እንዲህ እግረ መንገዱን ካጋጠመ ላይቀር ከአንጀት አንብቶ መገላገል ብዬ ያስነካሁት። ባልበላ አንጀታችን ሆነ እንጂ ሐሳቡ እንደማይከፋ እናንተስ መች አጣሁት ብዬ ነው? በዚህ ዘመን ደግሞ ስንቶች ንፁኃን አገር ለማፍረስ በተነሱ ወንበዴዎች ማለቃቸውንና ቀዬአቸው መውደሙን ሳስብ ዕንባዬ እንደ ጅረት ይወርዳል፡፡ ሰላም ሲጠፋ አልቃሹ ብዙ ነው!
ውስጤ ሲረጋጋ ስለሟቹ ማንነት ጠየቅኩ። እነሱ ባይገባቸውም ይህንን አጋጣሚ እንደ ውለታ ቆጥሬዋለሁ። ሟቹ ጠንካራ ሠራተኛና የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነበር አሉ። በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች ዕርዳታ አሰባስቦ ኃላፊነቱን ከተወጣ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመለስ፣ በመኪና አደጋ ምክንያት መሞቱን ስሰማ ልቤ ተሸበረ፡፡ ከመሞቱ በፊት የሰሜን ሸዋዎቹን አባትና ልጅ በጀግንነት መሰዋት ሰምቶ፣ “ምነው እኔም እንደ እነሱ ዕድለኛ ሆኜ ታሪክ በሠራሁ…” ብሎ ሲቆጭ እንደነበረ ሲነግሩኝ ይህ ሰውማ አልሞተም ብዬ ራሴን አፅናናሁት፡፡ ጎበዝ በዚህ ዘመን የምንሰማቸው የአገር ፍቅር ስሜቶች፣ ለመስዋዕትነት ራስን ዝግጁ ማድረግ፣ ፅናት፣ የመንፈስ ጥንካሬ፣ እምነትና በአጠቃላይ ከራስ በፊት ለወገን ማለት ያስደምማሉ፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት የክፉ ጊዜ ደራሾች ያሉዋት ድንቅ አገር ናት፡፡ አቦ ሰላሟ ይብዛ!
ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው አይደል? እነዚህ አገር ለማፍረስ የተነሱ ወንበዴዎች ያዘጋጁልን ሥርዓት ተማሪዎች ከእነ ዩኒፎርማቸው ሲጋራና ጫት እንደ ብስኩት ሲገዙ፣ በትምህርት ሰዓታቸው ሥራ እንደሌለው ሰው ካፌ ተጎልተው ሲያጨሱ በአያገባንም ስሜት ዓይተን እንድናልፍ ያደነዘዘን መሆኑን መቼም አንረሳውም፡፡ ሁሉንም ታዳጊ እንደ ራስ ልጅ እንዳናይ ድንዛዜ ውስጥ እንድንገባ እንደተደረገ እግዜር ይወቀው። ትውልዱን ለማነፅ ኃላፊነት ያለባቸው ወላጆችና መምህራን ብቻ ሳይሆኑ ሁላችንም መሆን ሲገባን፣ በራስ ወዳድነት ስሜት ታጥረን ጥቅማችንን ስናባርር ትውልዱን መረዝነው፡፡ ልጆቻችንን እኛው ከንቱ አድርገን መልሰን መኮነኑ ምን ፋይዳ ይኖረዋል ሲባል፣ “ጎመን በጤና” እያልን ማኅበራዊ መስተጋብራችንን ለማፍረስ ድንጋይ አቀበልን፡፡ ይህ አልበቃ ብሎን ፍርኃታችንን ለመሸፈን አልኮል እየተጋትን በይመሻል ይነጋል አስተሳሰብ ውስጥ ተደበቅን፡፡ ልጆቻችንን አጥር ውስጥ ደብቀን በሌሎች ልጆች መክኖ መቅረት ተሳለቅን፡፡ አገራችንን ሰላም አሳጥተን የህሊና ሰላም አጣን፡፡ ሰላም ሆይ ዋጋሽ ስንት ይሆን!
እጅግ በጣም ከማከብረው ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ሐሳብ ስንለዋወጥ የነገረኝን ላጫውታችሁ። “ይገርምሃል እኛ አገር ሥራዎች በሙሉ ያሉት ከታች ነው። ግን ሁላችንም ራሳችንን ዝቅ ማድረግ አንወድም። ከታች ያሉት ካልሠሩ የላይኛው አይፀናም። መሠረቱ ነው ወሳኙ። ለምሳሌ በአገሪቱ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚሳተፉ በሙሉ የሚያነሱዋቸው ነጥቦች በከፍተኛ ደረጃ ያሉትን ጉዳዮች እንጂ፣ መሠረታዊውን ጉዳይ አይመለከቱም። ኅብረት መልካም ነገር ነው። ነገር ግን ኅብረት የሚያስፈልገው ትልቅ ተራራ ለመግፋት ወይም ቋጥኝ ለማንከባለል ብቻ አይደለም። ትንሽ የሚመስሉ ነገር ግን ውስብስብ የሆኑ ጉዳዮችም መተባበርን ይሻሉ…” አለኝ፡፡ እሱ ከነገረኝ ግማሹ ብቻ ቢገባኝም ከታች ወደ ላይ ያላትን ነገር ወድጄለታለሁ። እውነትም ሥራችን እኮ ከላይ ከላይ እንጂ ጥልቀት ያለው አይደለም። ለዚህም አይደል እንዴ አገር አፍራሾች በሐሰተኛ ወሬና በፕሮፓጋንዳ እያሸበሩ፣ በሌላቸው አቅም ተቆልለው ሲያፍረከርኩን የሰነበቱት፡፡ ሰላማችንን በሐሰት ቀምተው ላያችን ላይ ሊቆለሉ የነበሩት እኮ እኛ በቅርበት ሆነን ስላልተጠናከርን ነው፡፡ ሰላም የሚሰፍነው አንድ በመሆን ብቻ ነው!
