በመኮንን ዛጋ
ከዚህ ቀደም በዚሁ ጋዜጣ ላይ፣ ‹‹ብሔራዊ ውይይት ስንል ምን ማለታችን ነው?›› በሚል ርዕስ የብሔራዊ ውይይት ጽንሰ ሐሳብ መሠረታዊያንን በዝርዝር ለማስቀመጥ ሞክሬያለሁ፡፡ ይህ ጽሑፍ በወጣ ከሦስት ሳምንት ገደማ በኋላ መንግሥት አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ለማቋቋም የሚረዳ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በማርቀቅ፣ ለተወካዮች ምክር ቤት ሕግ ሆኖ እንዲፀድቅ አስተላልፏል፡፡ ይህም ረቂቅ አዋጅ ከእነ ውስንነቶቹ በጎ ጅምር መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡ የዚህ ጽሑፌ ትኩረት ደግሞ በጥቅሉ የብሔራዊ ውይይት መሠረታዊ መርሆዎች ላይ ነው፡፡
መርህ ስንል የድርጊት፣ የባህሪ፣ የአስተሳሰብ፣ የአወቃቀር ወይም የግምገማ መመርያ የሆነ ሐሳብ ወይም እሴት ማለት ሲሆን፣ ከሕግና ከዕሳቤ አንፃር ስናየው ደግሞ መርህ የሚባለው በማንኛውም የሁኔታ ማዕቀፍ ውስጥ መሆን ያለበት ወይም የሁነቱ አካላት ብዙውን ጊዜ መከተል ያለባቸው ደንብ ማለት ነው። ይኸውም የጉዳዩ ተካፋይ አካላት በሚፈለገው መልክና ሁኔታ ሊከተሉት የሚችሉት፣ ወይም የአንድ ነገር የማይቀር ውጤት ሊሆን ይችላል፡፡ በአጭር አገላለጽ መርሆ የሚባለው በሰፊው ማኅበረሰብ ዘንድ እንደ ተጨባጭ እውነት ተቀባይነት ያለው፣ እንዲሁም ለምክንያታዊነት ወይም ለአዎንታዊ ምግባር መሠረት ሆኖ የሚያገለግል መሠረታዊ አጠቃላይ ማዕቀፍ ነው፡፡
ስለሆነም ብሔራዊ ምክክሮች ወይም ውይይቶች ሊከተሏቸው የሚገቡና ለሁሉም አካላት በግልጽ መረዳትን የሚፈጥሩ መርሆዎች ሊኖሯቸው ይገባል። እነዚህ ለብሔራዊ ውይይት ክንውን ተዓማኒነት መፈጠር የሚጠቀሱ ቁልፍ መርሆዎች ናቸው፡፡
አካታችነት፣ ግልጽነትና ሕዝባዊ ሱታፌ፣ እምነት የሚጣልበት አወያይ/ሰብሳቢ አካል፣ ለተቋሙ ግልጽ ሥልጣንና በልኩ የተሰፋ ተገቢ መዋቅር፣ በአግባቡ የተሰናሰሉ ሕጎችና አሠራሮች መስጠት፣ የፖለቲካ አለመግባባቶችና የግጭት መንስዔዎችን ከሥር መሠረታቸው የሚዳስስ አጀንዳ መቅረፅና ተሳታፊዎች ከውይይቱ የተገኙ ውጤቶችን ወደ ትግበራ ለማስገባት የተስማሙበት ሥነ ዘዴ መርሆ ናቸው፡፡
እነዚህ ከላይ በአጭሩ የተጠቀሱት የውጤታማ አገር አቀፍ የውይይት የመርህ ምክረ ሐሳቦች አገራችን ካለችበት ነባራዊ ዓውዶችና ተለዋዋጭ ከሆነው የየግጭቶቹ መሠረታዊ ባህሪ ጋር መጣጣም እንዳለባቸው ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ እንዲሁም ብሔራዊ ውይይት ለቀጣዩ ፖለቲካዊ ሥርዓታችን መሠረታዊ ሁለንተናዊ ለውጥ፣ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ የሥልጣን ሽግግር፣ ለአገራዊ ሉዓላዊነትና የግዛት አንድነት መጠበቅ፣ ለዘላቂ ወንድማማችነትና አገራዊ ሰላም፣ እንዲሁም ለረዥም የጋራ ራዕይ ትርጉም ያለው አስተዋጽኦ ለማበርከት እንዲያስችሉት ካስፈለገ የሚከተሉትን መርሆዎች መጠበቅ አለበት፡፡
አካታችነት
