Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ስፖርት‹‹በርካታ ብሔራዊ ቡድኖች በጀት የሚፀድቅላቸው በፓርላማ ነው›› አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ...

‹‹በርካታ ብሔራዊ ቡድኖች በጀት የሚፀድቅላቸው በፓርላማ ነው›› አቶ ባህሩ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ

ቀን:

የአሁኑ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ተረክቦ ወደ ሥራ ከገባ ሦስት ዓመት አልፎታል፡፡ በእነዚህ ዓመታት የተለያዩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ሲከውን ከርሟል፡፡ ባለፉት ዓመታት በፌዴሬሽኑ የተከናወኑ ሥራዎች አካል መሆን የቻሉና በተለያዩ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩ ባለሙያዎች አብረው ይነሳሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል በኢትዮጵያ መድን እግር ኳስ ክለብ ውስጥ በተጫዋችነት ያለፈውና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት እያገለገለ የሚገኘው አቶ ባህሩ ጥላሁን አንደኛው ነው፡፡ ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የጀመረው የትምህርት ጉዞው፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዘልቆ፣ በጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቋል፡፡ ከጋዜጠኝነት ጎን ለጎን በእንግሊዝኛ ቋንቋና በአመራርነት ዲግሪ አግኝቷል፡፡ ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ በመስማት በተሳናቸው ትምህርት ቤት በዳይሬክተርነት ሲያገለግል የቆየው አቶ ባህሩ በብሥራት 101.1 ኤፍኤም ሬዲዮ በስፖርት ጋዜጠኝነት ሠርቷል፡፡ በስፖርት ጋዜጠኝነት የጀመረው ጉዞ ማረፊያውን በብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አድርጎ፣ ከሕዝብ ግንኙነት ወደ ጽሕፈት ቤት ኃላፊነት በማሳደግ በ2010 ዓ.ም. ግንቦት ወር ላይ ፌዴሬሽኑን የተረከበው አዲሱን የሥራ አስፈጻሚ ተቀላቅሎ በጽሕፈት ቤት ኃላፊነት እያገለገለ ይገኛል፡፡ በእነዚህ ዓመታት በአዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ስለተከናወኑ አጠቃላይ ጉዳዮችና ለአፍሪካ ዋንጫ እየተደረገ ስላለው አጠቃላይ መሰናዶ ከአቶ ባህሩ ጋር ዳዊት ቶሎሳ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- ከስፖርት ጋዜጠኝነት ወደ አመራርነት የመጣህበትን አጋጣሚ አስታውሰን?

አቶ ባህሩ፡- አጋጣሚውን ያገኘሁት ‹‹አልፋ መስማት የተሳናቸው ትምህርት ቤት›› በዳይሬክተርነት እያገለገልሁ፣ በጊዜው በፋና 98.1 ኤፍኤም እግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ አዘጋጅ መሰለ መንግሥቱ ጋር ይሠራ የነበረው የቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ ኤርምያስ አሽኔ አማካይነት ነበር፡፡ ኤርሚያስ የወንድሙ ሠርግ ስለነበረበት፣ የዕለቱን ዝግጅት እንድሸፍንለት ጠየቀኝ፡፡ ያኔ እግር ኳስ በሬዲዮ ተመልከቱ የቀጥታ ጨዋታ ዝግጅት ከፋና ለቆ ወደ ራሱ ሬዲዮ ጠቅልሎ ሊገባ ስድስት ቀን ሲቀረው ነበር፡፡ የዕለቱን ዝግጅት ከሸፈንኩ በኋላ ከአዘጋጁ መሰለ ጋር መተዋወቅ ቻልኩ፡፡ ከዚያ ከፋና ለቀን ወደ ብሥራት ኤፍኤም ገባን፡፡ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በመስማት በተሳናቸው ትምህርት ቤት የዳይሬክተርነት ሥራዬንም ሳላቆም በሬዲዮ በስፖርት ጋዜጠኝነት በቋሚነት መሥራት ጀመርኩ፡፡ ሬዲዮ ላይ የአገር ውስጥ እንዲሁም የውጭ አገር ስፖርት ዝግጅቶችን ሳዘጋጅ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አካል ብሆን ምን ልሠራ እችላለሁ? የሚል ጥያቄ በውስጤ ይንሸራሸር ጀመር፡፡ በጊዜው ከፌዴሬሽኑ ጋር በተያያዘ በርካታ ትችቶች ይቀርቡ ነበር፡፡ እኔም ብሆን የማነሳቸውና ፌዴሬሽኑ ማሻሻል ያለበትን ነገር አነሳ ነበር፡፡ ግን በደፈናው የምተች ብቻ አልነበርኩም፡፡ ይልቁንም የመፍትሔ ሐሳቦችን ከማቅረብ ባሻገር፣ የፌዴሬሽኑ ኃላፊነት ባልሆነ ጉዳይ እየጠቀስኩ ከባልደረቦቼ ጋር አየር ላይ እከራከር ነበር፡፡ ከዚያ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ወደ አመራር መምጣቱን ተከትሎ፣ የፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ቦታ ክፍት ሆነ፡፡ ከዚያ የትምህርት መረጃዬን ካስገባሁ በኋላ ተቀባይነት አግኝቼ በ2011 ዓ.ም. የካቲት ወር ላይ ሥራዬን ጀመርኩ፡፡

