Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየተፈናቃዮች ጉዳይ በጎ ከማድረግ ባሻገር

የተፈናቃዮች ጉዳይ በጎ ከማድረግ ባሻገር

ቀን:

የአገር ውስጥ መፈናቀል ዓለም አቀፍ ችግር ነው፡፡ ሰዎች በተፈጥሮም ይሁን በሰው ሠራሽ አደጋ ከቀዬአቸው ይፈናቀላሉ፡፡ ከተፈናቀሉት ውስጥ በመልሶ ማቋቋም ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱ እንዳሉ ሁሉ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በተሰደዱበት አካባቢ ለምደው እዚያው የሚቀሩም አሉ፡፡

በዓለም እስከ ሰኔ 2021 ድረስ ብቻ 57 ሚሊዮን ያህል ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡ 59 አገሮችም የአገር ውስጥ መፈናቀል አስተናግደዋል፡፡ 48 ሚሊዮን ያህሉ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉት በግጭት ምክንያት ነው፡፡ ቀሪዎቹ ደግሞ በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ ከቀዬአቸው የተሰደዱ ናቸው፡፡

ይህ መፈናቀል ታዲያ በራሳቸው በተፈናቃዮቹም ሆነ ተፈናቅለው በተሰደዱባቸው አካባቢ ነዋሪዎች ላይ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ሰብዓዊ ቀውስ ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ይህም በሁሉም በግጭትም ሆነ በተፈጥሮ አደጋ የተፈናቀሉ ዜጎች ባሉባቸው አገሮች የሚያጋጥም ክስተት ነው፡፡ በመሆኑም የየአገሮቹ መንግሥታት፣ ማኅበረሰቡ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሌሎች አገሮች፣ የአገር ውስጥ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና በጎ ፈቃደኞች ተፈናቃዮችን ለመርዳት ርብርብ ሲያደርጉ ይታያሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የኢትዮጵያም ሁኔታ ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በኢትዮጵያ በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ሰዎች ይፈናቀላሉ፡፡ በተለይ ከሦስት አሠርታት በፊት ጀምሮ በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ዓመታት እየቆጠረ በሚፈጠረው ድርቅና በልማት ሳቢያ ከቀዬአቸው ሲፈናቀሉ ማየት ተለምዷል፡፡ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ምላሽ እየተሰጠ ወደ ቀዬአቸው የመመለስ ሥራ በመሠራቱ እንጂ በጎርፍና በአካባቢያዊ ግጭትም በርካቶች ከቀዬአቸው ተሰደው ያውቃሉ፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በአካባቢያዊ ግጭትና በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ባለው ጦርነት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡ አካባቢዎቹ ወደ ተረጋጋ ሰላምና ፀጥታ እስኪመለሱም ተፈናቃዮች ባሉበት ሆነው የተለያዩ ድጋፎችን ከመንግሥትና ከተለያዩ አካላት ያገኛሉ፡፡ ይህ ግን ጊዜያዊ መፍትሔ እንጂ ዘላቂ አይደለም፡፡

በመሆኑንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ኅብረት  (ኢሰመድኅ) ሰሞኑን የተከበረውን የሰብዓዊ መብት ቀን አስመልክቶ የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ከተባባሪዎቹ ጋር አዘጋጅቷል፡፡ ከነዚህ መሀል አንዱ ለአገር ውስጥ መፈናቀል ዋናው ምክንያት ምንድነው? ተፈናቃዮችና የሰብዓዊ መብት ጉዳይ፣ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚናና በተፈናቃዮችና በአካባቢው ማኅበረሰብ መካከል ግጭት እንዳይፈጠር ምን መሠራት አለበት የሚለው ይገኝበታል፡፡

በውይይቱ ላይ ሐሳብ ካቀረቡት አንዱ በአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ድጋፍ ሥነ ዜጋና የመራጮች ትምህርት እንዲሁም የአካታችነት የሕግ ባለሙያ ሽመልስ ሲሳይ (ዶ/ር)  ናቸው፡፡ መሥሪያ ቤታቸውን ወክለው ሳይሆን እንደ ሕግ ባለሙያነታቸው በአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ዙሪያ ለሪፖርተር ቃለ መጠይቅ ሰጥተዋል፡፡

ዶ/ር ሽመልስ እንደሚሉት፣ ዓለም አቀፍ ክስተት የሆነው የአገር ውስጥ መፈናቀል በኢትዮጵያም ተከስቷል፡፡

በ59 አገሮች ውስጥ የሚገኙ 57 ሚሊዮን ያህል ሰዎች በዓም አቀፍ ደረጃ መፈናቀላቸውን ያስታወሱት ሽመልስ (ዶ/ር)፣ ከእነዚህ ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ0 እስከ 24 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶች መሆናቸው የመፈናቀል ሰለባ የሚሆኑት የኅብረተሰብ ክፍሎች እነማን እንደሆኑ ያሳየናል ብለዋል፡፡