ከዚህ ቀደም መሰል የአገራዊ ምክክር (ውይይቶች) ጉባዔ ያከናወኑ የበርካታ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ አካታችነት በብሔራዊ ውይይት የክንውን ሒደትም ሆነ ተጠባቂ ውጤት ረገድ ጉልህ የሆነ አዎንታዊ ሚና ያለው ቀዳሚውና አስፈላጊው መርሆ ሲሆን፣ በዚህም የአገሪቱ ጉዳይ ያገባናል ወይም ይገባናል የሚሉ ተሳታፊ ኃይሎች በውይይቱ አግባብነት፣ የሒደት ግልጽነትና ተተግባሪ ውጤት ላይ ለሚኖራቸው ማዕቀፋዊ ትምምን ወሳኝ መልህቅ ነው፡፡
ስለሆነም በአገራችን ዘላቂ ሰላም የሚያመጣ፣ የዜጎች ወንድማማችነትን የሚያጎለብትና የጋራ አገራዊ ራዕይ የሚሰንቅ፣ ፖለቲካዊ አለመግባባቶችንና ግጭትን ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በዘላቂነት ሊፈታ የሚችል፣ እንዲሁም የአገሪቱን አንድነት የሚያስጠብቅ ውጤታማ ብሔራዊ ውይይት ለማድረግ በሁሉም አካላት ዘንድ ቁርጠኝነት ካለ፣ ለሒደቱ ስኬታማነት በሚረዳ መንገድ በርካታ ባለድርሻ አካላትን ማሰባሰብ ይገባል፡፡
የውይይቱን ተግባራዊ የውጤት አቅም ከፍ በማድረግ የፖለቲካዊ አለመግባባቱንም ሆነ የኃይል ግጭቱን መሠረታዊ ገፊ ምክንያቶች (Real Drivers of the Conflict) ከመሠረቱ ለመፍታት ቅን መሻቱ ካለ፣ እውነተኛ አካታችነት ማለትም ሁሉም በአገሪቱ ጉዳይ ቁልፍ ፍላጎት ያላቸው ወካይ ግለ ሰብዕናዎች፣ ቡድኖች፣ ሴቶች፣ ወጣቶችና ሌሎችም በተለምዶ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ህዳግ የተገለሉ ቡድኖችን ጨምሮ እንዲሳተፉ መጋበዝ አለባቸው፡፡ ይህም የሥርዓተ መንግሥቱን የሥልጣን መሰላል ለመወጣጣት፣ በጦር ሜዳና በአመፅ ጉልበት በመፈታተሽ እንፈታለን የሚሉትንም የሚጨምር መሆን አለበት፡፡
በተጨማሪም የውይይት ሒደቱ ከመጀመሩ በፊት አካታች፣ ግልጽና በጋራ ምክክር ላይ የተመሠረተ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ማከናወን በቀጣይ እውነተኛ ብሔራዊ ውይይት በማካሄድ ሒደት ለሚኖረው ቅን ተሳትፎና የመግባባት ስሜት ጥልቅ መሠረት ይጥላል፡፡ ምክንያቱም በቅድመ ብሔራዊ ውይይት በውይይቱ ቅርፅ፣ ይዘትና ጥልቀት፣ እንዲሁም በአወያዩ አካል የአወቃቀር ቅርፅ፣ አቋም፣ ነፃነት፣ ገለልተኛነት፣ ተዓማኒነት፣ የችግር ቅርቃር ፈቺነትና አቻቻይነት ላይ የሚተላለፉ የመጀመርያ ውሳኔዎች፣ በተለይም ደግሞ እንዲሳተፉ የሚጋበዙ አካላት መጠንና ዓይነት እንደ ድኅረ ውይይቱ ውጤት፣ ሒደትና ግብ ያህል ጠንካራ የፖለቲካ መታገያ መድረክ ሊሆኑ ስለሚችሉ ነው፡፡ ስለሆነም እነዚህን ቅድመ ዝግጅቶች ሁሉንም ዋና ዋና የፍላጎት ቡድኖችን በሚያካትት መልኩ በሚዋቀር ከፍተኛ አዘጋጅ ኮሚቴ (Higher Order Preparatory Committee) አማካይነት፣ በጥንቃቄና በግልጽነት መርህ ተመሥርቶ ማድረጉ በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
ለአብነት ያህል የየመንን አገራዊ ህልውና ለማስቀጠልና የዜጎችን ሰቆቃና አስከፊ የእርስ በርስ ግጭትን ለማስወገድ በሚል፣ እ.ኤ.አ. በ2011 በተደረሰው የባህረ ሰላጤው የትብብር ካውንስል ስምምነት መሠረት ኃላፊነት የተሰጠውና የፕሬዚዳንት ዓሊ አብደላ ሳሌህን ከሥልጣን መነሳት ያመቻቸው የየመን ብሔራዊ ኮንፍራንስ (2013/14) ሰፋ ያለ የባለድርሻ አካላት፣ ግለሰቦችና ቡድኖችን በማካተቱ ረገድ ከፍተኛ ትኩረት የሚስብና እስካሁንም በጉልህ ተጠቃሽ ዓይነተኛ የውይይት መድረክ ነበር፡፡ ይኸው የብሔራዊ ውይይት ኮንፍረንስ ከባህላዊ የጎሳ መሪዎች፣ ከሃይማኖት አባቶችና ከፖለቲካ ልሂቃን ጎን ለጎን ወካይ ሴቶችንና ወጣቶችን በማካተት ወትሮ ከተለመዱት የየመን የፖለቲካ ሒደቶች በጉልህ ተጠቃሽ የአካሄድ ለውጥ በማድረግ ወሳኝ አካላትን በማሳተፍ፣ ሁሉም ሰላማዊና ታጣቂ ወገኖች እንዲወከሉ አስችሏል፡፡