- Advertisement -

ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የሕዝብ ግንኙት ኃላፊነት ከተረከብክ በኋላ ምን ያሻሻልከው ነገር አለ?

አቶ ባህሩ፡- እኔ ከመምጣቴ በፊት ዜና ተብሎ ለሚዲያው የሚሰጠው በኢሜይል ነበር፡፡ መረጃውም ይዘገይ ነበር፡፡ በበይነ መረብ ወይም በዌብ ሳይቱ ላይ መረጃ ቶሎ ቶሎ አይለጠፍም ነበር፡፡ እኔ እንደመጣሁ መጀመርያ መረጃ በኢሜይል እንዳይላኩ ማድረግ ነበር፡፡ ጥሪ እንጂ መረጃ በኢሜይል አይላክም፡፡ መረጃን አነፍንፎ የማግኘት የጋዜጠኛው ኃላፊነት ነው፡፡ ፌዴሬሽኑ መስጠት የሚፈልገው መረጃ ሲኖር ብቻ ነው ማሳወቅ የሚያስፈልገው፡፡ እኔ ወደ ሕዝብ ግንኙነት ከመምጣቴ በፊት ዌብሳይቱ ከሦስት ሺሕ ያልበለጠ ተከታይ ብቻ ነበረው፡፡ ቀድሞ ቲዊተር፣ ቴሌግራምና የተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ መዳረሻዎች አለንበት፡፡ ከዚያ በኋላ የማኅበራዊ ሚዲያችንን አድማስ እያሰፋን በመምጣት፣ መረጃዎቻችንን ቶሎ ቶሎ እያጋራን በመሄድ፣ በግል ከሚሠሩት የመረጃ ተቋማት ጋር በልጠን መፎካከር የቻልንበት አጋጣሚ ላይ ደርሰን ነበር፡፡ ከዚያም ባሻገር በተለያዩ ሚዲያዎች ላይ ፌዴሬሽኑንን የሚያመለክቱ ጉዳዮች በተሳሳተ መንገድ ሲቀርቡ እየተከታተልን ትክክለኛውን መረጃም ማቅረብ የጀመርንበትን ሒደት ፈጥረናል፡፡ አሁንም ከዚህ በተሻለ መጠን አሻሽለንና አዘምነን ለማቅረብ የሚያስችለንን አቅም ለመፍጠር ከተለያዩ የግራፊክስ ባለሙያዎች ጋር በጋራ እየሠራን እንገኛለን፡፡

ሪፖርተር፡- ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንና በሚዲያው መካከል ከፍተኛ መቃቃር ያለ ይመስል፣ ስድብ ቀረሽ ትችትና አስተያየቶች በሁለቱም ወገን ይቀርብ ነበር፡፡ አንተም በጋዜጠኝነት ሥራ ላይ እያለህ የዚህ አካል ነበርክ፡፡ ምንም እንኳ አንተ የምትጠይቅበት ጉዳይ ባይኖርም፣ ጋዜጠኛ መሆንና የፌዴሬሽኑ የሥራ አስፈጻሚ አካል መሆን ልዩነቱን እንዴት ትገልጸዋለህ?