ድንገት በሆነ ምክንያት ላልታወቀና ላልተወሰነ ጊዜ ከቤት መውጣት፣  የሚደረስበት ቦታ እስኪደረስ ባለውና መጠለያ ተብሎ በተዘጋጀ ቦታ ባእስኪደረስ ባሉ ሒደቶች የሚደርሱ ዘርፈ ብዙ ስቃዮች በአብዛኛው ማን ላይ እንደሆኑ የተፈናቃዮች የዕድሜ ክልል ያሳያል፡፡

እንደ ሕግ ባለሙያው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ ነገር የለም፡፡ በተለይ ከግጭት ጋር ተያይዞ ነገሮች ወዲያው ስለሚቀያየሩ የየአካባቢው ኅብረተሰብ የሚሸሽበትና መልሶ ቀዬው የሚገባበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በመሆኑም ይህን ያህል ሰው ከቀዬው ተፈናቅሏል ለማለት የሚያስችል የተረጋገጠ መረጃ ለማግኘት አሁን ላይ ያስቸግራል፡፡ ነገር ግን እስከ ሐምሌ 2013 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ የሕፃናት አድን ድርጅት ዩኒሴፍ ባጠናቀረው መረጃ መሠረት አራት ሚሊዮን ያህል የአገር ውስጥ ተፈናቃይ በኢትዮጵያ አለ፡፡ ይህም በአገር ውስጥ ግጭት በሚታወቁት ሶሪያና ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ካሉት የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥር በልጦ ይገኛል፡፡

የአገር ውስጥ መፈናቀል በኢትዮጵያ ሪፎርም ከተጀመረበት ከ2010 ዓ.ም. ወዲህ እየበዛ ይምጣ እንጂ ከዚህ በፊትም በድርቅ፣ በጎርፍና በተፈጥሮ ሀብት ይገባኛል ምክንያት በማኅበረሰብ ውስጥ በሚፈጠሩ ግጭቶች፣ አልፎ አልፎ ከዘርና ጎሳ ጋር ተያይዞ በደቡብ፣ በኦሮሚያ፣ በሶማሌ፣ በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉልና ጉሙዝ ክልሎች መፈናቀሎች ገጥመዋል፡፡

በጉልህ ባይነገርም ከልማት ጋር ተያይዞ በተለይ በከተማ ውስጥ መፈናቀል ነበር፡፡ ከዓምና ወዲህ ግን ለየት ያለ የአገር ውስጥ መፈናቀል ገጥሟል፡፡

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ቀድሞ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ወደ ጦርነት የተቀየረው ክስተት እንደ አገር የተፈተንበት ነው እንደሚሉት ሽመልስ (ዶ/ር) አገላለጽ፣ ይህ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎች ከቀዬአቸው ተፈናቅለው መጠለያ ካምፕ እንዲገቡ በተለይ ሰኔ 2013 ዓ.ም. ላይ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ዕርምጃ ከወሰደ በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው የሕወሓት ኃይል ወደ አማራና አፋር ክልል ያደረገው መስፋፋትና ወረራ ችግሩን አባብሶታል፡፡ ይህን ተከትሎ በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ፣ በአፋር አምስት ወረዳዎች፣ በደቡብ  ጎንደርና በሰሜን ጎንደር በኋላ ላይ ደግሞ ጉዳዩ በአጭሩ ተቋጨ እንጂ እስከ ሰሜን ሸዋ ድረስ የተስፋፋው ግጭት በርካታ ዜጎች ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉና መጠለያ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከዚህ ቀደም በድርቅና በሌላም ምክንያት ከአካባቢያቸው ተፈናቅለው በሌላ አካባቢ የሠፈሩና እዚያው በሠፈሩበት ዓመታትን አስቆጥረውና መደበኛ ኑሮ ጀምረው ከሚኖሩ ውስጥ ጥቃትና ግድያ የሚፈጸምባቸው ስለመኖሩ አሁን ላይ አንዱ የመፈናቀል አሉታዊ አጀንዳ ሆኗል፡፡ አሁንም በጦርነት ምክንያት የተፈናቀሉና በሌላ አካባቢ የሠፈሩ ዜጎች ጊዜ በጨመረ ቁጥር ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር ግጭት ውስጥ እንዳይገቡ ምን መደረግ አለበት ስንል የጠየቅናቸው ሽመልስ (ዶ/ር) የሚከተለውን ብለውናል፡፡