ምንም እንኳን በኮንፍረንሱ መጀመርያ የቅድመ ዝግጅት ምዕራፍ ወቅቶች ላይ በእነዚህ ቡድኖች መካከል ያለው መስተጋብር የተዛባና ውጥረት የተሞላበት፣ አንዳንዴም ከአዳራሽ ውጪ በጦር ሜዳ ላይ ባላቸው የኃይል ድጋፍ በመተማመን እልህ የቀላቀለ የነበረ ቢሆንም፣ ባህላዊና ዘመናዊ ቁንጮ ልሂቃንን ማካተቱ ሁሉን ያሳተፈ ስለመሆኑ ለተጠቃሽ ውይይትነት እንዲበቃ ያስቻለ ነበር፡፡ እንዲሁም ውይይቱ ለወደፊቱም የሴቶች፣ የሲቪል ማኅበራትና የወጣቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎን ያማከለ ሰፊ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲከፈትም በጎ አስተዋጽኦ ሊኖረው ችሏል፡፡ በአጠቃላይ በብሔራዊ ውይይቱ እንዲሳተፉ 1/3ኛ ከፖለቲካ ቡድኖችና ሌሎች ተቋማት በምደባ ቀሪውን 2/3ኛ ደግሞ በቀጥታ የሕዝብ ምርጫ ተወክለው እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ የቱኒዚያው የብሔራዊ ውይይት መድረክ በጥቅሉ ሲታይ ተቃራኒ የፖለቲካ ኃይላትን ፊት ለፊት በማገናኘት ስምምነት ላይ እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ እንደ ተጠቃሽ ስኬት ቢገለጽለትም፣ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በምልዓት ያላካተተና ለሕዝብ ሁሉን አቀፍ ተሳትፎ በቂ ዕድሎችን ያልሰጠ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ምናልባትም በውይይቱ የተደረሰባቸው ስምምነቶች በወቅቱና በምሉዕ ባለመተግበራቸው የውይይቱን ሕዝባዊ መሻትና የሕጋዊ ቅቡልነት ገጽታ ያበላሸ ሊሆን ችሏል፡፡ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚቀርቡ ከቱኒዚያ ውጪ ያሉ የፍላጎት ቡድኖች እንደሚያመለክቱት፣ አንዳንድ ዜጎች ውይይቱን ሥር ነቀል ለውጥ ያላመጣ እንዲሁ ለፖለቲካዊ የሥልጣን ድልድል ብቻ የሚደረግ እንቅስቃሴ አድርገው ወስደውታል፡፡
ግልጽነትና ሕዝባዊ ሱታፌ
ይህ የብሔራዊ ውይይት ሁለተኛው አንኳር መርሆ ሲሆን፣ ውይይቱ ዋና ዋና የሚባሉትን ሁሉንም የፍላጎት ቡድኖች በምልዓት የሚያካትት ቢሆንም እንኳ ለምልዓተ ሕዝቡ በቂ፣ ወቅታዊና ተያያዥ መረጃዎችን ለመስጠትና ወደ ውይይቱ ቀልቡን ለመሳብ የሚያስችሉ በቂ የሱታፌ ዕድሎች ከሌሉ ሕዝቦች ለውይይቱ በድርጊትም ሆነ በዝምታ አዎንታዊ ተሳትፏቸውን ከመንፈጋቸውም በላይ፣ ማኅበረሰባዊ ቅቡልነትን የማሳጣት ከባድ አደጋ አለው፡፡ ለዚህም ነው ብሔራዊ ውይይት በአዳራሹ ውስጥ ካሉ ተወካዮች ባሻገር የሰፊውን ሕዝብ ተሳትፎ የሚያስተናግዱና የሕዝቡ የራሱነቱን ማበልፀጊያ ሥልቶች ሊኖሩት ይገባል የሚባለው፡፡