አቶ ባህሩ፡- ቀድሞ ውጪ ሆነህ የምትተቸው ጉዳይና ውስጥ ሆነህ የምትመለከተው ጉዳይ ለየቅል ነው፡፡ ግን የፌዴሬሽኑ ዋነኛ ኃላፊነት ወይም ተጠቃሚነት እስከ ምን ድረስ ነው? የሚለውን ጉዳይ ሳጤነው፣ በጋዜጠኝነት ጊዜ የተቸሁበትን ወቅት ሳስብ እፀፀታለሁ፡፡ ጋዜጠኛው ውጪ ሆኖ የሚፈልገው መረጃ ላይ ብቻ ነው ትኩረት የሚያደርገው፡፡ ውስጥ ሆኜ ስመለከተው ደግሞ ፌዴሬሽኑ በማይመለከተው ጉዳይ ላይ ሲተች እንደነበር ተረድቻለሁ፡፡ ለምሳሌ በርካታ አገሮች ለብሔራዊ ቡድናቸው በጀት የሚያፀድቁት በፓርላማ ነው፡፡ ግን አንድም የሚዲያ አካል ፌዴሬሽኑ ለምን በመንግሥት ድጋፍ አይደረግለትም ብሎ ሲጠይቅ አይስተዋልም፡፡ ሌላው በፌዴሬሽን ውስጥ በኃላፊነት ማገልገል ከጀመርኩ በኋላ የተረዳሁት ሚዲያውና ፌዴሬሽኑ ተግባብቶ ቢሠራ የኢትዮጵያን እግር ኳስ ማሳደግ እንደሚችል ነው፡፡ ይኼ ማለት ፌዴሬሽኑ መተቸት ባለበት ጉዳይ ተተችቶና የሚጠቅመውን ወስዶ ለማለት ነው፡፡ በፊት የነበረው የሆነ አካል ለመምታት ታስቦና አንድ ርዕስ ተመርጦ ያንን አካል መተቸት ብቻ ነበር፡፡ አሁን በመጠኑም ቢሆን እየተሻሻለ መጥቷል፡፡ ግን አሁንም ቢሆን በቂ መረጃ ሳይዝ በግርድፉ በዘመቻ የሚተች አለ፡፡ ስለዚህ ሚዲያው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑን ግዴታ፣ ተጠያቂነትና ኃላፊነት እስከ ምን ድረስ ነው የሚለውን በደንብ አጥርቶ ተመልክቶ መተቸትና መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ከተረከበ ሦስት ዓመት አልፎታል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ቀድሞ ከነበረው ሥራ አስፈጻሚ በተሻለ የሠራቸው ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

አቶ ባህሩ፡- አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ኃላፊነት ከተረከበ በኋላ በርካታ ሥራዎችን መተግበር ችሏል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ዋና ዋና ተግባሮችን ለመጥቀስ፣ ለረዥም ጊዜያት ሲነሳ የነበረውን ሊጉን መተዳደር ያለበት በክለቦች ነው የሚለው ተጠቃሽ ነው፡፡ ለዚህም ጥያቄ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥቶ፣ ክለቦች ራሳቸው ሊጉን እንዲያስተዳድሩ ተደርጓል፡፡ በዚህም የክለቦች ጨዋታቸው በቴሌቪዥን የቀጥታ ሥርጭት እንዲኖራቸው ከማድረጉም በላይ፣ ዓመታዊ ገቢ እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ ፌዴሬሽኑ የማርኬቲንግ አሠራሩን በማሻሻል ከተለያዩ የንግድ ተቋማት ጋር የስፖንሰርሺፕ ስምምነት በመፈራረም የፋይናንስ አቅሙን ማሳደግ ችሏል፡፡ በዚህም መሠረት ፌዴሬሽኑ ከነበረበት የ16 ሚሊዮን ብር ዕዳ 12 ሚሊዮን ብር መክፈል ችሏል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከተቋቋመ 77 ዓመት በላይ ቢሆነውም፣ የራሱ የሆነ ቢሮ አልነበረውም፡፡ በአንፃሩ አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ፌዴሬሽኑ ባደረገው ጥረት የራሱ የሆነ ቢሮ እንዲኖረው አስችሏል፡፡ ላለፉት 11 ዓመታት የካፍ የልህቀት ማዕከል ዝግ ሆኖ ቢቆይም፣ አሁን ሥራ ጀምሮ ቀድሞ ብሔራዊ ቡድኑ ለማቆየት ለሆቴል ሲወጣ የነበረውን ወጪ መቀነስ ተችሏል፡፡ ሌላው የታዳጊዎችን ከሥር መሠረቱ ለማጠንከር፣ ከቻይናና ከእስራኤል ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድኖች ጋር በጋራ ለመሥራት ውል ማሰር ተችሏል፡፡ በከፍተኛ ውዝግብ ታጅቦ የዘለቀውን የብሔራዊ ሊግ ውድድር በአግባቡ እንዲካሄድ ያደረግንበት መንገድ ቀላል አይደለም፡፡ በሁሉም ክልሎች እንዲከናወኑ የተደረገው ከ15 ዓመት በታች የሙከራ የእግር ኳስ ፕሮጀክቶች ሥልጠና እንዲጀምር ተደርጓል፡፡ ከዚህ ቀደም ከ17 ዓመት በታች ውድድሮች በተፈለገው መንገድ ማከናወን ስላልተቻለ፣ በዓመቱ መጨረሻ በተመረጡ ከተሞች እንዲከናወን ተደርጓል፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ላይ የዕድሜ ማጭበርበር ትልቅ ችግር ነበር፡፡ አሁን ግን ፌዴሬሽኑ የራሱን የሕክምና ባለሙያ ቀጥሮ፣ ተመሳሳይ ችግሮች እንዳይፈጠር እየሠራ ይገኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ለውጡን ከዚህ እያየነው ነው፡፡ ከዚህም በላቀ ሁኔታ እግር ኳሱን ለማሻሻል የበለጠ ለመሥራት ዕቅድ ነድፈናል፡፡   