በዓለም አቀፍ ሕግና በቅርቡ በአፍሪካም በወጣው ‹‹የአፍሪካ ኮንቬንሽን ኦን ዘ ራይትስ ኤንድ ፕሮቴክሽን ኦፍ አይዲፒስ›› ሰነድ የአገር ውስጥ መፈናቀልን ከስደተኛ በተለየ መልኩ በአገራቸው ውስጥ ከሚኖሩበት ቀዬ ባልፈለጉት፣ ባላሰቡት፣ እነሱ ባልወሰኑት ሰው በሠራሽና ተፈጥሯዊ ምክንያት አካባቢያቸውን ለቀው ወደ ሌላ ቦታ ለመሄድ ተገደዱ እንጂ ዜጎች ናቸው ይላል፡፡

በመሆኑም በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና በሌሎች ሕጎች መሠረት እነሱን የመጠበቅ፣ የሚያስፈልጋቸውን ማሟላት፣ ለዘርፈ ብዙ ጥቃቶች እንዳይጋለጡ የመከላከል ግዴታ የመንግሥት ሆኖ ይቀጥላል፡፡

መፈናቀል በባህሪው ጊዜያዊ ነው፡፡ ሆኖም አሁን ባለንበት ሁኔታ ባሉ ሕጎች የአገር ውስጥ ተፈናቀዮች በተፈናቀሉበት ሥፍራ ስለሚቀዩበት ጊዜ የተቀመጠ ነገር የለም፡፡ ጊዜያዊ የሚለው ግን ለምን ያህል ጊዜ እንደሆነ አይታወቅም፡፡ ይህ የሚወሰነው እንደ ሁኔታው ነው፡፡ ለመፈናቀሉ ምክንያት የሆነው ችግር ሲስተካከል ይመለሳሉ የሚል ግምትን የያዘ ነው፡፡

በመሆኑም ተፈናቃዮች ባሉበት ቦታ ለምደው የሚቀሩበት ሁኔታ አለ፡፡ ለዚህ ሶማሌ ክልል የሚገኘውን መጠለያ ካምፕ ማንሳት ይቻላል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት በነበረ ግጭትና የተፈጥሮ አደጋ የተፈናቀሉ ዜጎች እንዲሰፍሩበት የተደረገ መጠለያ አሁን ላይ ራሱን የቻለ ከተማ ሆኗል፡፡ በሥፍራው ሱቅ፣ ባንኮችና ሌሎች አገልግሎቶች አሉ፡፡ ከተፈናቃዮች ካምፕነት ወደ ነዋሪዎች መሥፈሪያነት ተቀይሯል፡፡

ይህንን መንግሥት አስፈላጊውን መሠረተ ልማት እንዲሟላና ሌሎች የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መብቶቻቸው ተሟልቶ ወደነበሩበት እንዲመለሱ የማድረግ ኃላፊነት ነው፡፡ ከዚህ ጎን ለጎን በማኅበረሰብና በዓለም አቀፍ ተቋማት የጋራ ትብብርና ጥረት መሠረታዊ የመማር፣ የጤና፣ ሠርቶ የመኖር፣ ገቢ አግኝቶ ራስን የማስተዳደርና ሌሎች ዘርፈ ብዙ መብቶቻቸው እንዲሟላ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

ሰዎች ከአካባቢያቸው ለመፈናቀል ምክንያቱ ግጭት ወይም የተፈጥሮ ምክንያት ቢሆንም፣ ሄደው በሚሰፍሩበት ቦታ የአካባቢው ነዋሪዎች ስላሉ አዲስ የኅብረተሰብ ክፍል ሲቀላቀል የሀብት ውስንነት ይገጥማል፡፡ ነገር ግን ካለው ኅብረተሰብ ጋር አስማምቶ ባህላቸውን፣ እምነታቸውንና ቋንቋቸውን አስተሳስሮ በትብብርና በአንድነት የሚኖርበትን ማመቻቸት የመንግሥትና የሁሉም ባለድርሻ አካላት ዋነኛ ሚና ነው፡፡ ከዚህ ጋር የሚቃረኑ አሠራሮች ካሉ ማረምና ማስተካከል ያስፈልጋል እንጂ ከአንድ አካባቢ ከ20 እና ከዚህ ዓመት በላይ የኖረን ሰው እንደ ተፈናቃይ እየቆጠሩ መኖር አይቻልም፡፡

መፈናቀል ጊዜያዊ መፍትሔ እንደሆነ ያስታወሱት ሽመልስ (ዶ/ር)፣ ሆኖም ዜጎች በየትኛውም ክፍል ሄደው ከመኖርና ከመሠራት ጋር መያያዝ ይገባዋል ብለዋል፡፡ ተፈናቃይ መሆንን ሳይሆን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የትም ቦታ ሄዶ መሥራት፣ መኖር፣ አገልግሎቶችን ከአድሎ በፀዳ መልኩ አግኝቶ መኖር እንደሚቻል ማሳየት ያስፈልጋል፡፡