ስለሆነም መሠረታዊ የተባለውን የሰፊው ሕዝብ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በአካባቢያዊ መዋቅር ደረጃ የሚደረጉ የውይይት ሒደቶችን አጀንዳ በአገር አቀፍ ደረጃ ከሚካሄደው ብሔራዊ ውይይት ጋር በማስተሳሰር፣ እንዲሁም በተጓዳኝ በየወቅቱ ሕዝባዊ ምክክር በማድረግ፣ መረጃን በሚመለከተው ቃል አቀባይ አካል በተደራጀ መንገድ በመደበኛነት በማሠራጨትና ለማኅበረሰቡ በቀጥታ ተደራሽ በሆኑ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ሰፋፊ የዜና ሽፋን በመስጠት ሊከናወን ይችላል፡፡
ለአብነት በኬንያ እ.ኤ.አ. በ2004 በሕገ መንግሥቱ ማሻሻያ ላይ በተደረገው የቦማስ ስብሰባ ወቅት እንደነበረው ሁሉ በመድረኩ የሚታደሙ የሕዝብ ወኪሎች የየወቅቱን ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ አጀንዳዎች በመንተራስ ከሚወክሏቸው ቡድኖች ጋር በመደበኛነት ምክክር እንዲያደርጉ ሊፈቀድላቸው ይችላል፡፡
በተጨማሪ በሴኔጋል እ.ኤ.አ. ከ2008/09 በተካሄደው የብሔራዊ ውይይት ወቅት፣ ስለውይይቱ በቂ ግንዛቤ የሚያስጨብጡ አወያይ ቡድኖች ከእያንዳንዱ የሴኔጋል አካባቢያዊ አስተዳደር ግዛቶች፣ ነዋሪዎችና ገዥዎች ጋር ምክክር ያደረጉ ሲሆን፣ በዲያስፖራውም በኩል በፈረንሣይ፣ በአሜሪካና በካናዳ የሚኖሩ ዜጎች እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ ለሚደረገው ሕዝባዊ ምክክር የብሔራዊ ውይይቱ ተሳታፊ አባላት (ወይም ውይይቱን የሚመራው አካል ሴክሬታሪያት) የተገኘውን መረጃ የመተንተን አቅም መኖሩም አስፈላጊ ነው፡፡
እምነት የሚጣልበት አወያይ/ሰብሳቢ አካል
በአገራችን ፖለቲካ ውስጥ በዋነኝነት ከሚታዩ ያለ መግባባት መንስዔዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ጥርጣሬ የተዛባ ምልከታ (Fear and Perception) ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን (ግለሰቦች ወይም ቡድኖች) ዙሪያ መለስ ተሳትፎን ለማስጠበቅና ሊፈጠሩ የሚችሉ የአድሏዊነት አመለካከቶችን ለማስወገድ፣ በሁሉም አካላት ዘንድ ተዓማኒ ሰብሳቢ ወይም አወያይ አካል መሰየም ከሁሉም በላይ አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ሰብሳቢ አካል እንደ ሁኔታው አንድ ግለሰብ፣ የሰዎች ስብስብ፣ ተቋም ወይም የተቋማት ጥምረት ተደርጎ ሊወስድ ይችላል።
ይህ ሰብሳቢ አካል በተቻለ መጠን በአብዛኞቹ የአገሪቱ ዜጎችና ተወያይ ቡድኖች ዘንድ ተቀባይነት ያለውና የተከበረ መሆን ያለበት ሲሆን፣ ከሚከናወነው ውይይት ጋር ግልጽ የሆነ የጥቅም ግጭት የሚያመጡ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ መሻቶች ወይም ግቦች ሊኖሩት አይገባም፡፡ በቅርብ ጊዜያት በቱኒዚያና በሴኔጋል የተካሄዱት ብሔራዊ ውይይቶች በየሒደቶቹ ስኬታማነት የተመዘገበው በአብዛኛው በሰብሳቢዎቹ ተዓማኒነት በመሆኑ፣ አወያዩ አካል ለዚህ ስኬት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡
ለምሳሌ በቱኒዚያ (እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2014) ባሉት ጊዜያት በተካሄደው ብሔራዊ ውይይት ላይ አራት የሲቪል ማኅበራት፣ እነዚህም የቱኒዚያ አጠቃላይ የሠራተኞች ማኅበር፣ የቱኒዚያ የአሠሪዎች ማኅበር፣ የቱኒዚያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበርና የቱኒዚያ የሰብዓዊ መብቶች ሊግ ተጣምረው አንዳንዴም በተናጠል እንደ ሰብሳቢ አካላት ተሰይመው አገልግለዋል፡፡ እያንዳንዳቸው ማኅበራት ለረዥም ጊዜያት በማኅበረሰቡ ዘንድ በነበራቸው የሞራል ልዕልናና ሰፊ ሕዝባዊና የአባላት መሠረት፣ የእነዚህ ድርጅቶች ጥምረት በአብዛኛው የቱኒዚያ ሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተዓማኒነት ያለው ሆኖ የሚታይ ነበር፡፡
በሌላ በኩል በሴኔጋል እ.ኤ.አ. ከ2008/09 የተካሄደውን ብሔራዊ ውይይት ቀደም ሲል የዩኔስኮ ዋና ዳይሬክተር የነበሩትና በሴኔጋል ዜጎች ዘንድ በእጅጉ የተከበሩት ሴኔጋላዊው አማዱ ማህታር ኤም’ቦው በሰብሳቢነት መርተውታል፡፡ ሚስተር ኤምቦው በ87 ዓመታቸው መባቻ በሰብሳቢነት በመሩት ውይይት ታማኝ የሕዝብ አገልጋይ መሆናቸውን በማስመስከር የአገራቸውን ዜጎችና የተሳታፊ ጓዶቻቸውን ክብር እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን፣ በውይይቱ ሒደት የተገበሩት የአመራር ሥልታቸውም ለሒደቱ ከፍተኛ ሕጋዊ ቅቡልነት አበርክቷል፡፡
በተቃራኒው ደግሞ በሱዳን ውስጥ እስካሁንም ድረስ ለረዥም ጊዜያት ያለ ስኬት የሚንገታገተው የብሔራዊ ውይይት ሒደት በአሉታዊነቱ የሚጠቀስ አስገራሚ ተምሳሌት ነው፡፡ ብሔራዊ ውይይቱ እንዲካሄድ ለመጀመርያ ጊዜ ምክረ ሐሳብ ከቀረበበት እ.ኤ.አ. ጥር 2014 ጀምሮ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር እስከ ሥልጣናቸው መልቀቂያ ድረስ በዝግጅቱ ሒደቶች ውስጥ የላቀ ሚና ሲጫወቱ የቆዩ ሲሆን፣ ገና ከመነሻው ይህ ሒደት ለሁሉም ወገኖች ክፍትና ግልጽ ተሳትፎ እንዲኖራቸው አያስችላቸውም የሚል ጥርጣሬ አስነስቷል፡፡ በዚህም ምንም ዓይነት ስኬት ሳይመዘገብ በሱዳን ሕዝባዊ አመፅ ተካሂዶ ፕሬዚዳንቱን ለመፈንቅለ መንግሥት ዳርጎ በእስር እንዲማቅቁ አድርጓል፡፡
በተቋማዊ አደረጃጀት አንፃር ስንመለከት ደግሞ የአወያዩን መዋቅር፣ አደረጃጀት፣ ቁመናና የሥልጣን ገደብ መወሰን የተወያይ ወገኖች መሆን ያለበት ሲሆን፣ ይህ የሚወሰነው በቅድመ ውይይት ደረጃ ላይ በሚደረገው የብሔራዊ ምክር ቤት ጉባዔ ላይ መሆን ይገባል፡፡
ለተቋሙ ግልጽ ሥልጣንና በልኩ የተሰፋ ተገቢ መዋቅር፣ በአግባቡ የተሰናሰሉ ሕጎችና አሠራሮች መስጠት
የበርካታ አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየን ከሆነ፣ አብዛኞቹ ብሔራዊ ውይይቶች የሚካሄዱት ከነባር የመንግሥት መዋቅር ውጪ በሆነ ነፃና ገለልተኛ ተቋም ነው፡፡ እንደሚታወቀው አብዛኞቹ ብሔራዊ ውይይቶች የሚካሄዱት በወቅቱ ያለው ተመራጭ መንግሥት (Incumbent Government) እና ነባር የሥርዓተ መንግሥቱ ተቋማት በሕዝብ ዘንድ ሕጋዊ ቅቡልነት በማጣትም ሆነ፣ በተዓማኒነት መነጽር ጎድለው በመታየታቸው፣ ወይም አሁን ያለውን ነባራዊ የችግር ሁኔታ ከመሠረቱ ለመለወጥ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ወይም