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ እግር ኳስ ቡድን ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ ማለፍ ችሏል፡፡ ከጥር መባቻ ጀምሮ በካሜሮን አስተናጋጅነት በሚከናወነው አፍሪካ ዋንጫ ጨዋታ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ እያደረገ ያለው ዝግጅት ምን ይመስላል?

አቶ ባህሩ፡- የአፍሪካ ዋንጫን በተመለከተ ፌዴሬሽኑ ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ አሠልጣኞቹ ቴክኒካል የሆኑ ነገሮችን ማለትም ተጫዋች መመልመል፣ ተጫዋቾቹ ከዚህ ቀደም የነበራቸውን የጉዞ ሒደት ማጣራት በተመለከተ ዝግጅት እያደረጉ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር የብሔራዊ ቡድኑ፣ ከተለያዩ የፕሪሚየር ሊግ ክለብ አሠልጣኞች ጋር እየመከሩ ይገኛሉ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ከአስተዳደራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡ ይኼም ብሔራዊ ቡድኑ ቅድመ ዝግጅት የሚያደርግበትን አገር፣ ከተቻለ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ወይም በምዕራብ አፍሪካ የወዳጅነት ጨዋታና ቅድመ ዝግጅት እንዲደረግ እየሠራን እንገኛለን፡፡ ብሔራዊ ቡድኑ ቢያንስ ሁለት የወዳጅነት ጨዋታ ለማድረግ እየጣርን እንገኛለን፡፡ በሁለቱ አኅጉራት ዝግጅት ማድረግ ካልተቻለ ደግሞ፣ ብሔራዊ ቡድኑ ቀድሞ በካሜሮን ዝግጅት ለማድረግ አቅደን እየሠራን እንገኛለን፡፡ ለዚህ ሁሉ ግን መንግሥት የሚለቅልን በጀት ይወስነዋል፡፡ ይኼ ሁሉ ዕቅድ ካልተሳካ ግን በአገር ውስጥ ዝግጅት ለማድረግ ሐሳብ አለን፡፡ ግን ቡድኑ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ አገር ተጉዞ ዝግጅት የሚያደርግበት ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች እየታዩ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ሒደት መንግሥት ያለበት የህልውና ሁኔታና ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዝግጅቱን ማጓተታቸው አልቀርም፡፡ ሆኖም ያለውን ነገር ለመንግሥት አሳውቀን ምላሽ እየተጠባበቅን እንገኛለን፡፡ ከታኅሣሥ 17 ጀምሮ ለብሔራዊ ቡድኑ ሽኝት ይደረጋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...