ምሁሩ የባሻዬ ልጅ አንድ አስገራሚ ጉዳይ ነገረኝ፡፡ “አንበርብር ማንጠግቦሽ በአውሮፕላን መብረር ቢያምራት አይግረምህ…’’ አለኝ፡፡ ፈጠን ብዬ፣ “እንዴት?’’ አልኩት፡፡ “አየር መንገዱ በዓለም ዙሪያ በጣም የሚያስቀና ስኬት የተጎናፀፈ ነው፡፡ ለራሱ የፈጠረውን የገጽታ ግንባታ አገሪቱ ሞዴል ብታደርገው ጥሩ ነበር፡፡ ከአየር መንገዱ በስተቀር እስቲ አንድ የረባ ድርጅት ጥራልኝ፡፡ በዓለማችን ቁጥር አንድ ከሚባሉት ተርታ ተሠልፎ በሽልማት ለምን እንደሚንበሸበሽ ለማወቅ ብትሞክር ስኬቱ ምን እንደሆነ ይገባሃል፡፡ በአፍሪካ በአስተማማኝ አትራፊነት ቁጥር አንድ ነው፡፡ ለረጅም ዘመናት ያለ በአመራሮቹና በሠራተኞቹ የተቀናጀ ጥረት ስለሚመራ የአፍሪካ የኩራት ምንጭ ሆኗል፡፡ በእዚህ ደረጃ የሚጠራ አንድ ኢትዮጵያዊ ድርጅት እስቲ ጥራልኝ…’’ ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ተረጋግቼ ማሰብ ሳይኖርብኝ አይቀርም፡፡ ለዚህ ደግሞ የአዕምሮ ሰላም ያስፈልጋል!
“አንበርብር ራዕይ ያለው አገር ማደግ ያለበት በዚህ ዓይነት አካሄድ ነው…’’ ብሎ ቆም ሲል አንገቴን ቀና አደረግኩ፡፡ “ራዕይ አልባ ነን ማለት ነው?’’ በማለት ጥያቄ አቀረብኩ፡፡ በየቦታው ራዕይና ተልዕኮ የሚሉ ታፔላዎችን የለጠፉ መንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ለምን አይታሰቡም በማለት፡፡ “አንበርብር የምን ማደነጋገር ነው? ከመፈክር ባለፈ ውጤት የማይታይበትን ወሬ ተወው…’’ ሲለኝ እንደገና ደነገጥኩ፡፡ “እናስ?’’ አልኩት ዓይኖቼ ፈጠው፡፡ “አንበርብር ዘመኑ የውድድር ነው፡፡ ውድድርን ታሳቢ ያላደረገ ራዕይ አልባና ውጤታማ ያልሆነ ጉዞ በጨለማ ውስጥ መደናበር ነው፡፡ የአገሪቱ አየር መንገድ የፈነጠቀውን የራዕይ አቅጣጫ መሠረት ያደረገ ግስጋሴ መጀመር እንጂ፣ በእንቶ ፈንቶ የታጀለ አጉል ወሬ ምን ይበጃል? አንበርብር ለኑሮህም ለአገርህም ራዕይ ይኑርህ፡፡ ይህ ራዕይ የይስሙላ ሳይሆን በዕቅድ ላይ ይመሥረት፡፡ አለበለዚያ የገበቴ ውኃ ይመስል የሚዋልል ነገር ተሸክሞ አራንባና ቆቦ ሲረግጡ መዋል ለማንም አይጠቅምም፡፡ ጠቃሚው ነገር ደረትን ነፋ፣ አንገትን ቀና አድርጎ አቅዶ መሥራት ነው፡፡ ከአገር አልፎ በዓለም አቀፍ ደረጃ አስመኪ የሆነ ዝና ማግኘት የሚቻለው ጠንክሮ በመሥራትና ሰላማዊ የሥራ ድባብ በመፍጠር ነው…’’ እያለ ሲመክረኝ ውስጤ ረሰረሰ፡፡ የእናንተም ውስጣችሁ በሰላም ይረስርስ፡፡ ሰላም ዋጋው አይተመንምና ለሰላም እንትጋ፡፡ መልካም ሰንበት!