ፖለቲካዊና ሕጋዊ አቅም በማጣታቸው የተነሳ በተጨባጭ እጃቸው ላይ ያሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች በቁርጠኝነት መፍታት ባለመቻላቸው በሚፈጠር ግጭት ወቅት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ምልዓተ ሕዝቡም ሆነ የፖለቲካ ልሂቃኑ እነዚህን ተቋማት ተማምኖ ለመዳኘትና መፍትሔ ሐሳብ እንዲያመጡ ለመጠበቅ መተማመን ይጎድላቸዋል፡፡ ስለሆነም የብሔራዊ ውይይት ክንውንን የሚያዘጋጅ፣ የሚመራና ትግበራውን የሚከታተል ነፃ፣ ገለልተኛና ጠንካራ መዋቅር ያለው አወያይ ተቋም ማዋቀር ተገቢ ነው፡፡ ይህንንም የመምራት ልዕልና ያለው ሰብሳቢ መመደብም ተጠቃሽ መርህ ነው፡፡
በተጨማሪም ብሔራዊ ውይይት የራሱ የሆነ ወጥ የአሠራር ሒደት፣ የሚከተላቸው ቅደም ተከተሎችና ውሳኔዎችን የሚወስንበት በአግባቡ የተናበበ የደንብና መመርያ ማዕቀፍ ይኖረዋል፡፡ ይህም ግልጽና በጥንቃቄ የተቀረፀ፣ ከቡድኑ ስብጥርና ከጉዳዮች ባህሪ ጋር የሚስማማ መሆን አለበት፡፡ እንዲሁም እነዚህ አሠራሮች የውይይቱ ተሳታፊዎች በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረስ ካልቻሉ ያለ መግባባት ዕገዳዎችን ለማስወገድ፣ ወይም የችግር ቅርቃሮችን ለመስበር የሚያስችሉ ሥልቶችን አጣምረው ማካተት አለባቸው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ አንድ ዓይነት መልክ ያለው በመግባባት ላይ የተመሠረተ የውሳኔ አሰጣጥ ሥነ ዘዴን በመተግበር፣ የሁሉም ቡድኖች ትርጉም ያለው ተሳትፎ እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፡፡ በተጨማሪም መመርያው በግልጽ አስገዳጅ ሆኖ ቀደም ሲል በተደረገ የሰላም ስምምነት፣ በተወካዮች ምክር ቤት አዋጅ፣ በቻርተር፣ በፕሬዚዳንታዊ ድንጋጌ ወይም በአንዳንድ ሌሎች መልኮች የተቋቋመ ከሆነ ለብሔራዊ ውይይቱ ግልጽ ዓላማና የሥልጣን ጥንካሬ ምንጭ ይሰጣል፡፡ ለዚህ አንዱ ማሳያ የቱኒዚያው የብሔራዊ ውይይት መድረክ ቀድሞውን የተሰጠው ግልጽ ተልዕኮ በመኖሩ፣ የሲቪል ማኅበራት ጥምረቱ ለአራት ግቦች መሳካት በተረጋጋ መልኩ ጥረት እንዲያደርጉ አስችሏቸዋል፡፡ የጊዜያዊ አስተዳደር መንግሥት መምረጥና ማቋቋም፣ አዲስ ሕገ መንግሥት ማፅደቅ፣ የምርጫ አስፈጻሚ አካል ማቋቋምና የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ማውጣት ናቸው፡፡ ይህም ለስኬታማነቱ አንበሳውን ድርሻ ይዟል፡፡
የፖለቲካ አለመግባባቶችና የግጭት መንስዔዎችን ከሥር መሠረታቸው የሚዳስስ አጀንዳ መቅረፅ
የማንኛውም ብሔራዊ ውይይት ዋነኛ ዓላማ በአንድ አገር ውስጥ በሚነሱ ቁልፍ ያለ መግባባት ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ ለመድረስ፣ ወይም የመግባቢያ ማዕቀፍ መፍጠር የሚያስችል ሁሉን አስማሚ ባይሆንም እንኳ የሁሉንም ተካፋይ ወገን ሐሳብ ለማካተት የሞከረ ተመራጩን አማካይ መንገድ መፈለግ እንደሆነ ዕሙን ነው፡፡ ብዙውን ጊዜም እነዚህን ጉዳዮች በሚገባው ልክ አበጥሮና አጥርቶ ለመለየት፣ እንዲሁም በውይይት አጀንዳነት መቅረብ አለመቅረባቸው ላይ ለመስማማት ለወራት ወይም ለዓመታት የሚዘልቁ ሰፋፊ የቅድመ ድርድር ወይም የምክክር መድረኮች ያስፈልጋሉ፡፡