እንደ ሽመልስ (ዶ/ር) ተፈናቃዮችን ወደ መጡበት አካባቢ የመመለስ መርሐ ግብር ሲከናወን ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡ አንዳንዴ ከፍላጎት ውጭ የሚመለሱበት ሁኔታ ሊጤን ይገባል፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ከአካባቢያቸው በግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ችግሩ አስተማማኝ መፍትሔ ሳያገኝ መልሶ በቀዬው ማቋቋም አይገባም፡፡ አመላለሱም በተፈናቃዮች ፈቃድ ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት፡፡

ለሕይወታቸው፣ ለንብረታቸውና አካላዊ ደኅንነታቸው ዋስትና የሚሰጥ መሆን አለበት፡፡ አስፈላጊው መሠረተ ልማትና ሌሎች መሠረታዊ ፍላጎቶች መሟላትም አለባቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ለሚዲያና ለፖለቲካ ፍጆታ ዘለቄታዊ መፍትሔ ሳያስቀምጡ ተፈናቃዮችን  በችኮላ በአስተዳደራዊ ውሳኔ ብቻ ወደ ቀዬአቸው መመለስ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ ተፈናቃዮችንም ዳግም ለሰብዓዊ መብት ጥሰት ያጋልጣል፡፡

በመፈናቀል ጊዜ ዘርፈ ብዙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ያጋጥማሉ ያሉት ዶ/ር ሽመልስ ለዚህ በቀዳሚነት የሚጋለጡት ደግሞ ሴቶችና ሕፃናት ናቸው፡፡ ለመደፈር፣ ለረሃብ፣ ለከባድ የጤና እክል፣ ላልታወቁ ኃይሎች ጥቃት የመጋለጥ ዕድል፣ ለመጥፋትና ለሌሎች ስቃዮችን የመጋለጥ ዕድላቸውም ሰፊ እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ በመሆኑም ከመፈናቀላቸው በፊት፣ ተፈናቅለው መዳረሻቸው እስኪደርሱና መጠለያ ከገቡ በኋላና ባላቸው የቆይታ ጊዜ ሁሉ ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡

ለዚህ ደግሞ ግንዛቤ መፍጠር ወሳኝ ነው፡፡ እስከ ዛሬ በነበርንበት አካሄድ የተፈናቃዮች ጉዳይ የችሮታ ወይም የበጎ አድራጎት ወይም ለዕውቅናና ለምስጋና ተደርጎ ብቻ መታየት የለበትም፡፡ ተፈናቃዮችን መርዳት የመብት ጉዳይም ነው፡፡

ለተፈናቃይ ምን ይደረግ? ሲባል ሰብዓዊ ድጋፍን ብቻ ያማከለ ነው፡፡ የሰብዓዊ መብት ድጋፍን በደንብ አይዳስሰውም፡፡ ስለሆነም ሕጎቻችን፣ ሕጎችን ለማስፈጸም የሚቋቋሙ ተቋማት ለሕጎቹና ተቋማቱ መሠረት የሆኑት ፖሊሲዎች መቀረፅ ያለባቸው የትኛውም የአገር ውስጥ ተፈናቃይ በአገር ውስጥ በተከሰተው ተፈጥሯዊም ሆነ ሰው ሠራሽ ምክንያት ከለመደውና ኑሮዬ ብሎ ሕይወትን ከጀመረበት ቀዬ ሳይፈልግ ሲፈናቀል ከሰብዓዊ ድጋፍ ጎን ለጎን ሰብዓዊ መብት ጥበቃንም አካተው ነው፡፡

መፈናቀሉ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ አንድምታ ስላለውና በተለይ ከተቀባይ ማኅበረሰቡ አካባቢ ላይ የሕዝብ ቁጥር ስለሚጨምር፣ ኑሮ ስለሚወደድ፣ የፍጆታ እጥረት ሊመጣ ስለሚችል ይህንን ታሳቢ አድርጎ መፍታት ይገባል፡፡ እንደ አገር ችግሩን መፍታት ይገባል፡፡

እንደ አገራዊ ችግር አገራዊ ምላሽ የሚፈልግ መሆኑን ለተቀባይ ማኅበረሰቡ ማስተማር፣ በዘርፍ ለሚንቀሳቀሱ መንግሥታዊም ሆኑ መንግሥታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩን በባለቤትነት የሚመሩት የመንግሥት አካላት ችግሩን በዚህ መልኩ መረዳት ያለባቸው ሲሆን፣ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ላይም በስፋት መሥራትን ይጠይቃል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...