ይህም በአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ከባቢ ውስጥ የሚከሰቱ ማናቸውንም ነባራዊና ወቅታዊ ያለ መግባባት መንስዔዎችን፣ ወይም የግጭት ጫሪ ጭብጦችን ሊያካትት ይገባል፡፡ ለአብነትም ብሔራዊ ማንነት፣ የአገረ መንግሥት ሥርዓተ ውቅር (State Structure)፣ የሃይማኖት ሚና በመንግሥት ውስጥ፣ የፖለቲካዊ መብቶች፣ የዜጎች መሠረታዊ ነፃነቶች፣ የተቋማት ማሻሻያና መልሶ ማበጀት፣ የመከላከያና ደኅንነት ተቋማት ነፃና ገለልተኛነት፣ የጋራ ማንነት፣ የመሬት ሥሪት፣ የምርጫ አሠራሮችና የመንግሥት አወቃቀር (ብዙውን ጊዜ ስለፌዴራሊዝሙ አላባዊያን የሚደረግ ክርክር)፣ ወዘተ. ከብዙ በጥቂቱ የሚነሱ አጀንዳዎች ናቸው፡፡
ስለሆነም በብሔራዊ ውይይት የአጀንዳ ቀረፃ ቅድመ ዝግጅት ወቅት፣ በሁሉም ቁልፍ የፍላጎት ቡድኖች በሚነሱ ዋና ዋና ቅሬታዎች ዙሪያ ተጨባጭ የውይይት መድረክ መዘጋጀት ይኖርበታል፡፡ ሆኖም ይህ የቅድመ ዝግጅት አጀንዳ ቀረፃ ደረጃ ብዙውን ጊዜ በተንጠባጠቡ ዝብርቅርቅ ጉዳዮች ሲጠመድ ይታያል፡፡ በመሆኑም በቀጣይ በሚተካው መንግሥታዊ መዋቅር ወይም በሙያዊና ቴክኒካዊ አካላት በተሻለ መንገድ ዘላቂ መፍትሔ በሚሰጥባቸው ጥቃቅን አጀንዳዎች አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ የለበትም፡፡
የመንን እንደ ምሳሌ ብናነሳ በአገሪቱ የተካሄደው የብሔራዊ ውይይት ኮንፈረንስ ሩቅ ዓላሚ፣ አካታችና ሰፋፊ አጀንዳዎች ቢኖረውም፣ በጣም አወዛጋቢ በሆነው የፌዴራሊዝም ጉዳይ ላይ እስካሁን ድረስ አመርቂ ስምምነት ማምጣት አልቻለም፡፡ ሌላው ለተዋቀረው የፌዴራሊዝም ሥርዓት በሚተገበሩት የፋይናንስና ፖለቲካዊ የአሠራር ሥርዓቶች ላይ አለመግባባት መቀጠሉ፣ ከብሔራዊ ውይይቱ ኮንፈረንስ ማጠቃለያ በኋላ ከ15 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የተቀሰቀሰውን የእርስ በርስ ግጭት የሚያቀጣጥል ዋነኛው የቅሬታ ምንጭ ሆኗል፡፡
ተሳታፊዎች ከውይይቱ የተገኙ ውጤቶችን ወደ ትግበራ ለማስገባት የተስማሙበት ሥነ ዘዴ መርሆ
በአገራዊ ውይይቶች መባቻ የተገኙ የውሳኔ ሐሳቦች በአዲስ ሕገ መንግሥት፣ በሕግ በሚደነገግ አዋጅና ደንብ፣ በፖሊሲ ማዕቀፍ ወይም በሌሎች መሰል አቃፊ መርሐ ግብሮች እንዲተገበሩ የሚያስችሉ መላው ተሳታፊ አካላት የተስማሙባቸው ተተግባሪ ዕቅዶችን መሰነድ አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ብሔራዊ ውይይቶች በሰፊ ፖለቲካዊ የሽግግር ማዕቀፍ ውስጥ ስለሚካሄዱ ብዙውን ጊዜ ከሽግግር ፍትሕ፣ ከሕገ መንግሥት አወጣጥና ከምርጫዎች ጋር መደበኛ ወይም መደበኛ ያልሆነ ግንኙነት አላቸው፡፡ ማንኛውም ብሔራዊ ውይይት ግልጽ የትግበራ ዕቅድ ማዕቀፍ ከሌለው በስተቀር፣ ምንም ዓይነት ተጨባጭ ውጤት ሳያመጣ ሰፊ ጊዜና ሀብትን እንዲባክን ያደርጋል፡፡
ለምሳሌ እ.ኤ.አ. በግንቦት ወር 2015 በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የተካሄደው የባንጉይ ውይይት መድረክ ይህንን መሰል የአካሄድ ስህተት በመከተሉ፣ በተጨባጭ መሬት ለመዉረድ ከማዳገቱም በላይ የመክሸፍ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ምንም እንኳን የባንጉይ መድረክ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ የፖለቲካ ሽግግር ታሪክ ወሳኝ ምዕራፍ በመሆኑ በተጓዳኝ ዜጎች ሕሳባቸውን እንዲያሰሙ ያደረገ የማይገኝ አጋጣሚ የነበረ ቢሆንም፣ መድረኩ በችኮላ የተደራጀና ሕጋዊ የሥልጣን ወሰኑና ተልዕኮውም እምብዛም ግልጽ አልነበረም፡፡ የባንጉይ የውይይት መድረክ የትግበራ ኮሚቴ ለሳምንታት የዘለቀው ውይይት ሲጠናቀቅ የተቋቋመ ቢሆንም፣ ኮሚቴው ከመድረኩ የወጡትን የውሳኔ ሐሳቦች ተግባራዊ የማድረግ አቅም ወይም ሕጋዊ ሥልጣን እንዳለው ግልጽ አልነበረም፡፡
ከላይ ለመዘርዘር እንደ ሞከርኩት በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄዱ ብሔራዊ ውይይቶች ሁሉን አቀፍ፣ መጠነ ሰፊና አሳታፊ የሆነ ኦፊሴላዊ የድርድርና የማኅበረሰባዊ ውል ስምምነት ማዕቀፍ የሚሆን መውጫ የሁሉን አሸናፊነት መንገድ ያበጃሉ፡፡ ይህም በሥርዓተ መንግሥት፣ በመንግሥታዊ አስተዳደርና በአገር ግንባታ ረገድ የተፈጠሩ የፖለቲካ ቀውሶችን ለመፍታትና ለፖለቲካዊ ሽግግር ጥርጊያ መንገድ ሊያስተካክል ይችላል፡፡
በጥቂቱ ከቶጎ በ2006 ዓ.ም. እስከ የመን (2013/2014) የተካሄዱ ብሔራዊ ውይይቶችን እንደ ማሳያነት ብንጠቀም እንኳ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ የመጡ ማኅበራዊ አለመግባባቶችን፣ የፖለቲካ ቀውሶችንና ሽግግሮችን አስከፊ ግጭትና መፈራረስ ሳያስከትሉ ለማስተናገድ እንዲሁም ራስ ሠር የሆነ አዋጭና ዘላቂ የመፍቻ መንገድ ለማበጀት እንደ ተመራጭ ተስፋ ሰጪ ጎዳና ይቆጠራሉ፡፡
ብሔራዊ ውይይቶች፣ ድርድሮችና መግባባቶች የሚዘጋጁት በዋናነት ሰፋፊ አገራዊ ጉዳዮችን በአጀንዳነት ለማስናገድና አለመግባባቶችን በሆደ ሰፊነት፣ የረዥም ጊዜ የወደፊት ብሔራዊ ጥቅምና ራዕይ (National Interest and Vision) ዘላቂና ዙሪያ መለስ መፍትሔ ለማምጣት በሚያስችል መንገድ ሲሆን፣ እነዚህም እስከ የፖለቲካዊ ሥርዓትን ማሻሻያ፣ ነባር ወይም አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ፣ መደንገግና ዘላቂ የሰላም ግንባታን ባካተቱ ተልዕኮዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ብሔራዊ ውይይቶች ይደረጋሉ፡፡ በተለይም ለረዥም ጊዜ በቆዩ የግጭት መንስዔዎች ተሳስበው በፖለቲካዊ አመፅ ወይም በትጥቅ ትግል ወደ ፖለቲካዊ መድረክ በመጡ አካላት የሚነሱ፣ መሠረታዊ የመብትና የፖለቲካ ጥያቄዎችን በቅንነትና በማያዳግም ሁኔታ በማስተናገድ ብሔራዊ ጉዳዮችን ለመፍታት ሁነኛ ሥልቶች ናቸው፡፡
ስለሆነም ብሔራዊ ውይይቶች የሚያስገኙትን አገራዊ ፋይዳ ተገንዝበው መንግሥትም ሆነ ተሳታፊ ወገኖች መርሆዎችን በተከተለ መንገድ ወደ ትግበራ እንዲገቡ፣ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ አጥብቄ እጠይቃለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካካት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